Saturday, 19 August 2017 14:57

በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ የሚያስከትል ውል መፈረም!?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

  • “የኮርቤቲ ቅሌት” ተብሎ ይሰየም ይሆን? ኮርቤቲ ምንድነው? ኮርቤቲ - በእንፋሎት ሃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ነው። ስንት ያመነጫል? ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙ - ከጊቤ3 ጋር እኩል ነው። ወጪውስ? የግንባታ ወጪው ግን፣ ከጊቤ3፣... በ50 ቢሊዮን ብር ይበልጣል።
• የ50 ቢሊዮን ብር ብክነት በማን እና መቼ ይካካሳል? ክፍያ ተቀባይ፣ የውጭ ኩባንያ ነው።እዳው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ላይ ነው። በየዓመቱ 550 ሚሊዮን ዶላር፣ የመክፈል እዳ! በዓመት 12 ቢሊዮን ብር! ለ25 ዓመት የሚዘልቅ የመጨረሻ ውል ሊፈረም ተቃርቧል።
• የእዳው ድምር... ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ

      እንደዘበት የገባንበት የአካባቢ ጥበቃ ድራማ
“አረንጓዴ ልማት”፣ “የአየር ንብረት ለውጥ”፣ “የሙቀት ግሽበት”፣ “የአካባቢ ጥበቃ”... “Climate change”, “global warming” “Environment”, “Green Economy”... በሚሉ ሃረጋት የተዥጎረጎረው ዓለማቀፍ ጨዋታ፤ ተብሎ የተጀመረው ጨዋታ፣... ከአመት አመት መዘዙን እያወረደው ነው። ጥፋቱ የሚብሰው ደግሞ፣ በኢትዮጵያና በሌሎች ድሃ አገራት ላይ ሆኗል። ብዙ ቢሊዮን ብር ሃብት በከንቱ እየባከነ ነው። የኮርቤቲ ቅሌትና ብክነት ደግሞ፣ ከእስካሁኖቹ ሁሉ ይከፋል።
ያኔ ገና ሲጀመር፣ “የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ”፣ በዚህም ሆነ በዚያ፣ “ለድሃ አገራት፣ የእርዳታ ገንዘብ ያስገኛል” ተብሎ ነበር የሚታሰበው። “እነ አሜሪካ፣ እነ አውሮፓ... ለድሃ አገራት እርዳታ መስጠት አለባቸው፤ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ መመደብ አለባቸው”... እየተባለ በአለም ዙሪያ ሲለፈፍ፣ ማን ያልሰማ አለ?
“ተጨማሪ እርዳታ!... ከዓመት ዓመት የማይቋረጥ!... 100 ቢሊዮን ዶላር!”...
ይሄው ነበር፣ የዘመናችን “ግሎባል መዝሙር”።
ድሃ አገራት፣ ክረምት ከበጋ፣ እርዳታ ሲጎርፍላቸው፣ በዶላር ሲጥለቀለቁ አይታያችሁም? የማይነጥፍ የቢሊዮን ዶላሮች ጎርፍ፤ ብዙዎችን ቢያስጎመጅስ እንዴት ይገርማል?
በእርግጥ፣ “የማይቋረጥ ቋሚ ምፅዋት”፣... ለዘለቄታው እንደማይበጅ፣... በየአጋጣሚው፣ በግል ሕይወትም ሆነ በአገራት ታሪክ ሁልጊዜ የምናየው እውነት ነው። ትርፍ የለውም። ይልቅስ፣ ከታታሪ የስራ እና የቢዝነስ ሰዎች ይልቅ፣ እብሪተኛ ባለስልጣናትና ‘አጨናባሪ’ የኤንጂኦ ጌቶች፣ በድሃ አገራት እንዲነግሱ ያደርጋል። በዚህም፣ አዳሜና አገሬው ሁሉ፣... በፖለቲካ ሽኩቻና በእርዳታ ሽሚያ ይተራመሳል። ምናለፋችሁ? “የዘላለም ምፅዋት”፣ ለኑሮም፣ ለሰላምም፣ ለህሊናም... አይበጅም። “ከሰው በታች ያደርጋል”፣ “ወደ ተራ እንስሳነት ያወርዳል”።
ቢሆንም ግን... የእርዳታ ጎርፍ፣... ያጓጓል። ለዘለቄታው ባይበጅም፣...  “በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር እየተመደበ፣ እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ፣ ዓለምን የሚያዳርስ ሰፊ የእርዳታ ውቅያኖስ እየመጣ ነው.”.. ተብሎ ሲዘፈንና ሲጨፈር...  ያስጎመጃል፤ ይፈታተናል። “ዳር ቆመን የበይ ተመልካች መሆን የለብንም” የሚል ስሜት እየበረታ ይመጣል።
ዳር ከመቆም ይልቅ፣ መሃል ገብቶ፣ “የግሎባል መዝሙር” ዋና አጫፋሪ መሆን ይሻላል የሚል ምኞት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ይመጣል። ሌላው ቢቀር፣ ከአሜሪካ በተለይም ከአውሮፓ ፖለቲከኞች፣ የገሚሶቹን ወዳጅነት ያስገኝልናል የሚል ማመካኛ ዘዴዎችም ይበራከታሉ።
የበይ ተመልካች ከመሆን ይልቅም፣ ዋና የድግስ አስተናባሪና የምፅዋት አከፋፋይ መሆን ይቻላል። የምፅዋት ጎርፍ፣ ለወደፊት ባያዛልቅም፣ የዛሬን ችግር ለማለፍ፣ ለጥቂት ዓመታት፣ ለአራት አምስት ዓመት፣ ትንሽ ተጨማሪ እርዳታ ብናገኝ፣... ራሳችንን ችለን በሁለት እግር ለመቆምና ለመራመድ፣ በራሳችን አቅም ለመገስገስ ሊረዳን ቢችልስ?
ያጓጓል፣ ያስጎመጃል። በዚህ ስሜትና ግፊት፣ ኢትዮጵያ፣ ወደ አለማቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ዋይታና ሆይሆይታ ውስጥ አልገባችም? በደንብ ገብታለች። መግባት ብቻ ሳይሆን፣ ከዋና አስጨፋሪዎችና አስተናባሪዎች መካከል አንዷ ሆና ነበር። ኢትዮጵያ የመሪዎች ጎራ ውስጥ ለመቀላቀል የቻለችውም፣ በአንዳች ተዓምር አይደለም። በአንድ በኩል፣ ከኢትዮጵያ ነባር ታሪክ ጋር ተያይዞ የመጣ የመልካም ስምና የክብር ቅርስ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የነበራቸው አስደናቂ አቅም ተጨመረበት። እናም፣ ኢትዮጵያ፣ በአለማቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ውስጥ፣ ከዋና ተዋናዮቹ ጋር ለመቀላቀል ገባችበት፡፡ ትልቅ ስህተት!
ነገር ግን፣ አቶ መለስ፣ በጭፍን ዘው ብለው አልገቡም።
ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ አስደናቂ አቅሞች መካከል አንዱ፣ አላባንና ገለባን አለማምታታት ነው (ዲስኩርንና ቁምነገርን አለማደበላለቅ፣ ዋና አላማን አለመዘንጋትና በወረት አርማ አለመዝረክረክ... በማለትም ልንገልፀው እንችላለን።.
በተደጋጋሚ እንደሚሉት፣ “በአቋም ባንስማማም፤ ከድህነት እንድንወጣ የሚያግዘን እስከሆነ ድረስ፣ እንቀበለዋለን። ባያግዘንስ? ልማትን የማያደናቅፍ እስከሆነ ድረስ፣ ጠላታችን አይደለም”።
ለዚህም፣ ምክንያታቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል። ኢትዮጵያ፣ ጨርሶ ለመቀናጣት የምትሞክርበት ሁኔታ ውስጥ አይደለችም። የሕልውና አደጋ ላይ ናት ብለው ያስባሉ። ተተራምሳ፣ ተበጣጥሳ፣ ድራሿ የሚጠፋበት፣ የእንጦሮጦስ አፋፍ ላይ ናት። ከዚህ ጥፋት ለመዳን፣ ከአንሸራታቹ የገደል አፋፍ ለማፈግፈግና ትንሽ እፎይታ ለማግኘት፣ ለበርካታ ዓመታት ያለ ፋታ፣ ሳይዘናጋና ሳይዛነፍ በፅናት የሚካሄድ ጥረትና ስራ ያስፈልጋል ብለው ነበር የሚያምኑት። ከድህነት መላቀቅና ወደ ብልፅግና መራመድ ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ፣ ከድህነት የመላቀቅ ፋታ ማግኘት፣... ከአሰቃቂና ከወራዳ የድህነት ኑሮ መላቀቅ፣... አለበለዚያ ግን፣ አገሪቱ በህልውና መቀጠል አትችልም። በእርግጥ፣ ይህንን የትርምስ፣ የመጠፋፋትና የመበታተን አደጋ፣ እውነተኛ አደጋ ነው ብሎ ከምር እና በደንብ የሚገነዘብ ብዙ ሰው የለም። አደጋው ግን የምር ነው - በሌሎች አገራት በየተራ እያየነው ነው። በኢትዮጵያውም ጫፍ ጫፉን፣ በተለያዩ የቀውስ ፍንጮች አይተናል። እንዲያም ሆኖ፤ ሕልውናን የሚደመስስና መመለሻ የሌለው፣ የመጨረሻ ትርምስና ጥፋት፣ በኢትዮጵያ ላይ እንዳንዣበበ የሚገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ፖለቲከኞች ብዙ አይደሉም። ለዚህም ይመስለኛል፤ ጠ/ሚ መለስ፣ ሳያሰልሱ በየጊዜው እየደጋገሙ ለማስረዳት ብዙ ዓመታት የፈጀባቸው። በሁሉም የፖለቲካ ውሳኔ፣... በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዳይ ላይ፣ ነጋ ጠባ ይህንኑ ሃሳብ እያነሱ ለማስጨበጥ፣ ለበርካታ ዓመታት ሞክረዋል። “ቀዳሚውና ዋናው መመዘኛ ምን እንደሆነ እወቁ። የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ተገንዘቡ። መመዘኛውን በፅናት ያዙ። መቼም ቢሆን ቸል አትበሉ። የሞት ሽረት፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ፣ አትዘንጉ፤... ለአፍታም ቢሆን አትርሱ” የሚል የዘወትር ውትወታ፤ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መለያ ነው። ከሌሎች ሁሉ ጎልቶ የሚታይ መለያ! ለዓመታት አጥብቀው የያዙት፣ ዋና ጉዳያቸውም ይሄው ነው። ነገሩ፤ የሕልውና ጉዳይ ከሆነ፣... የትርምስና የሰላም ጥያቄ፣ የእልቂትና የመሻሻል አማራጭ ከሆነ... ሁሉም ነገር በዚህ መነፅር መታየት እንዳለበት ካመኑ፤... ጠ/ሚ መለስ፣ ነገሩን፣ ዋነኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማጠንጠኛ ጉዳይ እንዲሆን መጣጣራቸው፣“የእያንዳንዱ አቋምና የእያንዳንዱ ድርጊት ቀዳሚ መመዘኛ፣... ይሄው ነው”... የሚል ቋሚ መርህ ለማፅናት፣ ያለመሰልቸት እልፍ ጊዜ ለመናገርና ለማብራራት የተገደዱትም፤ የሞት ሽረት ጉዳይ ስለሆነባቸው ነው። ጉዳዩ፣... የአገር ሕልውና ጉዳይ ሆኖ ስለታያቸውም ነው፤ ለሃያ ዓመት ሚሊዮን ጊዜ እየደጋገሙ ከመናገር ያልተቆጠቡት። በቃ! ቀዳሚው መመዘኛ ይሄው ነው፤... ማለትም... ማንኛውም ውሳኔ፣ ማንኛውም ድርጊት፣... እንዲህ ይመዘናል።
“ከድህነት ለመላቀቅ ይጠቅማል?... ከጠቀመ ጥሩ!”
በሌላ አነጋገር ደግሞ...
“ከድህነት እንዳንላቀቅ ያደናቅፈናል?... ካደናቀፈን፣... ከዚያ በላይ ሌላ ጠላት የለንም”
በዚህ መመዘኛም ይመስለኛል፤ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ በአለማቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ድርማ ውስጥ ለመግባት የተገፋፉት?
የጠ/ሚ መለስ ሁለት ዋና ዋና ትኩረቶችን ተመልከቱ።
የአካባቢ ጥበቃ ድራማ ውስጥ ተዘውትረው የሚነሱ፣ “የካርቦን ልቀት”፣ “የሙቀት ግሽበት”... ምናምን የሚባሉ ጨዋታዎች ላይ ብዙም አላተኮሩም አቶ መለስ።
1ኛ) ከ100 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ኢትዮጵያ ስንት ማግኘት ትችላለች የሚል ነው አንዱ የአቶ መለስ ትኩረት።
2ኛ) የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መከላከል ነው ሁለተኛው የአቶ መለስ ትኩረት። ለዚህም ነው፤ የጊቤ3 ግንባታን የሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችን፣ አቶ መለስ በፅኑ ሲያወግዙ የሰማናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖቹ፣ “የድህነት ጠበቃ” ቡድኖች ናቸው በማለት ነበር - አቶ መለስ የተናገሩት። መናገር ብቻ አይደለም። የጊቤ3 ግንባታን ሲቃወሙ የነበሩ ከደርዘን በላይ የአካባቢ ጥበቃ ማህበራት፣ ዛሬ የሉም። እንዲጠፉ የተደረገበት መንገድ ተገቢም ሆነ አልሆነ፣ አቶ መለስ ጉዳዩን በቸልታ አላዩትም። ለምን?
የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን ለማስቆም የሚደረግ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ፣ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ያነጣጠረ የጥፋት ዘመቻ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ለዚህም ነው፤ አቶ መለስ የማያሻማ አቋም የያዙት።
ያለ ኤሌክትሪክ፣ ከድህነት መውጣት አይቻልም። ከድህነት መውጣት ካልተቻለ ደግሞ፣ የአገር ሕልውና ያከትምለታል። ከዚህ የባሰ ጠላት የለም።... በእንዲህ አይነት ስሌት ነው፤ አቶ መለስ በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች አማካኝነት የሚካሄዱ የጥፋት ዘመቻዎችን ለማውገዝና ለመከላከል ጥረት ያደረጉት። “ከድህነት እንዳንላቀቅ ያደናቅፈናል?... ካደናቀፈን፣... ከዚያ በላይ ሌላ ጠላት የለንም” ብለዋልኮ።
ዛሬስ?
እስከ 50 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የድሃ አገር ሃብት፣ በከንቱ እንዲባክን የሚያደርግ ፕሮጀክት፣ ትልቅ ጥፋት አይደለም ወይ? ከዚህ የባሰ ጠላት ይኖራል ወይ?
ይህንን የጥፋት ዘመቻ ማስቆምስ አይገባም ወይ?
ብክነቱ እስከመቼ እና እስከየት ድረስ ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ፣ የሚወሰነው በዚህ ነው። ከጊዜ በኋላማ፣ በእነዚህ ብክነቶች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉና ድርሻ ያላቸው ሰዎች ሁሉ፣ የህግ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። ከዚያ በፊት፣ ይህንን የአገር ብክነትና ይህንን የሕልውና  ጠላት እንዴት ነው ዛሬውኑ ማስቆም፣ የሚቻለው።
የአቶ መለስን የመመዘኛ መርህ እንደገና መለስ ብለን እናስታውስ። አቶ መለስ ሌሎች ስህተቶች ይኖሯቸው ይሆናል። የመመዘኛ መርሃቸው ግን ትልቅ ፋይዳ አለው። ከከንቱ ብክነትና ከሕልውና ጥፋት ለመዳን ልንጠቀምበት እንችላለን።
እናም፣ ደግመን ደጋግመን ብናስተውለውና ብናስበበት ይሻላል እላለሁ። የመመዘኛ መርሃቸው ግልፅና ቀላል ነው።
ማንኛውም ውሳኔ፣ ማንኛውም ድርጊት፣... እንዲህ ይመዘናል።
“ከድህነት ለመላቀቅ ይጠቅማል?... ከጠቀመ ጥሩ!”
በሌላ አነጋገር ደግሞ...
“ከድህነት እንዳንላቀቅ ያደናቅፈናል?... ካደናቀፈን፣... ከዚያ በላይ ሌላ ጠላት የለንም”
ይህን መመዘኛ ቸል ማለት ምን ማለት ነው?
የቢሊዮን ብሮች ብክነትና የአገር ድህነት
መመዘኛው ቸል ከተባለ፤ ብዙ ቢሊዮን የድሃ አገር ሃብት ይባክናል። ሁለት ሦስት ቢሊዮን ብር ብቻ አይደለም በከንቱ የሚባክነው። አስር እና ሃያ ቢሊዮን ብር ይባክናል - በነፋስ ተርባይኖች ላይ እያየን አይደል? በአዲስ አበባ ባቡር አማካኝነትም ቢሊዮን ብሮች እየባከኑ ነው። ከዚህም በላይ 30 እና 40 ቢሊዮን ብሮች ይባክናሉ - መንግስት የስኳር ቢዝነስን አካሂዳለሁ ብሎ በገባባቸው ፕሮጀክቶች አማካኝነት ብዙ ቢሊዮን ብሮች ባክነዋል። እየባከነም ነው። ፈፅሞ በማያዋጣ የእንፋሎት ሃይል ማመንጫ አማካኝነትም፤ 40 ቢሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ይባክናል - በየአመቱ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር (500 ሚሊዮን ዶላር) በላይ ለመክፈል የሚያስገድድ ውል መፈረም፣ ሌላ ምን ትርጉም አለው? አሁን ባለው ምንዛሬ፣ ወደ 12 ቢሊዮን ብር ገደማ በአመት መክፈል እንደማለት ነው። በአስር ዓመት፣ 5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ነው (ወይም 110 ቢሊዮን ብር)። ክፍያው፣ በዚሁ ይቀጥላል... ለ25 ዓመት።
ከሕዳሴ ግድብ ጋር አነፃፅሩት። የሕዳሴ ግድብ፣ ከ3 እጥፍ በላይ የኢሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ይችላል። ወጪውም፣ አምስት ቢሊዮን ዶላር ነው - 110 ቢሊዮን ብር።
ሦስት እጥፍ የኤሌክትሪክ ሃይል! 22000 ጊጋዋት አወር ገደማ እንደሚያመነጭ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውሱ። ይሄ፣ በጭራሽ የተጋነነ ስሌት አይደለም። ከዚህም በላይ ማመንጨት ይችል ይሆናል። ይህንን ለማረጋገጥም፣ እስካሁን የተገነቡትን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች፣ መመልከት ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ፣ በአማካይ ከሚጠበቅባቸው የማመንጨት አቅም በላይ ነው፣ ኤሌክትሪክ የሚያመነጩት።
ወጪውን በንፅፅር ማየት ይቻላል።
የሕዳሴ ግድብ...
ለ7000 ጊጋ ዋት አወር፣... 1.7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል።
40 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው።
የጊቤ ግድብ ወጪም ከዚህ ጋር ይቀራረባል።
ለ7000 ጊጋ ዋት አወር፣... 1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ
40 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው - ይሄኛውም።
የእንፋሎት ሃይል ጣቢያውስ?
ለ7000 ጊጋዋት አወር፣.... 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ!
90 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው።

የወጪው ልዩነት ብዙ ነው። ተመሳሳይ የሃይል መጠን ለማግኘት፤... በእንፋሎት ሃይል ጣቢያ አማካኝነት እጥፍ ወጪ ፈሰሰ ማለት ነው።
በዚያው ልክ ብዙ ሃብት ይባክናል - ለዚያውም የድሃ አገር ሃብት።
50 ቢሊዮን ብር ልዩነት፣ 50 ቢሊዮን ብር ብክነት... ይዘገንናል።
ምን ይሄ ብቻ!
የእንፋሎት ሃይል ጣቢያ በተፈጥሮው፣ ለበርካታ ብልሽቶች የተጋለጠ ነው። የጥገና ወጪው፣ በጣም ብዙ ነው። ተጨማሪ ወጪ ደግሞ፣ ተጨማሪ ብክነት ነው።
ለመሆኑ ይሄ ሁሉ ብክነት በማን ይካካሳል የሚለው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው።
የ50 ቢሊዮን ብር ብክነት በማን እና መቼ ይካካሳል?
ክፍያ ተቀባይ፣ የውጭ ኩባንያ ነው።እዳው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ላይ ነው።
በየአመቱ 550 ሚሊዮን ዶላር፣ የመክፈል እዳ! በዓመት 12 ቢሊዮን ብር!
ለ25 ዓመት የሚዘልቅ የመጨረሻ ውል ሊፈረም ተቃርቧል።
የእዳው ድምር...
ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ!
ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ!
ይህንን አይን ያወጣ ጥፋት ለማስቆም አለመቻል፤ የቁም ሞት ነው።

Read 1989 times