Saturday, 26 August 2017 12:05

ግብጽ በአሜሪካ የእርዳታ ቅነሳና እገዳ ክፉኛ ተበሳጭታለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   - አገሪቱ የ300 ሚ. ዶላር ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ አጥታለች
                     - የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን እስክታሻሽል ድረስ የ195 ሚ.ዶላር ድጋፍ ታግዷል

      የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ አሜሪካ ለግብጽ ከምትሰጠው አመታዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የገንዘብ እርዳታ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ያህል ቅናሽ ማድረጉንና ተጨማሪ የ195 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ማገዱን ባለፈው ማክሰኞ ያስታወቀ ሲሆን የግብጽ መንግስት በውሳኔው ክፉኛ መበሳጨቱ ተዘግቧል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ የትራምፕ አስተዳደር የወሰደውን የእርዳታ ቅናሽና እገዳ እርምጃ ክፉኛ የተቸ ሲሆን እርምጃው በሁለቱ አገራት መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነትና ግብጽን መርዳት ያለውን ጠቀሜታ በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብሎታል፡፡
አሜሪካ ለግብጽ የምትሰጠውን እርዳታ መቀነሷ፣ የሁለቱን አገራት የጋራ ጥቅሞች እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ሲልም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር፣ በግብጽ የሚታየው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱና የሲቪክስና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ የሚደረጉ እገዳዎችና የመብት ጥሰቶች ባለመሻሻላቸው፣ ለግብጽ ሲሰጥ የቆየውን የ65.7 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍና የ30 ሚሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ እርዳታ ገንዘብ፣ ለሌሎች አገራት ለመስጠት መወሰኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከዚህ በተጨማሪም ለግብጽ ልትሰጥ ያቀደቺውን የ195 ሚሊዮን ዶላር የወታደራዊ እርዳታ ማገዷን የዘገበው ቢቢሲ፤ ግብጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትንና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የጣለቺውን አፋኝ ህግ እስክታሻሽል ድረስ ገንዘቡ በባንክ እንደሚቆይ መነገሩን አመልክቷል፡፡
ግብጽ ከአሜሪካ ከፍተኛውን አመታዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ከሚያገኙ ቀዳሚዎቹ አገራት አንዷ እንደሆነች የጠቆመው ዘገባው፤ በየአመቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ስታገኝ እንደነበርም አስታውሷል፡፡

Read 2043 times