Sunday, 03 September 2017 00:00

የ“እውነት” ቀን ያስፈልገናል!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(14 votes)

  ከጭፍን ፕሮፓጋንዳ፣ ከአሉባልታ ዘመቻ፣ ከቅዠትና ከብዥታ ለመገላገል ፣ የእውነት ጭላንጭል ሲፈነጥቅ ለማየት አንዳች እድል የሚፈጥር፣ ለወደፊትም ፏ ወዳለ የእውነት ብርሃን ለመጓዝ መንፈሳችንን አነቃቅቶ ብርታት የሚሰጥ፣ የ“እውነት ቀን” ያስፈልገናል።
በብሩህ የእውነት መንገድ ብቻ ነው፤ አእምሮን መጠቀምና ግንዛቤ መጨበጥ፣ መማርና እውቀትን ማዳበር የምንችለው። ‘ነፃነት’ ትርጉም የሚኖረውም፣ ለእውነት ከፍተኛ ክብር የምንሰጥ ከሆነ ብቻ ነው። የጆርጅ ኦርዌል ድርሰት ውስጥ የሰፈረችውን አንዲት አባባል ላስታውሳችሁ። ነፃነት ማለት፣... “ሁለት ሲደመር ሁለት አራት ነው ብሎ የማሰብና ይህንን እውነት የመናገር ነፃነት” ካልሆነ፤ የነፃነት ክብር ምኑ ላይ ነው? የነፃነት ትርጉም ትልቅነትን መገንዘብ የምንችለው፣ እውነትን ከማክበር ጋር ስናስተሳስረው ነው። ያኔ፣ “የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ” ይሆናል፤ የነፃነት ጥያቄ።
በአጭሩ፣ እውነትን ሳናከብርና ብሩህ የእውነት መንገድን ሳናፈቅር ስንቀር ነው፤ አሁን እንደምናየው፣ የብዙ ሰዎች አእምሮ፣ እርባና ቢስ የቅዠት ፋብሪካና ‘የአረም እርሻ’ ሆኖ የሚቀረው። በእውነት ምትክ፣ ጭፍን ፕሮፓጋንዳና የአሉባልታ ዘመቻ ውስጥ እንባዝናለን። በእውቀት ምትክ ጭፍን እምነት፣ በግንዛቤ ፋንታ ጭፍን ስሜት ውስጥ እየተዘፈቅን እንላወሳለን። በመወያየትና በመማማር ምትክ፣ በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ግራ ቀን እንላተማለን።  
ለእውነት ደንታ ቢስ ሆነን፣ ቀስ በቀስም እንደ ባላንጣና እንደ ደመኛ ጠላት፣ እውነትን አዳፍኖ ለመቅበር የምንቅበዘበዝበት፣ ካልተቻለም ወደ ጨለማ ለመሸሽ የምንደናበርበት አገራዊ ባህል ካልተቀየረ፣... ሌላው ሁሉ... አንድም ወገኛነት፣ ወይም የይስሙላ፣ አልያም የለየለት ውሸት ይሆናል። የእውነት ብርሃን በተጠላበትና እንደ ቁምነገር በማይታይበት አገር፣ “እውቀት፣ ሳይንስ፣ ሂሳብ፣ ትምህርት፣ ንባብ” ብሎ ማውራት ከንቱ ነው።
አዎ፤ “የንባብ ቀን” የሚል ማነቃቂያ ዝግጅት መፍጠር ጥሩ ነው። ነገር ግን፣ “የንባብ ቀን” ትልቅ ትርጉም የሚኖረው፣ ከውሸት ለመራቅና የእውነትን ችቦ ለመለኮስ መነሳሳትንም ከጨመረ ብቻ ነው። በተለኮሰው ብሩህ የእውነት ጎዳናም፣ የየራሳችንን የግል አእምሮ ተጠቅመን እውነታን ለመገንዘብና ለማሰብ፣ እውቀትን ለመጨበጥና ለማዳበር የምንፈልግ ከሆነ ነው - ንባብና የንባብ ቀን ፋይዳ የሚኖራቸው። እውነትን በማክበር ላይ የተመሰረተውና አእምሮን በመጠቀም የምንጀምረው የብሩህ ጎዳና ጉዞ፣ ቀስ በቀስ ከእያንዳንዱ ሰው ማንነት ጋር እየተዋሃደ፤ በራሱ የሚተማመን ቅንነትንና ፅናትን የተቀዳጀ ጠንካራ ሰብዕና ላይ እንደሚያደርስ ስናውቅ ነው - ለንባብ ቀን ተገቢውን ዋጋ መስጠት የምንችለው። አለበለዚያ፣ ስም ብቻ ሆኖ ያልፋል። እኛም፣ እየተባባሰ በመጣው ነባር የጭፍንነት ቅዠትና የጨለማ ብዥታ ውስጥ ጠፍተን እንቀራለን። ይሄ፣ የሩቅ ሃሳብ አይደለም። በየእለቱ በየአካባቢያችን የምናየው ኑሯችን ሆኗልኮ። ግን ለምን? “ተነጋግሮ መግባባት እየጠፋ፣ ውንጀላና ስድብ፣ ጭፍን ፍረጃና ጭፍን ጥላቻ ሲበራከትና አገር ምድሩን ሁሉ ሲያጥለቀልቅ የምናየው ለምንድነው?”
አሃ! ከምር እውነትን ማክበር ካልጀመርን፣ ለወጉ ያህል ለእውነት ዋጋ መስጠት እንኳ ሲያቅተን እያየን፣... ከእውነት ሌላ በምን መግባባት ይቻላል? በየትኛው አማራጭ የመግባቢያ ዘዴ? ሌላ መግባቢያ አማራጭና ዘዴ የለም። ብዙዎች ደግሞ፣ በጊዜያዊ ስሜት ተገፋፍተንም ሆነ እንደ ቀልድ ቆጥረን የገባንበት የውሸት አዘቅት፣ መውጪያ አሳጥቷቸዋል።  

ውሸትን ከመቀበል - ውሸትን እስከ ማክበር
ሌላ ሰው ላይ እስከ ሆነ ድረስ፣ በውሸት ማሞገስም ሆነ ማጥላላት፣ ውሸትን በመተማመን የሚካሄዱ የፕሮፓጋንዳም ሆነ የአሉባልታ ዘመቻዎች፣ ብዙም ደንታ ሳይሰጠን ተቀብለነው ለማለፍ ፈቃደኞች ነን። ችግር የለውም ብለን እናስባለን።
የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው ሰው ላይ ከሆነስ? ይሄኔ የውሸት ፕሮፓጋንዳና አሉባልታ ያስፈልጋል? ብዙ ሰዎች፣ ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ አይፈልጉም። በፕሮፓጋንዳና በአሉባልታ ዘመቻ ላይ ያላቸው አቋም፣ “እንደ ሁኔታው” ነው።
የምንደግፈውን ሰው ለማሞገስና ለማዳነቅ፣ የምንቃወመውን ደግሞ ለማንቋሸሽና ለማውገዝ... ማንኛውም ሰበብና ማመካኛ ይፈቀዳል፤ እውነት ሆነ ውሸት፣ ለውጥ የለውም። እንዲያውም፣ ‘ለእውነት ሳንበገር’፣ በግላጭ የሚታዩና ቁልጭ ብለው የተመዘገቡ መረጃዎችን ሽምጥጥ አድርገን እየካድን፣ በጭፍን የምንደግፍና የምንቃወም ከሆነ ነው፣ ትልቅ ክብር ሆኖ የሚታየን። ያለ የሌለውን ውሸት ደጋግመን እየዘከዘክንና አዳዲስ ውሸት እየጎለጎልን፣... በዚህም በዚያም ብለን፣ ‘ለመሪያችን’፣ ‘ለፓርቲያችን’፣ ‘ለቡድናችን’ ውዳሴና አድናቆት ስናዥጎደጉድ፣... አልያም የውግዘትና የውንጀላ ማዕበል ስናጎርፍበት ነው፤... በጭፍን የድጋፍና የተቃውሞ ስሜት መስከራችን እንደ ብቃት ተቆጥሮ፣... ‘የቁርጥ ቀን ልጅ፣ ታማኝ ደጋፊ፣ ቀንደኛ ተቃዋሚ” የሚል ማዕረግ የምናገኘው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ በየቡድናችን ውስጥ፣ እልቅና የምንቀምሰውና የቡድናችንን አባላት ‘የማስፈራራት ፈቃድ’ መያዝ የምንችለው በጭፍንነታች ልክ ነው። በጭፍን ደጋፊነት ወይም ተቃዋሚነት፣ አዲስ ሪከርድ በበጠስን ቁጥር፣ በሌሎች ተራ አባላት ላይ መንገስ እንችላለን።
ተቃራኒውን ደግሞ ተመልከቱ።
“ትክክለኛ ሃሳብ፣ ትልቅ ስኬትና ከፍተኛ ብቃትን ስመለከት፤... እቀበላለሁ፣ እደግፋለሁ፣ አደንቃለሁ። የተሳሳተ ሃሳብ፣ ጎጂ ጥፋትና ክፉ ዝቅጠትን ሳይ እተቻለሁ፣ እወቅሳለሁ፣ እፀየፋለሁ” የሚሉ ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች፣... እንደ ደጋፊ ወይም እንደ ተቃዋሚ አይቆጠሩም።
ወይ በጭፍን ታማኝነት አይደግፉ፣ ወይ በትዕዛዝ ግፊት አይደግፉ!
ወይ በጭፍን ጥላቻ አይቃወሙ፣ ወይ በሆይ ሆይታ ግፊት አይቃወሙ! “ፓርቲዬ ያውቃል፤ ሕዝብ ያውቃል” ብሎ ራሱን አያታልልም። ‘የፓርቲውንና የቡድኑን ውሳኔና መግለጫ እየተከተለ፣ ጭብጨባና ጉምጉምታን እየመዘነ፣ በፉጨትና በእሪታ ጩኸቶች እየተነዳ፤ በጭፍን ስሜት አይሰክርም። በጭፍን ድጋፍ አይደነፋም፤ በጭፍን ተቃውሞ አይሳደብም።
የፓርቲው አዝማሚያ፣ የሕዝብ ስሜት፣ የጭብጨባና የጉምጉምታ ነፋስ፣ ከእለት እለት አቅጣጫው በተቀያየረ ቁጥር፣ ያንኑ ተከትሎ እየተነሳ መንጎድና መነዳት አይፈልግም።
ይልቅስ፣ ተጨባጭ እውነታ ነው የሁልጊዜ መነሻው። የራሱን አእምሮ በመጠቀም፣ መረጃዎችን አገናዝቦ፣ እውነትና ሐሰትን፣ ትክክልና ስህተትን ይለያል። ድርጊቶችንና ውጤታቸውንስ? ለሰው ኑሮ የሚኖራቸውን ፋይዳ ለመመዘን በሚያስችሉ መርሆች አማካኝነት፣ ጠቃሚንና ጎጂን፣ ጥፋትንና ልማትን፣ ስኬትንና ውድቀትን ይለያል። እውነት፣ “እንደሁኔታው” አይቀያየርም። ጥፋትና ስኬት፣ “እንደ ሁኔታው” በሚል የማይጨበጥ ነፋስ፣ የሚዘወሩ አይደሉም። ይሄ የእውነትና የቅንነት ሰብዕናና ባህል በአገራችን፣ ብርቅ ነው - ብዙ አይገኝም።
“እንደ ሁኔታው”... ነው የነገሰው። ለምን?

“ነው፤ አይደለም፤... እንደ ሁኔታው” - በታክስ እና በአድማ!
በሰው ኑሮና ንብረት ላይ ዘው ብሎ እየገባ አዛዥ ናዛዥ የመሆን ሱስ፣ በሰበብ አስባቡ የሰውን ኑሮ ለማናጋት የመወሰንና በዘፈቀደ የመፍረድ ጥፋት፣... “እንደ ሁኔታው”፣ አንዳንዴ ተገቢ የሚሆነው፣ አንዳንዴ ደግሞ ተገቢ የማይሆነው ለምን ይሆን? እስቲ ግራ ቀኙን ለማየት፣ ከአንደኛው አቅጣጫ እንጀምር።
ለእያንዳንዱ ሰው ኑሮና ንብረት ደንታ በሌለው የዘፈቀደ ውሳኔ፣ የታክስ እዳ መጫን ተገቢ ነው? ወይስ ትልቅ ጥፋት? መንግስት ያመነውን ብቻ ተመልከቱ። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም እንደተናገሩት፣ 40% ያህል የታክስ ውሳኔዎች፣ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ናቸው። 200 ሺ ሰዎች ላይ፣ የተሳሳተ የታክስ ሸክሞችን የሚጭን የውሳኔ መዓት እንደ ማለት ነው። የስንት ቤተሰብ ኑሮ እንደሚናጋ አስቡት!
በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በቲቪና በሬድዮ በየእለቱ ያስተላለፉትን ፕሮፓጋንዳ ደግሞ አስታውሱ።
‘የታክስ ውሳኔዎቻችን በመረጃና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የታክስ ከፋዮች ቅሬታ፣ ከግንዛቤ ችግር የመነጨ ነው። ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ የማጭበርበር ድርጊትም አለ’ በማለት ነገሩን ሲያጣጥሉና እግረ መንገዳቸውም እንደተለመደው እንደ ዘበት ዜጎችን ሲወነጅሉ ሰምተናል። እሺ፣ ያኔስ ‘መስሏቸው’ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣...
በመቶ ሺ የሚቆጠር ስህተት እንደተፈፀመ በግልፅ ከታወቀ ወዲህም ቢሆን፣... ዛሬም ጭምር፣ ‘የግንዛቤ ችግር ነው’ የሚለውን ማጣጣያ ከመደጋገም ያልተመለሱ ‘ጭፍን ደጋፊዎች’ በርካታ ናቸው። ለምን? በቃ! የመንግስት ባለስልጣን ግምትና ውሳኔ፣ ምንም ሆነ ምን፣ “ትክክለኛና ተገቢ ነው” እያሉ፣ በጭፍን ያነበንባሉ። የታማኝ ደጋፊነት ማስመስከሪያ ነው። ደግሞም፣ ‘በጭፍን ደገፍክ’ ብሎ ‘የሚገመግማቸው’ እንደማይኖር ያውቃሉ። ‘ለእውነት የማይበገር ጭፍን ድጋፍ’... በኛ አገር፣ “ያዋጣል”፤ እንደ “ብልህነት” ይቆጠራል።
‘ጭፍን ድጋፍ’ ሞልቷል። ለምሳሌ፤ በታክሲ እና በአውቶቡስ ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ በየትኛው ጎዳና ላይ መስራት እንዳለባቸው ማዘዝና በየትኛው ጎዳና መስራት እንደሌለባቸው መከልከል፤ “ተገቢ ነው”። ለምን? ለሕዝብ ጥቅም በማሰብ የተደረገ ነው በማለት ማሳበብ ይቻላል።
ኑሯቸውን በሱቅ ስራ የሚመሩ ሰዎችም፣ ለማንና ለማን፣ ስንት ሊትር ዘይትና ስንት ኪሎ ስኳር፣ በምን ያህል ዋጋና መቼ መቼ መሸጥ እንዳለባቸው የሚዘረዝር የትዕዛዝና የክልከላ ውሳኔ ቢፈራረቅባቸው፣ “ተገቢ ነው”። ለምን? ውሳኔዎቹ፣ “ድሃውን ሕብረተሰብ ለመደገፍ” የታሰቡ ናቸው በማለት ማመካኘት እንችላለን።
“በመኪና ጭነው ያመጡትን ቡና፣ መርካቶ ወስደው ሊሸጡ የሞከሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ” የሚል ዜና በተደጋጋሚ ሰምተናል። ሰርቀው ያመጡት ቡና ይሆን? አይደለም። እንዲያውም ያልተሰረቀ ቡና እንደሆነ በደንብ ታውቋል። ሚዛን ለማጭበርበር ወይም ሌላ ነገር አደባልቀው ለመሸጥ ሞክረው ይሆን? አልሞከሩም። እንዲያውም፣ ሚዛኑ አልተዛባም፤ የቡናው ጥራት ደግሞ፣ አጓጊ ነው። ታዲያ፣ ምን አጠፉ? የሰሩት ወንጀል ምንድነው?
በገዛ ጥረታቸው ያመረቱትንና በገዛ ገንዘባቸው ገዝተው ያመጡትን ጥራት ያለው ቡና፤ መርካቶ ወስደው ለመሸጥ መሞከራቸው ነው እንደ ጥፋት የተቆጠረባቸው። ጥራት ያለው ቡና አምርቶ፣ እዚሁ አገር ውስጥ ለመሸጥ መሞከር ወንጀል ነው ተብሎ ተፈርጇል። ለምን? “ወደ ውጭ አገር እየተሸጠ፣ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት አለበት፤ ይህም ለአገር ልማት የታሰበ ነው” በማለት ማመካኘትና ገበያተኞች የታሰሩት በሕጉ መሰረት እንደሆነ መናገር እንችላለን - የተገቢነት ካባ እንዲላበስ።
ይሄ የጭፍን ደጋፊዎች የዘወትር መለያ ምልክት ነው። በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሁሉ፣ በጭፍን ይደግፋል።
በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሁሌም ለማጯጯህ የሚመኝ ጭፍን ተቃዋሚስ? ያው፣ ከላይ የጠቀስናቸውን ምሳሌዎች፣... የታክስ ጫና፣ የባለ ሱቅ፣ የባለ ታክሲና ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንደ ቁም ነገር አይቆጥራቸውም - ጭፍን ተቃዋሚ። ነገር ግን፣ “የተቃውሞ መቀስቀሻ ሰበብ” የሚሆኑለት ከሆነ፣ አውራ መሪ በመሆን እሪታና ውግዘቱን ያወርደዋል። የትራንስፖርት፣ የስኳርና የዘይት እጥረቶችንም ይኮንናል። የሰዎች ኑሮና ንብረት ላይ እንደ ዘበት የሚተላለፉ የታክስ ውሳኔዎችን አወግዛለሁ በማለት አድማዎችን ይቀሰቅሳል። “ሰዎች ሰርተው የመኖር መብት ተነፈጉ። ጥረው ግረው ባፈሩት ንብረት እንዳፈይጠቀሙ ተከለከሉ። አቤት ቢሉም ሰሚ አላገኙም። የቅሬታ ድምፃቸውንም እንዳያሰሙ ታፈኑ፤ በግዴታ እንዲሰሩ ታዝዘዋል። ሱቃቸውን እንዲከፍቱ፣ መኪናቸውን እንዲያንቀሳቅሱ እየተገደዱ ነው” በማለት ያማርራል። ግን፣ “ነፃነትና መብት እንዲከበር” አይደለም ጩኸቱ። ለምን? የተቃውሞ አድማ ሲጠራ፤ “በዚህኛው ጎዳና፣ በዚያኛው መንገድ ላይ፣ መኪና አይንቀሳቀስም። ሱቅ አይከፈትም። ገበያ ሄዶ መሸጥና መግዛትም አይኖርም” በማለት ያውጃል፤ ያውጃሉ።
ግን፤ ሃሳባችሁን የሚደግፍም ሆነ የማይደግፍ ሰው፤ የሌሎችን ኑሮና ንብረት ሳይነካ፣ በተለያየ ምክንያት፣ መኪና ቢያንቀሳቅስና ተሳፋሪዎችን ቢያጓጉዝ፣ ሱቅ ቢከፍትና ቢሰራ፣ ገበያ ቢሄድና ቢሻሻጥስ? በራሱ ኑሮና ንብረት ላይማ፣ መብቱ ነው ብላችሁ ታከብራላችሁ?
አይ፤ “እንደዚያ የሚያደርግ ሰው አይኖርም”፤.... “ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ የሚንቀሳቀስ ሰው አይኖርም”፤... “እርምጃ ይወሰድበታል”... የሚሉ ምላሾችን ይሰጣሉ። “የሰዎችን ነፃነት ማፈን፣ መብታቸውን መጣስ፣ ኑሮና ንብረታቸውን ማናጋት፣... ለመንግስት አይፈቀድም፤ ለተቃዋሚ ይፈቀዳል” እንደ ማለት ነው። ለምን? የሕዝብን ድምፅ ለማሰማት የታሰበ ስለሆነ!
“በተቃራኒው ደግሞ፤ የሰዎችን ነፃነትና መብት መጣስ፣ ኑሮና ንብረታቸውን ማናጋት፣... ለመንግስት ይፈቀዳል፤ ለተቃዋሚ ግን አይፈቀድም”... በጭፍን ደጋፊዎች ዘንድ። ለምን? የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የታሰበ ስለሆነ!
አቤት ተመሳሳይነታቸው!
“የሰዎችን ነፃነት ማፈንና መብት መጣስ፣ በፕሮፓጋንዳና በአሉባልታ ዘመቻዎች እልፍ ውሸቶችን መንዛት ይቻላል፤ ይፈቀዳል፤ ያስፈልጋል...” በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ልዩነታቸው፤ “ውሸት በመንዛት የበላይነትን መያዝ ያለበት ቡድን የትኛው ነው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተጠናወታቸው የጭፍን ስሜት ልዩነት ነው። ተቀናቃኝነታቸውም፣ ነፃነትን ለማፈን፣ መብት ለመጣስ፣ የሰዎች ኑሮና ንብረት ላይ ለመግነን በሚደረግ የቡድኖች ሽሚያ ላይ፣ በቲፎዞነት እየተጠረነፉ የመጯጯህና የመበሻሸቅ ሱስ ነው - የነገረኛ ጎረቤታሞች ሱስ። ግን በዚሁ አይቆምም። በጊዜ ካልታረመ፣ እየተማገዱና እየማገዱ አገር ምድሩን ሁሉ ወደሚያጠፋፋ፣ የአውሬ ፉክክር መግባት አይቀርለትም።

Read 6864 times