Sunday, 27 August 2017 00:00

የላምቦርጊኒ የቅንጦት ሞባይል 2,500 ዶላር ተተምኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የቅንጦት መኪኖችን በማምረት የሚታወቀው ላምቦርጊኒ፤ አሁን ደግሞ አልፋ ዋን የተባለና 2ሺህ 450 ዶላር የሚሸጥ በአይነቱ የተለየ የቅንጦት ሞባይል አምርቶ በገበያ ላይ ማዋሉ ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በይፋ የተመረቀውና 4 ጊጋ ባይት ራም እና 64 ጊጋ ባይት ስቶሬጅ ያለው አልፋ ዋን ስማርት ፎን፣ ተጨማሪ 128 ጊጋ ባይት ሚሞሪ እንደሚቀበል የዘገበው ሜይል ኦንላይን፤ ባለ 20 ሜጋ ፒክስልና ባለ 8 ሜጋ ፒክስል ካሜራዎች እንደተገጠሙለትም አመልክቷል፡፡
ሁለት ሲም ካርድ የሚወስደውና በውድ የጣሊያን ቆዳ የተለበጠው አልፋ ዋን፤ በመጀመሪያው የሽያጭ ምዕራፍ ለእንግሊዝና ለተባበሩት የአረብ ኢሜሬትስ ገበያ እንደቀረበ ቢነገርም፣ የመሸጫ ዋጋው እጅግ ከመጋነኑ የተነሳ በብዛት የመሸጥ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
የአልፋ ዋን የመሸጫ ዋጋ በዚህ አመት ለገበያ ከቀረቡት ሌሎች ታዋቂ ዘመናዊ ስማርት ፎኖች በ300 እጥፍ ያህል እንደሚበልጥ የጠቆመው ዘገባው፤ ይዞታው ከሌሎች ስማርት ፎኖች ጋር ተመሳሳይ እንደመሆኑ የመሸጫ ዋጋው ይሄን ያህል መጋነን አልነበረበትም የሚል ትችት እየተሰነዘረበት እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡
ሰሞኑን ለገበያ የቀረበው አዲሱ ጋላክሲ ኤስ 8 ስማርት ፎን፣ በ900 ዶላር እየተሸጠ እንደሚገኝና አዲሱ የአፕል ምርት አይፎን 8 ደግሞ ቢበዛ 1 ሺህ ዶላር የመሸጫ ዋጋ ሊተመንለት እንደሚችል እየተነገረ መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፤ አልፋ ዋን 2 ሺህ 500 ዶላር መሸጡ አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩ መብዛታቸውን ገልጧል፡፡

Read 1758 times