Saturday, 07 April 2012 08:37

ናይል በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ሊመታና ፍሰቱም 40 በመቶ ሊቀንስ ይችላል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተፅዕኖውን እያሳረፈ ነው፡፡ ግግር በረዶ እየናደ፤ በጐርፍ እያጥለቀለቀ፣ በሰደድ እሳት እያቃጠለ፣ በድርቅ እየመታ፣ … በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ለሞት ለረሃብ ለበሽታና ለሰቆቃ … እየዳረገ ነው፡፡ ይህ አስከፊ አደጋ በናይል ተፋሰስ አካባቢም ጥላውን አጥልቷል፡፡ አካባቢው በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እንደሚመታ፣ የውሃውም ፍሰት በ13 ዓመት ውስጥ (በ2025) እስከ 40 በመቶ እንደሚቀንስ፤ በተፋሰሱ ስር ያሉ አገሮች የውሃ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሊጐዳ እንደሚችል ኢትዮ ናይል ዲስኮርስ ፎረም ገልጿል፡፡

ፎረሙ፣ “ክላይሜት ቼንጅ ዎተር ኤንድ ኢነርጂ ሴኩሪቲ ኢን ኢትዮጵያ ኤንደ ኢምፔሊኬሽንስ ኦን ኮኦፕሬሽን ኢን ዘ ናይል ቤዚን” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የአንድ ቀን ውይይት፤ በነጭና በጥቁር አባይ ወንዞች የሙቀት ጨረር እንደሚኖር፣ በዝናብ ትንበያዎች ላይ ልዩነቶች እንደሚፈጠሩ ትንበያዎች እንደሚያመለክቱ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተደረጉ ዘጠኝ የአየር ንብረት ኩነቶች እንዳሳዩና የናይል ፍሰት ከዜሮ እስከ 40 በመቶ በ2025 እንደሚቀንስ በውይይቱ ላይ የተሰራጨ አንድ የናይል ቤዚን ዲስኮርስ መረጃ አመልክቷል፡፡

ናይል፣ ከግብፅ በስተቀር በሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች፣ ከ60 እስከ 90 በመቶ ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ውሃውም፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት ይውላል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ከውሃ ጋር የተያያዙ በሽታዎችን፣ ድርቅና ከባድ ዝናብ ወይም ከፍተኛ ሙቀት የሚያስከትል ሲሆን፤ በተፋሰሱ አገሮች መሃል ግጭት ሊጨምርና የዓሳዎችን ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የተባበሩን መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ደረጃ መሠረት፤ ከግብፅና ከኬንያ በስተቀር ዘጠኙ የተፋሰሱ አገሮች ብሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፣ የመጨረሻዎቹ ያላደጉ አገሮች ሲሆኑ 100 ሚሊዮን ያህል ዜጐቻቸው በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ እንደሚተዳደሩ አመልክቷል፡፡ በዚህ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሲደመር፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ችግሩን ያገዝፈዋል፡ ፎረሙን በክብር እንግድነት ተገኝተው የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚ/ር ዲኤታ አቶ ወንድሙ ተክሌ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማትን እየተፈታተነ መሆኑ ጠቅሰው፤ ከምንጊዜውም የበለጠ ጐርፍ፤ ድርቅና አደጋ እያስተዋልን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ የአየር ንብረት ለውጥ በሁሉም አካባቢ ሕዝብ እየሞተና በቅርቡ የሞንጐሊያ በድርቅ መመታት፣ የታይላንድ በጐርፍ መጥለቅለቅ፣ ከአውስትራሊያ እስከ ሂማሊያ ያሉ ማኅበረሰቦች የተከሰተው የሰደድ እሳት ቃጠሎ ዛሬ ዓለማችን ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ የአየር ንብረት ቀውስ ውስጥ መሆኗን የሚያመላክት ግልፅ ማስረጃ ነው ብለዋል፡፡

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እጅግ ከተጋለጡ አኅጉሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ተፅዕኖ ከሚፈጥርባቸው አገሮች አንዷ ናት፡፡ የአጭርም ሆነ የረዥም ጊዜ ተፅዕኖን ለመቋቋም ያላት አቅም አናሳ መሆኑን በመገንዘብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት አገር ውስጥ የሚቀሩትንም ሆነ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቱን በሚገባ ለማስተዳደር ባለው የመጨረሻ አቅም፣ እቅድና ስትራቴጂ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን መላመድ፣ ለውሃ አስተዳደር አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሰው የናይል ቤዚን ዲስኮርስ መረጃ፣ በውሃ አስተዳደር በውሃው ዘርፍ ባሉ ማሻሻያዎችና በአየር ንብረት ለውጥ መካከል ያለው ትስስር ሁልጊዜም ደካማ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከውሃ ጋር በተያያዙ የመላመድ ጉዳዮች ከሚያጋጥማቸው ችግሮች በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ድርጅቶች እንዲሁም በናይል ቤዚን ስር ባሉ አገሮች መካከል ጠንካራ ትብብርና ቅንጅት አለመኖሩ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር መላመድና ጉዳቱንም ለመግታት የተባበረ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ያለው የቤዚኑ ዲስኮርስ መረጃ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ውሃ እንደ ሀብት በበቂና በተገቢው መንገድ ለኅብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ የውሃ አስተዳደር ከፕላኒንግ ዲዛይንና ትግበራ ጀምሮ የውሃ ፕሮጀክቶችን ወይም ፕሮግራሞችን ዘላቂ ለማድረግ የባለ ድርሻ አካላት ሙሉ ትብብርና ተሳትፎ እውን ሲሆን እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የአየር ንብረት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከዕቅድ ጀምሮ በመሳተፍ ማኅበረሰብንና መንግሥታተን ማገናኘት አለባቸው፡፡ ይህም ማኅበረሰቦች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ በክልላዊና አገራዊ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች የማኅበረሰቦችን ቅድሚያ ጥያቄ ለማወቅና ከውሃ ጋር የተያያዙ የመላመድ እንቅስቃሴዎችን እንዲያግዙ ይረዳል በማለት አስገንዝቧል፡፡

 

 

Read 2381 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 08:40