Sunday, 20 August 2017 00:00

ከ100 ቀናት በላይ ስራ ያቋረጡት የናይጀሪያው መሪ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      “ስራቸውን ይቀጥሉ፣ አልያም ስልጣን ይልቀቁ!” ተብለዋል

       የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ በህመም ምክንያት መደበኛ ስራቸውን ካቋረጡ በዚህ ሳምንት ከ100 ቀናት በላይ እንደሆናቸው ያስታወሰው ቪኦኤ፣ የአገሪቱ ዜጎች ባለፈው ማክሰኞ አደባባይ ወጥተው ባሰሙት ተቃውሞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ አልያም ስልጣናቸውን እንዲለቅቁ መጠየቃቸውን ዘግቧል፡፡
ቡሃሪ መደበኛ ስራቸውን አቋርጠው በለንደን ለወራት ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ በተደጋጋሚ ለህክምና ስራቸውን ሲያቋርጡ የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ምክትል ፕሬዚዳንታቸውን ቢወክሉም የአገሪቱ ዜጎች ግን ስራ መፍታቱ በዝቷል፣ ወይ ጠቅልለው ስራ ይጀምሩ አልያም ስልጣናቸውን ያስረክቡ ሲሉ በመዲናዋ አቡጃ ባደረጉት ተቃውሞ ጠይቀዋል ብሏል፡፡
“ስራ ይጀምሩ፣ አልያም ስልጣን ይልቀቁ!” የሚል መፈክር ይዘው አደባባይ የወጡት ናይጀሪያውያኑ፣ ከፕሬዚዳንት ቡሃሪ ደጋፊዎች ተቃውሞ እንደገጠማቸውና መጠነኛ ግጭትና ብጥብጥ መፈጠሩን የጠቆመው ዘገባው፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪዎች ግን ፕሬዚዳንቱ ወደ አገራቸው ተመልሰው ምላሽ እስከሚሰጡ ድረስ ተቃውሟቸውን በሌሎች የአገሪቱ ከተሞችም አጠናክረው ለመቀጠል ማቀዳቸውን እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት ስራቸውን አቋርጠው በተደጋጋሚ ወደ ውጭ አገራት መሄዳቸው በአንዳንድ የአገሪቱ ተቃዋሚዎች ዘንድ ቅሬታን ከመፍጠር አልፎ ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ በይፋ እስከመጠየቅ እንዳደረሳቸው የጠቆመው ዘገባው፣ በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2017 በአገር ውስጥ ካሳለፉት ጊዜ ይልቅ በውጭ አገራት ያሳለፉት ጊዜ እንደሚበልጥም ገልጧል፡፡ ቡሃሪ ባለፈው ሳምንት ከለንደን በሰጡት መግለጫ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገራቸው ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን ለመቀጠል በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተለይ ደግሞ የፕሬዚዳንቱን ህመም ምንነትም ሆነ የጤና ሁኔታቸውን በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ለህዝቡ አለመሰጠቱ ጥርጣሬንና ስጋትን መፍጠሩን አመልክቷል፡፡

Read 1884 times