Monday, 21 August 2017 00:00

ግማሽ ሚሊዮን የመናውያን በኮሌራ ተጠቅተዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በ4 ወራት 2 ሺህ የመናውያን በኮሌራ ሞተዋል፤ በየቀኑ 5 ሺህ ሰዎች በኮሌራ ይጠቃሉ

     በእርስ በእርስ ጦርነት በፈራረሰቺዋ የመን፣ በተከሰተውና በአለማችን ታሪክ እጅግ የከፋው እንደሆነ በተነገረለት የኮሌራ ወረርሽኝ የተጠቁ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ያህል እንደደረሰ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ አንስቶ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የኮሌራ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ 2 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ ከሃምሌ ወር ወዲህ በየቀኑ 5 ሺህ ያህል ሰዎች በኮሌራ እየተጠቁ እንደሚገኙም ገልጧል፡፡
የግልና የአካባቢ ንጽህና ሁኔታዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውና የውሃ አቅርቦት መቆራረጡ የኮሌራ ወረርሽኙ በፍጥነት እንዲሰራጭ ምክንያት መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፣ ከ14 ሚሊዮን በላይ የመናውያን የንጹህ ውሃና የአካባቢ ንጽህና አገልግሎት አቅርቦቶችን በቋሚነት እንደማያገኙ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ በበኩሉ፣ በየመን በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ከተጠቁት ዜጎች መካከል 41 በመቶ ያህሉ ህጻናት እንደሆኑ በማስታወስ፣ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው ብሏል፡፡
በአገሪቱ ያለው የጤና አገልግሎት የኮሌራ ወረርሽኙን ለመግታት እንዳልቻለ የዘገበው ቢቢሲ፣ ከሁለት አመታት በላይ የዘለቀው የአገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ባደረሰው ጥፋት ሳቢያ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን አመልክቷል፡፡ በየመን የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ 30 ሺህ ያህል የአገሪቱ የጤና ሰራተኞችም ለአንድ አመት ያህል ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው አስታውሷል፡፡
መፍትሄ ያልተገኘለት የአገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ከመጋቢት ወር 2015 አንስቶ ባለው ጊዜ ውስጥ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት፣ ከ46 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ መዳረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1762 times