Saturday, 19 August 2017 13:04

የቡቾ (የቡሄ) ትዝታዎች - (በላስታ ላልይበላ አካባቢ)

Written by  አጥናፉ አበራ አክሊል
Rate this item
(1 Vote)

 ክረምት ይዟቸዉ ከሚመጣዉ ነገሮች መካከል ቡቾ (ቡሄ) አንዱ ነዉ፡፡ እኔ በተወለድኩበት ላስታ፣ ላልይበላ ቡቾ ይባላል፡፡ ሀይማኖታዊ ትዉፊቱ እንዳለ ሆኖ ቡቾ ማለት ሙልሙል ዳቦ ነዉ፤ ለወቅቱ መጠሪያም ያገለግላል፡፡  ከዚህ በታች የቀረበዉ ጽሁፍም ወንድ እረኞችና ቡቾ ያላቸዉን መስተጋብር ብቻ ይመለከታል፡፡  
ፍልሰታ ገባሁ ገባሁ ስትል፣ ከነሀሴ መባቻ ቀደም  ብሎ በሀምሌ የመጨረሻዎቹ ረቡዕ አርብ ላይ እረኞች ጥርሾ እንይዛለን፡፡ ጥርሾ መያዣዉ ይባላል፡፡ ጥርሾ ከዳቦ እሚለይበት ሳይቦካ መጋገሩ፣ ጋጋሪዎቹ እናቶቻችን እንዲበስልላቸዉ በጣቶቻቸዉ ወጋ ወጋ አድርገዉ፣ ምጣድ ሙሉ ሆኖ፣ ከዳቦ ሳሳ ብሎ መጋገሩ ብቻ ነዉ። ታዲያ አንድ ሙሉ ጥርሾ እየተቆረሰ፣ ለብዙ ልጆች ምሳ ሊሆን ይችላል፡፡ መያዣችንም የድሃ ልጅ ሰባብሮ በአኩፋዳ፣ የሀብታም ልጅ በአገልግል ነዉ፡፡ ይህንን የበላ እረኛ ረሃብ እስከ ማታ ሳይነካዉ፣ እያፎጫጨ፣ ከፍየል ከበጎቹ ጋር አማን ይዉላል፡፡ እናቴ ‹‹ከሆድ ይተኛል›› ትለዋለች፡፡ ይህንኑ ጥርሾ ራያዎች ስሙን ለዉጠዉ መንገሌ ይሉና በወተት እያማጉ ይበሉታል፡፡ ይጣፍጣል፤ አሁን ራሱ አንዳንድ ስኒ ምራቅ እየዋጥኩ ነዉ ማወጋችሁ። ለናንተም እምጣ! ማለት ተፈቅዷል፡፡
ዋናዋ  ጾም ፍልሰታ ከተጀመረች በኋላ እናቶቻችን የሰጡንን ይዘን ወደ ዱር ለእረኝነት ብንሰማራም ራሴን ጨምሮ ረሃብ የማንችለዉ ብዙ ነን፡፡ እኔ እንደዉ ለወጉ ምሳ ይቋጠርልኝ እንጂ ከምጠብቃቸዉ በግና ፍየሎች ጋር ከቤት ወጥቼ ሰዋራ ቦታ ስደርስ፣ በዙሪያዉ ሰዉ አለመኖሩን አረጋግጨ፣ ወደ ኮፈዳየ ዘዉ ማለቴ አይቀርም፡፡ አያቴም ይህንን እያወቀች ከወንዱ አያቴ ቁጣ ለመዳን ነዉ ‘የምትቋጥርልኝ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ ‹መቸም ሰዉ የለም› ብዬ እየቀነስኩ ለመቆርጠም፣ በርከት ያለ ሽምብራ ከኮፈዳዬ ዝቄ በጉንጩ ቋጠርኩ፡፡ ካጎነበስኩበት ቀና ስል ከየት መጡ ሳይባል መምሬ ደምሌ ድንገት ከበጎችና ፍየሎቼ መሃል ደርሰዋል፡፡ ገና  እንዳየኋቸዉ ጉልበታቸዉን ለመሳለም፤ እንደሚገጥም የበግ ሙክት (ዳል) ከላይ ተንደርድሬ እስራቸዉ ገባሁ፡፡ ሽምብራዬን እንደ በግ ኩሪያ በእግራቸዉ መሀል ከዘረገፍኩ በኋላ ጉልበታቸዉን ስሜ ተነስቼ ተሳለምኩ፡፡ የአይናቸዉ አለማስተዋል ምንኛ እንደጠቀመኝ ልብ ይባልልኝ፡፡ ትንሽ ከፍ ሲሉ ዞሬ አየኋቸዉ አግራቸዉን እያራገፉ ነበር፡፡ ቀጥለዉም በከዘራቸዉ ኮንጎ ጫማቸዉን ኮረኮሩ፡፡ ሶስት ያህል ሽምብራዎች ሳይቀረቀሩባቸዉ አልቀሩም፡፡ ማምለጤ በጀ እንጂ እንዲያ ከረጢት እንደመሰልኩ አይተዉኝ ቢሆን ኖሮ የሚያሳልሙኝ ስንቱን ልጅ ባሳለሙበት ከዘራቸዉ ነበር፡፡      
ታዲያ አልፎ አልፎ እንዲህ ያለዉ ነገር ያጋጥም እንጂ እረኞቹ ጋርም ቢሆን ድንጋይ ወደ ሰማይ ወርዉረን፣ ሰዓት እናዉቃለን የምንለዉ ነገር ነበር፡፡ ድንጋዩን ሽቅብ ወርዉረን፤ ተመልሶ ከመጣ፣ ሰዓት ገና ሲሆን፤ በዚያዉ ከቀረ ደግሞ ሰዓት እንደደረሰ ይቆጠራል፡፡ ሀብታሙ የተባለ የእረኝነት ባልደረባችን የሚወረዉረዉ ድንጋይ ግን ተመልሶ መጥቶ አያዉቅም፡፡ ስለዚህ ሰዓት የመጠንቆል እድል ለሀብቴ በብዛት ይሰጠዋል፡፡ ትንሽ ወደ ጎን ጋደም አድርጎ ተመልሶ በማይመጣበት አኳኋን ሽቅብ ይወረዉረዉ እንደነበር የደረስኩበት ግን በቅርብ ጊዜ ነዉ፡፡ ለካ ሀብቴ የመሬት ስበት (ግራቪቲ) ቀድሞ ተገልጦለት ኖሯል፡፡
የምንበላዉ ለምድ አንጥፈን ዙሪያዉን ከበን፣ አብሮን ባለዉ ትልቅ እረኛ ተባርኮ ነዉ፡፡ ለምድ ከነጸጉሩ በመደበኛ ልብስ ላይ ለብርድም፤ ሸክም እንዳይጎረብጥም የሚለበስ የበግ ቆዳ ነዉ፡፡ ለምድ ከተነሳ ዘመዱ ብልባል ለምን የኔስ ይቀርብኛል ብሎ ያኮርፍ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ ከከብት ቆዳ ታርቦና ተለስልሶ የሚዘጋጅ የቆዳ ልብስ ሲሆን በብዛት በትልልቅ ሰዎች ይዘወተራል፡፡ ብልባል ሲነሳ ደግሞ የቀያችን ሽማግሌ አባ አስናቀ፣ ከላይ ከናቲራ ነገር ከታች ብልባል ብቻ አሸርጠዉ በተራራዉ ብቅ ይላሉ። አባ አስናቀ፣ በዱር ሲዘዋወሩ ጎርፍ ያመጣዉ ግንድ አያግኙ እንጂ ካገኙ ብልባሉን አዉልቀዉ ተሸክመዉበት ይመጣሉ፡፡ ዉሀ ሊቀዱ ወደ ወንዝ ከእንስራቸዉ ጋር የሚሄዱ ሴቶች ጋር ከተገጣጠሙ ሴቶቹ፤ ‹‹ኧረ እናቴ ድረሽ›› ብለዉ መንገድ ይቀይራሉ፡፡ አላፊ አግዳሚዉ ሁሉ በፈገግታ ታጅቦ እየጎበኛቸዉ ቢያልፍም፤ ነገርዬዉን  እንደ ጢማቸዉ አንዠርገዉት ሲሄዱ በቃ ለአባ አስናቀ ጉዳያቸዉ አይደለም፡፡    
ወደ ላይኛዉ የወጋችን አናት እንመለስ፡፡ በክረምት ማንኛዉም እንስሳ ወደ ዱር ከመሰማራቱ አስቀድሞ የመንደራችን መሀል የሚገኝ ጠፈፍታ ቦታ (ምሳግ) ፀሀይ እየሞቀ ይመሰገጋል፡፡ በተለይ ስራ በሌለ ቀን ብዙ እረኛና የመንደሩ ሰዉ እዚህ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ ጅራፍ ይፈተላል፤ ኮፈዳ ይሰራል፡፡ ብዙ ጨዋታ ይደራበታል፡፡ ጎረምሶች ታዳጊዎችን ትግል ያጋጥሙና ተሸናፊዉን በያዙት ጅራፍ ገርፈዉ፣ ያንኑ ጅራፍ ለአሸናፊዉ ይሸልማሉ፡፡ ስለዚህ ማንም እረኛ ሽልማቱ ቢቀር እንኳ ቢያንስ ላለመገረፍ የቻለዉን ያህል ተፍገምግሞ ካልተሳካ እያመመዉም ቢሆን ከወደቀበት ተነስቶ ይፈረጥጣል፡፡  የተሸናፊ አበሳ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ታናሽ ወንድም ወይም እህት ያየ እንደሆነ ‹‹እኔን ብቻ ነዉ የምትጥሰዉ›› ብሎ ያላግጥና፣ ማታ ከቤተሰብ መሀል ሲያሳጣ መከራ ነዉ፡፡ ቤተሰቡም ‹‹ሊጥ ዋጭ፤ አሁን አንተ የኔ ልጅ ነህ. . . . ›› የሚሉ ስድብና ማሸማቀቂያዎችን ምድጃ ከቦ ሲያወርድ ያመሻል፡፡ እና  ተሸናፊ ሌት ተቀን አስቦ ድሉን መመለስ ይኖርበታል። ወይም ከባለ ድሉ ጋር በመመካከር፣ ሁለተኛዉ ቀን ላይ በተራዉ አዉቆ እንዲወድቅ ስምምነት ላይ ሊደረስና እፎይ ሊባል ይችላል፡፡ ይሄን ለማድረግ የሁለቱ የቀድሞ ወዳጅነት ትልቅ ዋጋ አለዉ፡፡       
ይህን ሁሉ በምንሆንበት በዚሁ ምሳግ፣ ሽንት ከወደ ላይ በኩል መንገድ ገብቶ እየተንኮለኮለ ቁልቁል ይመጣል፡፡ አባ አስናቀ ከፍ ብለዉ ጸሀይ የሚሞቁ የመንደሩ ሰዎች ጋር ከእነ ብልባላቸዉ ተቀምጠዉ እየተጨዋወቱ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ‹‹ለትልቅ ሰዉ ይመስል እንዴት ሰዉ ስራዬ ብሎ ለሽንት ይነሳል?›› ይላሉ፡፡ እና ሽንታቸዉ ከብልባላቸዉ ስር ከሚገኝ የዛለ የተፈጥሮ የግል ቧንቧ ተነስቶ ቁልቁል እንዲፈስ አያግዱትም፡፡
እንግዲህ መቸም ቀኑ እየሄደ ፍልሰታ እንደነገሩ ሆና፣ ዳቦ ተክታልን ትጠናቀቃለች፡፡ በዚህ ሰሞን ወዳጅ ዘመድ ልጅ ወዳለበት ቤት በልጆች ቁጥር ልክ፤ ከመሶብ በማይተናነስ አገልግል ቡቾ ይልካል ወይም ይወስዳል፡፡
ይሄ ጊዜ ለእረኞች በጣም ተወዳጅ ጊዜ ነዉ፡፡ ወደ ምንሄድበት ቤት ከልጆች ጋር መጫወቱ፤ በዚሁ አሳቦ ለተወሰኑ ቀናት ከእረኝነት ገለል ማለቱና መላላኩ፣ በራሱም ቢሆን ደስ የሚል ነገር አለዉ፡፡ በምላሹ ሌላ ቡቾም፣ ከኛ ቤት ላለነዉ  ልጆችም ይዞ መምጣት ይኖራል፡፡
የአንዱ ዓመት የቡቾ በዓል በተላኩበት ጊዜ ግን በመንገድ ያልጠበቅሁት ነገር እንዳጋጠመኝ እንዴት ይረሳል? በዚህ ሰሞን ጅራፍ ግርፊያ የበዓሉ አንድ አካል ነዉ፡፡ ተሸናፊ አንድ ቡቾ ይከፍላል፡፡ ጎበዝ የሆነ ተጋራፊ ወደ ማታ ላይ እረኛዉ ሁሉ ተሰባስቦ ባይበላበት የሚሰበስበዉ ቡቾ መስከረምን ለማዝለቅ አያንገራግረዉም፡፡ እናም እኔ በምዘልቅበት እንደ ምሰሶ በቆመ አቀበት ወገብ እረኞች ጅራፍ ግርፊያ ይጫወቱ ነበር፡፡ አራት ያህል ሙልሙል ዳቦዎች መቋጠሬ ትዝ ይለኛል፡፡  
አንዱ እረኛ ታዲያ በያዝኩት ዳቦ (ቡቾ) እንድጫወትበት አግባባኝ፡፡ እምቢ ማለቱ የፍርሀት እንዳይመስልብኝና የምሸነፍም ስላልመሰለኝ ተስማማሁ። ከሰጡኝ ጅራፍና ከዱላየ በስተቀር ሌላዉን ሁሉ ጓዜን አስቀመጥኩ፡፡ ዱላዉን ተጠራጥሬ እምቢ አልጥልም ስላልኩ እንጂ የጨዋታዉ ህግ የሚፈቅድ አይደለም። ከወዲያ አንድ፣ ከወዲህ አንድ ግርፊያዉ ተጀመረ፡፡ ከትንሽ የጅራፍ ምልልስ በኋላ ከወደታች የከፋ ስሜት ተሰምቶኝ እግሬ ደም ለበሰ፡፡ የጅራፉ ጫፍ ላይ የታሰረች ምላጭ ባቴን ቀርድዳኝ ኖሯል፡፡ ለክፉ ቀን የያዝኩትን ዱላ በጅራፉ ቀየርኩ፡፡ ተጋጣሚዬም ድንገት እግሬ ስር መሸብለሉን ተከትሎ፣ እረኛዉ ሁሉ እንደ ንብ ተገልብጦ እኔ ላይ ሰፈረ፡፡ እንደምንም ሽቅብ  አምልጬ ድንጋይ አንከባልዬ ነዉ የመለስኳቸዉ፡፡  እንድጫወት ያግባባኝ እረኛ፣ ዳቦዎቹን አንድ አንድ ጊዜ እየገመጠ ከአገልግሉ እየፈታ ቁልቁል አሽከረከራቸዉ፡፡ ከማረፋቸዉ በፊት በረጅሙ ገደል እየተፈረፈሩ አለቁ፡፡ ወደ የት እንደምሄድ፣ ለምጠየቀዉ ጥያቄም ምን እንደምመልስ ስለጨነቀኝ፣ ባለሁበት ተቀምጬ ያለቀስኩት ለቅሶ የተለየ ነበር። ይሄዉ እንግዲህ ቡቾ እንዲህም ጉድ ሰርቶኛል ነዉ የምላችሁ!    
ሌላኛዉ የዚህ በዓል አይቀሬ ነገር ‹‹እሆዬ›› (ሆያ ሆዬ) ነዉ፡፡ እሆዬ በላስታ፣ በቡሄ ሰሞን ብቻ የሚባል ነዉ፡፡  ቀን ገደል ለገደል ስንንከራተት ዉለን፤ ከወትሮዉ አስቀድመን፣ ግልገሉን ወደ ቤት ከተን ስንወጣ፣ እራት የምንበላበት ጊዜ እንኳን የለንም፡፡ ጅራፍ በየቀየዉ ሲኖጋ ልባችን ይሸበራል፡፡ እራት ትዝ አይልም፤ ወይም በእጃችን ይዘን እየገመጥን እንወጣለን፡፡
ከትልልቅ ሰዎች ቤት ይጀመራል፤ ወደ ቤቱ በር አካባቢ ሲደረስ የሚከተለዉ ግጥም፣ ለስለስና ዘለግ ባለ ዜማ በቅብብል ይባላል፡፡  
‹‹ክፈት በለዉ ተነሳ
ያያ ወንዱን ጎረምሳ
ክፈት በለዉ በሩን
ያያ ወንዱን
እሜቴ ይነሱ
እሳት ያድበሰብሱ
እባባም ይነሱ
ሱሪዎን ይልበሱ››
ቀጥሎ ደግሞ የቤቱ ደጃፍ ላይ በዜማ እንዲሁም በዱላ መሬት እየተረገጠ ይባላል፡፡
‹‹ . . .እሆይ ንሆዬ
 እሆይ ንሆዬ
እሆዬ ‘ላለሁኝ
ዳቦ እወዳለሁኝ
እሆ!..
ሆ በል
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ
    ደጃፉን ሲነኩት ይላል አቤት አቤት
 እሆ!..
ሆ በል
እሆይ ንሆዬ
    [አምባዬ አክሊሉ] የደማስ ባለቤት
እሆ!  
ሆ በል!
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ . . . . ››  ጌታዉን እመቤቲቱን በማወደስ  እንቀጥላለን፡፡
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ
እሆይ ንሆዬ በል!
መሬት ጭሬ ጭሬ አወጣሁ መግላሊት
እሆ !
ሆ በል!
እሆይ ንሆዬ
[አበባዬ አስማረ] የሆዴ መድሀኒት
እሆይ ንሆ በል! …››
የሚበቃዉን ያህል ካልን በኋላ፣ እኚሁ ጌታ ወይም እመቤት ጭፈራችንን አስቁመዉ ያናግሩናል፡፡
‹‹ እንዴት ናችሁ ልጆይ?››
‹‹መስጌ ...ን፤ ደህና ነነ . . . ›› ከጭፈራዉ ተግ ብለን፣ በህብረት እንመልሳለን፡፡
እንኳን ለዓመቱ አደረሳችሁ አለበለዚያም መሰል ምኞታቸዉን አክለዉ፤
‹‹አዳ ምን ፈልጋችሁ ነዉ የመጣችሁት?››  ይላሉ፡፡
‹‹. . . የለመድነዉን ‹ምሳችንን› ነዉ እንጂ››
‹‹ምሳችሁ ምንድነዉ?››
‹‹ዳቦና ጠላ››
ባልና ሚስቱ ትንሽ ምክክር ያደርጉና፤
‹‹በሉ እንግዲህ ላሚቱ/ሞቹ/ ደህና የወለደች/ዱ/ እንደሆነ (ካሉ)፤ አዝመራዉም ደህና ካፈራ፤ ለዚያ ያድርሰን እንጂ፤ አንድ ኩሪት ጠላ፣ ከነ መክደኛዉና አንድ ገንቦ እርጎ፣ የህዳር ሚካኤል ይቆያችኋል›› እንባላለን፡፡   መክደኛ የተባለዉ ሙጌራ ዳቦ ነዉ፡፡ ይሄኔ ተጨብጭቦ አልልታ ይቀልጣል፡፡ እንደዉ ይሄ ለአብነት ተጠቀሰ እንጂ የምንሰጠዉ እህል ዉሀና የምንሰጥበት ቀን እንደየ ቤቱ እንደየ ማጀቱ የተለያየ ነዉ፡፡  
አሁንም በሌላ ዜማና ግጥም ቅብብሎሽ፣ ምድር በዱላ እየተረገጠ ይጨፈራል፡፡   
‹‹አይ ስምምየ
ሲሞ
ስምምዬ
ሲሞ
ስምምዬ
ሲሞ ….››   ዳቦና ጠላዉ ቃል ከተገባ በኋላ የሚባለዉ አብዛኛዉ ግጥም የ‹ብልግና› የምንላቸዉን ቃላት ይጠቀማል፡፡ በመጨረሻም ራሳችን መርቁን ብለን አመስግነን፤ አለበለዚያ ደግሞ ራሳቸዉ ‹ይመሽባችኋል› ብለዉ መርቀዉ፣ ወደ ሌላ ቤት ያሰናብቱናል፡፡ ‹‹እስቲ ግቡ›› ብሎ ምድጃ ዳር ‹‹እንዲህ በሉ እስቲ›› እያለ ግጥም እየሰጠ አረጋገጡን እያሳየ፣ አብሮን የሚረግጥም የሚያስረግጠንም አባወራ ይኖራል፡፡ ወደ ሌላ ራቅ ወዳለ ቤት የምንሄድ ከሆነ፣ ሌላ ጭፈራ (አሀይ ሎጋ አይነት) እየጨፈርን እንሄዳለን፡፡ በዚህ መልኩ እንግዲህ በየቤቱ ዙረን ዙረን፣ በጣም ሲመሽ ከአንዱ ቤት ‹‹እደሩ መሽቷል… ሌላዉን ነገ ትሉታላችሁ… ጅብ እንዳይበላችሁ›› እንባልና እንገባለን። እንደየ አቅሙ ቢለያይም እራት የሚያበላንም ሊኖር ይችላል፡፡ ከምናድርበት ቤት እርስ በራሳችን የምንሰራዉ ተንኮል፣ ለሰሪዉና ለተመልካቹ እጅግ አስቂኝ፣ ለሚሰራበት ደግሞ የሚያናድድ ነዉ፡፡ ጥቂቶቹን እናንሳ፡፡
ሁሉም ሰዉ ሲተኛ  አንድ ተንኮለኛ ወይም በህብረት ሆኖ በጨለማ ዉሀ ፈልጎ ወይም ሳይታወቅ፣ ዉሀዉን ቀድሞ ያዘጋጅና አመድ በወፍራሙ ያቦካል፡፡ ከዚያም ልክ ወፍራም “ሰገራ” በሚመስል መልኩ አድበልብሎ፣ እንቅልፍ ባሸነፋቸዉ እረኞች ቁምጣ ዉስጥ መክተትና ጧት ሲነሱ፣ ከቁምጣቸዉ እየሾለከ ሲወድቅ፣ ከራሳቸዉ ቂጥ እንዳመለጠ አስመስሎ፣ ለዚያ ሁሉ ሰዉ መሳቂያ መሳለቂያ ማድረግ አንዱ ነዉ፡፡
ሌላኛዉ ብልትን በጅራፍ ይሁን በሌላ ገመድ ከወጋግራ ወይም ከሌላ እረኛ ጋር ማሰር ሲሆን ይሄ የተደረገበት እረኛ ነግቶ ከመነሳቱ በፊት በእንቅልፍ ልቡ ሲገላበጥ፣ ስለሚሸመቅቀዉ ጮሆ ራሱን ያጋልጣል፡፡ እንደዉ አይጣል ነዉ እንጂ እረኛ መስላዉ ባለቤቲቱን እመቤት ሁለት እግሯን በጉንጉን ገመድ ግጥም አድርጎ ማሰርም ያጋጥማል፡፡ የሚታሰረዉን ፈልጎ ሲያጣዉስ!?
ሌሊት በደንብ ያልሰማ ሲነጋ ማነዉ የጮኸዉ ብሎ ጠይቆ፣ አሁንም መሳቂያ ያደርገዋል፡፡ የብረት ምጣድ ወይም የምጣድ ‹ጥላት›፣ አገር ደህና ብሎ በተኛ እረኛ ፊት ድምቅ ብሎ ይቀባል፡፡ ያዉ መንጋት አይቀርም፡፡ ንጋት ላይ ጥቁር አህያ አለያም ጭምብል ያጠለቀ ተዋናይ መስሎ፣ በማን እንደሚሳቅ እስኪያዉቀዉ አብሮ ሲስቅ ማርፈድም አለ፡፡
እኒህና የመሳሰሉት ተንኮሎች የተሰሩበት እረኛ፣ የተንኮሉ ባለቤት ማን እንደሆነ ጠይቆ ያዉቃል እንጂ ለጠብ አይጋበዝም፡፡ በቀጣዩ ቀን ግን ቢችል ብድሩን ይመልሳል፣ ካልሆነ ግን ቁልጭ ብሎ ያድራል፡፡ የሆነዉ ይሁን ብሎ እንቅልፍን የሚልፍም አይጠፋም፡፡  
እሆየ የምንልበት የጊዜ እርዝማኔ፣ ሁሉንም የመንደሩን ቤቶች ብለን እስከጨረስን ድረስ ስለሆነ እስከ አራት አምስት ቀን… እሰከ ሳምንትም ሊዘልቅ ይችላል፡፡
አስቀድመን የምንመርጠዉ አለቃ፤ ማን ምንና ለመቼ እንደቀጠረን ይከታተላል፡፡ ቀኑ ሲደርስም ባለ ድግሱ እረኛም ሆነ አለቃዉ ወይም ራሳቸዉ ባለቤቶቹ ለእረኞች ያሳዉቃሉ፡፡ እኛም በዕለቱ ማታ እየጨፈርን እንሄዳለን። ባለቤቶቹ የተሳሉትን ስለት ቆጥረዉ ለአለቃዉ በኛ መሀል ያስረክባሉ፤ እልል ብለን ከተቀበልን በኋላ ለራሱ ለአባዉራዉ አስባርከን፣ በማዕድ በአግባቡ ተሰርቶ እቤት ያለዉ ሰዉ ሁሉ ይበላል፤ ጎረቤትም ሊጋበዝ ይችላል፡፡ ሁሉም ሰዉ በልቶ ሲጨርስ ደግሞ ተነስተን አመስግነን፣ መርቀንና አጨብጭበን፣ ማዕዱን ከፍ እናደርጋለን (እናነሳለን)፡፡
ከዚህ በኋላ እንግዲህ ‹‹እስቲ ደ’ሞ አንገታችሁ ይታይ›› ተብለን አንገታችን የሚታይበት ነዉ፡፡ በድምጥም ሆነ በእስክታ የቻልነዉን እያዋጣን፣ ሞቅ አድርገን እያወደስን፣ እየተወዳደስን ስንጫወት እናመሻለን፡፡ ሽልማትም ይኖራል፡፡ ሌሊቱን ያለ አንቅልፍ የምናነጋበት ጊዜም አለ፡፡ እሳት ጠፋ ካለ ደግሞ እስከሚነድ ከቤት፣ አለዚያም ከጎረቤት የመጡ እኩዮቻችንን የምንጎነትልበት ልዩና የማይገኝ አጋጣሚ ይህ ነዉ፡፡           
በነገራችን ላይ እሆዬ ባይ እረኛ፣ በሚያድርበት ቤት ዉስጥ የምትገኝ ልጃገረድ፣ በቤተሰብ በኩል ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላታል፡፡ እናም በአንዱ ሌሊት ከአባቷ ጎን ለጎን የተኛች ልጃገረድ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ጩኸቷን ለቀቀችዉ፤ ሁሉም በርግጎ ከያለበት ተነሳ፡፡ የተተናኮላትን እረኛ ሊፈርዱበት አባቷ ደህና ሽመል አዘጋጅተዉ፤ እኛም ተደብዳቢዉን ለማየትና ለስላቅ አሰፍስፈን እሳት ቢነድ፤ ተረስቶ ያልታሰረ የአህያ ዉርንጭላ፣ ጆሮዉን ሸምጥጦ ቆሞ ተገኘ፡፡ ለካ አጅሬ ጥሬ ፍለጋ ሲያልፍ፣ ጆሮዋ ላይ ‹ቡፍፍ› ብሎባት ኖሯል፡፡
ከፍ ሲል የቀረበዉ ቃል የገቡልን አባወራዎችና እማወራዎች በቀጠሩን ቀን መሰረት፣ በቃላቸዉ ተገኝተዉ የደገሱልን እንደሆነ ነዉ፡፡ ከዚህ ሌላ ግን ቀን የሚያዛዉር ጭራሹንም “እንቆቅላችሁ” የሚል አይታጣም፡፡ የቀን ቅያሬዎቹን ያለ ማቅማማት የምንቀበል ሲሆን “አንሰጥም” ብለዉ የሚክዱት ግን በራሳቸዉ ላይ ሌላ መዘዝ ይከተልባቸዋል፡፡
በማግስቱ ማልደን ተነስተን አባዉራዉን ወይም እማዉራዋን እንደሞቱ በማስመሰል፣ ለወዳጅ ዘመዱ እንዲደርስ እያልን ጥሪ እንጠራለን፡፡ በዚህም ለኛ እምቢ ያሉትን እህል ዉሀ፣ ሩቅ አገር ያለ ዘመድ ሀዘንተኛ ሆኖ መጥቶ ለቃቅሞ እንዲበላባቸዉ እናደርግ ነበር፡፡ ይሄ አካሄድ ግን በጣም አደገኛና ጸብም የሚያስነሳ በመሆኑ እየቆየ እየቀረና እየጠፋ መጥቷል፡፡
በጠቅላላ  እንግዲህ ወንድ እረኞችና ቡቾ (ቡሄ) ከብዙ በሙጫዉ እንዲህ ነዉ ዝምድናቸዉ፡፡ ነገር ግን ላስታ ሰፊ እንደመሆኑ፣ በሁሉም ላስታ አካባቢዎች ተመሳሳይ አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

Read 1446 times