Saturday, 19 August 2017 14:48

የእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሰራተኞች ቅሬታና የዳይሬክተሩ ምላሽ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“ዳይሬክተሩ ሰራተኛን ይቆጣሉ፣ ያስፈራራሉ፣ ያሸማቅቃሉ” - ሠራተኞች
                        “በተፈጥሮዬ ቁጡ ስለሆንኩና ውጤት ስለምፈልግ ነው” - ዳ ይሬክተሩ

       የእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ጽ/ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ፣ ወደ እንቅስቃሴ ከገባ ገናዓመት አልሞላውም፡፡ ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ የሚነገርለትየቱሪስት መዳረሻ ልማት፤ ለአጠቃላይ ግንባታው 4.8 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ፤ የባህል ዘርፍ ዳይሬክቶሬት፣ የስፖርት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት እና የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ዳይሬክቶሬት አካትቶ፤ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር የተቋቋመ ነው፡፡ የካ እና ጉለሌ ክ/ ከተሞች ላይ የሚመሰረተው ይህ ግዙፍ የቱሪስት መዳረሻ በሚገኝበት ቦታ ላይ ከ8 ሺህ 9 መቶ በላይ የመንግስትና የግል ባለይዞታዎች የሚገኙ ሲሆን
በአሁኑ ወቅት እነዚህ ባለ ይዞታዎች በምን መልኩ ተነስተው፣ ግንባታው ይጀመር በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ የቱሪስት መዳረሻው እንዴት ይገንባ፣ ምን ምን ነገሮችን ያካትት? አጠቃላይ የቦታው ሁኔታ እንዴት አገልግሎት ላይ ቢውል ውጤታማ ይሆናል … በሚለው እ.ኤ.አ በ2012፣ ዓለም ባንክ በ22 ሚ. ብር የራሱ በጀት፣ ጥናት አሰርቶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ፤ ዳይሬክተርና አላማ ፈፃሚዎች እንዲሁም ደጋፊ ስራ
ሂደቶች ተዋቅረው፣ ባለሙያዎችም ተቀጥረውለት ስራ ቢጀምርም በሰራተኛውና በማኔጅመንቱ መካከል ቅሬታና አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ ብልሹ አሰራሮች፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች፣ የመንግስትን ንብረት ያለአግባብ መጠቀም የመሳሰሉት ቅሬታዎችና አቤቱታዎች፣ ከሰራተኞቹ ይደመጣል፡፡ የአዲስ
አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በተነሱት ቅሬታዎች ዙሪያ ከፕሮጀክቶቹ ዳይሬክተር፣ ከዶ/ር ህያብ ገ/ጻዲቅ ጋር በቢሮአቸው ተገኝታ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡

      ዶ/ር ህያብ መቼ ነው የፕሮጀክት ጽ/ቤት ዳይሬክተር ሆነው መስራት የጀመሩት?
ፕሮጀክቲ የተቋቋመው በደንብ ቁጥር 69/2008 መሰረት ነው እኔ ሹመቱን አግኝቼ የተቀጠርኩት ሰኔ 2008 ዓ.ም ነው፡፡
እስቲ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ያስረዱኝ…
በፕሮጀክቱ ዙሪያ ሰፊ ጥናት ተካሂዷል፤ በጥናቱ መሰረት ባለሙያዎችም ተቀጥረዋል፡፡ አንድ ዳይሬክተርና ደጋፊ የስራ ሂደቶችን ጠቅልሎ የሚይዝ አንድ ምክትል እንዲሁም የዓላማ ፈፃሚዎችን የሚይዝ ምክትል ያለው ነው፡፡ ሲጠና የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ሁሉ ያለው ነበር፡፡ ሲፀድቅ ግን፣ ማርኬቲንጉ የምርት ውጤት ካደገ በኋላ ቢሆን ይሻላል በሚል አይሲቲውና ማርኬቲንጉ እንዲቆይ ተደርጎ፣ አንድ ምክትል ተቀንሷል፡፡ ደጋፊ ስራ ሂደት አልነበረውም፡፡ እኔ ከመጣሁ በኋላ አጥንተን ነው የተጨመረው፡፡ በአጠቃላይ በእነዚህ መዋቅሮች ባለሙያዎች ተቀጥረው ነው ስራ የተጀመረው። ፕሮጀክቱ የስፖርት ዘርፍ፣ የባህል ዘርፍና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳይሬክቶሬቶች አሉት። ባለሙያዎችም ሲቀጠር ከየዘርፉ የመጡና ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡
ደጋፊ የሥራ ሂደቶች ሲባል ኃላፊነታቸው ምንድን ነው?
ፋይናንስ፣ ግዢና የሰው ሀብት አስተዳደር የሚባሉት ናቸው ደጋፊ የስራ ሂደቶቹ፡፡ አሁን ደግሞ ግንባታ ስለሚካሄድ ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት እንዲኖረው አስፈቅደን በቅጥር ላይ እንገኛለን፡፡
ፕሮጀክቱ በተጠቀሱት ዘርፎች ወደ 58 ሰራተኞችን መቅጠሩን ሰምቻለሁ፡፡ ጽ/ቤቱ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች የተሻለ ደሞዝ ይከፍላል ይባላል፡፡ ነገር ግን ሰራተኞች በብዛት የሚፈልሱበት መስሪያ ቤት መሆኑ ይገለፃል። ለምንድን ነው ሰራተኞች ቶሎ ቶሎ የሚወጡት?
የሰራተኛ ፍልሰት ጉዳይ በሳይንስ ጥናትም የሚታወቅ ነው፡፡ የተለያዩ ምክንያቶችም አሉት። የውጭና የውስጥ ገፊና ሳቢ (Pulling and pushing factors) ምክንያቶቹ ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ ገፊ ምክንያት ሳይኖር ከውጭ የሚስብ ነገር ስላለ ብቻ ሰራተኛ ይፈልሳል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሳቢ ነገር ባይኖርም ገፊ ምክንያት ካለ ይለቅቃል። ይሄ ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እኔ ግን ሳቢ ወይም ማራኪ ምክንያቶች ብዬ የማስባቸው፣ ይሄ ፕሮጀክት ሜጋ ፕሮጀክት እንደመሆኑ ጥሩ እውቀት ያላቸውና ውጤታቸውም ከ2.75 በላይ ያላቸው እንዲያመለክቱ ነው ያደረግነው፡፡ እኛ የምንፈልገው 37 ሰው ብቻ ቢሆንም ያመለከተው ሰው ግን ከ1 ሺህ 300 በላይ ነበር። ሌላው ቀርቶ ከ2.75 በላይ በርካታ ሰው አመልክቶ ነበር። በተለይ ስፖርቱ አካባቢ ከ3.6 እና 3.8 በላይ ነበር ውጤታቸው። ከዩኒቨርሲቲም፣ ከትልልቅ ተቋማትም ለቅቀው የመጡም ነበሩ፡፡ የመጡት ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ከደሞዙ በተጨማሪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዳሉ አስበው ነው፡፡ እዚህ ጥቅማ ጥቅም ደግሞ አልተፈቀደም ነበር፡፡
ጥቅማ ጥቅም ምን ምን ያጠቃልላል?
የትራንስፖርት፣ የሞባይል፣ ኢንተርኔት መሰል ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቀጣሪዎች ይሄንን ስላላገኙ ሊፈልሱ ችለዋል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደሞዝም ተጨምሮ ነበር፡፡ እዚህ ረዳት ፕሮፌሰሮች ሁሉ መጥተው ተቀጥረው ነበር፡፡ ለረዳት ፕሮፌሰር ከ13 ሺህ በላይ ሆኗል ደሞዝ፡፡ ለጥናትና ምርምር የሚሰጠውም ገንዘብ ትልቅ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እዚህ ያለውን ነገር ሲያዩት አላዋጣቸውም፤ በዚህ ምክንያት እየለቀቁ ወደነበሩበት ዩኒቨርሲቲ ተመልሰዋል፡፡ ሌላ የተሻለ ስራ ሲወጣም እየተወዳደሩ በተሻለ ደሞዝ ለመስራት የሚሄዱ አሉ፡፡ እኒህ ሳቢ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ከገፊ ምክንያቶች ደግሞ እኔ በመጣሁበት ወቅት ሰው እየተቀጠረ ነው ያገኘሁት፡፡ ቢሯችን የነበረውም አራት ኪሎ በሚገኘው ቅዱስ ፕላዛ፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር አንድ ክፍል ነበር። በጣም ተጣበን ፈርኒቸር በሌለበት፣ በማይመች የስራ ከባቢ ነበር የምንሰራው፡፡ ክፍሎቹ ለሱቅ የተዘጋጁ ነበሩ። በነዚህ ክፍሎች ውስጥ ጠረጴዛ እንኳን ማስገባት አንችልም ነበር። እዛው ተጨማሪ ቦታ ብንጠይቅም ማግኘት አልቻልንም። በዚህ ምቹ ሁኔታ ያለመኖር ሰራተኛ ይሄዳል፡፡ በወቅቱ ሼልፍ የኢንተርኔት አገልግሎትና ጠረጴዛ በሌለበት ነው ሲሰሩ የነበሩት። በዚህ በዚህ ምክንያት ሊለቁ ይችላሉ። እኔ እንኳን ዋና ዳይሬክተር ሆኜ፣ የሆነ ጨርቅ ላይ ተቀምጬ ጠረጴዛ ሳይኖረኝ ነበር ስሰራ የቆየሁት፡፡ ይሄ የፋሲሊቲ አለመሟላት ዋነኛው ገፊ ምክንያት ነበር፡፡
ሁለተኛው ይሄ ፕሮጀክት እንደመሆኑ መስራትና በአግባቡ ማስረከብ ያለብንን ስራ ማስረከብ አለብን፡፡ አንዳንዴ ቅዳሜና እሁድ መስራት ሁሉ ይጠበቅብናል። ማታም ጭምር መስራት ሊኖርብን ስለሚችል፣ የስራ ጫናው አንዱ ገፊ ምክንያት ነው። በስራው ወቅት ኢንተርኔት ስላልነበረን ያንን ስራ ለማፋጠን በኪስ ገንዘባቸው ነበር ለኢንተርኔት እየከፈሉ የሚሰሩት። መረጃ ጉግል አድርገው አጥንተው ሰርተው፣ ከዚያ በየሳምንቱ ሐሙስና አርብ ሪፖርታቸውን ኢ-ሜይል ነው የሚያደርጉት። ይህን የሚሰሩት በራሳቸው ወጪ ነው፤ ስለዚህ ይሄም አንዱ ለመልቀቅ የሚገፋቸው ምክንያት ነው፡፡
ለምን እናንተ ወጪውን አትሸፍኑላቸውም?
ወጪውን የምንሸፍንበት መመሪያ የለም፡፡ ይሄ ነው ያስቸገረን፡፡
እነሱስ የኢንተርኔት አቅርቦት ሳይኖር በኪሳቸው ወጪ የሚሰሩበት መመሪያ አለ?
ይሄ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስራው ደግሞ በተቀጠሩት ሰራተኞች የግድ መሰራት አለበት፡፡ ነገሮች እስከሚስተካከሉ መስዋዕትነት እንክፍል በሚል ተስማምተን ነው ስራው እየተሰራ ያለው፡፡ እኔ ቱሪዝምም ማኔጅንትም ተምሬያለሁ፡፡ ዲግሪዬን በቱሪዝም፣ ማስተርሴን በቢዝነስ አድምንስትሬሽን፣ ፒኤችዲ ደግሞ በቱሪዝም ነው ያገኘሁት፡፡ ኮርፖሬት ወርልድ የተባለ ትልቅ ኩባንያ ውስጥም ሰርቻለሁ። በባህሪህ ምን ዓይነት ማኔጀር ነህ ካልሽኝ፣ ውጤት ጠባቂ ወይም ውጤት ማየት የምፈልግ ማኔጀር ነኝ፡፡ ለአንድ የስራ ውጤት ሂደት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን አንድ ስራ ምን ላይ ደረሰ ስል ሄጄ ሰውየውን አጣሁት፣ ቢሮው ተዘግቷል፣ ኢ-ሜይል አድርጌ ምላሽ አላገኘሁም፣ ስልክ ደውዬ አላነሳልኝምና መሰል ምክንያቶች ለእኔ ሪፖርት አይደለም፡፡ እንደነገርኩሽ ውጤት ጠባቂ ነኝ፡፡
አንድ ኢ-ሜይል ምላሽ ካላገኘ ደግሞ ኢ-ሜይል ማድረግ ያስፈልጋል፣ አንድ ቢሮ ከተዘጋ ውጤት ለማምጣት ደጋግሞ መሄድ፣ ደጋግሞ ስልክ መደወል ያስፈልጋል፡፡ ጽ/ቤታችሁ እንደነገሩኝ፣ እነዚህን አቅርቦቶች አላሟላም፡፡ ባልተሟሉ ሁኔታዎች ከሚሰራ ሰራተኛ እንዴት ውጤት ይጠብቃሉ?
ነገሮች እስከሚስተካከሉ መስዋዕትነት እንክፈል በሚል ስምምነት ላይ አንዴ ከደረስን በኋላ ውጤቶች መምጣት አለባቸው፡፡ አንድ ማኔጀር ውጤት ጠባቂ ሲሆን ሰራተኛው ጫና ይሰማዋል፡፡ አንድ ሰው ደርሼ መጥቻለሁ ሰውየውን አላገኘሁትም ሲል፣ ችግር የለውም ከተባለ ነገር ነው የሚበላሸው፡፡
ሰራተኞቹ ያቀረቡት ቅሬታ እርስዎ እንደሚሉት፤ የስራ ጫና፣ የጥቅማጥቅም አለመኖርና የደሞዝ ማነስ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ችግር ከስራቸው እንደሚያስለቅቃቸው ነው የተናገሩት፡፡ በተለይ የእርስዎ ባህሪ ለሰራተኛው ምቹ እንዳልሆነ፣ አንድ ሰው ይሄ አይሆንም ብሎ ከተገዳደረ ዛቻና ማስፈራሪያ በማድረግ፣ ማህደርህን አበላሻለሁ በማለት ሰራተኛ እንደሚያሸማቅቁ ሰምቻለሁ፡፡ አንዱ እንደውም ‹‹ወህኒ እወረውርሃለሁ›› ስላሉት መልቀቂያ እንኳን ሳይወስድ ብን ብሎ መጥፋቱን ባልደረቦቹ ነግረውኛል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ሰው እንግዲህ እያጋነነ የሚያወራቸው ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ተናድዶ የሚያወራው ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ቅድም ያነሳሽው የሰው ሀብት አስተዳደር ላይ ቅሬታ ያቀረበውን ሰው ማን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ እኛ እስካሁን 1 ሺህ 300 ሰው ሰራተኛ ስንቀጥር በኤክስኤል ነው፡፡ ኤክስኤሉን አውቶሜት አድርጌ፣ ኳንቲፋይ ተደርጎ፣ የሚፈለገውን የሰውየውን ብቃት እንዲያወጣ አድርገን ነው የሰው ሀብቱን የገነባነው፡፡
እዚህም ላይ ችግር እንደነበረ ሰምቻለሁ ምን አይነት ችግር?
የሚፈለገው ሰው ውጤት ከ2.75 በላይ እንደሆነ በማስታወቂያው ላይ ስላልገለፃችሁ ብዙ ሰው ለሲቪ ኮፒ፣ ለትራስፖርት ወጪና ለጊዜ ብክነት ወጪ ተዳርጓል… እቀጠራለሁ ብሎ አመልክቶና ጓጉቶ መቅረቱም ሌላ የስነ-ልቦና ጫና አለው፡፡ ለምንድነው መስፈርቶቹን ሳትገልፁ ማስታወቂያ የለቀቃችሁት?
እዚህ ላይ የምገልፀው የስራ ማስታወቂያው ሲወጣ አልነበርኩም፤ ቅጥር ላይ ነው የደረስኩት። ማስታወቂያው ጋዜጣ ላይ ከወጣ በኋላ ነው የመጣሁት። 1300 ሰው ለቅጥር አመልክቶ ነው ያገኘሁት፡፡ ግን ይህን ሁሉ ሰው ምን እናድርገው የሚባለው ነገር በኮሚቴ ነው የተወሰነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ሰው 37 ነው የተፈለገው፡፡ አቅምና ጥራት ያለውን ሰው እንዴት እንምረጥ ሲባል፣ የኔ ጥቆማ በኤክሴል አውቶሜት ተደርጎ ይሰራ፣ ግሬዳቸው ወደ ቁጥር ይቀየርና ያለምንም ጣልቃ ገብነት ውጤቱ በኤክሴል ይሰራ ተብሎ በዚያ መሠረት ነው የቀጠርነው፡- የስራ ልምድ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ ግሬድ ተሰጥቶት በቁጥር ነው የተቀጠሩት፡፡ ስለዚህ የሰው ሀብት ላይ ቻሌንጅ ተደረክ የሚለው ሀሰት ነው፤ እኔ ኤክሴል ላይ መፅሀፍ ፅፌያለሁ፤ በዚህ ልምድም አለኝ፡፡ የትኛውም ተቋም ብትሄጂ ለቴሲስ ግሬድ ተጨንቆ የሚቀጥር አታገኚም። እኛ ግን በፕሮጀክትና በመደበኛ ልምድ በቴሲስ በስራ ልምድ የውስጥ መስፈርቶች አውጥተን ከ3.4ና ከዚያ በላይ ውጤት ያላቸውን ቀጥረናል፡፡ የቴሲስ ግሬድ አስፈላጊነትን የሚያምን ማህበረሰብም መፈጠር አለበት፡፡ በዚህ አሰራር ከፕሮጀክቱ በላይ ለማህበረሠቡ በጎ ውጤት አምጥቻለሁ ብዬ ነው የማምነው፡፡ በሰራተኞቻችን ስብስብና በብቃታቸው የማይቀና ተቋም የለም፡፡ በጣም ችሎታና ብቃት ያላቸው፣ በጥንቃቄ የተመረጡ ናቸው፡፡ ቤቱ የሳይንቲስቶች ስብሰብ ነው፡፡
እርስዎ ሰውን ያመናጭቃሉ፤ ያስፈራራሉ ስለተባለው አልነገሩኝም?
እኔ በባህሪዬ ቁጡ ነኝ፤ ስራ ተሰርቶ ውጤት ካልመጣ እቆጣለሁ፡፡ እንደነገርኩሽ ውጤት ጠባቂ ነኝ፡፡ አንዱ መልቀቂያ እንኳን ሳይወስድ ብን ብሎ ጠፋ ብለሻል። እሱ ልጅ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እንዳለው ስላወቅኩ አስጠነቀቅኩት እንጂ አላስፈራራሁትም፡፡ የልጁን ስም መጥቀስ ካስፈለገ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቡድን መሪ ነበር፡፡ እኛ በፕሮጀክቱ ሳይት አካባቢ ያሉ የአዕዋፍና የእፅዋት ዝርያዎችን የሚያጠኑ ባለሙያዎችን አሰማራን። ስምምነታችን በቀን 150 ብር አበል ለመክፈል ነበር። ይህ ልጅ ግን እነሱ ስራውን በ300 ሺህ ብር ካልሆነ፣ ለእኛ እንዳያስረክቡን ሲያግባባቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ብሩ ሂደት ውስጥ ባይገባም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ውስጥ ስለገባ፣ ይሄንን ነገር እያደረግክ ነው፣ በስራህ ትቀጣበታለህ ስለው፣ መልቀቂያ አስገብቶ ጠፋ፡፡ ስራውን ስለሚያውቅ ነው የጠፋው፡፡
ፕሮጀክቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ብቁ ናቸው ብለዋል፡፡ ሰው በመሆናቸው የተሳሳተ እሳቤ ውስጥ ሲገቡ እንደ ታላቅና እንደ ዳይሬክተር ከመምከርና ከማስፈራራት የትኛው ይቀድም ነበር?
በእርግጥ ስራው አደገኛ ሙከራ ነበር፤ ያሰማራናቸው ባለሙያዎች፣ “ያ ብር ካልተከፈለን ጥናቱን አንሰጥም” ብለው ነበር፡፡ በዚህ አልሳካ ሲል በሌላ መንገድ ብር ለማግኘት እንዲችሉ መንገድ ሲያመቻችና ሲጠቁም ስለነበር በአጉል ባህሪው እንዲታቀብ አስጠንቅቄዋለሁ፡፡
ከቢሮ ኪራይ ጋር በተገናኘም ሠራተኞች የሚያነሱት ቅሬታ አለ፡፡ ጉዳዩን ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋርም ያገናኙታል?
በምን መልኩ ነው የቢሮው ኪራይ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የሚገናኘው?
የመጀመሪያው አራት ኪሎ የሚገኘው ቅዱስ ፕላዛ ህንፃ ላይ የነበረው የጽ/ቤቱ ኪራይ እስከ ባለፈው ሰኔ ተከፍሎበት ሲያበቃ፣ ከመጋቢት ጀምሮ አሁን የምትገኙበት የትግራይ ልማት ማህበር ንብረት ወደ ሆነውና ቦሌ በሚገኘው ህድሞና ህንፃ መግባታችሁ ነው። ሁለተኛው ፕሮጀክቱ የሚገኘው እንጦጦ፣ እናት መስሪያ ቤቱ አራት ኪሎ ሆኖ እያለ፣ አራት ኪሎ ፒያሳ፣ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ያሉ ባለ ህንፃዎች ጨረታ ውስጥ ሳይገቡ፣ ቦሌ መሆኑ፣ ለትራንስፖርትና ለኑሮ ውድነት ዳርጎናል የሚል ነው፡፡ ሶስተኛው አሁን ለምትገኙበት ቢሮ ፓርቲሽን ስራ 1.2 ሚ ብር መውጣቱ አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ በነዚህ ምላሽ ቢሰጡን?
ፓርቲሽን ለአንድ ቢሮ አስፈላጊ አይደለም የሚለውን አልቀበለውም፡፡
እኛ የፓርቲሽኑን ስራ በተመለከተ የቦሌ ክ/ከተማ ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ግምት ወስደናል፡፡ ዲዛይኑም የተሰራልን በዚሁ ጽ/ቤት ነው፡፡ ዲዛይኑ ከተሰራ በኋላ ግምቱ የተጋነነ እንዳይሆንም ግምቱ በጽ/ቤቱ ተሰርቶልናል። ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ያወጣው ግምት ወደ 3 ሚ ብር ነው፤ ለፓርቲሽኑ ስራ ማለቴ ነው፡፡ እኛ ግምቱን የወሰድነው በጀት አለን የለንም የሚለውን ለማወቅ ነው፡፡ ገንዘቡ አለን የለንም የሚለውን ካረጋገጥን በኋላ ጨረታ አወጣን። ጨረታው 1.2 ይሁን ብቻ እርግጠኛ አይደለሁም። ግን የክ/ከተማው ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ካወጣው ግምት በ1/3ኛ ባነሰ ገንዘብ ነው የተሰራው። ስለዚህ የተጋነነ ነው የሚለውንም አልቀበለውም፡፡ ቢሮው ለምን ቦሌ መጣ ለተባለው ደግሞ ቢሮው ቦሌ መምጣቱን የተቃወመ ምን ያህል ነው የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
መጀመሪያ እኮ እርስዎ የሰራተኛውን ፍላጎት (ኒድ አሴስመንት) አሰርተው፣ ቢሮው ቦሌ ይሁን ያለው ሰራተኛ አንድ ብቻ ነበር… አይደለም?
ይሄ የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ እኛ ጨረታ ስናወጣ ያስቀመጥነው መስፈርት፣ የካም ጉለሌም ፒያሳም አራት ኪሎም… በሙሉ ጨረታው ላይ ገብተዋል፤ አልከለከልናቸውም፡፡ የካም ጉለሌም አራዳም ብናገኝ እንጠላም ነበር፡፡ ነገር ግን ጨረታው ውስጥ የፈለግናቸው ክ/ከተሞች ጨረታውን አልተወዳደሩም፡፡ አንድም የፈለግነውን ካሬ ሜትር ያህል ቦታ አልነበራቸውም አሊያም አልሰሙም ማለት ነው፡፡
ማስታወቂያ አላወጣችሁም እንዴ?
ግልፅ ጨረታ በማስታወቂያ አውጥተናል። ሌላው ቀርቶ ሰራተኞቻችንን ሰብስበን፣ በተለይ ቡድን መሪዎችን የምታውቋቸው ህንፃ አከራይ ተቋማት ካሉ፣ አራዳም ይሁን ሌላም ቦታ ጥሩ ቢሮ የሚያከራዩ ፈልጉና ይወዳደሩ አልን፡፡ አንድ ቡድን መሪ፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ህንፃ አለ፣ “ተከራዩ የመንግስት ተቋም ስለሆነ፣ ጠይቁንና ዋጋው ላይ እንደራደር” የሚል ሀሳብ አላቸው ብሎ መጣ፡፡ ህጉ አይፈቅድም፤ እንደ ማንኛውም ተቋም ይወዳደሩ አልን፡፡ ብዙ ሰው የሚፈልገውን ህንፃ እንዴት ተወዳደሩ እንባላለን አሉ እሱ ባለመግባባት እዚህ ላይ ቆመ፡፡  ከሌላ ክ/ከተማ የተወዳደረ የለም፡፡ ካሉን ስድስት የግዢ ዘዴዎች አንዱና ዋናው ግልፅ ጨረታ ነው፡፡ ይህን አድርገን ህድሞና ህንፃን አገኘን ገባን፡፡ የትኛውም ህግ ደግሞ ቦሌ ቢሮ አይሁን አይልም፡፡ አሁን የኮንስትራክሽን ቢሮ የተገመተልን 600 ካሬ ሜትር ነው። ይህን ያህል ነበር የሚያስፈልገው፡፡ ምቹና ተስማሚ ቢሮ አገኝተናል፤ ሌሎችም የመንግስት ተቋማት እዚሁ ህንፃ ላይ ተከራይተው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ቢሮአችን ቦሌ ቢሆን ምንም የምንኮነንበት ምክንያት የለም። ለምን የካ አልሆነም፣ ለምን አራዳ አልሆነም… አማራጭ መገደብ ነው፡፡  
የአራት ኪሎው ቢሮ እስከ ሰኔ ተከፍሎ እዚህ ከመጋቢት ጀምሮ መግባታችሁና ደብል የቢሮ ኪራይ መክፈሉ አግባብ ስላልሆነ የተነሳውን ቅሬታ አልመለሱልኝም?
ሁለቱም ጋ ደብል አልተከፈለም፤ ልዩነት የሚባል ነገር አለ፡፡ አዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ በእኛ መዋቅር መሰረት፣ ለዚህ ተቋም ምን ያህል ካሬ እንደሚያስፈልገው ግምት ሰጠን፡፡  ያ ግምት ሲቀነስ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ከያዝነው ቢሮ ካሬ ተቀንሶ ነው እዚህ የገባነው፡፡ አራት ኪሎ የነበረው እርግጠኛ አይደለሁም፤ ወደ 150 ኪ ሜትር ነው፤ እሱን ቀንሰን ነው ጨረታ ያወጣነው፡፡ አየሽ ልዩነቱን እዚህም አልከፈልንም፡፡ እዛ ቢሮ ውስጥ እስከ ሰኔ አንድ ዳይሬክተሬት ክፍል ቀርቶ ስራውን በዚያ ሲሰራ ነበር፡፡ ስለዚህ ልዩነቱን እንጂ ሙሉ በሙሉ አልነበረም ስንከፍል የነበረው፡፡ ከሰኔ በኋላ አንድ መቶ ካሬ ሊጨምርልን የሚችል ብለን ነው መስፈርት ያወጣነው፤ ህንፃው አሁን ጨመረልን
ለቢሮ ፓርቲሽን የወጣው 1.2 ሚ.ብር እና ለዚህ ቢሮ በዓመት የሚከፈለው 4.ሚ ብር አንድ ላይ ሆኖ ተቋሙ የራሱን ቢሮ መገንባት ነበር የሚሉ አሉ…?
ይሄ እንግዲህ ሰው ብዙ ሊያወራ ይችላል፤ ሁሉም ነገር እንደሚወራው ቀላል ስላልሆነ በዚህ ላይ አስተያየት መስጠቱ ተገቢ አይደለም፡፡
ከቅጥር ከደሞዝ አከፋፈል ጋር በተያያዘም የተነሳ ቅሬታ አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ አይነት ደረጃ ኖሯቸው፣ ደሞዛቸው ከፍና ዝቅ የሚል እንዳለ ሰምቻለሁ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
ሌላው ደጋፊ የስራ ሂደቶች ሲቪል ሰርቪስ ህግና ደንብ መሰረት የተቀጠሩ ሲሆን እርስዎና ዋና የስራ ሂደቶቹ በሲቪል ሰርቪስ ባልፀደቀ ደሞዝ ነው ቅጥራችሁ። ለምሳሌ የእርሶ ደሞዝ 25 ሺህ ብር ነው ተብሏል። በሌላ በኩል አበልን በተመለከተ የቢሮው ሰራተኞች ስራ ሰርተው አበል ሲፈቀድላቸው የሚያፀድቁት እርስዎ እንደሆኑና በአከፋፈሉ ውስጥ ራስዎን አስገብተው አበል እንደሚወስዱም ሰምቻለሁ፡፡ ምላሽዎ ምንድን ነው?
ከባድ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው የተከፈተው፤ ይህንን አልቀበለውም፡፡ እኔ አበል ባፀድቅም ራሴን እዛ ውስጥ አስገብቼ አላውቅም፡፡ የደሞዝ ስኬልን በተመለከተ 25 ሺህ ብር በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር የለም ለተባለው ይሄ ፕሮጀክት ነው፡፡ ደሞዙን የተከልኩትም ያፀደኩትም እኔ አይደለሁም፡፡ የዳይሬክተር ደሞዝ ስንት ይሁን የሚለው የፀደቀው በካቢኔ ነው፡፡ መጀመሪያ 33 ሺህ ይሁን ተብሎ ፕሮፖዝ እንደተደረገና በኋላ በ25 ሺህ ብር እንደፀደቀ እኔ ከመጣሁ በኋላ መረጃው ደርሶኛል፡፡ እኔ ቅጥር ሲካሄድ መሀል ላይ ነው የመጣሁት፡፡ የመዋቅር ጥናቱ ላይም አልነበርኩኝም፡፡ በፀደቀው መዋቅር መሰረት ነው የተቀጠርኩት፡፡ ተመሳሳይ የትምሀርት ደረጃ እያላቸው ደሞዛቸው ለምን ተለያየ ላልሺው፣ መጀመሪያ የፀደቀው መዋቅራዊ ጥናት እርከን ነበረው፡፡ እርከኑ ሶስት ገባ ብሎ መቀጠር አለበት ይላል፡፡
ሶስት ገባ ብሎ ማለት ምን ማለት ነው?
ለምሳሌ የደሞዝ እርከን አለ፡፡ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት ሶስት እያለ ይሄዳል፡፡ ሶስት ገባ ብሎ ሲባል ለምሳሌ 16 ሺህ ተወስኖ ከነበረ 18 ሺህ ሆኖ እንዲቀጠር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይሄ ለአላማ ፈፃሚዎቹ ነው፡፡ ይሄ ማስታወቂያ ወጥቶ ቅጥር ላይ እኔ መጣሁ ማለት ነው። አሁንም ማስታወቂያ ሲወጣ፣ እኔ አልነበርኩም። በወጣው ማስታወቂያ የተወዳደሩት ተቀጠሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ዘግይተን ደጋፊ የስራ ሂደት ስናስፈቅድ፣ ሶስት ገባ ብሎ መቅጠር አይቻልም ተባለ ግዢ ፋይናንስና የሰው ሀይል አስተዳደር ናቸው፡፡ ግዢ በፕሮጀክትም ሆነ በሲቪል ሰርቪስ ያው ግዢ ነው፡፡ በሲቪል ሰርቪስ የደሞዝ መዋቅር ነው የሚቀጠሩት ተባለ እኔ እንደውም ሶስት ገባ ብለው እንዲቀጠሩ ብዙ ጊዜ ሲቪል ሰርቪስ ተመላልሼ ለማስፈቀድ ሞክሬ አልተቻለም፡፡
በኋላ ግን ቅሬታ አቅርበው የተስተካከላቸው ሰራተኞች እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ሊሆን ቻለ?
የተስተካከሉ የደሞዝ መደቦች አሉ፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ተሳስቶ ከፍተኛና መካከለኛ ባለሙያ በሚሉ መደቦች ላይ ደረጃውን እኩል አድርጎት ነበር፡፡ ሲቪል ሰርቪስ የፈቀደውን ተቀብለው፣ የኛ ተቋም ማስታወቂያውን ጋዜጣ ላይ አወጡ፡፡ ሰራተኞች ያንን ደረጃ አይተው ከሌላ ቦታ ስራቸውን ለቅቀው መጥተው ተቀጠሩ። ቅጥር ላይ ደሞዙ እኩል መሆኑን ስናረጋግጥ፣ መደቡ ከፍተኛ መካከለኛ ይላል፤ ደሞዙ እኩል ነው፤ እንዴት ነው ይሄ፤ እንዴት ይስተካከል ብለን ደብዳቤ ፃፍንላቸው። እነሱ ደግሞ ይሄ የኛ ስህተት ስለሆነ መካከለኛ የነበረው ከፍተኛ ይሁንና ደረጃቸው እኩል ሆኖ ይከፈል የሚል ማስተካከያ ፃፉልን፡፡ በዚያ መሰረት ተስተካክሏል። እኛ በግላችን የምንሰራው ማስተካከያ የለም ሲቪል ሰርቪስ ብቻ ነው የሚያስተካክለውም የማያስተካክለውም፡፡
ሌላው የተነሳባችሁ ቅሬታ የመንግስት ንብረትን ለግል ጥቅም ማዋል የሚል ነው፡፡ እርስዎና አቶ ገ/መስቀል የተባሉ የጽ/ቤቱኃላፊ ተጨማሪ ስራዎች እንዳላችሁ መኪናና ነዳጅ ለራሳችሁም ስራ እንደምታውሉ ቅሬታ ቀርቧል፡፡ እርስዎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ያስተምራሉ። አቶ ገ/መስቀልም ሜክሲኮ በሚገኘው ቱሪዝም ኮሌጅ ቋሚ ሰራተኛ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡
እኔ ስለራሴ ብቻ ልመልስ:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅዳሜና እሁድ አስተምር ነበር፡፡ ለዚያ ስራ ግን መኪና አልጠቀምም:: የተባለው ሀሰት ነው:: ለዳይሬክተሮች ሹፌሮች እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወቂያ ወጥቶ፣ ሾፌሮች ሲቀጠሩ ነው የመጣሁት፡፡ ሹፌሮቹ ግን ያለመኪና ነው የተቀጠሩት፡፡ ይህ ቅጥር የተካሄደው በባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው፡፡ ሹፌሮቹ ሲቀጠሩ መኪና ስላልነበረ መኪና እስኪገዛ ቅጥሩን አዘገየነው። ተሯሩጠን ሶስት መኪኖች ሲገዙ ግን ሹፌር ቶሎ ለማግኘት አልቻልንም፡፡ አቶ ገ/መስቀል ዳይሬከተር ናቸው፡፡ ሹፌር ሲጠፋ ራሳቸው እንዲይዙ አደረግን፤ የመንጃ ፍቃድ ስላላቸው፡፡ ሁለት ሾፌሮች አሉ፤ አንዱ የኔ ሾፌር ናቸው። ሌላው የሌላ ዳይሬክተር ሾፌር ነው፡፡
ስለዚህ መኪኖቹን ለምሳሌ እርስዎ ዘመድ ጥየቃ ሽርሽር ሲሄዱም ሆነ ለሌላ ስራ መጠቀም ይችላሉ?
እኔ እዚህ አካባቢ ዘመድም የለኝም፡፡ ሽርሽር ሄጄ አላውቅም ብዙ ጊዜዬን በስራ ላይ ነው የማሳልፈው። መኪናም ቢሆን ከተፈቀደልኝ ነዳጅ ፍጆታ በታች ነው የምጠቀመው፡፡ ከኖርሙ ውጭ እንድንጠቀም አይፈቀድልንም፡፡ የእኔ ለአንዱ ወር የተፈቀደልኝ ሳያልቅ ነው ሌላው ወር የሚደርሰው፡፡ መኪና ይዤ መንቀሳቀስ ግን እችላለሁ፡፡
በወር ምን ያህል ሊትር ነዳጅ ይፈቀድልዎታል?
220 ሊትር ነዳጅ ይፈቀዳል፡፡ የእኔ አሁን ማየት ከቻልሽ ካርዱ ላይ ከ10 ሺህ ብር በላይ ነዳጅ አለው። ኖርሙ ኮፈቀደው
በታች ነው የምጠቀመው፡፡ በአጠቃላይ ባህሪዬ ስራ ካልተሰራና ውጤት ካላየሁ ቁጡ ነኝ፡፡ ብዙ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶብኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፒኤችዲ የለውም እስከማለት ተደርሶ፣ የትምህርት ማስረጃዬ ተፈትሾ ተረጋግጧል፡፡ ስራዬን በአግባቡ የምሰራና ያንንም በተግባር የማሳይ ነኝ፡፡ ቁጣዬን፤ ማሸማቀቅ ማስፈራራት እያሉ የሚተረጉሙት ስሜን ለማጥፋት ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጥኩት ለአገሬ ያለኝን የራሴን አበርክቶ ለማዋጣት እንጂ በተሻለ ደሞዝ፣ በተሻለ ሁኔታ መስራት እችላለሁ። ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ትልልቅ አለማቀፍ ኩባንያዎች ላይ ሰርቼ ልምድ አካብቻለሁ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በርካታ የቢሮው ሰራተኛ ስራ በመፈለግ ላይ እንዳለስ ያውቃሉ?
ሁሉም ሥራውን በትጋትና በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ስለመሆኑ እንጂ አሁን ስላልሺው ነገር መረጃ የለኝም፡፡

Read 3346 times