Sunday, 27 August 2017 00:00

ሴቶችና ወሲብ - በኢትዮጵያ የ17ኛው ክ/ዘ ሥነ ፅሁፍ ውስጥ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(15 votes)

  በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ፣ ለሴቶችና ለወሲብ የነበረውን አመለካከት በመተቸት፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የተፃፉ ሁለት የፍልስፍና ድርሳናትን እንዳስሳለን፡፡ ድርሳናቱን በድብቅ ያዘጋጁት ደግሞ “አራት አይናው” ዘርዓያዕቆብና የእሱ ተማሪ የነበረው ወልደ ህይወት ናቸው፡፡
መቼም ስለ ሴቶቻችን መብት፣ እኩልነትና ነፃነት በተመለከተ የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ህይወትን ያህል ሽንጡን ገትሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከራከረላቸው ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ይቅርና በዘመናዊ ትምህርት የተፈጠሩት የ20ኛው ክፍለ ዘመን  ምሁራኖቻችን እንኳ ስለ ሴቶች መብት የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ህይወትን ያህል አልተከራከሩም፡፡
ከዚህ ውስጥ ዘርዓያዕቆብ የሴቷ የትዳር ምርጫ እንዲከበርላት ከመሟገት ጀምሮ ስለ ሴቶች እኩልነት፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ንብረት የማፍራት መብትና በትዳር ውስጥ ከባሏ ጋር እኩል የመወሰን መብት እንዲኖራት የተሟገተ ሲሆን፤ ወልደ ህይወት ደግሞ ስለ ሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ተጨንቆ ያለ ዘመኑ ፅፏል፡፡
ሴቶችንና ወሲብን በተመለከተ የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ህይወትን ፍልስፍና አስገራሚ የሚያደርጉት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን  የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በጭራሽ ሊታሰቡ የማይችሉና ያለ ምንም ዓይነት ውጫዊ ግፊት (ይልቅስ በጥልቀት ከማሰብ ብቻ) የመጡ ሐሳቦች መሆናቸው ነው፡፡ አውሮፓውያኑ ስለ ሴቶች መብት መጠየቅ የጀመሩት 19ኛው ክ/ዘ ላይ ሲሆን፣ ጥያቄውም የመጣው በኢንዱስትሪው አብዮት ውጫዊ ግፊት የተነሳ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ግን እንደ ሴቶችና ወሲብ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሱት ምንም ዓይነት ውጫዊ (ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ) ግፊት ባልነበረበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ በተለይ ዘርዓያዕቆብ የሴቶችን ጥያቄ ከማህበራዊ ጥያቄነት አሳልፎ ወደ ሥነ ኑባሪያዊ ጥያቄነት (Ontological Question) ከፍ ማድረጉ ነው፡፡ እስኪ ከዘርዓያዕቆብ እንጀምር፡፡
በዘርዓያዕቆብ አመለካከት፤ በማህበረሰባችን ውስጥ ለሴቶች ዝቅተኛ ቦታ እንድንሰጥ ያደረገን፣ ለሴቶች ተፈጥሮ ያለን የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ነው። ይሄም ሸውራራ አመለካከት፣ በኦሪቱ ህግ ላይ ሳይቀር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ “በፈጣሪ ጥበብ…” ይላል ዘርዓያዕቆብ፣
በፈጣሪ ጥበብ ከሴት ማህፀን በየወሩ ደም እንዲፈስ ስርዓት አቁሟል፡፡ ይህ የደም መውረድ ለሴት ህይወትና ልጆች ለመውለድ ያስፈልጋል። ይህ የማይወርዳት ሴት መካን ነች፤ መውለድ አትችልምና፡፡ የኦሪቱ ህግ ግን ይሄንን የፈጣሪ ጥበብ እርኩሰት አደረገው፡፡
ከንግስተ ሳባ ዘመን ጀምሮ በኦሪቱ ህግ ስትተዳደር ለነበረችው ኢትዮጵያ፣ ይህ የኦሪቱ ትምህርት በማህበረሰባችን ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፤ ለዘመናትም እንደ ባህል ተቀብለነው ኖረናል። በዚህ የኦሪቱህግ የተነሳም በወሊድ አሊያም በወር አበባ ምክንያት ፈሳሽ ያለባቸው ሴቶች፣ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ መገለልና የስነ ልቦና ጥቃት ሰለባ ሆነው ኖረዋል፡፡ ለሀገራችን ሴቶች ትልቅ ሸክም የሆነባቸው የኦሪቱባህል መሆኑን ዘርዓያዕቆብ ደርሶበታል፡፡ በመሆኑም ይሄንን ሸክም ማንሳት ማለት ለሴቶች ትልቅ እፎይታ ነው፡፡
በዘርዓያዕቆብ አመለካከት፣ የአንድ ማህበረሰብ ባህል በዋነኛነት የሚመነጨው ተፈጥሯዊ ከሆነው ግዴታ ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጥሮ ለሰው ልጅ የኢኮኖሚያዊ ህልውናው ምንጭ ብቻ ሳትሆን የባህሉም፣ የእውነትም ምንጭ ናት፡፡ ዘርዓያዕቆብ በሐተታው ውስጥ “እውነት ግን አንድ ናት” የሚለውም ይሄንን የተፈጥሮ ህግና ሥርዓት ነው፡፡
ዘርዓያዕቆብ፤ የሴቶችን አጠቃላይ ሥነ ህይወት የሚመለከተው የተፈጥሮ ህግና ስርዓት አካል አድርጎ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ለተፈጥሯዊ ክስተቶች ያለን ግንዛቤ፣ እንዲሁም ለተፈጥሮ ህግና ስርዓት የምንሰጠው “ትርጉም” በቀጥታ በማህበራዊ አደረጃጀታችንና ባህላችን ውስጥ ይንፀባረቃል። ዘርዓያዕቆብ የሴቶችን ሥነ ህይወትና የወር አበባ የሚመለከተው ከዚህ አስተሳሰብ አንፃር ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ የተፈጥሮ ህግና ስርዓት በምንሰጠው “ማህበራዊ ትርጉም” ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ተፈጥሮን ስናስነውር፣ ለተፈጥሮ ህግና ስርዓት የምንሰጠውን “ማህበራዊ ትርጉምም” እናበላሸዋለን፡፡ የኦሪቱ ችግር ይሄ ነው፡፡ ሴቷ የኦሪቱ ህግ ላይ የገጠማት ችግር ይሄው ነው፡፡
የሴቶች የወር አበባ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ለዚህ ተፈጥሯዊ ክስተት ግን የሰጠነው “ማህበራዊ ትርጉም” የተንሸዋረረ ነው፡፡ ተፈጥሮን ልንጋፋው አንችልም፤ ልናሻሽለው አሊያም ልንቀይረውም አንችልም፤ እንዳለ ከመቀበል ውጭ፡፡ ተፈጥሮ የተፈጠረው እንደወረደ ልንቀበለው እንጂ አቃቂር ልናወጣለት አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ ተፈጥሮን በፀጋ ከመቀበል ውጭ ልናስነውረው አይገባንም፡፡
እኛ ግን ተፈጥሮን እርኩሰት አደረግነው፤ ዘርዓያዕቆብንም ይበልጥ የሚያናድደው ነገር ይሄ ነው — እግዚአብሔር መልካም ነው ብሎ የሚያስብ ማህበረሰብ፣ እንዴት እግዚአብሔር የፈጠረውን ተፈጥሮ እርኩሰት ያደርጋል!!?
የሴቷ አጠቃላይ ህይወት (ውበቷ፣ ትዳሯ፣ መውለዷ፣ ልጆቿን ተንከባክባ ማሳደጓ… ሁሉ) ከሥነ ህይወቷ/ከሥነ ተፈጥሮዋ ጋር የተቆራኘ ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰጣት ደረጃም እንዲሁ ከሥነ ህይወቷ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እናም ይሄንን ሥነ ህይወቷን ገና ከመነሻው ማስነወር፣ አጠቃላይ ህይወቷን ያስተጓጉልባታል፡፡ ለዚህም ነው ዘርዓያዕቆብ “የኦሪቱ ህግ የወር አበባን እርኩሰት ማድረጉ አጠቃላይ የሴትን ልጅ ህይወት ከባድ አድርጎባታል፤” የሚለው፡፡ ዘርዓያዕቆብ እንዲህ ይላል፡-
ይህ የኦሪቱ ህግ፣ ጋብቻንና የሴትን ህይወት ከባድ አድርጎታል፤ የመረዳዳት ህግንም ይሽራል፤ ልጆች ማሳደግን ይነሳል፤ ፍቅርንም ያስቀራል። ስለዚህ፣ ይህ የኦሪቱ ህግ ሴትን ከፈጠረ አምላክ የመጣ ሊሆን አይችልም፡፡
ስህተቱ የመጣው ተፈጥሮ ላይ ሳይሆን ማህበረሰቡ ለተፈጥሮ የሰጠው ማህበራዊ ትርጉም ላይ ነው፡፡ የትርጉም ስህተት የመጣው ደግሞ የሴትን ተፈጥሮ፣ በወንድ አእምሮ በመተርጎሙ ነው። ሴትን በወንድ አእምሮ ለመረዳት መሞከር ከባድ ብቻ ሳይሆን ስህተትም ላይ ይጥላል፡፡ ለዚህም ነው ወንዶች ህግ አውጭ፣ ወንዶች የማህበረሰቡ መሪ፣ ወንዶች የሃይማኖት መሪ፣ ወንዶች የቤተሰብ መሪ በሆኑበት ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉ ሴቷ ከወንዱ በኋላ የምትመጣው፡፡
ዘርዓያዕቆብ በጣም ብዙ ቦታ ላይ ከተፈጥሮ ህግ ጋር የተስማማና የበለፀገ ባህል ለመፍጠር፣ እሱ የነበረበትን ባህል ሲተች ይታያል፡፡ በዘርዓያዕቆብ አመለካከት፤ አንድ ማህበረሰብ የበለፀገ ባህል እንዲኖረውና ወደ ፊትም እያደገ ለመሄድ፣ ከተፈጥሮ ህግና ስርዓት ጋር መስማማት አለበት፡፡ የሰው ልጅ ባህልና ሥልጣኔ ለተፈጥሮ ህግና ስርዓት አወንታዊ ትርጉም በመስጠት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። የኦሪቱ ህግና ባህል ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ በጣም የወረደው ለዚህ መርህ ስለማይገዛ ነው፡፡
ዘርዓያዕቆብ ለዚህ ችግር እንደ መፍትሄ የሚያቀርበው ደግሞ የችግሩ መሰረት ላይ እንድናተኩር ነው፡፡ ይሄውም የማህበረሰቡ ባህልና ልማድ ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን የችግሩ ምንጭ ለተፈጥሮ ያለን ግንዛቤ ነው፡፡ በመሆኑም፣ መሰረታዊው ችግር የስነ ኑባሬ (Ontological) ነው — የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት ነው ችግሩ፤ ማህበረሰባችን ተፈጥሮን የሚያይበት መንገድ ነው ችግሩ፡፡ በዘርዓያዕቆብ አመለካከት፣ ባህላችን ሴቶቻችንን ያሳነሰውና ያዋረደው፣ የሴቶችን ተፈጥሮ የርኩሰት፣ የደካማነትና የመረገም ምልክት አድርጎ ስለወሰደው ነው፡፡
ተፈጥሮን በተፈጥሮነቱ መረዳት ሲያቅተን፣ ለተፈጥሯዊ ክስተቶች የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትርጉም እንሰጣለን፤ የወር አበባን እርግማን ነው እንላለን፤ ለምፅን መቅሰፍት ነው እንላለን፤ የፀሐይ ግርዶሹን የእግዚአብሔር ቁጣ ነው እንላለን፡፡ ተፈጥሮን ስናሳስት፣ ሴቷንም እናሳስታለን፤ ተፈጥሮን መረዳት ሲያቅተን፣ የሴቷም ነገር እንቆቅልሽ ይሆንብናል፤ ተፈጥሮን ስናስነውር ሴቷንም እናስነውራታለን፡፡
በመሆኑም ለሴቶች ያለን አመለካከት፣ ለተፈጥሮ ካለን አመለካከት የሚቀዳ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተፈጥሮ ጭቆና፣ ከሴቶች ጭቆና ጋር የግድ የሚዛመደው፡፡ የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና አስገራሚ የሚያደርገው ነገር ይሄ ነው፡፡ ተፈጥሮን የሚጨቁን ሰው፣ ተፈጥሮን የሚያንጓጥጥ ማህበረሰብ የግድ ወደ ሴቶች ጭቆና ማምራቱ እንደማይቀር ዘርዓያዕቆብ ደርሶበታል፡፡ እንዴት? ተፈጥሮና ሴት ምን አገናኛቸው?
ተፈጥሮ ሁለት ዓይነት መገለጫዎች አሉት — ግዑዛዊና ስጋዊ/ስሜታዊ፡፡ ግዑዛዊ የምንለው የእኛን ህልውና ከቦ የሚገኘውን ተፈጥሮ ነው። የለበስነው ሥጋና ስሜቶቹም እንዲሁ ተፈጥሯዊ ናቸው፡፡ የችግሩም ምንጭ፤ “ስሜታዊ ተፈጥሯችን መጨቆን አለበት” የሚል ማህበረሰብ፣ ባህልና ሃይማኖት መምጣቱ ነው፡፡ ይሄ ነው የዘርዓያዕቆብም ተቃውሞ፡፡ “መልካም ስነ ምግባርም ሆነ መንፈሳዊ ከፍታ የሚገኘው በስሜት ጭቆና ነው” ብሎ የሚያስብ ማህበረሰብ፣ የግድ ወደ ሴቶች ጭቆና ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሴቶች የስሜት ምንጭ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። እናም ወንዱ ስሜቱ እየገነፈለ እንዳያስቸግረው፣ “የስሜት ቋት” የሚላትን ሴቷን በህግ፣ በባህልና በሃይማኖት ያስራታል፡፡
ሌላው ስለ ሴቶች መብት ከተፃፉ የሀገራችን የ17ኛው ክፍለ ዘመን ሥነ ፅሁፎች ውስጥ እጅግ አስገራሚ የሚያደርገው የዘርዓያዕቆብ ተማሪ የነበረው ወልደ ህይወት፣ በሐተታው ምዕራፍ 24 ላይ የፃፈው ነገር ነው፡፡
ዘርዓያዕቆብ ስለ ሴቶች መብትና ሰብዓዊ ክብር ሲሟገት፣ አንድ መሰረታዊ ነገር ረስቶ ነበር። ይሄውም የሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ነው። ይሄንን ክፍተት ምልዑ የሚያደርገው ወልደ ህይወት ነው፡፡ በመሆኑም፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ውስጥ የተነሳው የሴቶች መብት ጥያቄ፣ ሁሉን አቀፍ ነበር ማለት እንችላለን፡፡
የወሲብ ጉዳይ የእያንዳንዳችን የጓዳ ውስጥ ገመና ቢሆንም ወልደ ህይወት ግን ያለ ጊዜው የመወያያ አጀንዳ እንዲሆን ወደ አደባባይ አውጥቶታል፡፡ ምዕራባውያን በሴቶች የመብት ንቅናቄ ውስጥ የሴቷን የወሲብ ህይወት ዋነኛ የትግላቸው አጀንዳ አድርገው ማቅረብ የጀመሩት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው፡፡ ወልደ ህይወት ግን ከምዕራባውያኑ 300 ዓመት ቀድሞ ጉዳዩን ወደ አደባባይ አውጥቶታል፡፡
ወልደ ህይወት፤ ፍልስፍናው ውስጥ የሴቷን የወሲብ ህይወት እንዲያነሳ ያደረገው፣ “በፍቅር ውስጥ አንዳቸው ሌላቸውን ደስ ያሰኙ ዘንድ ይገባቸዋል” የሚለው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ወሲባዊ እርካታ ነው ብሎ በማሰቡ ነው፡፡ በዚህ የወልደ ህይወት እሳቤ መሰረት፣ “የአወስቦ ሥርዓት” እግዚአብሔር ከፈጠረው ጥበብ ሁሉ የሚልቅ፣ ከጣዕምም ሁሉ የበለጠ ጣዕም ያለው ሲሆን፤ ወሲብ ልጅን መፍጠሪያና ትውልድንም መቀጠያ መሆኑ ደግሞ ሰው ከእግዚአብሔር የመፍጠር ባህሪ ጋር እንዲመሳሰል አድርጎታል፡፡ “በመሆኑም በትዳር ውስጥ ወሲብን እጅግ ልንደሰትበትና ልንሰለጥንበት ይገባናል” ይላል፤ ወልደ ህይወት፡፡
ይህ የወሲብ እርካታ ግን የወንዱ ብቻ ሆኖ፣ ሴቷ እንዳትረሳ ወልደ ህይወት ያስጠነቅቃል፤ እንዲህ በማለት፡-
የሩካቤን ጣዕም ከሚስትህ ጋር ተካፈለው እንጂ ለብቻህ አትሻው፡፡ ከአንተ እርካታ ኋላ ቀርታ ጣዕሙ እንደይጎድልባት፣ እርሷም በአንተ እስክትደሰት ጠብቃት እንጂ እግዚአብሔር የሰጣትን ፈንታዋን ከልክለህ በችኮላ አታድርገው፡፡ ይህንንም ፍቅር ካላደረክላት ታዝንብሃለች፣ ትንቅሃለች፡፡ ጋብቻህም ለእግዚአብሔር በረከት የተዘጋጀ አይሆንም፡፡
በትዳር ውስጥ ሳይቀር ስለ ወሲብ ማውራት ነውር በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ጭራሽ ስለ ሴቷ የወሲብ ስሜት እርካታ ተጨንቆ መፃፍ እጅግ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን እንኳ፣ ወንዱ የራሱን ወሲባዊ እርካታ እንጂ ስለ ሴቷ ስሜት ብዙም አይጨነቅም፡፡
ይሄም ነገር በተለይ በትዳር ውስጥ ቤተሰብ እስከመበተን የሚያደርስ አደጋ ቢኖረውም በህብረተሰቡ ውስጥ ግን በግልፅ አይወራም፡፡ “ይሄንን ያህል ቤተሰብን የመበተን ኃይል ያለውን ጉዳይ፣ የጓዳችን ገበና ብቻ አድርገን ማስቀመጥ የለብንም” የሚል ነው የወልደ ህይወት ሐሳብ፡፡ በመሆኑም ባለትዳሮችም ሆኑ ማህበረሰቡ፣ በሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ላይ በግልፅ መነጋገር አለባቸው፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ የወንዱን የወሲብ ስሜት ብቻ ተከትሎ የተፈጠረ አንድ ባህል አለ - “የጭን ገረድ” የሚባል፡፡ ይህ ባህል ህብረተሰባችን ስለ ወንዱ ስሜት እንጂ ስለ ሴቷ የወሲብ ህይወት ግድ እንደሌለው በግልፅ ያሳየበት ነው፡፡ እናም በዚህ ባህል ውስጥ የሴቷ ሚና፣ ወንዱን በወሲብ ማርካት ብቻ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ይሄንን “የጭን ገረድ” የሚባል ልማድ እንዲቀር በማስነገር፣ ሴትን እንደ “ወሲብ ዕቃ” የመመልከቱን ባህል ለመለወጥ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ወልደ ህይወት ግን ከአፄ ቴዎድሮስ 200 ዓመት በፊት ነበር፣ ስለ ሴቶች የወሲብ ስሜት እርካታ ግዴለሽ የሆነውን ባህል በመተቸት፣ ስለ ሴቷ የወሲብ ስሜት እርካታ ተጨንቆ የፃፈው፡፡
(ከአዘጋጁ፡- ፀሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እንዲሁም “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”፣ “ፍልስፍና ፩ እና ፪” መፅሐፍት ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው)
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 7444 times