Saturday, 19 August 2017 14:56

ከፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ስርዓት ወደ አውራ ፓርቲ ስርዓት (የ25 ዓመት ጉዟችን)

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(6 votes)

  ኢህአዴግ በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የቅንጦት ነገር ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብሎ አበክሮ የነገረን ገና ስልጣን በያዘ በማግስቱ ነበር። ከ25 ዓመት አገዛዝ በኋላ የነገረን ደግሞ “በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ባለው የአውራ ፓርቲ ስርአት ተቃዋሚዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ ፖሊሲያቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ሊዘጋጅ ይገባል” ብሎ ነው፡፡
ይህ እልፍ ኢትዮጵያውያን በማያወላውል ቁርጠኝነት የታገሉለትና ከፍተኛ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉለት የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ምስረታ አላማና ግብ መጨንገፉን የሚያረዳ በመሆኑ፣ ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቡ አሳዛኝ እጣ ነው፡፡
ነገሩን በጣም ኮሚክ የሚያደርገው ግን ኢህአዴግ ከመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ይልቅ ወደ አውራ ፓርቲ ስርአት ያደረገውን ሽግግር ያለ አንዳች እቅድና ጥረት እንዲሁ በመለኮት ሀይልና ፀጋ የተከናወነ አስመስሎ ለማቅረብ መሞከሩ ነው፡፡ እውነታው ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሽግግሩ ኢህአዴግ ቀድሞውኑ በሚገባ አስቦበት፣ በጥንቃቄ ያቀደውና ላለፉት 25 ዓመታት ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ የደከመበት የልፋቱ ውጤት መሆኑን በሚገባ እናውቃለን፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጉዳይ ምንም አማራጭ የሌለው የሞት የሽረት ጉዳይ ነው እያለ ምሎ ቢገዘትም፣ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረውና አድራጊ ፈጣሪ ሊሆን በማይችልበት እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሊፈጥራት የሚፈልገውን “አዲሲቷን የኢህአዴግ ኢትዮጵያ” መፍጠር እንደማይችል ገና ከጅምሩ ያውቃል። እናም በድህረ - ደርግ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ መርመስመስ የጀመሩት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በፖለቲካ ድራማው ከተመልካችነት አሊያም ከአጃቢነት የዘለለ ጉልህ ሚናም ሆነ ቦታ እንዳይኖራቸው ማድረግ የግድ ነው ያለው ኢህአዴግ፤ ለዚህ ውሳኔው ተግባራዊነት በሙሉ ሀይሉና ግለቱን በጠበቀ ተነሳሽነት የተንቀሳቀሰው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ የድራማው መሪ ተዋናይ በመሆን ነው፡፡
ኢህአዴግ ለዚህ አላማው እውን መሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴውን አሀዱ ብሎ የጀመረው የዲሞክራሲያዊ ስርአት ምሰሶ የሆኑትን የዲሞክራሲ ተቋማት፣ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ነው፡፡ “ዛፍ በፍሬው ይታወቃል” እንደሚባለው፣ ነፃና ገለልተኛ መሆን ይገባቸው የነበሩ የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ የኢህአዴግ አመራር ተቀባይና አስፈፃሚ ሆነው አረፉት፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳም የማታ ማታ ሁሉንም እኩል ማጫወት የማይችል፤ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ወደ ኢህአዴግ ያጋደለ ሆነ፡፡
 ኢህአዴግ ልቡ የፈቀደውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በፈለገው ጊዜና ቦታ፣ ለዚያውም በመንግስት ገንዘብና ሀብት ማካሄድ ሲችል፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ መክፈት ተራራ የመናድ ያህል ግዙፍ ፈተና ሆነባቸው፡፡ ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ ማየትም እንደ ብርቅ ነገር የሚቆጠር ሆነ። ይሁን እንጂ አህአዴግ ይህንን ሁሉ አድርጎም አንጀቱ በመጠኑም እንኳ ሊርስ አልቻለም፡፡ እናም ቀጣዩ የቤት ስራው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በዋናነት መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን እለት በእለት በማጥበብ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “የእግር መትከያ ቦታ” እንዳያገኙ ማድረግ ነበር፡፡
በዚህም ኢህአዴግ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም ሶስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ከተካሄደበት ከግንቦት ወር 1997 ዓ.ም ወዲህ መደራጀት እንጂ ተደራጅቶ ተቃዋሚ የሆነ ንቁ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማካሄድ በእጅጉ አስቸጋሪና አደገኛም ጭምር እንዲሆን አደረገው። ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉና የተሻለ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ወጣት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ከስንት አንድ ብቅ ሲሉ የማታ ማታ መክረሚያቸው የት እንደሚሆን መገመት፣ ማንም የማይስተው፣ ከግምቶች ሁሉ እጅግ ቀላሉ ግምት ሆነ፡፡
እንደ መሪዎቹ ሁሉ፣ በአንፃራዊነት በእግሩ መቆም የቻለና የተሻለ የህዝብ ድጋፍ ያሰባሰበ ተቃዋሚ ፓርቲም የመጨረሻ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማናችንም የሚታወቅ ነገር ሆነ። ቅርንጫፍ ቢሮ ለመክፈት ተቸገርን በሚል ስሞታ ሲያቀርቡ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ይባስ ብሎ ተራ ስብሰባ የሚያካሂዱበት የሆቴል አዳራሽ እንኳ እንደፈለጉ ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ደጋፊ መሆን ማንም የሚሰጠውና የማይነሳው፣ በህገ መንግስቱ የተደነገገ መሰረታዊ የዲሞክራሲ መብት መሆኑ ቀርቶ፣ከአንበሶች ዋሻ ገብቶ እንደ መውጣት ያህል የሚቆጠር አደገኛ ነገር ሆነ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና ደጋፊዎች በመሆናቸው ብቻ ስንት ወንድምና እህቶቻችን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት እንደከፈሉ፤ ስንቶቹ ከስራቸው እንደተፈናቀሉ፤ ስንቶቹ በሰበብ አስባበሱ ዘብጥያ ተጥለው፣ የምድር ፍዳቸውን እንዳዩ፤ ስንቶቹ ሀገራቸውንና ቤተሰባቸውን ጥለው እንደተሰደዱ፤ በዚህ የተነሳም የስንቶቹ ቤተሰብ እንደፈረሰ በሚገባ የምናውቀውና ላለፉት 25 ዓመታት በየቤታችን የተሸከምነው መከራ ስለሆነ፣ ሌላ እማኝ መቁጠር ፈጽሞ አያስፈልግም፡፡ እኔም እናንተም፣ኢህአዴግ ራሱም የሚያውቀውን የ25 ዓመት ታሪክ ሳምንት እንቀጥለዋለን። የሳምንት ሰው ይበለን!  

Read 2967 times