Sunday, 20 August 2017 00:00

በየዘመኑ የሚገለጠው የሰው ልጅ!!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(4 votes)

    ዲበ አካላዊው ፍልስፍና (Metaphysics) ከሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው፤ “የሰው ልጅ ተፈጥሮ እንዴት ያለ ነው?” የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ በጣም መሠረታዊ የሆነበት ምክንያት፣ “ውጫዊው ዓለም የሰው ልጅ ውስጠት ነፀብራቅ” በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የውጭው የሚወሰነው በውስጡ ነው፤ ልክ “አንድ ሀገር ማንን ትመስላለች” ቢሉ መሪዋን እንዲሉ፡፡ በመሪው ፍላጎት፣ ባህሪና አስተሳሰብ ልክ ተሰፍተው ተቋማት ይቋቋማሉ፤ እነዚህም ተቋማት ዜጎችን ይቀርፃሉ፡፡ በመሆኑም የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ማጥናት፣ የውጭውን ዓለም መልክና ባህሪ ለማቅናት ይረዳናል፡፡
የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከአንድ ዓይነት ግብዓት የተሰራ ቢሆን ኖሮ፣ የሰውን ልጅ ለማወቅ ያንን ያህል አስቸጋሪ አይሆንም ነበር፡፡ በሁለት ምክንያቶች ግን የሰው ልጅ ተፈጥሮ እንዲህ ነው ብሎ ዕቅጩን መናገር አልተቻለም። የመጀመሪያው፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ የተለያየ ባህሪ ካላቸው፣ ከተለያዩ ግብዓቶች ወይም ኩነቶች መስተጋብር የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ በእነዚህ የተለያዩ ግብዓቶች የማያቋርጥ መስተጋብር የተነሳ የሰው ልጅ ተፈጥሮ በየዘመኑ እንደ አዲስ የሚገለጥ (ተገልጦ ያላለቀ) መሆኑ ነው፡፡
ምንድን ናቸው እነዚህ ግብዓቶች? መፅሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርአን፣ የሰው ልጅ ከነፍስና ከሥጋ እንደተሰራ ይናገራሉ፡፡ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሄንን አስተምህሮ ይበልጥ በመተንተን የነፍስን ባህሪ ነባቢት፣ ለባዊትና ህያዊት በማለት በሦስት ስትከፍለው፣ ሥጋዊን ባህሪ ደግሞ ከአራት ቁሳዊ ባህሪዎች (እሳት፣ አፈር፣ ውሃና አየር) እንደተሰራ ታስተምራለች፡፡ በእነዚህ ሃይማኖቶች አስተምህሮ መሰረት፤ ነፍስና ሥጋ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ባህሪ ስላላቸው፣ ትክክለኛው የሰው ልጅ መገለጥ ያለበት በነፍሳዊ ባህሪው ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ፈላስፎች የሰው ልጅ በስሜትና በአመክንዮ መስተጋብር የሚገለጥ፣ ተለዋዋጭ ተፈጥሮ እንዳለው ይስማማሉ፡፡ ሃይማኖቶች ደግሞ ስሜትና አመክንዮ የሚባሉት ግብዓቶች ላይ “ነፍስ ወይም መንፈስ” የሚል ሦስተኛ ግብዓት ይጨምራሉ። በመሆኑም ትክክለኛው የሰው ልጅ እንደ ልሂቃኑ አስተምህሮ ከሦስቱ ግብዓቶች በአንደኛው አሸናፊነት የሚገለጥ ነው – ወይ በስሜት አሊያም በአመክንዮ ወይም ደግሞ በመንፈስ!!!
በተለያዩ ዘመናት ላይ የሰው ልጅ ከሦስቱ ኩነቶች በአንዱ እየተገለጠ እዚህ ዘመን ላይ ደርሰናል። የሚያሳዝነው ግን እስከ ዛሬ ድረስ ያለው የሰው ልጅ ስልጣኔ፣ የሰውን ልጅ በምልዑነት (ስጋዊ፣ አመክኖያዊና መንፈሳዊ ህይወትን ባጣመረ መልኩ) መግለጥ አለመቻሉ ነው፡፡ በስልጣኔያችን ሁሉ የሰው ልጅ እየተገለጠ ያለው ሁልጊዜ በአንደኛው ፅንፍ ብቻ ነው፡፡ እስኪ ከጥንቱ ጀምረን የሰው ልጅ የተገለጠባቸውን ኩነቶች እንመልከት።
ፕሌቶ፤ የሰው ልጅ ህይወት ሁልጊዜ ለበላይነት እርስበርስ በሚሻኮቱ ሦስት ነገሮች የተገነባ ነው ይላል — ስሜት፣ መንፈስና አመክንዮ (Appitite, Spirit and Reason/Intellect). ፕሌቶ፣ “አመክንዮ ቋሚ የሆነ የማይለዋወጥ የነፍስ ባህሪ ስለሆነ፣ ተለዋዋጭ የስጋ ባህሪ የሆኑትን ስሜትንና መንፈስን መግዛት አለበት፤” የሚል አመለካከት አለው፡፡ በመሆኑም፣ በፕሌቶ አመለካከት ትክክለኛው የሰው ልጅ መገለጥ ያለበት በአመክንዮ ብቻ ነው — ዓለማዊ ህይወትን ንቆ ለዕውቀት ብቻ የሚተጋ፣ ስጋዊ ስሜቶቹን በአመክንዮ ኃይል ድል የሚያደርግ ሰው!! አብዛኛዎቹ የጥንቱ ዘመን ምዕራባውያን ፈላስፎች የሰውን ልጅ በአመክንዮ ነበር የገለጡት፡፡
መካከለኛው ዘመን ላይ ደግሞ “የጥንቱ አመክንዮ” ተሻረና የሰው ልጅ በመንፈስ ብቻ ተገለጠ፡፡ ክርስትናም የዚህ የአዲሱ ሰው መገለጥ ምክንያት ሆነ፡፡ በዚህም በጥንቱ ዘመን ላይ የሰው ልጅን በአመክንዮ የገለጠውን ጥበብ አንፈልግም ተባለ፡፡ “በአመክንዮ የተገለጠው የሰው ልጅ ትክክለኛው የሰው ልጅ አይደለም፤ ትክክለኛው የሰው ልጅ ገና አሁን ነው የተገለጠው” ተባለ፡፡
 በዚህም በመንፈስ የተገለጠው አዲሱ የሰው ልጅ ዓለምን እየናቀ ህይወቱን በየገዳማቱ አደረገ፤ ከምድር ጋር ሲታገሉ የነበሩ እጆቹም፣ አሁን ወደ ሰማይ ብቻ ተዘርግተው ቀሩ፡፡ ዕውቀትም — ስነ ምግባርም፣ ህይወትም — እስትንፋስም፣ ርዕይም — ህልምም ሁሉ መንፈሳዊ ህይወት ብቻ ሆነ፤ መንፈሳዊ ህይወት የማናቸውም ነገር መጨረሻና መደምደሚያ ሆነ፡፡ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስም እንዲህ ይላሉ፡-
በዚያ ዘመን ትምህርትና ዕውቀት የሚባል ነገር ሕሊና በገዛ ራሱ ህግጋት እየተመራ በመመርመር የሚገኝ መሆኑ ቀርቶ አንዲት መፅሐፍ በመተርጎም ብቻ የሚገኝ ሆነ፡፡
በዚህም የተነሳ፣ የሰው ልጅ በራሱ ጥረት ዕውቀት ማመንጨት የማይችል ደካማ መሆኑ ተሰማው፡፡ የሰው ልጅ መለኮታዊ እገዛ ካልተደረገለት በራሱ መቆም የማይችል ደካማ ሆነ፤ በራሱ ስልጣንና ኃይል የሌለው፣ በራሱ ምንም ነገር ማድረግ የማይችል ልፍስፍስ ሆነ። ህመሙን የሚፈውስለት፣ ስብራቱን የሚጠግንለት፣ ውድቀቱን የሚሸከምለት፣ ጤናውን የሚጠብቅለት፣ ስነምግባሩን የሚያንፅለት፣ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ችግሮቹን የሚፈታለት… ሁሉ ሌላ ውጫዊ ኃይል ሆነ፡፡ በአጠቃላይ መላው ህይወቱ የራሱ አይደለም፤ ይልቅስ ከእሱ ውጭ ለሆነ ሌላ መለኮታዊ ኃይል የተሰጠ ነው እንጂ፡፡ በአውሮፓ ለ1000 ዓመታት እንደዚህ ሆነ፤ በእኛ ሀገር ደግሞ ለ1600 ዓመታት፡፡
በዚህም ምክንያት፣ በመንፈስ የተገለጠው የሰው ልጅ፤ በመንፈሳዊ ህይወቱ ከተጎናፀፈው ከፍታ በተቃራኒ በዓለማዊ ህይወቱ ጎስቋላ ሆነ፡፡ ተፈጥሮም ሰለጠነችበት — ወረርሽኝ እየመጣ በጅምላ ህይወቱን ያጭደው ጀመር፤ ጎርፍ እየመጣ ያለ መጠለያ ያስቀረው ነበር። እንደዚህም ሆኖ ግን በመንፈስ የተገለጠውን የሰው ልጅ ለመጠበቅ ሲል በመስቀል ጦርነቶች ህይወቱን እየገበረ ኖሯል፡፡ ህይወቱን ሊገብር በሄደበት በእነዚህ ጦርነቶች መካከል ግን የአያቶቹን መፃህፍት ከጠላት እጅ አገኛቸው። መሳሪያውንም አስቀምጦ፣ የመፃህፍቶቹንም አቧራ አራግፎ ያነባቸው ጀመር፡፡ እጅግ ተደነቀ፤ አይኖቹን ማመን አቃተው! “እውነት የኔ አያቶች ናቸው ይሄንን ምጡቅ ዕውቀት የፃፉት!” አለ፡፡ ራሱን ወቀሰ፤ በራሱ አፈረ፤ ህይወት ሊያጠፋ ሄዶ፣ ህይወት ይዞ ተመለሰ፤ “አያቶቼ ማሩኝ” አለ፡፡ በዚህም ከጥንቱ ሰው ጋር ዳግም ሊወለድ ትንሳኤ (Renaissance) ይሁን አለ፡፡
ይሄም በመንፈስ የተገለጠው ሰው ዘመን ማብቂያ ሆነ፡፡ አውሮፓውያን የድሮው ናፍቆት በረታባቸው፡፡ በጥንቱ ዘመን የተገለጠውን የሰው ልጅ ናፈቁ፡፡ በመንፈስ የተገለጠውን የሰው ልጅም አይንህን ላፈር አሉት፤ ከእሱም ጋር ያስተሳሰራቸውን ገመዶች ሁሉ አንድ በአንድ መበጠስ ጀመሩ፡፡ የሰውን ልጅ በእልህና በትዕቢት ዳግም በአመክንዮ ገለጡት፡፡ ሲሰለጥንባቸው የነበረው ተፈጥሮ ላይ ሊሰለጥኑበት የሰውን ልጅ ዳግም በአመክንዮ ገለጡ። ተፈጥሮንም እንደ ዕቃ ቆጥረው እስትንፋሱን ነጠቁት፤ እጁን ጠምዝዘውም አስገበሩት፡፡ እንዳሰቡትም የሰውን ልጅ ኃይል ከውስጥ አወጡት፤ በዚህም ተፈጥሮ ላይ ታላላቅ ድሎችን አስመዘገቡ፡፡ የምድሩም አልበቃቸው ብሎ ጠፈሩን ያስሱ ጀመር፡፡
በምድሩና በጠፈሩ ላይ ያገኙት የዕውቀት የበላይነት ግን ትዕቢትን አመጣባቸው፡፡ ዳግም በአመክንዮ የተገለጠው የሰው ልጅም ራሱን እንደ አምላክ መቁጠር ጀመረ፤ በዚህም “የአመክንዮ አምልኮ” ውስጥ ወደቀ፡፡ ከመለኮት ጋር የነበረውን ትስስርም በጠሰ፤ “እግዚአብሔርም ሞቷል” አለ (ፈላስፋው ኒቸን ያስታውሷል)፡፡ በዚህም የሰው ልጅ ከምንጩ ተገነጠለ። ህይወት ትርጉም ሰጪውን አጣ፡፡ በአመክንዮ የተገለጠው የሰው ልጅ ፍርሃት፣ ድብርት፣ ብቸኝነት፣ ስልቹነት፣ ትርጉም የለሽነት ወረረው፡፡ የማህበራዊነት ስሜቱን ተነጥቆም የሰው ልጅ በየፊናው ተበታተነ፡፡ በዚህም የወንድማማችነት ስሜት ጠፋ፡፡ እናም ወንድም ወንድሙን ለመግዛት ተመኘ፤ ተመኝቶም አልቀረም፣ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ ሰብዓዊነት ታላቅ ፈተና ውስጥ ወደቀ፤ ሁለት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶችንም ፈጠረ፤ በእርስበርስ ጦርነቶችም የሰው ልጅ በጅምላ ተፈጀ፡፡
በአመክንዮ ብቻ የተገለጠው የሰው ልጅ እጣ ፈንታ አሳዛኝ ሆነ፡፡ የአንድ ፅንፍ መገለጥ መጨረሻው ውድመት ሆነ፡፡ የሰው ልጅ ስልጣኔ ምልዑን ሰው በመግለጥ ረገድ ገና አልተሳካለትም፡፡ ሁልጊዜም ጉዟችን ከአንደኛው ፅንፍ ወደ አንደኛው ፅንፍ መላጋት ነው፡፡ ይሄም የፅንፍ ጉዞ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ደግሞ Post-modernists (Deconstructionists) የሚባሉ ልሂቃን መጡና አመክንዮንና በአመክንዮ የተገለጠውን ሰው አፈር አበሉት፡፡ እርስበርስ የሚግባባበትን መሰረትም ናዱት። እውነትና ስነምግባርም አንፃራዊ ሆነ፤ የአንተና የእኔ እውነት ተለያዩ፤ የእሱና የእሷ የሥነ ምግባር ምንጭም አራንባና ቆቦ ሆኑ፤ ግለሰባዊነት ያለቅጥ ገነገነ፡፡ በዚህም የሰው ልጅ እርስበርስ የማይግባባ ፍጡር ሆነ፡፡
ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ በጣም አንፀባራቂ ሆኖ የሚወጣው እዚህ ጋ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብ የሰውን ልጅ ለመግለጥ የሚሞክረው በመንፈሳዊነትና በዓለማዊነት፣ በሂብራይዝምና በሄለኒዝም፣ በመንፈሳዊነትና በፍልስፍና፣ በስሜትና በአመክንዮ፣ በመንፈስና በስጋ መካከል ሚዛኑን ጠብቆ ነው፡፡ ይሄም እስከ ዛሬ ድረስ ያልተሞከረው መካከለኛው መንገድ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ፀሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እንዲሁም “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”፣ “ፍልስፍና ፩ እና ፪” መፅሐፍት ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 3659 times