Saturday, 19 August 2017 14:45

የፍቅር አውሎ ነፋስ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምኑም፣ ምናምኑም ግራ እየገባው ያለው ምስኪን ሀበሻ እንደገና ወደ አንድዬ ሄዷል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— እንዴት ከረምክ!  ለመሆኑ ደህና ነህልኝ ወይ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አ…አንድዬ!…
አንድዬ፡— ምነው ተርበተበትክ፣ እኔንም ደህና ነህ ወይ አትለኝም እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ… ት…ትንሽ ግራ ስለገባኝ ነው፡፡ ግን አንድዬ በ…በደህናህ… ይቅርታ አንድዬ፣ ይቅርታ፣ እየዘባረቅሁ ነው፡፡
አንድዬ፡— ግዴለም፣ እሱን ማለቴ መዘባረቁን ፈቅጄላችኋለሁ፡፡ ሰላም ባልኩህ ጭራሽ ትደነግጣለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አይ…እንደው…
አንድዬ፡— ምነው፣ ስታየኝ ወፈርኩብህ፣ ከሳሁብህ? ንገረኛ…
ምስኪን ሀበሻ፡— ተው አንድዬ፣ ተው እንደሱ አይነት ቃላት እየተናገርክ አታስደንግጠኝ፡፡
አንድዬ፡— እሺ እንዳልክ ይሁን…ለመሆኑ ደህና ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምኑን ትጠይቀኛለህ። ‘እንደው ዝም፣ እንደው ዝም ይሻላል’ ብላለች ዘፋኟ፡፡
አንድዬ፡— አመጣኸው ደግሞ፣ ይሄን ዘፈን አመጣኸው፣ እንደው የሆነ ነገር በመጣ ቁጥር ይሄ ዘፈን፣ ተረት መጥቀሰ አይተዋችሁም ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በተረቶቻችንና በዘፈኖቻችን ውስጥ እኮ ስንት ቁም ነገር አለ መሰለህ…አንድዬ፣ እውነቴን ነው የምልህ፣ ሰላምታህ በጣም ነው ያስደነገጠኝ፡፡
አንድዬ፡— ለምን?…ከዚህ በፊት ሰላም ብዬህ አላውቅም? እኔስ ፍጡሬን፣ ያውም አንተን ምስኪኑን ሀበሻ  ሰላም ማለት አያምርብኝም!…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደሱ ማለቴ ሳይሆን፣ በፊት ስመጣ ቆጣ ብለህ ነበር የምትቀበለኝ፣ እንደውም እሰለችህ ነበር…
አንድዬ፡— ያኔ ነበራ፣ አንዳንዴ አንተንም ደስ ይበለህ እንጂ፡፡ የምታለቅስበት፣ እኔ ላይ ሽቅብ ጣትህን እየወዘወዝክ ‘ወይ ውረድ፣ ወይ ፍረድ’ እያልክ የምትከስበት… እንደውም አንዳንዴ መክሰስ ሳይሆን የምታስጠነቅቀኝ ነው የሚመስለኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ተው እንደሱ አትበል! እንደሱ ስትል ጨርቅ የሆነች ልቤ ብትን ብላ ቢያበቃላትስ…
አንድዬ፡— እሺ፣ በል አሁን ሰላምታ ሳቀርብልህ ለምን ግራ እንደተጋባህ ንገረኝ፡፡  
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደው በደስታና በፈገግታ ስትቀበለኝ፣ ይሄን ለውጥ ምን አመጣው ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔስ ብሆን ምን ላድርግ ብለህ ነው፡፡ አሁን፣ አሁን በእናንተ መበሳጨት ትቼ ታሳዝኑኝ ጀመር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አየህልኝ አይደል!…የመከራችንን ብዛት--- አየህልኝ አይደል!…
አንድዬ፡— ታዲያ መከራችሁን ማን አመጣባችሁ? እኮ ንገረኛ፣ መከራችሁን ያበዛባችሁ ማነው፣ እኔ ነኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ እንደ እሱ አትበል! እኛ አንተ መች መከራችንን አበዛህብን አልን! አንተ ምን በወጣህ!
አንድዬ፡— እውነትህን ነው፣ እኔ ምን በወጣኝ፡፡ ታዲያ እኔ ምንም ሳላደርጋችሁ በየጊዜው ‘ይቅር በለን’ የምትሉኝ ለምንድነው?  
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ታዲያ አንተ ይቅር ካላልከን፣ ማን ይቅር ይለናል?
አንድዬ፡— እንደሱ አይደለም፣ ይቅር በለን ስትሉ ጥፋት መሥራታችሁን እያመናችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ይቅርታችሁን ጥፋቱን ከፈጸማችሁበት ሰው፣ ወይ ቡድን ጠይቁ እንጂ እኔ ምን ላድርግ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ከሁሉም በላይ የአንተ ይቅርታ ይበቃላ፣ አንድዬ!
አንድዬ፡— የተበደለውስ?… ጥፋት የተፈጸመበትስ! ንገረኛ… ተበዳይ ይቅር ሳይላችሁ፣ እኔ ‘እሰይ፣ አበጃችሁ’ እንድላችሁ ነው የምትፈልጉት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የአንተ ይቅርታ እኮ ሁሉንም ሀጢአት በአንዴ ነው የሚደመስስልን!
አንድዬ፡— መጀመሪያውኑ እንደሱ አትለኝም! ታዲያ፣ ሀጢአታችሁን እያጠራቀማችሁ እንደ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይቅር በለን በሉኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በሰላምታህ አስደስተኸኝ አሁን አስቆጣሁህ እንዴ!
አንድዬ፡— ቆይማ፣ እኔ የምለው…መቼ ነው እናንተ ሰዎች ረጋ የምትሉት! መቼ ነው ልብ የምትገዙት!…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንደሱ ሳይሆን…ምን መሰለህ፣ ብቻ የሆነ የሰፈረብን፣ አልለቅ ያለን ሰይጣን አለ መሰለኝ…
አንድዬ፡— ይኸው ጀመረህ፣ ጀመረህ! የሰለቸኝ ነገራችሁ ጀመረህ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይሄን ያህል ምን አጠፋሁ?…
አንድዬ፡— ሀጢአቱን ሁሉ ወደ ሌላ መውሰድ ጀመረህ፡፡ እኔ ዘንድ በመጣህ ቁጥር ‘እነሱ እንደዛ አድርገውን፣’ ‘እነዛ እንደዚህ አድርገውን’ ሳትል የተመለስክበት ቀን አለ? ይሄ በሌላ ማሳበብ፣ ጣታችሁን ወደ ራሳችሁ ሳይሆን ወደ ሌላ መቀሰሩ አይሰለቻችሁም!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን እናድርግ!  ዓለም ላይ የእኛን ያህል ጠላት የበዛበት የለም እኮ!
አንድዬ፡— (ከት ብሎ ይስቃል) በስንት ዘመኔ አሳቅኸኝ! ሳቅ በጣም ናፍቆኝ ነበር፡፡ ቆይ፣ ልጠይቅህ…ለምንድነው ከሌሎች ተለይቶ እናንተ ላይ ጠላት የበዛው?
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛ ምኑን አውቀነው አንድዬ! ብቻ አይወዱንም፣ በቃ ትንሹም ትልቁም፣ ነጩም ጥቁሩም አይወዱንም…
አንድዬ፡— ምን አድርጋችኋቸው ነው ጠላቶቹ የበዙባችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምንም፣ አንድዬ እኛ በየትኛው አቅማችን ምን እናደርጋለን!
አንድዬ፡— ታዲያ ምንም ካላደረጋችኋቸው ለምን ብለው ይጠሏችኋል?…
ምስኪን ሀበሻ፡— እኔ እንጃ አንድዬ..
አንድዬ፡— እኔ እንጃ እኮ የትም አያደርስም፡፡ ይኸው እኔ እንጃ ስትሉ ስንት ዘመናችሁ፡፡ ያለ የሌለ ጠላት ማብዛቱን ትታችሁ እስቲ ትንሽ ትንፋሽ ውሰዱና ራሳችሁን በደንብ መርምሩ፤ እስቲ ጣቶቻችሁ ወደ ራሳችሁ ይዙሩ! ብቻ ለክፉም ለደጉም ዛሬ ደግሞ ምን እግር ጣለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዓመቱ እየተገባደደ ስለሆነ አንተን ለማመስገን ነው፣ ለዚህ ላደረስከን ምስጋና ላቅርብ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ!  አንዳንዴ እንዲህ ለስለስ ያለ ነገር ተናገር እንጂ…ስጦታው የታል?
ምስኪን ሀበሻ፡— አ..አንድዬ፣ የምን ስጦታ?
አንድዬ፡— ስጦታ ነዋ! ልታመሰግነኝ አይደል እንዴ የመጣኸው… ባዶ እጅ ይመጣል እንዴ? እንደው ብታጣ አረቄ ቢጤ እንኳን… (ይስቃል)
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ በስመአብ በል… ይቅርታ አንድዬ  ማለት የፈለግሁት…
አንድዬ፡— ግዴለም ለአንተ ስል በስመአብ እላለሁ። እናንተ ከጠዋት ጀምሮ መሽቶ እስኪነጋ ስትጠጡ ውላችሁ የምታደሩትን እኔስ አያምረኝም…ስቀልድ ነው፡፡ ልታመሰግነኝ ስለመጣህ ደስ ብሎኛል…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ፣ መርቀን፣ ‘በመጪው ዓመት ችግራችሁን ሁሉ የፍቅር አውሎ ነፋስ ይዞላችሁ ይሂድ’ ብለህ መርቀን…
አንድዬ፡— አንተ ጨረስከው አኮ፣ ምርቃቱን አንተ ጨረስከው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ግዴለህም መርቀን…
አንድዬ፡— ጥሩ፣ እኔ የምመርቃችሁ ግን አንተ ባልከው አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በመሰለህ መርቀን…
አንድዬ፡— የፍቅር አውሎ ነፋስ ችግሮቻችሁን ሁሉ ይዞላችሁ እንዲሄድ የሚያስችል ልቦናውን ይስጣችሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመትን በምኞትና በህልም ብቻ ሳይሆን በንጹህ ልብና በንጹህ አእምሮ እንድትቀበሉት ይሁን፡፡ አይበቃህም፣ ምስኪኑ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ይበቃኛል አንድዬ፣ ይበቃኛል!
አንድዬ፡— ለክፉም ለደጉም እኔን የማትጨቀጭቁበትና ሥራ የማታስፈቱበት መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ!
አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ምስኪን ሀበሻ፡— ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5044 times