Saturday, 12 August 2017 00:00

የአማራ ክልል ከተሞች በንግድ አድማ ላይ ሰንብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በቅርቡ የተደረገውን የቀን ገቢ ግብር ግመታን በመቃወም፣ አብዛኞቹ የአማራ ክልል ከተሞች በንግድ አድማ ላይ መሰንበታቸውን  ምንጮች ለአዲስ አድማስ የገለጹ ሲሆን የክልሉ መንግስት አድማውን በውይይት እያስቆምኩ ነው ብሏል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ም/ኃላፊ፣ አቶ ፀጋዬ በቀለ፤ በአንዳንድ የክልሉ የወረዳ ከተሞች እንደተባለው የንግድ መደብሮችን በመዝጋት አድማ ሲካሄድ እንደሰነበተ ጠቁመው፣ በየከተሞቹ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች አብዛኞቹ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቅሬታቸውን በህጋዊ አግባብ ለሚያቀርቡ የግብር ማሻሻያ መደረጉን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከንግዱ ማህበሰረብም ጋር በተደረገ ውይይት፣ መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው ብለዋል፡፡   የንግድ ስራ ማቆም አድማ ሲደረግባቸው ከሰነበቱ ከተሞች መካከል ባህርዳር፣ ደብረማርቆስና ወልድያ እንደሚገኙበት ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ከየአካባቢው የተጠናቀረ መረጃ ማሰባሰቡን የገለፀው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤አብዛኞቹ የምስራቅ ጎጃም ከተሞች በአድማ ላይ መሰንበታቸውንና  ሱቃቸውን የዘጉ ነጋዴዎች እየታሰሩ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፣ ለአዲስ አድማስ እንዳብራሩት፤ አድማው ከተደረገባቸው የአማራ ክልል ከተሞች መካከል፡- ሞጣ ቀራኒዩ፣ ሸበል በረንታ፣ ብቸና፣ ደብረወርቅ፣ መርጦ ለማርያም፣ ፈለገ ብርሃን፣ ዳንግላ፣ ደምቦጫ፣ እሮብ ገበያ፣ ኮምበልቻ፣ ዋድላ፣ ደሴ ይገኙባቸዋል፡፡
በአብዛኞቹ ከተሞች የተደረገው የንግድ አድማ ከሰኞ እስከ ሐሙስ የዘለቀ እንደነበር አቶ አዳነ አስታውቀዋል፡፡ ሁኔታዎቹ አሳሳቢ ናቸው ያለው፣ መኢአድ፤መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቋል፡፡   

Read 2168 times