Saturday, 19 August 2017 12:50

“ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ” ዛሬ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  ላለፉት ሁለት ዓመታት የገና እና የፋሲካ ኤክስፖዎችን ያዘጋጀው ኢዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንትስ፤ የዘንድሮ አዲስ ዓመትን “ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ” ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚከፈት ገለፀ፡፡ ከዚህ ቀደም አዳዲስ ፈጠራዎችን በመጨመር ኤክስፖው የፌስቲቫልነት ይዘት እንዲኖረው ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሰው ኢዮሃ፣ ዘንድሮም “የመስቀል ወፍና አደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ” በሚል መርህ ኤክስፖውን ደማቅ ለማድረግ መዘጋጀቱን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ትልልቅ የመንግስት ሀላፊዎች በሚገኙበት የሚከፈተው ኤክስፖው፣
በታዋቂ የባህል ውዝዋዜ ቡድኖች ይታጀባል ተብሏል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 መጨረሻ ለ22 ቀናት በሚዘልቀው የንግድ ትርኢትና በዛር፤ ከ40 በላይ የከተማችን ተወዛዋዦች፣ የባህላዊና ዘመናዊ ዳንስ ውድድር፣ የሚወዳደሩበት ከአንድ ዓመት ህፃን ጀምሮ ህፃናት የሚዝናኑበትና የሚቆዩበት የህፃናት ኮርነር፣ ለአካል ጉዳተኞች ልዩ የመቀመጫ ስፍራ፣ አምራቹ በአብዛኛው የሚሳተፍበት በመሆኑ ጎብኚው በማከፋፈያ ዋጋ የሚገበይበትና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን የኢዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንትስ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አዩ አለሙ ገልፀዋል፡፡  በኤክስፖው ላይ ከመቶ በላይ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን፣ አራት ትልልቅ ባንዶችና ታዋቂ ዲጄዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከ400 በላይ የውጭና የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲሁም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንደሚሳተፉበት ወ/ሮ አዩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ወደ ኤክስፖው የሚገቡት ታዳሚዎች የሚሸለሙበትን አሰራር ኢዮሃ ያዘመነ መሆኑን ጠቁመው፣ የእጣው የትኬት ቁጥር በ8856 ስለሚወጣ፣ ጎብኚዎች የእጣ ቁጥራቸውን ወደተገለፀው ቁጥር መላክ አለባቸው ተብሏል፡፡

Read 1810 times