Saturday, 26 August 2017 12:14

የቀድሞ/ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መፅሐፍ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

 ለሁሉም ዜጎች የሚዳረስበት መንገድ ይመቻቻል ተብሏል
     የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ፤ በህይወት እያሉ የፃፏቸው የፖሊሲ ትንታኔዎች የተሰባሰቡበት “የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ የልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ”የተሰኘ መፅሐፍ ሰሞኑን የተመረቀ ሲሆን መፅሃፉ ለሁሉም ዜጋ የሚዳረስበት መንገድ ይመቻቻል ተብሏል፡፡ መፅሐፉ በውጭ ፖሊሲ ጉዳይ፣ በሀገር ደህንነት፣በግብርና የገጠር ልማት፣ በማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ስትራቴጂ እንዲሁም በልማትና ዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ የአቶ መለስን አተያዮችና ትንታኔዎች ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ መፅሐፉ ባለፈው ረቡዕ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት በቤተ መንግስት የተመረቀ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ “መፅሐፉ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠል የብርሃን ችቦ ሆኖ ያገለግላል” ብለዋል፡፡ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በበኩላቸው፤ መፅሐፉ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ለማድረግ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ የገለፁ ሲሆን፤ መፅሃፉን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ለጥናትና ምርምር እንዲጠቀሙበት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

Read 3987 times