Saturday, 26 August 2017 11:41

በዘንድሮ ክረምት፣መብረቅ የ40 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በአደጋው 140 እንስሳት ሞተዋል፤በሰብልና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል
   በዘንድሮ ክረምት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመብረቃ አደጋ የ40 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን 149 እንስሳትም በዚሁ አደጋ መሞታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሰውና በእንስሳት ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ በሰብልና በመኖሪያ ቤቶች ላይም  ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል - የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ደምሴ፡፡
አደጋዎቹ የደረሱት በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች መሆኑ ታውቋል፡፡
በክረምቱ መጀመሪያ ሰኔ ወር ላይ፣ በሃዲያ ማሻ በመብረቅ፣ 1 ሰው ህይወቱ ሲያልፍ፤ በምዕራብ ሸዋ፣ በሚዳገንና በአሶሳ በድምሩ 44 ከብቶች ሞተዋል። በሐምሌ ወር ደግሞ በአማራ ክልል ስማዳ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ዋግ፣ ዳህኑ፣ ወልዲያ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል፡- ዶዶላና  ሄሪ እንዲሁም በትግራይና አፋር ክልሎች በተከሰተው የመብረቅ አደጋ፣ በጠቅላላው የ13 ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ፣ 25 ከብቶችንም መግደሉ  ታውቋል፡፡
ከነሐሴ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ደግሞ በሃረር፣ ወለጋ፣ መንዝ፣ ዋግህምራ፣ ወረባቡ፣ አልቡኮ፣ ጎንደር፣ አድዋ፣ አሶሳ፣ በከማሼና በአፋር በደረሰ የመብረቅ አደጋ 18 ሰዎች ሲሞቱ፣ 80 ከብቶችም እንደተገደሉ፣ ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን  ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ባለፈው ረቡዕ በሰሜን ሸዋ የደረሰ የመብረቅ አደጋ፣ በአረም የግብርና ስራ ላይ የነበሩ የ9 ዓመት ህፃንን ጨምሮ የ8 ሰዎች ህይወትን እንደቀጠፈም ታውቋል፡፡ በእንስሳትና በሰው ላይ ከደረሰው አደጋ በተጨማሪ በሃረር - ጃርሶ፣ አልቡኮ ወረዳዎች በድምሩ 12 ቤቶች ሲፈርሱ፣ 79ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልም ጉዳት እንደደረሰበት ወ/ሮ አልማዝ አስታውቀዋል፡፡ የመብረቅ አደጋ ሊከሰት የሚችለው በዝናብ ወቅት ትላልቅ ዛፎች ስር በመጠለል መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ አልማዝ፤ ክረምቱ ቀጣይነት ያለው እንደመሆኑ፣ ሰዎች ዛፍ ስር መጠለል እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡    

Read 2717 times