Sunday, 27 August 2017 00:00

“ኢትዮ ዞዲያክ” አዋርድ መስከረም 8 ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

የፊልምና ሙዚቃ ሥራዎች ተወዳድረው ይሸለማሉ

      “ኢትዮ ዞዲያክ” የተባለው የሽልማት ድርጅት፣ በዓመቱ ምርጥ የተባሉ የኪነ ጥበብ ውጤቶችንና ከያኒያንን አወዳድሮ፣ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ አሸናፊዎችን እንደሚሸልም አስታወቀ፡፡ የሽልማት ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት በሳፋየር አዲስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ሽልማቱ በተለያዩ የፊልምና የሙዚቃ ዘርፎች እንደሚሰጥ ጠቁሞ፣ ውድድሩም- የዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፣ ምርጥ ቪዲዮ ክሊፕ፣ ምርጥ አልበም፣ ምርጥ የሴት ተዋናይ፣ ምርጥ የወንድ ተዋናይ፣ ምርጥ አዲስ ዘፋኝ፣ ምርጥ ነጠላ ዜማና ሌሎችም ዘርፎንች እንደሚያካትት ገልጿል፡፡
አሸናፊዎች ወርቅ ቅብ ዋንጫ እንደሚሸለሙ እንዲሁም ለምርጥ አዲስ ድምፃዊና ለምርጥ ተስፋ የተጣለባቸው ተዋናዮች፤ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን የሽልማት ድርጅቱ ጠቁሟል። የዳኝነቱ ሂደት 50 በመቶ በተመልካች፣ 50 በመቶው በዳኞች የሚከናወን ሲሆን ለተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ግን 80 በመቶ በተመልካች እንደሚወሰንና፣ የዳኞቹ ሚና 20 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ተወዳዳሪዎች “ምርጥ 10” ውስጥ ከገቡ በኋላ በ8251 የሞባይል አጭር
መልዕክት፣ ተመልካች “ምርጦች” የሚላቸውን መደገፍ ወይም መምረጥ እንደሚችል ታውቋል፡፡

Read 2587 times