Sunday, 03 September 2017 00:00

መንግሥት የአገሪቱን የሚዲያ ምህዳር ሊያሻሽል አስቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

· ነፃ ያልወጣ ህዝብ ግንኙነት፣ መረጃ በነፃነት ሊሰጥ አይችልም -
የ“ሰንደቅ” አዘጋጅ
· መንግሥትን ሲያብጠለጥሉ ለሚውሉ ሚዲያዎች እንዴት
የዲሞክራሲ ፈንድ ይሰጣል? - የብሮድካስት ባለስልጣን ኃላፊ
· “የመንግሥት ኃላፊዎች ከግል ሚዲያዎች ይሸሻሉ” - ጥናት
· በግል ሚዲያ የውይይት መድረክ፣ “ቃና” እንዲታገድ ተጠየቀ
· መንግስት፤ ለማገድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ የለኝም አለ

ሰሞኑን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ባዘጋጀው የግል ሚዲያዎችን የተመለከተ የውይይት መድረክ ላይ በብሮድካስት ባለስልጣን የቀረበ ዳሰሳዊ ጥናት፤ የመንግስት ባለስልጣናት የግል ሚዲያዎችን በጥርጣሬ እንደሚያዩና ከሚያዘጋጇቸው የውይይትና የክርክር መድረኮች እንደሚሸሹ አመለከተ፡፡
በሀገሪቱ የሚሰራጩ ፕሬሶችን የመመዝገብ እንዲሁም የብሮድካስት ሚዲያዎችን የመቆጣጠር ስልጣን በህግ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የስራ ኃላፊ፣ በሚዲያዎች ላይ ባቀረቡት ጥናት፤ በመንግስት የህዝብ ግንኙነቶችና በግል ሚዲያዎች መካከል ያለው ግንኙነት አለመተማመን የሚስተዋልበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ የመንግስት የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ፤ ያለመስጠት ችግር በስፋት እንደሚስተዋልባቸው የሚገልፀው ጥናቱ፤ መረጃን በተገቢው መንገድ አደራጅቶ ያለመያዝ ችግር እንዳለባቸውም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል የግል ሚዲያዎች ለሚሰሯቸው የዜና ዘገባዎች፣ ከመንግስት ወገን ያሉ መረጃዎችን በተመለከተ፤ “የስራ ኃላፊዎችን በተደጋጋሚ ልናገኛቸው ሞክረን አልተሳካም” የሚሉ ምክንያቶችን የማስቀመጥ ዝንባሌ በስፋት መለመዱን ጥናቱ ይገልፃል፡፡
የግል የብሮድካስት ሚዲያዎች፣ ብሄራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ፕሮግራሞችን ቀርፆ ከማሰራጨት ይልቅ ስፖርትና መዝናኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በመንግስት በኩል እንደማይደገፍ በጥናቱ ተንፀባርቋል። የግል ህትመት ሚዲያውን ጨምሮ ሌሎች የግል ብሮድካስት ሚዲያዎች፣ ከመንግስት ሚዲያዎች በአንፃራዊነት ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ በኩል የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ዳሰሳዊ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ ሆኖም ግን በሀገሪቱ የቀሩት ጥቂት የህትመት ሚዲያዎች፣ በአሁን ወቅት በከፍተኛ ቀረጥ፣ ታክስና የህትመት ዋጋ ንረት እየተንገላቱ መሆኑን ጠቅሶ፤ ማበረታቻና ድጋፍ ማጣታቸው ለውደቀት እየዳረጋቸው ነው ብሏል - ጥናቱ፡፡
በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር ዶ/ር ተሻገር ሽፈራው፤ “የግል መገናኛ ብዙኃን የይዘት አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፤ የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙኃን፣ የይዘት ባህሪ፣ ወጥነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ካለባቸው መረጃ የማግኘት ችግር የተነሳ በአመዛኙ፣ የተጠናቀቁና የበቁ ዘገባዎችን ለመስራት እንደሚቸገሩም ዶ/ር ተሻገር ጠቅሰዋል፡፡
ከአቅም ውስንነት የተነሳም ዘገባዎቻቸው አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተመሰረቱ እንደሆኑና ክልል ያሉ ጉዳዮችንና በሀገር አቀፍ ደረጃ መዳሰስ ያለባቸውን ርዕሰ ጉዳዩች የመዘገብ ሂደታቸው ደካማ መሆኑን ገልፀዋል - የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህሩ፡፡  ይህ ችግር በግል መገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በመንግስት መገናኛ ብዙኃንም እንደሚታይ የጠቀሱት አጥኚው፤ የሚሉትን ያህል “የህዝቡን ብዝሃነት አያንፀባርቁም” ብለዋል፡፡ በአንፃሩ የግል ሚዲያዎች የሚያተኩሩት፣ በመንግስት ሚዲያዎች የማይነኩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ አማራጭ የሀሳብ ማንሸራሸሪያ ለመሆን ችለዋል ያሉት ዶ/ር ተሻገር፤ የዲሞክራሲ ጅምር ባለባቸው ሀገራት የግል ሚዲያዎች ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች እድል መስጠታቸውም የተለመደ አዎንታዊ ባህሪ ነው ብለዋል።
በቀረቡት ሁለት ዳሰሳዊ ጥናቶችና በሚዲያ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያውን አስተያየት የሰጡት የዛሚ ኤፍኤም መስራች ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ፤ የግሉ ሚዲያ ያሉበትን ማነቆዎች የጠቀሱ ሲሆን፤ የመንግሥት መረጃዎች በተለይ ለዜና ግብአት የሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመንግስት መገናኛ ብዙኃን ብቻ በልዩነት መሰጠቱን ኮንነዋል፡፡ “በህግ የተፈቀደ የዲሞክራሲ ፈንድ እንኳ ለግል ሚዲያዎች አልተሰጠም፤ ለዚህ ፈንድ ምንድን ነው መስፈርቱ” በማለት ጠይቀዋል ወ/ሮ ሚሚ፡፡
የዲሞክራሲ ፈንድን በተመለከተ ምላሽ የመሰለ አስተያየት የሰጡት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘርዐይ፤ “መንግስትን ሲያብጠለጥሉ ለሚውሉ ሚዲያዎች እንዴት ነው የዲሞክራሲ ፈንድ የሚሰጠው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡  
ሌላው አስተያየት ሰጪ የኢነጋማ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን መኮንን በበኩላቸው፤ የግሉ ሚዲያ ችግር ከመንግስት የሚመነጭ ነው ብለዋል፡፡ “ዛሬ ከፍተኛ የሙስና ችግርና ምዝበራ የመኖሩ ምስጢር ጠንካራ የግል መገናኛ ብዙኃን አለመኖራቸው ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀደም ያሉት የግል ሚዲዎች ያለ ፍርሃትና መሸማቀቅ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ይጋፈጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ሀገር፣ በጣት የሚቆጠሩ ፕሬሶች መኖራቸው አሳፋሪ መሆኑን ያወሱት አቶ ወንድወሰን፤ መንግስት በልማት ላይ የሰራውን ያህል ረዥም ርቀት ተጉዞ በሚዲያዎች ላይ አልሰራም፤ እነዚህ ፕሬሶች አለመኖራቸው ይህቺን ሀገር በእጅጉ ጎድቷታል ብለዋል፡፡ “የመንግስት ሚዲያው በፍርሃት የሚርድ” ነው ያሉት የኢነጋማ ፕሬዚዳንቱ፤ “ጋዜጠኛውም በፍርሃት ተቀፍድዶ በነፃነት የማይሰራ ነው፤ ይህ ሁኔታ ሀገራችንን ለወደፊት በእጅጉ ይጎዳታል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። መንግሥት ሚዲያውን ማሳደግ የሚችለው ሚዲያውን በመድፈቅ ሳይሆን የተለየ አዲስ ሪፎርም በማካሄድ ነው፤ በነፃነት ሃሳብን መግለፅ በችሮታ የሚሰጥ ሳይሆን የህግ ድጋፍ ያለው ተፈጥሮአዊ መብት በመሆኑ የሚዲያ ነፃነት ምህዳሩ መስፋት አለበት” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል - አቶ ወንድወሰን፡፡
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ አዘጋጅ ሰለሞን ጎሹ፣ አፅንኦት ሰጥቶ የተናገረው፤ ዘገባን ሚዛናዊ በማድረግ ጉዳይ ላይ ሲሆን “በተደጋጋሚ የመንግስት አካላትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም” የሚሉ ሀረጎችን የምንጠቀመው ከሚገጥመን ችግር አንፃር ነው እንጂ ጥረት ሳናደርግ ቀርተን አይደለም ብሏል፡፡
በብሮድካስት ባለስልጣን ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ “ስማቸውን ለመጥቀስ ያልፈለጉ ምንጮች” በሚል የሚወጡ ዘገባዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው የተጠቆመ ሲሆን ጋዜጠኛ ሰለሞን በዚህ ላይ በሰጠው አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም የስራ ኃላፊነታቸውና ስማቸውን በድፍረት ተናግረው መረጃ የሚሰጡ አካላት እንደነበሩና አሁን ግን መረጃ ከመስጠት ባይቆጠቡም፣ አብዛኞቹ ስማችን እንዳይጠቀስ የሚል ተማፅኖ እንደሚያቀርቡ ገልጿል፡፡ አጥኚዎችና የመንግስት ኃላፊዎች፤ እነዚህ “ስማችን አይጠቀስ” የሚሉ ኃላፊዎች፤ ለምን ፍርሃት ውስጥ እንደወደቁ መፈተሸ አለባቸው፣ ፍርሃታቸው መነሻው ምንድን ነው የሚለው መመርመር አለበት ብሏል - ጋዜጠኛው፡፡
የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ በበኩሉ፤ በመንግስት የህዝብ ግንኙነት ላይ የተቀመጡ ባለሙያዎች የእውቀት ችግር ባይኖርባቸው እንኳ በአሰራሮች የተጠፈሩ፣ መንቀሳቀስ የማይችሉ ናቸው፤ ይሄ ባለበት የመረጃ ነፃነት ሊመጣ አይችልም ብሏል፡፡ “ነፃ ያልወጣ ህዝብ ግንኙነት፣ መረጃ በነፃነት ሊሰጥ አይችልም” ያለው ጋዜጠኛው፤ መንግስት የመረጃ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ በመጀመሪያ የህዝብ ግንኙነቶቹን ነፃነት ማስጠበቅ አለበት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “መረጃ ለሚዲያዎች መስጠት ማለት ለ3ኛ ወገን መስጠት አይደለም፣ ይሄ አስተሳሰብ በመጀመሪያ ከአስፈፃሚው አካል መነቀል አለበት” ብሏል ጋዜጠኛው፡፡
በቅርቡ ከእስር የተለቀቀው የ“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በሰጠው አስተያየት፤ መረጃ የማግኘት መብት የህዝብ ነው፤ ጋዜጠኛው የህዝቡ ወኪል ነው፤ ስለዚህ ጋዜጠኛው ስራውን ሲሰራ በመረጃ መታገዝ ነው ያለበት ብሏል፡፡
በግል ሚዲያዎች ላይ የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ በበኩላቸው፤ የተሰነዘሩት አስተያየቶች በግብአትነት ተወስደው፣ መንግስት ላቀደው የሀገሪቱን የሚዲያ ምህዳር፣ ሪፎርም የማድረግ ስራ ይጠቀምባቸዋል ብለዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ በስፋት ሲያከራክሩ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ፣ በሳተላይት ከውጭ የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የተመለከተ ሲሆን ብሮድካስት ባለስልጣን፣ አምስት ጣቢያዎች የሳተላይት ፍቃድ አግኝተው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁሟል፡፡
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አንዳንድ ጋዜጠኖች፣ በበኩላቸው፤ ከእነዚህ ጣቢያዎች መካከል የእንግሊዝኛ ፊልሞችን እየተረጎሙ፣ የሌላን ሀገር ባህልና ልማድ በህፃናትና ወጣቶቻችን አዕምሮ ውስጥ እያሰረፁ የሚገኙት ሊታገዱ ይገባል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዐይ፤ ችግሩ እሳቸውንም እንደሚያሳስባቸው ጠቁመው፣ “እንደውም ጣቢያዎያቹ ማህበረሰቡን እያደነዘዙት ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ጣቢያዎች ለማገድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳም፤ የአቶ ዘርዐይን ሀሳብ አጠናክረዋል፡፡ እሳቸውም ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ነገር ግን የማገድ እርምጃ የሚወሰድበት የህግ አግባብ የለም ብለዋል፡፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ እነዚህ ሚዲያዎች ህፃናትና ወጣቶች የራሳቸውን ባህል እንዲተዉ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ከሆነ፣ በዚህ መልኩ ሊቀጥሉ አይችሉም ብለዋል - “ጣቢያዎቹ መታገድ አለባቸው” ለማለት ግን አልደፈሩም፡፡
የውጭ ፊልሞችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ጣቢያ ማስተላለፍ የጀመረው “ቃና” ቲቪ፤ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜም በርካታ ኩባንያዎች ማስታወቂያዎችን ለማስተላለፍ የሚመርጡት ጣቢያ ለመሆን በቅቷል፤ ይላሉ - ምንጮች፡፡
ሆኖም፤ በርካታ የፊልም ባለሙያዎችና አርቲስቶች፤ የወጣቶችን ሥነ ምግባር ያበላሻል፣ ባህል ይበርዛል ወዘተ በሚሉ መረጃ በማይቀርብባቸው ውንጀላዎች ሽፋን፣ ጣቢያው እንዲዘጋ አያሌ ጥረቶችንና እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸውን ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡ የሚዲያ አባላት፣ መሰል ጣቢያዎች እንዲታገዱ በአደባባይ ሲገልፁ ግን የሰሞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ በውይይቱ የተሳተፉ ጋዜጠኞች፣ “እያንዳንዱ ቤተሰብ በጁ ላይ ባለው ሪሞት ኮንትሮል የመረጠውን ማየትና ያልመረጠውን ማጥፋት ወይም መዝጋት እየቻለ፣ ይታገድ ወይም ይዘጋ ወደ ሚል የነፃነት አፈና ለምን መሄድ እንዳስፈለገ ግራ ያጋባል” ብለዋል። “ነገ መንግስት ተነስቶ አንዱን የቴሌቪዥን ጣቢያ የተቃዋሚ ልሳን ነው በሚል ልዝጋ ቢል የምንቃወምበት የሞራል መሰረት አይኖረንም” ይላሉ ጋዜጠኞቹ፡፡
በተለይ ደግሞ ከሚዲያው አባላት መምጣቱ ያስደነግጣል ያሉት ጋዜጠኞቹ፤ መንግስት ‹የህግ ማዕቀፍ› የለኝም ቢልም፣ የግድ የሚዲያ ፈቃጅና ነሺ እንዲሆን ከመማፀን ያላነሰ ጥረት ማድረጋቸው ያሳዝናል ብለዋል፡፡ ቃና ቴሌቪዥን ለዕይታ ከበቃበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ተቃውሞና ተቀናቃኞችን አስተናግዷል፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢቢሲ የኮርያ ፊልም ወደ አማርኛ ተርጉሞ ለተመልካቹ ሊያቀርብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጣቢያው ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡   


Read 6125 times