Saturday, 19 August 2017 12:39

ኦባማ በትዊተር ተወዳጅነት ክብረወሰን አስመዝግበዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የትዊተር ጽሁፋቸው ከ3.2 ሚ. በላይ ላይኮችን አግኝቷል

      የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በቨርጂኒያ ግዛት በምትገኘው ቻርሎቴስቪል ከተማ የነጮች የበላይነት አራማጆች ከፈጠሩት የዘረኝነት ግጭትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በትዊተር ድረገጽ ላይ ያስተላለፉት አጭር ጽሁፍ፣ 3.2 ሚሊዮን ላይኮችን በማግኘት፣ በትዊተር ድረገጽ ታሪክ ከፍተኛውን የተወዳጅነት ክብረወሰን ይዟል፡፡
የኦባማ የትዊተር ጽሁፍ 1.3 ሚሊዮን ጊዚያት ያህል በሌሎች የትዊተር ተጠቃሚዎች የተሰራጨ ሲሆን ይህም ጽሁፉን በትዊተር ተጠቃሚዎች በብዛት የተሰራጨ አምስተኛው ጽሁፍ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ኦባማ ከአፓርታይዱ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ የግለ ህይወት መጽሃፍ የወሰዱትን፣ “ሰዎችን በቆዳ ቀለማቸው፣ በማንነታቸው ወይም በሃይማኖታቸው ሳቢያ እንዲጠላ ሆኖ የተወለደ ሰው የለም” የሚለውን አጭር ጽሁፍ፣ እየቅል ዝርያ ያላቸውን ህጻናት በመስኮት በኩል ሰላምታ ሲሰጡ ከሚያሳይ ፎቶግራፋቸው ጋር ቅዳሜ ዕለት በትዊተር የለቀቁት ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት ጽሁፉ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨትና ተወዳጅነት በማግኘት የትዊተርን ክብረወሰን መያዙንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በትዊተር ተወዳጅነት ክብረወሰኑን ይዞ የነበረው ከወራት በፊት በማንችስተር የአርያና ግራንዴ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ከተከሰተው የሽብር ጥቃት ማግስት ድምጻዊቷ ያስተላለፈቺውና 2.7 ሚሊዮን ጊዜ ላይክ የተደረገው የሃዘን መግለጫ መልዕክት እንደነበርም አስታውሷል፡፡
በትዊተር የማህበራዊ ድረገጽ ታሪክ በርካታ ቁጥር ባላቸው ተጠቃሚዎች ላይክ ከተደረጉ የመጀመሪያቹ ምርጥ 10 የትዊተር ጽሁፎች መካከል ስድስቱ የኦባማ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኦባማ በስማቸውና ፖተስ44 በሚል በከፈቷቸው ሁለት የትዊተር አካውንቶች እንደሚጠቀሙም ጠቁሟል፡፡

Read 1058 times