Saturday, 12 August 2017 00:00

አቶ በቀለ ገርባ “ከእስር ቢለቀቁ አመፅ ሊያነሳሱ ይችላሉ” በሚል ዋስትና ተከለከሉ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ቀድሞ የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ቀርቶ፣ በወንጀለኛ ህጉ ይከላከሉ በሚል ፍ/ቤት ብይን የሰጠባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ “ከእስር ቢለቀቁ በድጋሚ አመፅ ሊያነሳሱ ይችላሉ” በሚል የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደረገ፡፡  
በኦሮሚያ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰ ህዝባዊ አመጽ ጋር ተያይዞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው፣ በሽብር ድርጊት በመሳተፍ ወንጀል፣ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይን የሚመለከተው ፍ/ቤት፤ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በሰጠው ብይን፣ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው የማስረጃ ዝርዝር፣ የሽብር ወንጀልን የሚያመላክቱ ባለመሆናቸው፣ “ግዙፍ ባልሆነ መሰናዳትና መገፋፋት” ወንጀል እንዲከላከሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡  
ይህን ተከትሎም እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠበት አንቀፅ ዋስትና የሚፈቀድበት በመሆኑ፣ ለፍ/ቤቱ የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ሁለት ምክንያቶችን በማቅረብ ዋስትናው እንዳይፈቀድ ተቃውሟል፡፡ “መጀመሪያውኑ ዋስትናውን የተከለከሉት በሽብር ወንጀል ጉዳይ ነው፤ አሁን የክሳቸው አንቀፅ ቢቀየርም የዋስትና ጥያቄ መነሳት የለበትም፤” ያለው አቃቤ ህግ፤ ተከሳሹ ከሀገር ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር የሚገናኙ በመሆኑ ከአገር ቢወጡ አይመለሱም ሲል ተከራክሯል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሹ  ከእስር ቢለቀቁ ህዝብን የማነሳሳት ተግባራቸውን ሊቀጥሉበት ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡  
የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የተከሰሱበት አንቀጽ የዋስትና መብት የማይከለክል መሆኑን በመጥቀስ እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ ከዚህ ቀደም ከሀገር ወጥተው የተመለሱ በመሆናቸው ወጥተው ይቀራሉ የሚለው ግምት አይኖርም  በማለት የዋስትና ጥያቄ  ለፍ/ቤቱ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍ/ቤቱም፤”ተከሳሹ ከእስር ቢወጡ ህዝብን የማነሳሳት ተግባራቸውን ላለመቀጠላቸው ማረጋገጫ የለም” በሚል የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ጠበቃ አመሃ መኮንን፣ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ፣ከፊታችን ሰኞ ነሐሴ 8 ጀምሮ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

Read 2446 times