መጥፎ የፊልም ስራዎችን እና ባለሙያዎችን በመምረጥ ለራዚ አዋርድስ ድምፅ የሚሰጡት በ46 የአሜሪካ ግዛቶች ያሉ 657 ባለሙያዎች እና ከሌሎች 17 አገራት የሚጋበዙ ባለሙያዎች ናቸው፡፡የራዚ አዋርድን የሚወስዱ ዝነኞች በስነስርዓቱ ላይ ባለመገኘት የሚታወቁ ሲሆን አዳም ሳንድለርም በፕሮግራሙ ላይ ስለመገኘቱ ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ ከዓመት በፊት በአዳም ሳንድለር ፀሃፊነት፤ፕሮዲውሰርነትና ተዋናይነት የታዩት ሶስት ፊልሞች “ጃክ ኤንድ ጂል”፤ “ጀስት ጎ ዊዝ ኢት” እና “ዙ ኪፕር” ሲሆኑ ፊልሞቹ በድምሩ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቶባቸዋል፡፡ የሰራቸው ፊልሞች አክሳሪ ባይሆኑም ሳንድለር ትወና ይበቃዋል በሚል በአሜሪካ 97 በመቶ የሚሆኑት የፊልም ሃያሲዎች ክፉኛ ነቅፈውታል፡፡ በ32ኛው የራዚስ አዋርድ ላይ የ42 ዓመቱ አዳም ሳንድለር በ11 የሽልማት ዘርፎች ታጭቶ አስሩን መውሰዱ ስራ ያሳጣዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ በራዚ አዋርድ ታሪክ ታዋቂዎቹ ኬቪን ኮስትነር፤ ሄሊ ቤሪና ሳንድራ ቡሎክ በመጥፎ ተዋናይነት ለሽልማት ተመርጠዋል፡፡ ከ37 በላይ ፊልሞች የሰራው አዳም ሳንድለር በአማካይ በአንድ ፊልም እስከ 73 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገባ ይታወቃል፡፡ የቦክስ ኦፊስ ሞጆ መረጃ እንዳመለከተው በ20 ዓመት የሆሊውድ ቆይታው በሰራቸው ፊልሞች በዓለም ዙርያ ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል፡፡