Saturday, 26 August 2017 12:02

ቻይና የዓለማችንን ፈጣን ባቡር ዳግም ልታስወነጭፍ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     “ጥይቱ ባቡር” በሰዓት 350 ኪ.ሜ ይበርራል

      ፉዢንግ የሚል ስያሜ ያለውና በፍጥነቱ በአለማችን አቻ የማይገኝለት ቻይና ሰራሽ ባቡር፣ ከስድስት አመታት በፊት በደረሰበት አሰቃቂ አደጋ፣ 40 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት፣ 191 ያህሉን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ መዳረጉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ባቡሩ ቢበዛ በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር ብቻ እንዲፈጥን ማዕቀብ ጥሎበት ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን፣ ይሄው እንደ ጥይት የሚወነጨፍ ባቡር ዳግም በሙሉ አቅሙ ሊከንፍ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ፉዢንግ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ በሰዓት 350 ኪሎ ሜትር ፍጥነት፣ ከመዲናዋ ቤጂንግ ወደ ሻንጋይ ሊወነጨፍ ሞተሩን እያሞቀ ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ፤ 1ሺህ 250 ኪሎ ሜትር የሚደርሰውን ይሄን ርቀት በ4 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ያጠናቅቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ቻይና በርካታ ፉዢንግ ባቡሮች ቢኖሯትም፣ በፍጥነታቸው ሳቢያ አደጋ እንዳያስከትሉ በመስጋት እስከ መጪው መስከረም ወር አጋማሽ ድረስ ሰባቱን ብቻ በከፍተኛው የፍጥነት አቅማቸው እንዲበርሩ ልትፈቅድላቸው አቅዳለች፡፡
ቻይና የባቡሮቹን የፍጥነት አቅም የበለጠ በማሳደግ ባለፈው ሰኔ ወር በሰዓት 400 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ባቡር መስራቷን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአገሪቱ በድምሩ 19 ሺህ 960 ኪሎ ሜትር እርዝመት ያላቸው የፈጣን ባቡር ሃዲድ መስመሮች እንደተገነቡና እስከ 2020 ድረስም ተጨማሪ 10 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ለመዘርጋት መታቀዱን አመልክቷል፡፡
አገሪቱ በአለማችን እጅግ ትልቁ የሆነውን የፈጣን ባቡር ሃዲድ መስመሮች ኔትወርክ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት 360 ቢሊዮን  ዶላር  ወጪ እንዳደረገችም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1525 times