Saturday, 19 August 2017 14:45

በነጻነት ሃሳብዎን ያንሸራሽሩ! (እውነት እውነቱን)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 1. በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ50 በላይ የመንግስት ባለሥልጣናት በሙስና ተጠርጥረው ታስረው፣የ8 ባለሃብት ኩባንያዎችና ድርጅቶች በፍርድ ቤት
ታግደው፣ከ200 በላይ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ገና ሊያዙ እንደሚችሉ ተስፋ ተሰጥቶት፣ህዝቡ ግን አሁንም ዋናዎቹ መች ተያዙና እያለ ነው፡፡ ጨርሶ የልቡ
አልደረሰለትም፡፡ ግን እርስዎስ ምን አሉ?
ሀ) እኔም ከህዝቡ የተለየ ሃሳብ የለኝም!
ለ) ህዝብ መንግስትን ቢጠራጠር አይፈረድበትም!
ሐ) ሁሉም ከታሰሩማ ማን ይመራናል !? (ባይሆን ተራ በተራ)
ሠ) የኮንዶሚኒየምና የስቴዲየም ግንባታ፣ የጸረ- ሙስና ዘመቻ መቼ ነው?!
2. የመንግስት ባለሥልጣናት የሃብት ቆጠራ ተከናውኖ፣ የእያንዳንዱን ሹመኛ ሃብትና ጥሪት ይፋ እናደርጋለን ተብሎ አልነበር እንዴ? ቀርቶ ነው ወይስ ዘግይቶ?
ሀ) ሃብታቸው ተቆጥሮ አላልቅ ብሎ ይሆናል?!
ለ) ”ይሄማ ለህዝብ ፊት መስጠት ነው” በሚል፣ውድቅ ተደርጎስ ቢሆን?
ሐ) ለነገሩ ሃብት ተቆጠረ ማለት ሙስና ላለመብላት ግዝት ነገር አይደለም!
መ) መንግስት ድሮም ያመጣው፣የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት፣የባለሥልጣናትን ሃብት እንዲቆጥሩ ስለሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም
ሠ) አሁንማ በደንብ ተበርብሮ መቆጠር አለበት ( ስንት መ ቶ ሺ ነው፣”ለአስቤዛ” በሚል ቤት ውስጥ የተገኘው?)
3. ሰሞኑን የሶማሊያ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ከኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ትምህርትና ተሞክሮ ሲቀስሙ መሰንበታቸውን ከኢቢሲ ሰምተናል፡፡ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ፣ትግራይና አማራ ክልል ነው፣ የፌዴራሊዝም ልምድና ተሞክሮን ሲጋሩ የሰነበቱት፡፡ እውነት ግን ለጎረቤት ተሞክሮ የሚበቃ፣አስተማማኝ
የፌደራሊዝም ሥርዓት መሥርተናል እንዴ?
ሀ) አዲሲቱን ሶማሊያ ጉድ እንዳንሰራት!?
ለ) ከኢትዮጵያዊነት ጋር አኳርፎናል የተባለ መስሎኝ?!
ሐ) ተሞክሮው ለኛው ይሆን እንዴ (እምዬ ኢትዮጵያ ለምንለው!)
መ) ምናልባት የተሻለ ሌላ ሥርዓት ካለም፣ ክፍት ብንሆን ይበጀናል?!
ሠ) እኔ የሰለቸኝ እንዲህ ዓይነቱ የኢህአዴግ ድራማ ነው!
4. የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 5ኛ ሙት ዓመትን ምክንያት በማድረግ፣ ኢቢሲ፣ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር
እየቀነጫጨበ ሲያሰማ ሰንብቷል፡ ፡ በተለይ ስለ ዲሞክራሲ፣ስለ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት የተናገሩት፣የኢህአዴግ አይመስልም፡፡ አንዳንድ ሰዎችማ ማመን
እስኪያቅታቸው ድረስ በሰሞኑ የጠ/ ሚኒስትሩ ንግግር ተደምመዋል አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ተሰማዎት?
ሀ) ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገንም!
ለ) እኔ ወሬ ሰልችቶኛል፤በተግባር ማየት ነ ው የ ምፈልገው
ሐ) ኢህአዴጎች የገባቸው አይመስለኝም፤ ደጋግመው ይስሙት
መ) ኢህአዴግ አሁንም ሌላ ተናጋሪ አልተካም እኮ
ሠ) የአሁኑ ኢህአዴግና የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ኣራምባና ቆቦ ነው
• ውድ አንባቢያን፤ መልሶቻችሁ ከምርጫዎቹ ውስጥ ከሌሉ፣ረ) ብላችሁ የራሳችሁን አማራጭ መጻፍ ህገ መንግስታዊ መብታችሁ ነው፡፡

Read 1283 times