Saturday, 19 August 2017 12:55

ዜማ ብዕር ኢትዮጵያ፤ ዛሬ የቡሄ በዓልን ያከብራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ዜማ ብዕር ኢትዮጵያ የሴት ደራሲያን ማህበር፣ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ የቡሄ በዓልን በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊና ትውፊታዊ ዝግጅቶች፣ ፒያሳ ከጣይቱ ሆቴል ጀርባ በሚገኘው አልቤት ሆቴል እንደሚያከብር ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡ ማህበሩ ከ2004 ጀምሮ የቡሄ በዓል አመጣጥ ታሪካዊ ሁነቱን በሚገልጽ መልኩ፣ “ባህላችንን ጠብቀን ለትውልድ በማስተላለፍ፣ ኃላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል ሲያከብር መቆየቱን አስታውሶ፤ የዘንድሮንም ቡሄ በተመሳሳይ ዓላማ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ጋር በመተባበር እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡
እየተረሳ የመጣውን ባህል ለማስጠበቅ፣የባህል ቅብብል ከአባት አርበኛ ወደ አዲሱ ትውልድ ሽግግር፣የቡሄ ትርጓሜ፣ያሬዳዊ ዜማ፣ ቅኔ፣ ሽብሻቦ፣ ግጥም፣ ድራማ፣ ጥያቄና መልስ እንዲሁም የችቦ ማብራት ሥነስርዓት እንደሚከናወን ማህበሩ ጠቁሟል። ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት ያለውንና በማይዳሰስ ቅርስነት ዘርፍ የሚመደበውን የቡሄን በዓል በማክበር፣ ታሪካዊ አመጣጡን፣ ጭፈራውንና ተያያዥ ባህሉን ለትውልድ ለማስተላለፍ ማኅበሩ በትጋት መስራቱን እንደሚቀጥልም  ጋዜጠኛ የእናት ፋንታ ውቤ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ በዛሬው የቡሄ በዓል አከባበር ላይ የተለያዩ እንግዶች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዳይሬክተር፣ አምባሳደሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሰዓሊያንና ቀራፂያን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ብላለች፤ የማህበሩ ተወካይ ጋዜጠኛ የእናት ፋንታ ውቤ፡፡ 

Read 1433 times