Print this page
Saturday, 19 August 2017 14:53

ሙስና በኢትዮጵያ፤ በዓለም አቀፍ ሕግ እይታ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  “--አንድ የአሜሪካ ኩባንያ አንድ ጥቅም ለማግኘት፣ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ጉቦ በሚሰጥበት ጊዜ በአሜሪካ
በወንጀል ሲከሰስ፣ አትዮጵያዊው ባለሥልጣን በኢትዮጵያም ውስጥ ይጋለጣል ማለት ነው፡፡ የተቀበለውም ገንዘብ
አሜሪካ ከዘለቀና በኢትዮጵያ በኩል ጠያቂ ካለ፣ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ይችላል፡፡---”
                 በዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም

     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉቦ ወይም ሥልጣንን ተገን አደርጎ፣ አገርና ሕዝብን መበዝበዝ፣ በግዕዝ ቋንቋ ተሽሞንሙኖ፣ “ሙስና” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ በስልጣን መባለግና የሕዝብ ወይም የግለሰብ ንብረት መዝረፍ - “ሙስና”፣ ትርጉም፣ ከእንግሊዝኛ አቻው- corruption ጋር ጨርሶ አይመጣጠንም። ምናልባት “ሙስና” የሚለውን ቃል እንደ እንግሊዝኛው በሚሰቀጥጥና ከመነሻው አጸያፊ በሆነ የአማርኛ ቃል መለወጥ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡  
በእንግሊዝኛ አንድ ሰው “ኮረፕት” (corrupt) ሆነ ሲባል፣ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ዘረፈ ከማለት በተጨማሪ በሰበሰ፣ ተበላሸ፣ ቆሸሸ የሚል አንድምታንም ይጨምራል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው አገራዊ ብሂል የሚያመለክተው ጉቦ ባህል ሆኖ መኖሩን ቢሆንም  መጠኑ ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአንድ ሽንጥና ከጠርሙስ አረቄ ያልበለጠ ነበር፡፡ ዶላር ወይም ዩሮ በሚሊዮኖች ዘርፎ በተለያዩ አገራት ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን፣ የተንጣለሉ ቪላዎችን መግዛት፣ የውጭ ባንኮችን በማጠራቀሚያ ሂሳብ ማጣበብ በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ተጸንሶ ተወልዶ፣ ለአካለ መጠን የደረሰ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡
የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ የሚተባበሩአቸው ነጋዴዎችና ደላሎች ንቅዘት፣ ከሥርዓቱ ጋር ቁርኝት እንዳለው አሌ አይባልም። ስለዚህም ሙሰኝነት ሊከስም የሚችለው ሥርዓቱ ተለውጦ፣ መንግስት ለህዝብ ተጠሪ ሆኖ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡  
በአንድ ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት፣ በባለስልጣናቱ መሃከል የጋራ አስተሳሰብ፣ የጋራ እምነትና የጋራ ዓላማ ስላለ፣ አንዱ ሙሰኛ ባለስልጣን ሌላውን ባለስልጣን አያጋልጠውም፡፡ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግን የሕግ የበላይነት፣ የንግግርና የጽሁፍ ነፃነት በተረጋገጠበት ሁኔታ ሙስና ዋነኛ ችግር አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ፓርቲዎች ባለስልጣናት መካከል የሥልጣን ፉክክር ስለሚኖር፣ አንዱ ባለሥልጣን ሌላውን ሊያጋልጠውና በምርጫ እንዲወገድ ወይም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥርዓት፣ ሕግ አውጪው የፓርቲው ተጠሪ ስለሆነ፣ ሙስናን ለመከላከል የሚያወጣው ሕግ ጥርስ ያለውና ጠበቅ ያለ አይሆንም፡፡ የሕጉ አፈጻጸም ላይ ደግሞ በቅርቡ በአገራችን እንደታየው፣ አንዳንድ አይነኬዎችን ዘልሎ፣ ትኩረቱ በትንንሽ ባለሥልጣናት ላይ ይሆናል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ጎሰኝነት ከማንኛውም የፖሊስ ግብዐት በልጦ ባለበት  ሁኔታ ሙሰኝነት ባይስፋፋ ይገርም ነበር፡፡
በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ውስጥ በምትገኘው አገራችን፣ የሥርዓት ለውጥ ሳይኖር፣ ጥቂት ሙሰኞችን (ያውም ዋና ዋናዎቹ ሳይሆኑ) በማሰር ሙሰኝነትን አጠፋለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ አንድ የጠገበ ሙሰኛ ሲታሰር ሌላ የራበው ብቅ ይላል። በድሮ ጊዜ ታላቋ ብሪታንያ፣ ኪስ አውላቂዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት በስቅላት ትቀጣ ነበር ይባላል። ታዲያ ኪስ አውላቂዎቹ ሲሰቀሉ፣ ሌሎች ኪስ አውላቂዎች ከተሰበሰበው ሕዝብ ኪስ ይመነትፉ ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው እውነተኛና ዘላቂ የሥርዓት ለውጥ በማድረግ እንጂ ጥቂት ግለሰቦችን  በመቅጣት ብቻ  ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል  ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ በአብዛኛው ልንተነትን የምንሻው፣ በአገር ውስጥ የሚፈጸመውንና በዚሁ በአገራችን ፎቅ የሚሠራበትን ወይም ፋብሪካ የሚቋቋምበትን ወይም የተንጣለለ ቪላ የሚሠራበትን ሙስና አይደለም፡፡ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ግለሰቦች፣ ከግለሰብም ይሁን ከአገር ገንዘብ እየዘረፉ፣ ወደ ውጭ አገር የሚያሸሹትን፣ በእንግሊዝኛው Indigenous spoliation በሚባለው ላይ ሲሆን አገራትን ከእንዲህ ዓይነት የዘረፋ ወንጀል ለመከላከል የተደነገጉ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡  
በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት እንደገለጸው፤ ከአገር በሕገ ወጥ መንገድ የአገር ሃብት ተዘርፎ፣ ወደ ውጭ ከሚጓዝባቸው አሥር የአፍሪካ አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአማኒነት ያተረፈው እውቁ ፎርብስ መጋዚን (Forbes magazine) ከኢትዮጵያ በ20 ዓመታት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የወጣው ገንዘብ መጠን፣ ሰላሳ ቢሊዮን (30,000,000,000) ዶላር መሆኑን ዘግቧል፡፡ ይህ ገንዘብ ለመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ በረሃብ የሚሰቃዩ ስምንት ሚሊዮኖችንም ጨምሮ ቢከፋፈል፣ እያንዳንዱ 7200 ብር ይደርሰዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች፣ ይህ ከአገር የወጣው ገንዘብ ውሀ በልቶታል፤ ወደ አገር የሚመለስበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ገንዘቡ ያለበት አገር ሉዐላዊ እንደመሆኑ መጠን ገንዘቡ ወደ አገር እንዲመለስ የማድረግ ግዴታ የለበትም ይላሉ፡፡ ሆኖም ዛሬ የዓለም ሕግ በእጅጉ ተለውጦአል፣ በሉዐላዊነት ስም አንድ መንግሥት በአገሩም ውስጥ ቢሆን ያሻውን ማድረግ አይችልም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ሂትለር ብዙ ጀርመኖችን እየገደለ በነበረበት ወቅት ቸርቺል፤ “ግድያውን ማቆም አለበት” ሲል የሰማው ሂትለር፤ “ግማሹን የጀርመን ሕዝብ  ብገድል ቸርቺል ምን አገባው፣ ሉዐላዊ አገር መሆናችንን ዘነጋ ወይ” ሲል መለሰ። ዛሬ በሉዐላዊነት ስም ሕዝብን መጨፍጨፍ፣ የአንድን አገር ሕዝብ ገንዘብ ዘርፎ በዱባይ፣ በካናዳ፣ በአሜሪካ ወዘተ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ማነጽ፣ በሚስት ወይንም በልጅ ስም በተከፈተ ሂሳብ የሌላ አገር ባንክ አጣብቦ፣ ሕዝብን ለችጋር መዳረግ፣ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በቸልታ የሚያየው ነገር አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በዴሴምበር 10 ቀን 2003 ዓ.ም ያጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት የጸረ ሙስና ስምምነት፤ ሙስና የአንድ አገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብን የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ደንግጓል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ንብረታቸውን በአንድ ማዕከል ውስጥ እንዲያስመዘግቡ ያሳስባል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕግ አክብረው፣ ንብረታቸውን እንዳላስመዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ ይሄው የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት፣ በአንቀጽ 44፣ አንድ ባለሥልጣን ወይንም ግለሰብ በጉቦም ይሁን በሌላ መልክ ከአገሩ ገንዘብ ዘርፎ አገሩን ቢለቅ፣ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው፣ ዘራፊው እስከዘረፈው ገንዘብ ወደ አገሩ ተመልሶ፣ ለፍርድ ይቀርብ ዘንድ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት እንዲተባበሩ ተደንግጓል፡፡
ብዙ አገራት በተለምዶ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ፣ ኩባንያዎቻቸው በሌላ አገራት ገንዘባቸውን በሥራ ላይ በሚያውሉበት ጊዜ (invest) ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ ለአገራቱ ባለሥልጣናት ጉቦ መስጠት የተከለከለ ሲሆን ጉቦ በሰጡ ጊዜ ደግሞ በየአገራቸው በወንጀል እንደሚጠየቁ ሕጎቻቸው ይደነግጋሉ፡፡ የእነዚህ ሕግጋት ዋናው ዓላማ፣ በኩባንያዎቹ መሃከል ነፃ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ ቢሆንም ክሱ ግን ጉቦኞችን ማጋለጡ አይቀርም። አንድ የአሜሪካ ኩባንያ አንድ ጥቅም ለማግኘት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን ጉቦ በሚሰጥበት ጊዜ በአሜሪካ በወንጀል ሲከሰስ፣ አትዮጵያዊው ባለሥልጣን በኢትዮጵያም ውስጥ ይጋለጣል ማለት ነው። የተቀበለውም ገንዘብ አሜሪካ ከዘለቀና በኢትዮጵያ በኩል ጠያቂ ካለ፣ ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕግ የደነገጉት በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሲሆኑ ሌሎቹ እንዲያውም ገንዘብ ማሸሺያና መደበቂያ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ቻይና እንዲህ ዓይነት ሕግ የላትም። ስለዚህ የቻይና ኩባንያዎች  ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ጉቦ እንዳሻቸው ሊሰጡ ይችላሉ፤ ከዚያም አልፎ ለባለሥልጣናት የሰጡት ጉቦ እንደ ወጪ ተቆጥሮላቸው፣ ለመንግሥት ከሚከፍሉት ቀረጥ ሳይቀነስላቸው ሁሉ አይቀርም፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት ሕግጋት በተጨማሪ የሕዝብን ገንዘብ ዘርፎ ወደ ሌላ አገር ማሻገርና ሕዝብን ችግር ውስጥ መጣል ከሁሉም የከፋ የሙስና ዓይነት ሲሆን ይህም ወንጀል በሰብአዊ ፍጡር ላይ ከሚሠሩ ወንጀሎች (crime against humanity) አንዱ ሆኖአል፡፡ በተለይ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች እንደ ሰብአዊ መብት ጥሰትም ተወስደዋል፡፡
ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት፣ የአንድን ዘር በከፊል ወይም በሙሉ ማጥፋት (genocide) በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል (crime against humanity) የጦር ወንጀል (war crimes) ለመዳኘት ሥልጣን አለው፡፡ በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል፣ ዓይነቱ ብዙ ሲሆን በየጊዜው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች እዚህ ውስጥ መካተታቸው አይቀርም። አሸባሪነትና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ ወደ ሌላ አገር ማሸጋገር (indigenous spoliation) በሰብአዊነት ላይ የሚሠራ ወንጀል ውስጥ እንደሚካተቱ ጥርጥር የለውም፡፡ በነገራችን ላይ በዓለም ዙርያ የሄጉ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን ሥልጣን አንቀበልም ካሉት አምባገነን መንግሥታት ጋር ኢትዮጵያ የተሰለፈች ሲሆን ፍርድ ቤቱን አምርረው ከሚያወግዙ ጥቂት መንግሥታት መካከል ኢሕአዴግ አንዱ ነው፡፡
በሙስና ከአገር ተዘርፎ የወጣ ገንዘብ መንግሥት በሚመሠረትበት ጊዜ የተዘረፈውን ገንዘብ ወደ አገር ማስመለስ ይቻል ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ተዘርፎ የወጣ ገንዘብን ክስ ከፍቶ ለማስመለስ እንዲቻል፣ ክሱ ለረጅም ጊዜ በይርጋ እንዲታገድ የተባበሩት መንግሥታት የጸረ ሙስና ስምምነት ይደነግጋል። እዚህ ላይ ግን አንድ ችግር አለ፡፡ የተዘረፈው ገንዘብ የተቀመጠው ለሰብአዊ መብት ደንታ በሌላቸው በሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮችና በቻይና ከሆነ ማስመለሱ እጅግ ሊከብድ ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም የተዘረፈ የሕዝብ ገንዘብን በማስመለስ በምሳሌነት ናይጄርያና ጋቦንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የናይጄርያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኦባቻ፣ ከዘረፈው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከፊሉ በናይጄሪያ መንግሥት ጠያቂነት ለናይጄሪያ ተመልሶአል። እንዲሁም የቀድሞ የጋቦን ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ፣ፓሪስ ውስጥ የገዛቸው ምርጥ ምርጥ ቪላዎች ተሸጠው ገንዘቡ ወደ አገሩ ተመልሶአል፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው ዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 3266 times
Administrator

Latest from Administrator