Print this page
Saturday, 19 August 2017 14:50

“ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን፣ በሰው ሃይልም በማቴሪያልም እየገነባን ነው”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

 በተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና ጉዳቶችን ለማከም ታስቦ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ሚሊኒየም ሚዲካል ኮሌጅ ሥር የተቋቋመውና ከሁለት ዓመታት በፊት አገልግሎቱን መስጠት የጀመረው “አቤት ሆስፒታል”፤ የዕድሜ ምርመራን ጨምሮ አዳዲስ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ የሆስፒታሉን አዳዲስ አገልግሎቶች በተመለከተ ከሆስፒታሉ የፎረንሲክና ሥነ ምረዛ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ጌታሁን ካሣ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

       በሆስፒታሉ የሚሰጡት የህክምና እና የምርመራ አገልግሎቶች ምንድናቸው?
ሆስፒታሉ ሲቋቋም ከድንገተኛ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህክምና ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡ በዋነኝነት ከአደጋ ጋር የተያያዙ የአንገት መሰበር ችግሮች፣ የአንጎል ጉዳቶች፣ የቃጠሎ አደጋዎች--- ህክምናን ይሰጣል፡፡
ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለየ፣ በድንገተኛ አደጋ ጉዳት አጋጥሟቸው ለሚመጡ ህሙማን የሚደረግ የተለየ ህክምና አለ?
ሆስፒታሉን ከሌሎች ሆስፒታሎች የተለየ የሚያደርገው ነገር፣ አንድ ሰው በአደጋ ሲጎዳ ለሚገጥመው የጤና ችግር አስፈላጊ የሆነ ህክምና መስጠት የሚችሉ የተለያዩ ስፔሻሊስት ሃኪሞች መኖራቸው ነው፡፡ ለምሣሌ የመኪና አደጋ ቢከሰት፣ አጥንት ሊሰበር ይችላል። የአጥንት ሐኪሞች ይህን ያክማሉ፡፡ ጭንቅላት ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፣ ለዚህ ደግሞ ኒውሮሎጂስቶች ይኖራሉ፡፡ የውስጥ ደዌ ሃኪሞችም አሉ፡፡ እነዚህ 3 የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች በአንድ ቦታ ላይ ማግኘቱ፣ ለታማሚው ጠቀሜታው እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አንዱን ህክምና ብቻ ሰጥቶ፣ ለሌሎቹ ችግሮች ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር የማድረጉን ሥራ በማስቀረት፣ አደጋው የደረሰበት ሰው፣ አፋጣኝና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ታማሚው ከአንዱ ሆስፒታል ወደ ሌላው ሆስፒታል በመመላለስ የሚያጠፋው ጊዜ የጉዳቱን መጠን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ሆስፒታሉ ከአደጋ ጋር በተያያዙ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ምን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል?
ቅድም እንደነገርኩሽ፣ ሆስፒታሉ ሲቋቋም ለተለያዩ በአደጋ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህክምና ለመስጠት ታስቦ ቢሆንም በሥሩ የፎረንሲክ ህክምናና የሥነ ምረዛ ህክምና ክፍል ተቋቋመ፡፡ ይህ ክፍል ከተቋቋመ በኋላ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ፡፡ አገልግሎቶቹ በሦስት ይከፈላሉ። የመጀመሪያው የአስከሬን ምርመራ ሲሆን ይህም በተለያየ ሁኔታ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች (ከወንጀል ሁኔታ ጋር በተያያዘ) ራስን ማጥፋት፣ የሰው ግድያና መሰል ነገሮች ሲከሰቱ፣ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን ለጠያቂው አካል የመስጠት አገልግሎት አለን። ይህ አገልግሎት ቀደም ሲል በሚኒሊክ ሆስፒታል ብቻ የሚሰጥ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ የቅሬተ አካል ምርመራ እናደርጋለን፡፡ ይህ ምርመራ  ሰዎች ከሞቱ በኋላ ማንነታቸውን ለማወቅ የሚያስችል የምርመራ አይነት ነው፡፡ ይህ በአገራችን ያልነበረ፣ አዲስ የምርመራ አይነት ነው፡፡ ሌላው አስከሬን ከተቀበረበት ቦታ አውጥቶ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሰዎች ከተቀበሩ በኋላ በአሟሟታቸው ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ የሚያሣድሩ ነገሮች ከተፈጠሩ፣ የተቀበሩበት ሥፍራ ሄዶ አስከሬኑን አውጥቶ ምርመራ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ሌላው በሆስፒታላችን እየተሠጠ ያለው አገልግሎት የክሊኒካል ፎረንሲክ ምርመራ ነው፡፡ ይህ ማለት የዕድሜ ምርመራ የሚደረግበት የምርመራ አይነት ነው፡፡ የፆታዊ ጥቃት ምርመራና ሕክምናንም እንሰጣለን፡፡ ምረዛም በዚህ ውስጥ የሚካተት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እስከዛሬ በአገራችን ያልነበሩ የተለያዩ የምርመራ አይነቶችን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡
የዕድሜ ምርመራ አገልግሎት ፈልገው ወደ ሆስፒታላችሁ የሚመጡት ምን አይነት ሰዎች ናቸው?
በአብዛኛው የፍትህ አካላት ናቸው፡፡ ፖሊስ፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮዎች ሲሆኑ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሲፈፀም፣ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስና መሰል ነገሮች ሲከሰቱ ምርመራው ይፈለጋል፡፡
በግለሰብ ደረጃ የሚመጡስ የሉም?
ይመጣሉ፡፡ ብዙም ባይሆኑ ይመጣሉ፡፡ በእርግጥ ምርመራው ታስቦ የተጀመረው በተለያዩ የፍትህ ጉዳዮች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታትና ረዥም ጊዜ ይወስድ የነበረውን ሂደት ለማስቀረት ነው፤ ሆኖም ግን በግለሰብ ደረጃ ምርመራውን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ካሉ መስጠቱ ጉዳት የለውም በሚል ጀመርነው። እኔ ዕድሜዬን ማወቅ እፈልጋለሁ ብለው የሚመጡ ሰዎች፤ አገልግሎቱን እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ ይህም ዕድሜዬን ፈፅሞ አላውቀውም ለሚሉ ሰዎች መፍትሔ የሚሰጥና በጡረታ ዕድሜ መድረስና አለመድረስ ሣቢያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንም ለማስቀረት የሚያስችል አሠራር ነው። ይህንን አገልግሎት ፈልገው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከሃያ አምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ናቸው፡፡ በእርግጥ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ፣ በምርመራ የሚገኘው የዕድሜ ትክክለኛነት መጠንም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም በዕድሜ ብዛት በሰውነታችን ላይ የሚከሰቱ ለውጦች፣ የምርመራ ውጤቱ ትክክለኛነት ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ ነው፡፡
በትክክል የዕድሜ መጠንን ማወቅ አይቻልም ማለት ነው?
ቅድም እንዳልኩት ነው፤ እድሜ ሲጨምር የትክክለኛነት መጠኑም ማለት የስፋት መጠኑ ይጨምራል፡፡ በዝቅተኛ ዕድሜ ላይ ካሉ አንድ ዓመት ወደ ላይ ወይም ወደ ታች የዕድሜያቸውን ልክ ማወቅ ይቻላል፡፡ ዕድሜው ሲጨምር ሁለት ሶስት ዓመት እያለ ሊጨምር ይችላል፡፡ ትክክለኛውን (እቅጩን) ማወቁ ግን አሁን በደረስንበት ደረጃ አይቻልም፡፡
የዕድሜ ምርመራ ለማድረግ በቀን ምን ያህል ሰዎች  ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ?
የዕድሜ ምርመራን የጀመርነው ከሦስት ወራት ወዲህ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ስለ አገልግሎቱ በቂ መረጃ ያለው አይመስለኝም፡፡ እንደዛም ሆኖ በአማካይ በቀን አራት ሰዎች አገልግሎቱን ፈልገው ወደ ሆስፒታላችን ይመጣሉ።
ለአስከሬን ምርመራስ?
የአስከሬን ምርመራ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው በሚኒሊክ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡ ይህ በጣም ትልቅ መጨናነቅን የሚፈጥር ነገር ነበር፡፡ እኛ ከጀመርን በኋላ ሸክሙን ተካፍለነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛ አገልግሎቱን የምንሰጠው በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ላሉና የእኛን የምርመራ መረጃ ገላጭነት ፈልገው ለሚመጡ ሰዎች ነው። አገልግሎቱን መስጠት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከ2300 በላይ የአስክሬን ምርመራ አድርገናል። ይህም በአማካይ በቀን 7 እና 8 ሰዎችን እናስተናግዳለን ማለት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሚኒሊክ ሆስፒታል ተዘግቶ በነበረበት ወቅት እስከ 15 እና 20 ድረስ እናስተናግድ ነበር፡፡
ክፍያችሁ ምን ያህል ነው?
ለአስክሬን ምርመራ 100 ብር እናስከፍላለን። ለዕድሜ ምርመራና ለፆታዊ ጥቃት ምርመራዎች አናስከፍልም፡፡
አንዳንድ ሰዎች የአስክሬን ምርመራ በሚደረግበት ወቅት የተለያዩ የሰውነት አካላት ይወሰዳሉ የሚል ስጋትና ጥርጣሬ አላቸው፡፡ የአንድ ሰው የሰውነት አካል ከሞተ በኋላ ለሌላ ሰው አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ ወደዚህ ሆስፒታል ከመምጣቴ በፊትም ይህንን ጥርጣሬ እሰማው ነበር። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቀና ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ሰዎች የአስከሬን ምርመራ ሲደረግ በፊልምም የሚያዩት ይመስለኛል። የሰውነት አካል የሚታየው ተከፍቶ ነው፡፡ ይህ የግድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ጉዳት መታየት ይኖርበታል፤ ስለዚህ ሰውነት ተከፍቶ ከታየ በኋላ ይሰፋል፡፡ ይህን በማየት የሰውነት አካል ተወስዶብናል ይላሉ። ይህ ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነገር ነው፡፡ ሰው ህይወቱ ካለፈ በኋላ የሰውነት አካላቱ ከአገልግሎቱ ውጪ የሚሆኑበት የተወሰነ ጊዜ አላቸው። ሞት ማለት በራሱ ሂደት ነው፤ ሂደቱ በሦስት መንገዶች ይከናወናል፡፡ የመጀመሪያው የአንጎል ሥራ ማቆም፣ ቀጥሎ የልብ፣ ከዚያም የሣንባ ሥራ ማቆም ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሰውነታችንን የገነቡት ሴሎች፣ ቀስ በቀስ እየሞቱ ይሄዳሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ለሴሎቻችን የሚሰራጨው ደም ካቆመ በኋላ ባሉት ውስን ጊዜያቶች ካልሆነ በስተቀር፣ ሙሉ በሙሉ ከሞተና ጊዜው ካለፈ በኋላ የሚገኘውን የሰውነት አካል መልሶ መጠቀም አይቻልም፡፡ ለፎረንሲክ አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ስለዚህም የሰውነት አካል ተወሰደ የሚባለው ነገር ፈፅሞ ከእውነቱ የራቀ ነው።
በአገራችን የዲኤንኤ ምርመራ የሚያደርጉ ላብራቶሪዎች ባለመኖራቸው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማውጣት ወደ ውጪ አገር ልኮ ማስመርመር የግድ ነው፡፡ ይህንን ምርመራ በአገራችን ለመጀመር ሃሣብ የላችሁም?
ቅድም እንዳልኩት በዚህ በፎረንሲክና ሥነምረዛ ህክምና ክፍል ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል የፎረንሲክ ሣይንስ አንዱ ነው፡፡ የዚህ ምርመራ ሥራና ባለሙያዎችን የማብቃቱ ነገር በወረቀት ሥራ ላይ ነው ያለው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ይጀመራል የሚል እምነት አለን፡፡ ለዚህ ሥራ የሚሆኑ ባለሙያዎችን ወደ ህንድ ልከን እየሰለጠኑ ነው፡፡ የሁለት ዓመት ስልጠና ነው የሚወስዱት። በዚህ ሣይንስ ውስጥ ካሉት የምርመራ አይነቶች አንዱ የዲኤንኤ (የዘረመል) ምርመራ ነው። የዚህን ምርመራ አገልግሎት የሚፈልጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም አገልግሎቱን በአገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት ሲቸገሩ እናያለን። ወደ ውጪ አገር  እየተላከ ለሚደረገው ለዚህ ምርመራ የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ነው፡፡ እሱን አገልግሎት እዚሁ ለመጀመር ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ አንድ አደጋ ተከስቶ የሟቹን ማንነት ለማወቅ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን፣ ከስፍራው በመገኘት፣ ከፀጉር ከደምና መሰል ነገሮች የሟችን ማንነት ለማወቅ የሚቻልበት ምርመራንም ከዚሁ ጋር አብረን ለመጀመር አቅደናል። በተጨማሪም የአሻራ ምርመራ ቀደም ሲል በፖሊስ ይሰጥ የነበረውን፣ አሁን በዚህ ሆስፒታል እንዲሰጥ ለማድረግ ዝግጅታችንን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን።
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን እየገነባን ነው፤ በሰው ሃይልም በማቴሪያልም፡፡ ሆስፒታሉን ሜድኮ ሌጋል ኢንስቲቲዩት ለማድረግ ግንባታ እያከናወንን ነው። ማስተማሪያና አገልግሎት መስጫ ሆኖ ያገለግላል። በየክልሉ ያሉ እንግልቶች እንዲቀሩ ለማድረግ፣ በየክልሉ አገልግሎቶቹን ለማድረስ እንሰራለን። በዚህ አጋጣሚ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አመራሮች እያከናወኑ ያሉት ተግባር በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ ለመናገር እፈልጋለሁ። በተለይም ዶ/ር ዘሪሁን አበበ፣ ለፎረንሲክ ሜዲስን ዲፓርትመንት ለሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ወደፊትም እንዲቀጥልበት አደራ እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 6070 times