Sunday, 27 August 2017 00:00

የተጀመሩ የእርቅና ሽምግልና ሂደቶች የት ደረሱ?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በ2008 ዓ.ም በሀገሪቱ ተፈጥሮ ለነበረው ተቃውሞና ግጭት መፍትሄ ለመሻት ከተንቀሳቀሱ አካላት አንዱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሲሆን ሌላኛው 120 የተለያዩ አባላት ያሉት “የሽማግሌዎች ቡድን” ነበር፡፡ እነዚህ አካላት የሀገሪቱ ችግሮች በሽምግልና እና በእርቅ ነው ሊፈቱ የሚገባው የሚል አላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ አሁን የት ነው ያሉት? ዓላማቸውስ ከምን ደረሰ? የሁለቱንም ተወካዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፤ ተቋማቸው የእርቅ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሲገልፁ፤ ሌላው የሽምግልና ቡድን አባልና ፀሐፊ የሆኑት ፓስተር ዶክተር ዘካሪስ አ/ብርሃን በበኩላቸው፤የሽምግልና ቡድኑ አላማ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ መፍትሄ እንዲሰጥ ማሳሰብ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ይሆን? አሁን ስላገረሸው ውጥረት ምን ይላሉ? ቀጣይ ዕቅዳቸውስ ምንድን ነው? ተወካዮቹ ያብራራሉ፡-   

                           “የሚበጀውን ለማድረግ ማሸነፍም መሸነፍም እንዳለ መቀበል ይኖርብናል”
                                 ፓስተር ዶ/ር ዘካሪያስ አ/ብርሃን (“የሽማግሌዎች ቡድን” ፀሃፊ)

      ጀምራችሁት የነበረው አገራዊ ሽምግልና ምን ላይ ደረሰ?
ባለፈው ዓመት፣ መስከረም 17 ቀን 2009 ዓ.ም የተሰበሰብነው፣ ገለልተኛ የምንባል የዜጎች ስብስብ አካላት ነበርን፡፡ በቀላል አገላለፅ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምንል ወገኖች፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተውጣጥተን፣ መፍትሄ ለማፈላለግ የተሰበሰብን አድሆክ (Adhoc) ኮሚቴ ብለህ ልትጠራን ትችላለህ፡፡ መነሣሣቱን ወስዶ ያሰባሰበን፣ የኢትዮጵያ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ነበር፡፡
መድረኩ በመጀመሪያው ቀን ያሰባስበን እንጂ፣ ይህን ጊዜያዊ የሽምግልና ሚና መጫወት የጀመርነው፣ ወደ 120 አካባቢ የምንሆን ሰዎች ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ከ120 ሰዎች መካከል የተወሰንነው፣ ንዑስ ኮሚቴ አዋቅረን፣ የ120 ሰዎችን ጥያቄዎች በስፋትና ጥልቀት ባለው ውይይትና ክርክር ጨምቀን፣ 16 ነጥቦች በሚሆኑ ጥያቄዎች ይዘን፣ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር በተወካዮቻችን አማካኝነት አቅርበናል፡፡ ይህ እንግዲህ የሆነው የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይታወጅ ሲሆን ከዚያም በኋላ ቢሆን ሀሳባችንን ለተለያዩ የመንግስት አካላት አቅርበናል፡፡
የሽምግልናው መማክርት ሥራውን በዚህ መልኩ በማጠናቀቁና አድሆክ ኮሚቴ ስለነበር በጊዜው ለተፈጠረው አለመግባባት የበኩላችንን የዜግነት ግዳጃችንን ለመወጣት ሞክረናል፡፡ ያቀረብነው የህዝቡ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ቢመለስም ባይመለስም፣ ከስብስባችን ግብ አንፃር ውጤማ ነበርን፡፡ ተልኳችን ህዝቡ እየጠየቀ የነበረውን ጥያቄ ማቅረብ እንዲሁም ሽምግልናን ያማከለ ውይይት በመፍጠር፣ ለዜጎች የሚበጀው ነገር ይመጣ ዘንድ ማሳሰብ ነበር፡፡ ያንንም አድርገናል፡፡
ቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው? ሽምግልናውስ ቀጣይነቱ ምን ያህል ነው?
ይህ የሽምግልና አካል ከላይ እንደተገለፀው፣ አድሆክ ኮሚቴ በመሆኑ፣ ብዙዎቻችን ከዚያ በኋላ ሥራችንን አቁመናል፡፡ ምክንያቱም ግባችን ጥያቄዎችን  ለውይይት ማቅረብ ነበርና ነው፡፡ አሁን እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት፣ የተሰበሰብንበትም የምንሰባሰብበትም ምክንያት ያለን አይመስለኝም፡፡ በግል የምንገናኝ ሰዎች፣ የዚህ አድሆክ ኮሚቴ ሚና ማብቃቱን አውርተንበት የምናውቅ ይመስለኛል። በርግጥ ከመንግሥት አካላት በኩል ለውይይት ቀጠሮ እንደሚሰጠንና ውይይት እንደምናደርግ በተወካዮቻችን በኩል መልዕክት ደርሶናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለቀጣይ ውይይት ፈቃደኛነታቸውን እንዳሳዩ ተወካዮቻችን ገልፀዋል፡፡
አሁን በሀገሪቱ ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮችና ውጥረቶች መፍትሄው ምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት አሊያም በሚመጣው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በሰከነ መንፈስ በመወያየት፣ የፖለቲካ ትኩሳቱን አርግቦ፣ ለአገሪቱ የሚበጀውን መንገድ መርጦ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ውይይት ዋናው የዲሞክራሲ መንገድ፣ የመግቢያው በር ነው፡፡ ከውይይት የሚጠቅመውን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሀሁን መጀመር ነው፡፡ ጉንጭ አልፋ ክርክር ተግባር ሲያጅበው ነው ትክክል የሚሆነው። አሁንም ፍሬ ያለው ውይይት ያስፈልጋል፡፡ በውይይት ማሸነፍም መሸነፍም ሁልጊዜ የለም፡፡ አውራነት ሁልጊዜ የለም፡፡ የሚበጀውን ለማድረግ ማሸነፍም መሸነፍም እንዳለ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ አሁን አንተ ላነሳኸው ሀሳብ፣ ችግር ይኑርም አይኑርም፣ በውይይት መፍትሄ መፈለጉ ይሻላል። የፖለቲካ ሥርዓት፣ የእምነት አቋም መግለጫ ወይም አላማ አይደለም፡፡ መቀየር መለወጥና ለአገሪቱ የሚበጀውን መንገድ መያዝ ይገባል፡፡ እሱን ለማድረግ የመንፈስ ልዕልና እና ቁርጠኝነት ወዳለበት ከፍታ መሸጋገር ይገባናል፡፡

------------------


                                “አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል”
                                 መጋቢ ዘሪሁን ደጉ (የኢ/ሃ/ተ/ጉ ዋና ፀሐፊ)


         የሽምግልና እና የእርቅ ሂደቱን ምን ላይ አደረሳችሁት?
በአሁኑ ወቅት የዚሁ የእርቅ አካል የሆኑ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ጉዳዩ ጠዋት ተጀምሮ ማታ የሚያልቅ ነገር አይደለም፡፡ ውስብስብ ነው፡፡ በህዝቦች መካከልና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚሰራ ስራ እንደመሆኑ፣ በቂ ጊዜና በጀት እንዲሁም ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ነገሮችን ተራ በተራ እያስኬድን ነው፡፡ አሁን ዲላ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር የመፍታቱን ስራ እያገባደድን ነው፡፡
በዲላ እየሰራችሁት ያለው ሥራ  ምንድን ነው?
በወረዳ ደረጃ ባሉ መዋቅሮቻችንና በክልሉ መንግስት ድጋፍ፣ በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎችን እንዲፈቱ እያደረግን ነው፡፡ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ነው ይሄን እየሰራን ያለነው፡፡ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከወረዳ ከፍ ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ያሉ ችግሮች ላይ ጠንካራ ስራ ሰርተን እናጠናቅቃለን። ውይይት እያደረግን መጨረሻ ላይ ባህላዊውን እርቅ እያደረግን ነው የምንቋጨው፡፡ ቀጣይነት ያለው ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውን እየተመካከርን እየሰራን ነው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም አካባቢዎች፣ የእርቅ ውይይትና ምክክሮችን አድርገናል፡፡ እንግዲህ ተራ በተራ ነው እየሰራን  ያለነው፡፡
እስቲ በምሳሌ ያስረዱን --- እርቁ የሚፈጠረው እንዴት ነው? ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው?
 ለምሳሌ ዲላ አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶች፣ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በነዋሪዎች መካከልም መቃቃር ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖችና ጉዳት አድርሰዋል ከሚባሉ ወገኖች ጋር ውይይት በማድረግና ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ነው፣ እርቅ የምንፈጥረው፡፡ እርግጥ እንደምናስበው ሂደቱ ቀላል አይደለም፤ ውስብስብ ነው፡፡ ንብረት የወደመበት ንብረቱ እንዲመለስ፣ ወንጀል የሰራ በህግ እንዲጠየቅ ይደረጋል፡፡ በህግ የተያዙ ጉዳዮችን ለፍትህ አካላት ትተን፣ ከህግ በመለስ ያሉ ስራዎችን ነው የምንሰራው፡፡ በዋናነት በህዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት መልሶ በመገንባቱ ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሃገር ሽማግሌዎችና የመንግስት አካላትም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
አሁንም በየአካባቢው ውጥረቶች እንዳሉ ይገለፃል፡፡ እነዚህን ውጥረቶች ለማርገብ የእናንተ ሚና ምንድን ነው ?
እኛ የምንከተለው ሁለት አቅጣጫዎችን ነው። አንደኛው አቅጣጫ፣ ከመንግስት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አሁንም ቀጥለዋል። በቅርቡም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ውይይት የምናደርግበት የምክክር መድረክ እናዘጋጃለን፡፡ እንዴት ተባብረን የሃገራችንን ሠላም እናረጋግጥ? በሚል ውይይት እናደርጋለን፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው፣ የህዝቡን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ሠላም እንዴት ማጠናከር ይቻላል? መንግስት ደግሞ ምን ይጠበቅበታል? የሚሉትን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ፣ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ከክልል መንግስታት ጋርም ተመሳሳይ ውይይት እናካሂዳለን፡፡  
ህዝቡ አካባቢም ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ማቅረብ፣ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንመካከራለን። ምንም በማያውቀው ሠላማዊ ዜጋ ላይ ወይም በሃገሪቱ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ፈፅሞ የማንቀበለው ነው። ውጤቱም ጥሩ አይደለም። ስለዚህ የተሻለውን መንገድ የማሳየት ስራ ይጠበቅብናል፤ እየሰራንም ነው፡፡ ሌላው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ነው፡፡ መንግስት በእርግጥ ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው፡፡ እኛም በሂደቱ በታዛቢነት አለን፡፡ እንደ አንድ ተቋም እንግዲህ የምንችለውን ጥረት ሁሉ እያደረግን ነው፡፡
ይሄን ስራ ስትሰሩ ምን ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?
ከመንግስት በኩል ጥሩ ትብብር ነው ያለው፤ ጥያቄዎች በአግባቡ ቶሎ ይመለሱልናል፡፡ በተለይ ዲላ ላይ የዞኑ መንግስት ለሰላም፣ ለእርቅ፣ ለህዝቦች አንድነት ከምንጠብቀው በላይ ከፍተኛ ድጋፍ ነው ያደረገልን፡፡  የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬም ያሳዩን ትብብርም የሚደነቅ ነው፡፡ እንደ ተግዳሮት የምናነሳው፣ ስራው ከፍተኛ  ፋይናንስ የሚጠይቅ ነው፡፡ ትልቁ ተግዳሮታችን የፋይናንስ አቅም ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌላው ጥሩ ነው ያለው፡፡  
አሁን  የሚታዩ ውጥረቶች ምን ያህል ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው?
እኔ ቁጭ ብሎ በመነጋገር አምናለሁ፡፡ ህዝባችን እርስ በእርሱ የሚዋደድ፣በጋራ የሃገሩን ሠላም ለማረጋገጥ፣ ሃገሩን ለማልማት የሚተጋ፣ ለዘመናት የቆየ የትስስሮች ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡ በቀላሉ አደጋ ውስጥ የሚወድቅና በቀላሉ ለሌላ ችግር የሚጋለጥ አይደለም፡፡
ችግሮች ቢኖሩም ህዝቡ በባህሉና በሃይማኖቱ ጠንካራ ስለሆነ፣ ይሄ እሴት እንዳይሸረሸር ከመንግስትም ከኛ የሃይማኖት ተቋማትም ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡ የህዝቡን አንድነት አጠናክሮ በመሄድ ረገድ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ አንድነቱ እንዳይነካ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የምንለው እጅግ ጠንካራው ማንነታችን ነው፡፡ መንግስትም ከህዝቡ የሚነሳለትን ጥያቄ እያደመጠና በጥልቀት እየፈተሸ የመመለስ ስራን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ይሄ ከተደረገ አስደንጋጭ ችግር ውስጥ እንገባለን የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ግን መንግስት፣ ብዙ የቤት ስራ ይጠብቀዋል፡፡ መንግስት፣ የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ እስከተጋ ድረስ አገራችን ብዙ  ችግር አይገጥማትም፡፡  

Read 3854 times