Sunday, 27 August 2017 00:00

ፎርብስ፤ የአመቱ የአለማችን 100 የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮችን ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  አጠቃላይ ሃብታቸው 1.08 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል

       ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2017 የፈረንጆች አመት፣የአለማችን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ቀዳሚ 100 ቢሊየነሮችን ዝርዝር ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገ ሲሆን በአመቱ የ6.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የተጣራ ሃብታቸውን 84.5 ቢሊዮን ዶላር ያደረሱት  የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል፡፡
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ በ81.7 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛነትን ደረጃ ሲይዙ፣ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ በ69.6 ቢሊዮን ዶላር የአመቱ የአለማችን ሶስተኛው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለጸጋ መሆኑን ፎርብስ ለሶስተኛ ጊዜ ባወጣው አመታዊ ዝርዝሩ አመልክቷል፡፡
በአመቱ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘውም ማርክ ዙክበርግ ሲሆን የዙክበርግ የሃብት መጠን አምና ከነበረው በ15.6 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ ዙክበርግ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱትና ዕድሜያቸው ከ40 አመት በታች ከሆነ 16 ባለጸጎች አንዱ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ከዙክበርግ በመቀጠል በአመቱ ከፍተኛውን ሃብት ያፈሩት የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ ናቸው ያለው ፎርብስ፤ ሰውዬው ባለፉት 12 ወራት የሃብት መጠናቸውን በ15.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማድረግ መቻላቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ከአመቱ 100 የአለማችን የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ግማሹ አሜሪካውያን ሲሆኑ ስምንቱ ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ 33 ያህሉ እስያውያን ባለጸጎች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቻይና እና የሆንግ ኮንግ ቢሊየነሮች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ከ100 የዘርፉ ባለሃብቶች መካከል 11 የሚሆኑት የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረበት ቀንሷል ያለው ፎርብስ፤ ከፍተኛውን ኪሳራ ያስተናገደው ዢያኦሚ የተባለውን ስማርት ስልክ የሚያመርተው ኩባንያ መስራችና ባለቤት ሊ ጁን መሆኑንና፣ የሰውየው የሃብት መጠን በአመቱ በ2.9 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን አመልክቷል፡፡
የአለማችን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለሃብቶች አጠቃላይ ሃብት ድምር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ በማለፍ፣ 1.08 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንም ፎርብስ አስታውቋል።

Read 6058 times