Saturday, 12 August 2017 00:00

ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ 31.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 በጀት ዓመት ካደረጋቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች 31.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንና ከታክስ በፊት 14.6 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ በዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከወጪ ንግድ፣ ከሃዋላ፣ ከወጪ ምንዛሪ ግዥና ሌሎች አገልግሎቶች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡ ባንኩ ከብድር ተመላሽ መሰብሰብ የቻለው 64.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን 94.5 ቢሊዮን ብር ለልዩ ልዩ የሥራ መስኮች አዲስ ብድር መሰጠቱን ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ ስለቁጠባ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በሽልማት ላይ የተመረኮዘ ቁጠባን የማበረታታት ሥራ መሠራቱም ተገልጿል፡፡ በእነዚህ ተግባራት አማካኝነትም 76.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን መረጃው አመላክቷል፡፡ ይህ ክንውን የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 ከነበረበት 288.4 ቢሊዮን ወደ 364.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ አስችሏል ተብሏል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 485.7 ቢሊዮን ብር መድረሱንና የባንኩ ካፒታል ወደ 40 ቢሊዮን ብር ማደጉ ተገልጿል፡፡  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት 1222 ቅርንጫፎች መድረሱንና፣ ሂሳብ ያላቸው የባንኩ ጠቅላላ ደንበኞች ቁጥርም 15.9 ቢሊዮን መድረሱን መግለጫው አመልክቷል፡፡

Read 1784 times