Saturday, 19 August 2017 13:11

የአንድ ወጣት እጣ

Written by  ደራሲ- በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ዳሰሳ- በዘነበ ወላ ሕትመት-ፋር ኢስት ትሬዲንግ
Rate this item
(0 votes)

    የመጽሐፉ ርዕስ- የማይጻፍ ገድል
                   ደራሲ- በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
                  ዳሰሳ- በዘነበ ወላ
                     ሕትመት-ፋር ኢስት ትሬዲንግ

        ከሰላሳ ሶስት ዓመታት በፊት በአገራችን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ታውጆ ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ አማካኝነት ከአንድ እስከ አምስት ዙር በዘለቀው ዘመቻ፣ አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ስድስት መቶ ወጣቶች የዘመቻው አካል ሆነው፣ ወደ ሰሜኑ አገራችን ክፍል እንዲዘምቱ ተደርጓል፡፡ በዚህ ዘመቻም አያሌዎቹ እንደወጡ ሲቀሩ፣ ጥቂቱ በጣም ጥቂቱ ደግሞ ለዘር ተርፈው ያንን ገድል እየፃፉልን ነው፡፡
ይህንን ዘመቻ እንዳስብ ያደረገኝ በዚህ ዓመት ለንባብ የበቃው የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ‹የማይጻፍ ገድል› መጽሐፍ ነው፡፡ በእኔ መጠነኛ ንባብ ‹ውጥረትን በተስፋ የተወጣች ህይወት› በሚል ርዕስ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በ2004 ዓ.ም ለንባብ ያበቃው ጥራዝ ነበር፡፡ ለዓመታት እጄ ሳትገባ ከራርማ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አነበብኳት፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ከሰዎች ጋር ማውራት ይወዳል፡፡ አዳምጦ የወደደውን ይፅፈዋል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ስነ ፅሁፍም አብሮ አደጉ ነው፡፡ የምስራቁ ዓለም ፍልስፍናም ሆነ ስነ ፅሁፍ ብዙም ቀልቡን አይስበውም፡፡ መጓዝ ይወዳል፡፡ ባላጋንን ከዓለማችን እግሩ ያረገጠው አህጉር ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዱ ስናወጋ፤ “ዶ/ር ጌታቸው ከአርባ በላይ አገሮችን ጎብኝቷል” ብዬ ለወዳጆቼ ባወጋ፣ እሱም አብሮን ስለነበረ “ከሰባ በላይ አገሮችን ነው የጎበኘሁት” ሲል አርሞኛል፡፡ በዚህ ጉዞው ያጋጠሙትን ድንቅ ታሪኮች እንደዋዛ አያልፋቸውም፡፡ ቀደም ብሎ በጠቀስኩት ጥራዝ ውስጥ ስዊድን ስቶኮልም ካጋጠመው አንድ አንደበተ ርቱዕ ወጣት አውግቶት የቀሰመው መሆኑን ይገልፅልናል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ዋናውን ተራኪ ገረመው አለሙ ይለዋል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ የሚጠቅሳቸው ባህሪያት ሁሉ ስማቸው ተቀይሯል፡፡ በተረፈ በደም፣ በአጥንትና በስጋቸው የተፃፈውን እውነተኛ ታሪክ፤ ተነባቢ በሆነ ቋንቋ ተርኮልናል፡፡
ባለታሪኩ ገረመው አለሙ፤ የአዲስ አበባ የቡልጋሪያ አካባቢ ልጅ ነው፡፡ ከሞቀ ህይወቱ ወደ ብሄራዊ ውትድርና፣ ከዚያም ስልጠና በኋላም ከሰራዊቱ መኮብለልን በስደት በጅቡቲ በኩል አድርጎ አውሮፓ መዝለቅ እያለ… እያንዳንዷን ፈታኝ አሳር ተቋቁሞ፣ አውሮፓ በመግባት፣ የእርሱም ሆነ የጓደኞቹ ህይወት፣ እንዴት አስደሳች በሆነ ሁኔታ እንደተጠናቀቁ ያወጋናል፡፡
‹የቀትር ሕልም› በሚል ርዕስ ንጋቱ ክፍሌ ለህትመት ያበቃው ስራው፣ በ2007 ዓ.ም ነው ለህትመት የበቃው፡፡ ደራሲ ንጋቱ በዚህ ጥራዝ ሲያወጋን፣ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ስለተበላሸበት፣ ብሄራዊ ውትድርናን በፍቃደኝነት ተቀብሎ ነው የዘመተው፡፡ በዚህ ጥራዙ ውስጥ ውትድርናውን አሜን ብሎ ተቀብሎ ግልጋሎቱ እስኪጠናቀቅ በማሰልጠኛ ጣቢያው ኖሯል፡፡ በወታደራዊው ህይወት በዲሲፒሊን አክባሪነቱና በትጋት በመስራቱ፣ አሰልጣኝ ሆኖ በጣቢያው ተመድቦ እስከ መሾም ደርሷል፡፡ በዚህም ነው ከእሱ በኋላ የመጡትን ምልምል ወታደሮች እያሰለጠነና እየሸኘ ማህበራዊ ህይወቱን እያጣጣመ፣ ሥርዓቱ እስኪፈርስ እዚያው ነበር፡፡ መጽሐፉ በመቀጠል ልጅነቱን፣ ወጣትነቱን፣ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻውን እያለ …በመሰደድ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የተጓዘበትን ገድል በተነባቢ ቋንቋ ይተርክልናል፡፡
ብሔራዊ ወታደር በድሉ ዋቅጅራ ስራ ላይ ስንመጣ የዘመተው ተገዶ ነው፡፡ ይህ ሐምሌ 2009 ዓ.ም ለሕትመት በቅቶ፣ አንባቢያን እጅ የደረሰው ‹የማይጻፈው ገድል› ሲል ያስጠረዘው መጽሐፍ በ11 ምዕራፎች፣ በ298 ገፆች ነው የተደጎሰው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ማለት እንችላለን የሚያወሳው የብሄራዊ ውትድርና ታሪኩን ነው፡፡ ለአተራረክ እንዲያመቸው ወደኋላ ሄደት ብሎ 2004 ዓ.ም ከዶ/ር ዮናስ አድማሱ እና ከዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ጋር ባህር ዳር ላይ እናገኘዋለን፡፡ ለጠቅ አድርጎ በሽግግር ወቅት ጎርጎራ (አማራው ክልል) ያስተዋለውን ተርኮልን ሳይሰናበተን መጽሐፉን ይደመድማል፡፡
ዶ/ር በድሉ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ፅሑፍ መምህር ነው፡፡ ምን አልባትም ካቻምና በአካል ስድስት ኪሎ በጋራ እህታችን ቅድስት የሺጥላ ስራ ቦታ ተገናኝተን ስንጨዋወት፣ ስለዚህ ስራው አጫወተኝ፡፡ ይህንን ልምዱን ስሰማም የመጀመሪያዬ ስለሆነ (ውትድርናን የሚያውቅ መሆኑን) ገርሞኝ፣ ብቻውን ራሱን ችሎ ቢፃፍ ድንቅ ስራ እንደሚሆን እምነቴን ገለፅኩለት፡፡ እሱም በጉዳዩ አምኖበት፣ በአጭር ጊዜ ተጠርዞ ማየቴ አስገርሞኛል፡፡ አንዳንዶችን እያወራን ለዓመታት ስናምጥ፣ አንዳንዱ ከተፎ ደግሞ ባወጋህ ማግስት ለገፀ ንባብ አድርሶ ያሳየናል፡፡
እነሆ ይህ በፍጥነት ለንባብ የበቃን መጽሐፍ፤ አንብቤ እኔም የታየኝንና እርባናውን ማሳየቱን ወደድኩ፡፡ መጽሐፉ በምዕራፎቹ መተረክ ሲጀምር በግጥም ቡራኬ ይጀምራል፡፡ ሳነብ የግጥሙ ጭብጥ እልም የይልብኝና በስድ ንባብ የቀረበው ጭብጥ ቀልቤን ይዞት ይነጉዳል፡፡ አንድ ህንፃ ሲገነባ አንዱ ጡብ በሌላው ላይ እየተደራረበ፣ የተፈለገው ኪነ ህንፃ እውን እንደሚደረግ ሁሉ የብሄራዊ ወታደር በድሉም ስራ አንዱ በሌላው ምዕራፍ ላይ እየታነፀ፣ ወደ ታሪክ ፍፃሜ ይዞኝ ይነጉዳል፡፡
ወታደራዊው ሳይንስ፣ ዲስፒሊን በእያንዳንዱ ምልምል ነብስ ውስጥ የሚገነባውን ያህል ለሳይንሱም ሆነ ለዲሲፕሊኑ ባዕድ የሆነ ምልምሎችን እናስተውላለን፡፡ ወዶ ተቀበለው ተደስቶ ሲገበይ፣ ታፍሶ የመጣው የባህል የቋንቋ ባዳ ሆነው (አማርኛ ቋንቋ የማያውቁ አያሌዎች ነበሩበት) ለስልጠናው ባዳ ለሰልጣኙም እንግዳ ሆነው እናስተውላለን። ይህንን ደራሲው ያጋጠመውን ሁሉ ተራ በተራ፣ በተገቢው ስፍራ እያሳየን ትረካውን ይቀጥላል፡፡
“‹የሰው ልጅ ከስህተቱ የማራል› የምንለው ብሂል አለን፡፡ የፈንጂ ባለሙያ ግን የመማር እድል እንደሌለው በዚህ ጥራዝ ውስጥ እናስተውላለን። ምክትል መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ ስለፈንጂ አጠቃቀም ሲያስተምራቸው ይሳሳታል፡፡ ነብስ ከስጋው እስከምትለይ ትንፋሹ እስካለች ምልምል ወታደሮቹ ራሳቸውን እንዲያድኑ ይወተውታል፡፡ ብሄራዊ ወታደር በድሉ እንደሚነግረን፣ ማንም ልብ ያለው የለም፡፡ በመጨረሻ ፈንጂውን አቅፎት፣ ራሱን ብትንትን ሲያደርገው፣ በዙሪያው ያሉ ምልምሎች ያያሉ፡፡ ይህ ከሆነ 33 ዓመታት በኋላ እነሆ ይህ ጥራዝ ለመቶ አለቃ ላቀው በዛብህ መታሰቢያ እንዲሆን ጎልማሳው ፀሐፊ አበረከተ፡፡ መቶ አለቃ ላቀው በዛብህ ይገባዋል፡፡ ያንን ወታደራዊ እርምጃ በወቅቱ ወጣቱ መኮንን ባይከውነ ኖሮ፣ ምን አልባት ይህ ደራሲም በሕይወት ሳይተርፍ ቀርቶ፣ ወይ አካለ ጎዶሎ ሆኖ የዛሬው ሰብዕናው ይኖር ይሆን? ዳኝነቱን ለህይወት እንተወው፡፡
ያ አታካች፣ ፈታኝ የሆነው ወታደራዊ ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡ ምን አልባትም በኢትዮጵያ ሰራዊት ታሪክ ውስጥ በተገቢው መንገድ ስልጠናውን ያጠናቀቀው ምልምል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወዲያው 1977 ዓ.ም ጣምራ ባዕል የነበረው 10ኛው የአብዮት በአልና የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምስረታ በዓል ይከበራል፡፡ ብሄራዊ ወታደር በድሉ ዋቅጅራ፤ ለበአሉ ድምቀት ከጓደኞቹ ጋር አብዮት አደባባይ በመገኘት በሰልፍ ትርኢት አሳየ። በሰልፍ በርዕሰ ብሄሩ ፊት አለፉ፤ በማግስቱ ቀደም ብሎ ከጓደኞቹ ጋር ሲያውጠነጥኑት የነበረውን ሀሳብ አፅድቀው ከጓደኞቹ ጋር ጠፍተው፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄዱን እውን አደረጉት፡፡
 በድሉም አሰላ ገባ፡፡ ብዙም ውሎ ሳያድር አባቱ “መቼ ነው የምትመሰለው?” በማለት ይጠይቁት ጀመር፡፡ መክዳት አይታሰብም፡፡ አባቱ የፖሊስ ሰራዊት አባል ስለሆኑ፣ ከዲስፕሊኑ ውልፊት ማለት አይቻልም፡፡ ይህ እድል የወታደር ቤተሰብ አባል የነበሩ ወጣቶች ሁሉ እጣ ነበር፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ቀደም ብዬ ባነሳሁት መጽሐፍ ውስጥ ዳንኤል የተባለው ወጣት፣ አባቱ በቀድሞ ጦር ውስጥ መኮንን በመሆናቸው ተመልሶ ሄዶ ከጓዶቹ ጋር እንዲቀላቀል አድርገውታል፡፡ የብ/ወ በድሉ ዋቅጅራም በእናቱ ወትዋችነት እረፍቱ ለአንድ ቀን ተራዝሞለት፣ በሚቀጥለው ቀን ወደ ታጠቅ ጦር ሰፈር በመመለስ ከጓደኞቹ ጋር ተቀላቅሏል፡፡
ብሔራዊ ወታደር በድሉ ዋቅጅራ የአገልግሎቱን ጊዜ ያጠናቀቀው እዚያው ማሰልጠኛ ውስጥ የተሰጠውን ስራ በማከናወን ነው፡፡ አያሌ ጓደኞቹ በኤርትራ እና በትግይ ምድር ተመድበው እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ደረጀ ደምሴ የተባለ ወጣት ‹አባቴን ያቺን ሰዓት› በሚል ርዕስ ለህትመት ባበቃው የጄነራል ደምሴ ቡልቱን የጦር፣ ሜዳ ውሎ  በሚተርክ መጽሐፉ ውስጥ በብልጭታ ያሳየናል፡፡ የጀነራሉ ልጅ ደረጀ አንደኛው ኤርትራ በረሀ አውደ ውጊያ ላይ “የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ሰማሁ፣ ብሄራዊ ወታደሮች እያዳመጡ እንደሆን ተገነዘብኩ” ይለኛል፡፡ ደረጄ በርካታ አውደ ውጊያ ላይ አባቱን ጥየቃ እየሄደ መገኘቱን በትረካው ያወሳል፡፡ እነዚህ ኤርትራ በረሃ ያያቸው ብሄራዊ ወታደሮች፤ የበድሉ ዋቅጅራ ጓደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የት ደረሱ? መጨረሻቸውስ ምን ሆነ? ምንም መረጃ የለንም፡፡
ብ/ወ በድሉ ዋቅጅራ በቀጣይ ፈታኝ አስደሳች ሕይወቱን ከለል ሳያደርግ ያወጋናል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ፍቅረኛን መነጣጠቅ ሁሉ አይደብቀንም፡፡ ገድሉን በድል አጠናቆ እንዳሰበ ለጓደኞቹ ለማውጋት እንደቋመጠው ባይሆንም ሕይወት እንዳሰመረችው ዘና ባደረገ መልኩ ይጠናቀቃል፡፡
የብ/ወ በድሉ አሳር የሚፈጥረው አገልግሎቱን ጨርሶ ወደ ቤተሰብ ለመመለስ አንድ ሐሙስ በቀረው ወቅት ነው፡፡ መለዮ ለምን አላደረክም በሚል ሰበብ አንዱ ወታደር ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቀጣ ይልከዋል፡፡ ያቺ 24 ሰዓት የዓመት ያህል ረዝማ ይዛ የመጣቸውን መዘዝ፣ ስቃይና ራስን ስቶ ሆስፒታል እስከመተኛት ያደርሳል፡፡
በሰላም ወደ ቤተሰብ ተመልሶ ለመከራ የጣፈው ትውልድ አባል ነውና አገሪቱ እንደገና ለዳግም ግዳጅ ፈለገችው፡፡ ለዛውም የፋሲካ በእለቱ እለት ከቤተሰቦቹ ጋር ሲፈስክ አብዮት ጠባቂዎቹ ‹ተነስ ታጠቅ!› ሲሉት እናስተውላለን፡፡ በወቅቱ በድሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር፡፡ የእናት አገር ጥሪ ይቅደም በሚል ስሜት በክላሽንኮቭ አጅበው፣ ወደ ቀበሌ ጽህፈት ቤት ይወስዱታል፡፡ እዚህ ጋ የሞት የሽረቱ ትግል ይጀመራል፡፡
ማምለጥ፣ ጫካ ለጫካ መሽሎክሎክ፣ ለአደጋ መጋለጥ፣ ፈጣሪው ራርቶለት መንገድ ሲመራው ይስተዋላል፡፡ በታወቀ ሽፍታ ታጅቦ (ሽፍታው የአባቱ ውለታ አለበት) ሌት ከቀን ገስግሶ፣ ከአሰላ በእግሩ ተጉዘው  መቂ ደረሱ፡፡ ከመቂ አዲስ አበባ በመኪና በድሉ ይጓዛል፡፡ ከፊት ምን ይጠብቀው ይሆን ብለን እንሰጋለን፡፡ ይሁን እንጂ ሥርዓቱ ዜጎቹን የሚመራበት በቅጡ የተዘረጋ ደንብ ስለሌለው፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲደርስ ምንም ሳንካ አልጠበቀውም፡፡ ትምህርቱን በሰላም አጠናቆ፣ እትብቱ በተቀረበችበት ምድር ዳግም የረገጠው ስርዓቱ ከፈረሠ በኋላ ነው፡፡
ብ/ወ በድሉ እያንዳንዱ ባለታሪክ እንዴት፣ የት እንዳገኘውና ፍፃሜያቸው ምን እንደሆነ እያወጋን ነው የሚቀጥለው፡፡ መልከአምድሩን፣. ደኑን፣ አደኑን ሁሉ አብረን እንድናስተውለው ያደርገናል፡፡ የሳንቴ ደን አሁን ይኖር ይሆን? የዱር እንስሳቱስ? ያ ጥቅጥቅ ያለውን ዱር በጥበብ ቃላት ስሎ በማሳየት አዳርና ውሎውን በአግባቡ ይተርክልናል፡፡
ብ/ወ አዲ ድምፃዊም ነው፡፡ አብሿምም ነበር። ዘፍኖ የሚያዝናናውን ያህል ሲጠጣ ባህሪው ይለወጣል፡፡ አብዲ የተባለ አስተዋይ የመደበኛው ጦር አባል የአዲን ችግር ተረድቶ ብቻውን እንዲተዉት ያደርጋል፡፡ አዲ ስካሩ ሲበርድለትና ወደ ቀልቡ ሲመለስ በድርጊቱ ያፍራል፤ ካፍ የወደቀ ጥሬን ያህል፡፡
እዚህ ‹የማይጻፍ ገደል› መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ትልቁ እርባናው ከ33 ዓመታት በፊት የአንዱን ወጣት እጣ እንድናይ ያደርገናል፡፡ በዚህ ከባድ ፈታኝም ሁኔታዎችን አልፎ እንዴት የራሱ ሰው ሆነ ብለን እንዳናብስ ለስል እንገደዳለን። ዘመኑና የወጣቱን ህይወት በቅጡ እንድናየው ያደርገናል፡፡
እንደ እፀፅ ልናነሳ የምንችለው ጥቂት ነጥቦች አሉ፡፡ አዲን በድምፃዊነቱ ሲደነቅ ከቴድሮስ ካሳሁን ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በሕብረተሰባችን ውስጥ ቴዲ አፍሮ በድምፀ መረዋነቱ ሳይሆን የሚጠቀሰው በሚያነሳቸው ጭብጦች ነው፡፡ በሌላ አባባል ያንን ብአለ ለመግለፅ ልሞክር፡፡ ከአንዱ አስራ አምስት ዓመታት በፊት ጥይት ከሆኑ ደበበ ሰይፉ ተማሪዎች ጋር ስጨዋወት ለእነሱ አሪፍ የሚሏትን ሀሳብ አንድ ጓደኛችን በጨዋታ መካከል አነሳ፡፡ ተማሪዎቹም ይህ ሀሳብ በጣም ከየፋቸውና “በናትህ ፃፈውና የምናስበው ይኑረን!” ነበር ያሉት፡፡ ቴዲም ሲዘፍን የምናስበውን በመስጠት ነው የሚታወቀው ብዬ አስባለሁ፡፡ ቢ/ወ በድሉም አዲን ከጎልማሶቹ አልያም በዘመኑ ከነበሩት ወጣት አቀንቃኝ ጋር ማመሳሰል ይችል ነበር፡፡ በዘመኑ ካልነበረ ዘፋኝ ጋር ማነፃፀሩ እንደ ግድፈት የምንጠቅሰው ነው፡፡
ሌላው በገፅ 50, 66, 148 እያልን አዲስ ምዕራፍ ሲጀመር ባዶ ገፆ ያጋጥመናል፡፡ ይህም ምዕራፉን በስተቀኝ ለመጀመር በማሰብ ይመስላል፡፡ በዚህም በስተግራ የሚገኘው ገፅ ቁጥር ተሰጥቶት ባዶው ይስተዋላል፡፡ በርካታ ገፆች ላይ የፊደል መዘርዘር ይስተዋላል፡፡ ይህም ደራሲው በስተመጨረሻ ደጋግሞ ከማንበብ መታከቱን እንድናስተውል ያደርገናል፡፡
ደራሲው የባለታሪኮቹን መጨረሻ የሚያወጋንን ያህል ዘሎ የተወውም አለ፡፡ ጎርጎራ አብሮት መምህር የነበረው ገብረ መድህን ካህሳይ፣ በወያኔ አባልነት ቢጠረጠርም መምህር በድሉ ይከላከልለታል። ይህንን የሚያውቀው መምህር ገብረ መድህን ጦርነቱ እየከፋ ሲመጣ፣ ለክፉም ለደጉም ብሎ ከሚኖርበት ከከተማው ዳር ወደ ማሀል ለመጠጋት መምህር በድሉን  በደባልነት እንዲስጠጋው ጠየቀ። በድሉ በደስታ ተቀበለው፡፡ ገብረ መድህንም ወደ በድሉ ቤት ሲመጣ ሽጉጡንና ክላሽንኮቩን ተታጥቆ መጣ። በመጨረሻም ይህ ሰው  ምን ሆነ? በበድሉ ትንፋሽ ያለው ነገር የለም፡፡
በመጨረሻም ይህ መጽሐፍ የብሔራዊ ውትድርና ታሪክ በተነሳ ቁጥር ተጠቃሽ ሥራ ሆኖ እንደሚቀጥል እምነቴን መግለፁን እወዳለሁ፡፡ ርዕሱ “ከማይፃፍ ገድል” ይልቅ ‹የአንድን ወጣት እጣ› ቢሆን የተሻለ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ይኸው ተፅፎ አየነዋ፡፡    

Read 1544 times