Sunday, 03 September 2017 00:00

የንግድ ሥራና ትራንስፖርት ማቆም አድማ - ተጽዕኖና አንደምታው?

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግስት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የንግድ ሥራና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም አድማ ባለፈው ሳምንት ተደርጓል፡፡ እነዚህ አድማዎች ምን አንደምታ አላቸው? በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ነው? በቱሪዝም ዘርፉና በኢንቨስትመንት ላይስ? በመንግስት ላይ የሚያሳርፈው ፖለቲካዊ ጫና ምንድን ነው? አድማዎቹ ተባብሰው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሻገሩ መፍትሄው ምንድን ነው ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ፤ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄን፣አቶ ሞሼ ሰሙንና አቶ ክቡር ገናን በጉዳዩ ዙሪያ አወያይቷቸዋል፡፡ ሁሉም ሃሳባቸውን፣ አስተያየታቸውን፣ ስጋታቸውንና የመፍትሄ ሃሳቦቻቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡

                    “በማንኛውም የሀገሪቱ ጉዳይ ህዝብን ማሳተፍ ያስፈልጋል”
                          ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)

      የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግስት የንግድና ትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም አድማ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ተደርጓል፡፡ በእንዲህ ያሉ አድማዎች ማነው ተጎጂው?
እንዲህ ያለ አድማ ሁሉንም ነው የሚጎዳው፤ ሸማቹን፣ ነጋዴውን፣ መንግሥትን ይጎዳል። በአጠቃላይ እንደ ሀገር ደግሞ መረጋጋቱን ስለሚያበላሽ፣ ኢንቨስተሮች በሀገሪቱ ላይ የሚኖራቸውን መተማመን ይቀንሳል፡፡ ብዙ ኢንቨስተሮች እንደ ቢቢሲ ላሉት፣ የውጪ ሚዲያ በሚሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በተለይ የቻይና ኢንቨስተሮች፣ ኢትዮጵያን የመረጡበት አንዱ መመዘኛ፣ አገሪቱ የተረጋጋች፣ ሰራተኛውም ሰላማዊ በመሆኑ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እንደነዚህ አይነቱ ረብሻዎችና አድማዎች የሚያሳዩት፣ በአንድ መልኩ፣ ህዝቡ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን  የመናገር መብቱን መጠቀሙ ነው፡፡ ጉዳዩ ወደ መጥፎ ሁኔታ ሲሸጋገር ደግሞ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚም የተለያየ አላማ ያላቸው ወገኖች፣ የህዝቡን ቅሬታ ለራሳቸው አላማ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግስት፣ ህዝቡን በየጊዜው ቀርቦ ማነጋገር አለበት፡፡ በተለይ በወረዳ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች፣ ለህዝቡ ቀጥተኛ መፍትሄ መስጠት አለባቸው፡፡
ለምሳሌ በኦሮሚያ ለተደረገው አድማ በምክንያትነት ከቀረቡት ጉዳዮች አንዱ የግብር ጉዳይ ነው---
በየትኛውም አገር ነጋዴ በተቻለ አቅም ታክስ ባይከፍል ይመርጣል፡፡ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንኳ ታክስ አይከፍሉም ተብለው ሲብጠለጠሉ የሰጡት ምላሽ፤ “እኔ ብልህ ስለሆንኩ ነው ታክስ የማልከፍለው” የሚል ነበር፡፡ አብዛኛው ነጋዴ ታክስ መክፈል አይፈልግም፡፡ ያገኘውን ቆጥቦ ንግዱን ማስፋፋትና ኑሮውን ማሻሻል ነው የሚመርጠው፡፡ መንግስት ደግሞ መሰረተ ልማት ለማሟላት፣ ሀገር ለመገንባት ገንዘብ ያስፈልገዋል። ስለዚህ በግብር ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶችንና ችግሮችን በውይይትና  በሰለጠነ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል፡፡
መንግስት የግብር ሰብሳቢ ሰራተኞችን ሁኔታም መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ የአቅም ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ ሌላው የንግድ መደብሮችን እያሸጉ ጉቦ የሚጠይቁ እንዳሉም ይሰማል፡፡ እነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ የህዝብን ብሶት የሚቀሰቅሱት እንዲህ ያሉ ህገ ወጥ አሰራሮች ናቸው፡፡ በስፋት አድማ የሚያደርጉ ነጋዴዎች፣ ትልልቆቹ ወይም ለማህበረሰቡ በእጅጉ የቀረቡ አይደሉም፡፡ በየመንደሩ ያሉ ከህብረተሰቡ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው አነስተኛ ነጋዴዎች ናቸው። የእነዚህ ነጋዴዎች ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።
አድማው በመንግስት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳርፋል?
እርግጥ ነው ለጊዜው በመንግስት ላይ ምንም አይነት ቀጥተኛ ተፅዕኖ ላይኖረው ይችላል፤ ምክንያቱም የጸጥታ ኃይሉን ልኮ ህግ ሊያስከብር ይችላል፡፡ ነገር ግን አድማና ረብሻ ባለበት ቦታ ቱሪስት ሊመጣ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ከቱሪዝም በየዓመቱ ይገኝ የነበረው በቢሊዮን ብር የሚገመት ገቢ፣ አማራ ክልል ወይም ትግራይ ውስጥ ረብሻና አለመረጋጋት ከተከሰተ፣ ቱሪስት ወደ አካባቢው አይመጣም፤ ገቢውም አይገኝም። በዚህ በቀጥታ ተጎጂ የሚሆኑት የጎጃም የጎንደር ወይም የትግራይ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ህዝቡ ሲጎዳ ደግሞ መንግስት ላይ ነው ጫናው የሚያርፈው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ ጉዳቱ በአገር ደረጃ ነው የሚሆነው፡፡ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በምትፈልግበት፣ ግድቦች በሚገነቡበት፣ የባቡርና ሌሎች ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በዘረጋችበት አሁኑ ወቅት ከቱሪዝም የሚገኝ ገቢን ማጣት አገሪቱን ክፉኛ ይጎዳታል፡፡
በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣት ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቀ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣትም ከኮሌጅና የሙያ ተቋማት እየተመረቀ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ ምሩቃን ሥራ እስካላገኙ ድረስ ይሄን አድማ በመጠቀም ጉዳዩን ወደ ሌላ ነገር የማሸጋገር ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ባለፈው ዓመት እንደተመለከትነው፡- ፋብሪካ ማቃጠል፣ እርሻዎች ማውደም፣ መኪና መሰባበር ወዘተ --- የመሳሰለ አደገኛ ውጤት ሊኖረው ስለሚችል፣ የመንግስት ኃላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ እርግጥ የህግ አስከባሪዎች በምንም ሁኔታ  እንዲህ አይነት ነገር እንዲኖር አይፈቅዱም። ነገር ግን እንዲህ ያሉ አድማዎችና ተቃውሞዎች እየተጠናከሩ በሄዱ ቁጥር ህዝብ በገዥው ፓርቲ ላይ ያለው እምነት እየመነመነ ሊሄድ ይችላል፡፡ ሀገሪቱ ያላት አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በተለይ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መጥፎ ገፅታ እየያዘ ከመጣ፣ ኢንቨስተሮች እዚህ ሀገር መጥተው ኢንቨስት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉ አድማዎች በተራዘሙ ቁጥር ደግሞ የሰው የስራ ተነሳሽነት ስሜት እየቀዘቀዘ፣ ወደ ረብሻ የሚገፋፋበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይሄ አይነቱን ክስተት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተመልክተነዋል፡፡
መፍትሄው ታዲያ ምንድን ነው?
በዚህ ጉዳይ የሲቪክ ማህበረሰቡና ሚዲያዎች ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የምርመራ ስራ የሚሰሩ ሚዲያዎች መጠናከር አለባቸው፡፡ በሀገራችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የህዝብ ስብስቦች አሉ፡፡ የህዝብ ስብስቦች ስንል እድሮችን፣ ማህበሮችን ያካትታል። እነዚህ ቁልፍ አካላት ናቸው፡፡  እነዚህን የሲቪክ ማህበራት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በሌላው ዓለም መንግስት የማያውቀውን ነገር አጉልቶ በማውጣት እርምት እንዲደረግ በመጠቆም ረገድ ሚዲያው ያለው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ በሀገራችን ግን በሲቪክ ማህበራትም ሆነ በሚዲያ በኩል እስከ ዛሬ ያለው እንቅስቃሴ ደካማ ነው፡፡ በተለይ ሙስናን ለመዋጋት ሚዲያና የሲቪክ ማህበራት ወሳኝ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ያለአግባብ ሀብት ሲያካብት ቀድሞ ሊያውቁ የሚችሉት በየአካባቢው ያሉ የህዝብ ማህበራት ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመር አለበት፡፡ አንድ ወረዳ ላይ መንገድ በአግባቡ ላለመሰራቱ ዋናው ምስክሮች የሚሆኑት በወረዳው ያሉ ማህበራት ናቸው፡፡፡
ሌላው የዲሞክራሲ መንሰራፋት ጉዳይ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ስንል የፖለቲካ ባህልን መቀየር ማለት ነው፡፡ እኛ ገና የፖለቲካ ባህላችን እየዳበረ ያለ ሀገር ነን፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በተለይ ከ97 በኋላ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ልማታዊ መንግስት ሲባል፣ መንግስት ብቻ አይደለም መስራት ያለበት። ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ህዝቡን ለማሳተፍ ደግሞ የሲቪክ ማህበራት ወሳኝ ናቸው። በማንኛውም ጉዳይ የህዝብ ተሳትፎ ሲጠናከር ነው፣ ይህቺን ሀገር ወደፊት ሊያራምዳት የሚችለው። መንግስት ወደ ህዝቡ የበለጠ ቀርቦ፣ በአገሩ ጉዳይ በያገባኛል ስሜት እንዲሳተፍ ማበረታታትና መገፋፋት አለበት፡፡

------------------

                            “ህገ መንግስትን ሁልጊዜ መንከባከብ ያስፈልጋል”
                               አቶ ክቡር ገና

      በኦሮሚያ የተደረገው የንግድ ሥራና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም አድማ አንደምታው ምንድን ነው?
 ሁሌም እንዲህ አይነት የስራ ማቆም አድማ ሲደረግ የማይበላሽ ነገር የለም፡፡ በተለይ ትራንስፖርት የሀገሪቱ የንግድ አንቀሳቃሽ ዋና ሞተር ነው፡፡ በየአካባቢው ያለው የንግድ ስራ ማቆም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የህዝቡንም ኑሮ እንደሚያናጋ ግልፅ ነው፡፡
እነዚህ አድማዎች ከግብር ትመናው ጋር ብቻ የተገናኙ ናቸው ወይስ ሌላም ሰበብ አላቸው?
በመሰረቱ ግልፅ ሆኖ የሚታየው የፖለቲካም ችግር እንዳለ ነው፡፡ የፖለቲካ ችግርን ደግሞ በጊዜ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዱ የፖለቲካ ችግሮችን በፖለቲካዊ ውይይቶች ለመፍታት ይሞክራል። አንዳንዱ ደግሞ በኃይል ለመፍታት ይሞክራል። ይሄ እንደየ ሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል፡፡ እንደ‘ኔ ግን ፖለቲካዊ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በንግግርና በውይይት መፍታት የተሻለ ዘላቂ ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡  
እንዲህ ያሉ አድማዎች መንግስት ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳርፋሉ?
እንዲህ ያሉ አድማዎች የሚደረጉት መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ መልዕክት ለማስተላለፍ ሌሎች አማራጮች ሳይኖሩ ሲቀር ህዝብ እንዲህ ያሉ መንገዶችን ለመጠቀም ይገደዳል፡፡ እነዚህ ችግሮች የመጡበትን ዋና ምክንያት ለይቶ ቀጥተኛ መልስ ካልተሰጠ ጉዳቱ ይጨምራል፡፡ አድማ የሚያደርጉ አካላትም እኮ ደልቷቸው አይደለም ሱቃቸውን የዘጉት፤ ሱቅ ሲዘጉ መቸገራቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። መሰረታዊ የሆኑ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ አሁንም ችግሩ አንድ ሳምንት ጠፍቶ ተመልሶ የሚመጣ አይነት ከሆነ፣ መሰረታዊ ችግሩ አልተፈታም ማለት ነው፡፡
በዚህ ሂደት አንዱ ከአንዱ የበለጠ ይጎዳል ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ተያይዞ ነው የሚጎዳው። ተፅዕኖው በመንግስት ላይም ቀላል አይሆንም። ፈረንጅ ሀገር የሚደረጉ አድማዎች አሉ፡፡ ግን የእነሱ ምላሽ የሚያገኝበት የራሱ ጥበብ አለው፡፡ በኛ ሀገር እንዲህ ያለው አድማ መፍትሄ ሳይሰጠው የሚደጋገም ከሆነ  ጉዳቱ ቀላል አይሆንም፡፡ አድማው በየጊዜው ያዝ ለቀቅ እያለ የሚሄድ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ተፈላጊነት ላይ ያላት ቦታ እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል፡፡
የእነዚህ አድማዎችና ውጥረቶች መደጋገም ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
ከብዙ ሰዎች ጋር ስወያይ፣ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ነው በመጨነቅ የሚናገሩት፡፡ በኔ አስተያየት፤ ከመንግስት በኩል ግን የችግሩ አሳሳቢነት ጎልቶ የወጣ አይመስልም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሚ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጣ፣ እንደገና ኃይልን መምረጥ ነው የሚሆነው። እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚመረጠው ኃይል ነው ወይስ ውይይት? ይሄ ጠርቶ መቀመጥ አለበት፡፡ ሌላ አዲስ መፍትሄም መፈለግ ያሻል፡፡  
ለምሳሌ ምን ዓይነት መፍትሄ?
እኔ እንደሚገባኝ ጥያቄዎች ግልፅ አይደሉም። እንደየ አካባቢው ብዙ አይነት ናቸወ፡፡ የመሬት ጉዳይ የሙስና፣ የሃብት ፍትሃዊ ክፍፍል የመሳሰሉ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ በየቦታው የሚነሱ ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ተጠንተው መቅረብ አለባቸው፡፡ ሀገር ማስተዳደር እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ህገ መንግስት ስላለ ብቻ ሀገር አለ ማለት አይደለም፡፡ የህዝብ ጥያቄ ተፈታ ማለት አይደለም፡፡
ህገ መንግስትን ሁልጊዜ መንከባከብ ያስፈልጋል። ጥያቄዎች በህገ መንግስት እንኳ የማይመለሱ ከሆነ፣ ሀገርን ለማዳን ሲባል ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በጥያቄዎቻቸው ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከባዱን ነገር ተጋፍጦ መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል፡፡ ዋና ዋና ጥያቄዎችን ለይቶ፣ ከህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ በመወያየት መመለስ ወሳኝ ነው፡፡ ይሄ ሊደረግ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡     

--------------------
                                      “በሀገሩ ጉዳይ የተገለለ ሰው መኖር የለበትም”  
                                         አቶ ሞሼ ሰሙ

      ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ የተደረገው የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም አድማ ተቃውሞው ማገርሸቱን ከማሳየት ባሻገር ምን?
ከአስቸኴይ ጊዜ አዋጁ በፊት የነበሩ እንቅስቃሴዎች  ወይም  አድማዎችና አሁን  የሚታዩት  ባህሪያቸው የተለያየ ነው፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን መሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር ማዕከል አድርጎ የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት፣ የሙስና፣ የመሬት አጠቃቀም፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ባሉት ከ20 በላይ አመታት ውስጥ ተወልደው፣ በትምህርት ሂደት አልፈው ለአቅመ ስራ የደረሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች አሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉበት ስራ አለማግኘታቸው አንዱ ችግር ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያ የተነሳው ተቃውሞ መንግሥት በወሰደው የማመቅ እርምጃ ሁነኛ ምላሽ ሳያገኝ በእንጥልጥል ነበር የቀረው፡፡ ይህ ችግር ባለበት ሁኔታ ደግሞ የነጋዴውን ሰርቶ የመኖር አቅም የሚፈታተን አሉታዊ የግብር ትመና መጣሉ የተዳፈነውን ተቃውሞ ቀስቅሶታል፡፡ ይሄ አጀንዳ ማቀጣጠያ ነው እንጂ ዋናው መንስኤ ለዘመናት የተከማቹ አስቀድሜ የገለፅኳቸው ችግሮች ድምር ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ለብዙ የህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ኢንዱስትሪና ፋብሪካዎችን እስከ ማቃጠል አድርሷል፡፡ ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተለመደ አይደለም፡፡ ምናልባት በፊት አውቶቡሶች ይሰበሩ ይሆናል እንጂ ህዝቡ መጠቀሚያው በሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ይሄ የቁጣው ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡
የእነዚህ አድማዎች ኢኮኖሚያዊ አንደምታዎች እንዴት ይገለጻል? በኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖስ?
ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ፡፡ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ባለመረጋጋት መሃል ባለች ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎቱ አይኖራቸውም፡፡ ሰላም በሌለበት ሀገር ውስጥ ንብረቱን ይዞ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈለግ አይኖርም፡፡ ሰላም፣ መረጋጋት፣ በቂ የኃይል አቅርቦት፣ የሰው ኃይል--- እነዚህን ፈትሾ ነው ኢንቨስተር የሚመጣው፡፡ አድማና አለመረጋጋት መኖሩን ሲያውቅ ግን ሃሳቡን ይሰርዛል፡፡ ኢንቨስተሮች ከዚህ ሽሽት ወደዚህ ሀገር ባመምጣታቸው ሊገኝ የሚችልን የውጪ ምንዛሬ ያሳጣል፣ የስራ እድል አይኖርም፡፡ ገበያውም በአቅርቦት ችግር መመታቱ አይቀርም፡፡ በተለይ የትራንስፖርት መቋረጥ በዚህ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ በሌላ በኩል፤ የሀገር ቤት ባለሀብትም በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን አስተዋፅኦ መገደቡ አይቀርም፡፡ ገንዘቡን በአገሩ ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ በውጭ ምንዛሬ እየለወጠ ወደ ውጪ ማሸሽ፣ ገንዘቡ ወደ ሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይገባ አፍኖ መያዝ፣ የራሱን የንግድ እንቅስቃሴ ማቀዝቀዝ፣ ፋብሪካ መዝጋትና የመሳሰሉት ውስጥ ይገባል፡፡ ይሄን የሚያደርገው ሀብቱ እንዳይባክን በመስጋት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በፊናው በኢኮኖሚ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚገባውን ገንዘብ ይገድባል፣ ሀገሪቱ ከውጪ ገበያ ገቢ እንዳታገኝ ያደርጋል የንግድ ተቋማትና ፋብሪካዎች በቆሙ ቁጥር ለኪሳራ መዳረጋቸው አይቀርም፡፡ በዚህ ደግሞ መንግስት ከግብር የሚያገኘውን ገቢ ያጣል፡፡
ሌላው ደግሞ ማህበረሰቡ በቁጣ ተነሳስቶ የሚያደርሰውን ውድመት ተከትሎ፣ መንግስት ንብረቱን ለባለቤቶቹ የመተካት ግዴታ አለበት፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሀገሪቱ ለኩባንያዎች አለማቀፍ የኢንሹራንስ ሽፋን የላትም፡፡ ይህ አለመኖሩ ደግሞ መንግስት ለወደመ ንብረት ከበጀቱ ላይ ቀንሶ ለተጎጂዎች እንዲከፍል ነው የሚያስገድደው፡፡ ሌላው በዚህ ሂደት ውስጥ እንዲህ ያሉ ውጥረቶች ያለ መፍትሄ በተራዘሙ ቁጥር በማህበረሰቡ ውስጥ ግንኙነቱ ይላላል፣ አንድነቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፣ ሰዎች ተስፋ በመቁረጥ ስደትን አማራጭ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ችግሮቹ  በጊዜ እልባት ካላገኙ በሰው ልብ ውስጥ ተቀብረው የሚፈነዱበትን የተመቻቸ ሁኔታና ጊዜም ሊጠብቁ ይችላሉ፡፡
በዚህ ግርግር መሃል ደግሞ በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ሰዎች ገበያ ላይ ያሉ እቃዎችን ይደብቃሉ፣ በገበያው ላይ እጥረት ለመፍጠር ይሯሯጣሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በህብረተሰቡ ላይ የገበያ እጥረት ይፈጥራል፤ የዋጋ ንረትም ያስከትላል፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ የቱሪዝም ገቢያችን ይቀዛቀዛል፡፡ ጎብኚዎች ቅድሚያ ለህይወታቸው ደህንነትና ሰላም ይፈልጋሉ፡፡ ቱሪስቶች ባለመምጣታቸው ደግሞ በዘርፉ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ይጎዳሉ፡፡
አገሪቱ ለውጭ ኢንቨስተሮች  አለማቀፍ ኢንሹራንስ መግባት ያስፈልጋታል ማለት ነው?
ኩባንያዎች ላይ ጉዳት የሚደርሰው በተቃውሞ በሚፈጠር ቀውስ ብቻ አይደለም፡፡ በየጊዜው የክልል ድንበር ግጭቶች፣ የብሔር ግጭቶች የመሳሰሉ ይፈጠራሉ፡፡ በዚህ መሃል ንብረት ሊወድም ይችላል፤ የውጭ ሀገራት ሰዎች ንብረት ሲወድም በሀገር ውስጥ ኢንሹራንስ ለመሸፈን ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ሀገር ኢንሹራንስ መኖሩ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች አደጋ በንብረታቸው ላይ ቢደርስ፣አለማቀፍ አስተማማኝ ኢንሹራንስ እንደተገባላቸው ሲያውቁ ይረጋጋሉ፡፡ እንደ አንድ ሁነኛ ዋስትና ነው የሚቆጥሩት፡፡ ይህ ባልሆነበት ለእነዚህ ሰዎች ለንብረታቸው መተኪያ ስትከፍል ዞሮ ዞሮ የህብረተሰቡ ኪስ ነው የሚጎዳው። ለመሰረተ ልማት ይውል የነበረውና ከሰው የተሰበሰበው ግብር ነው ተመልሶ ለነዚህ ሰዎች የካሳ ክፍያ የሚውለው። ከዚህ ውጭ  መንግስት ያለ አግባብ ተጨማሪ ገንዘብ ካላተመ በስተቀር ከየትም አይመጣም፡፡
በእንዲህ ያሉ አድማዎች የመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆነው ማን ነው? መንግሥት ላይ የሚፈጥረው ጫናስ ምን ያህል ነው?
ሁለት የማህበረሰብ ክፍሎች በጣም ተጎጂ ይሆናሉ፡፡ አንደኛ ለእለት ጉርሳቸው በየእለቱ የሚያገኙትን ገቢ የሚያጡ ዜጎች አሉ፡፡ በሸክም ስራ፣ በጥበቃ፣ በጫኝ አውራጅነት የሚሰሩ፣ የእለት ገቢ ላይ ብቻ ተመስርተው የሚኖሩ አሉ፡፡ እንቅስቃሴዎች ሲቆሙ እነዚህ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ተጎጂዎች ይሆናሉ፡፡ ሁለተኛ በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ተጎጂ ይሆናል፡፡ አብዛኛው ሰው ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በአቅርቦቱ መቋረጥ የእለት ጉርሱን የሚያጣው የማህበረሰብ ክፍል ቀላል አይደለም፡፡ ሶስተኛ ተጎጂ የሚሆነው ሀገር ነው፡፡ መንግስት ተገቢውን ግብር የማግኘት እድሉን ስለሚያጣ ስራ መስራት አይችልም፡፡ እንቅስቃሴ የሌለበት ኢኮኖሚ ደግሞ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ ከፍተኛ አለመረጋጋትም ያስከትላል፡፡
የእነዚህ አድማዎች ፖለቲካዊ አንድምታስ ምንድን ነው?
እነዚህን አድማዎች በመጀመሪያ ያመጣው ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ያለው መተማመን መሸርሸሩ ነው፡፡ መንግስት ለጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ፣ ለህዝባዊ እምቢተኝነት ወይም ለአድማ አይነሳሳም፡፡ መንግስት ቦታ እያጣ መምጣቱን ማሳያው ይኸው ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው፡፡ አንድ ማህበረሰብ በራሱና በቤተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት መሆኑ  ግልፅ ነው፡፡ የስራ እድል የፈጠረለት ተቋም ላይ እርምጃ ሲወስድ ተስፋ የመቁረጥ ምልክት ነው፡፡ አሁን ከግብር ጋር በተያያዘ የመጣው እምቢተኝነት፣ የመጀመሪያው እምቢተኝነት ተቀጥላ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ አመት ምን እንደሚፈጠር ለመገመትም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ የተጣለው ግብር ከ40 በመቶ በላይ ስህተት ነበር ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ 40 በመቶ ስህተት ካለ፣ ለእርማትም የሚመች አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወዲያው ነው መቆም የነበረበት፡፡ እንደገና እንደ አዲስ ነው ጉዳዩ መታየት ያለበት፡፡ በዚህ ምክንያት ለተፈጠረው ምስቅልቅል፣ ቁጣ እና አለመረጋጋት ኃላፊነትስ የሚወስደው ማን ነው? መንግስት ትመናው 40 በመቶ  ስህተት አለው ብሎ ካመነ፣ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡
እነዚህ አድማዎች በመንግስት ለይስ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
ህዝቡ መጀመሪያ የሚያደርገው እነዚህ በደሎችና እሮሮዎችን ማሰማት ነው፡፡ ለእነዚህ ምላሽ ሲያጣ ደግሞ ተደራጅቶ በአንድ ላይ ወጥቶ መንግሥት ላይ ግፊት ይፈጥራል፡፡ ጉዳዩ ወደ ዲሞክራሲ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ የህግ የበላይነት ጥያቄዎች ሊያመራ ይችላል፡፡ ይሄን ደግሞ ህዝብ በራሱ እንዲከውነው እየተገደደ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ሊወክሉት የሚችሉ ኃይሎች፣ አጀንዳውን ተቀብለው ማስተናገድ ላይ ውስንነት አለባቸው፡፡ ይሄ እንግዲህ ችግሩ ምን ያህል መልኩንና ቅርፁን እየለወጠ እንደመጣ ያሳያል፡፡ ህዝብ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ሁኔታው አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች በፊት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም በፕሬሶች ነበር የሚነሱት፡፡ እነሱ በየጊዜው እየተመናመኑ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ፣ ህዝቡ ትግሉን ራሱ ለመውሰድ ተገደደ፡፡ ይሄ ፖለቲካዊ አንድምታው ቀላል አይደለም፡፡ ልክ እንደ አፄው ሥርአት ጊዜ ፋታ … ትንሽ ፋታ በማለት ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ ችግሮች በፋታ የሚፈቱ አይመስልም፡፡
ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄው ምንድን ነው?
አጭሩ መፍትሄ ትክክለኛውን የህዝብ ስሜትና ጥያቄ አውቆ፣ ለዚያ የሚመጥን መልስ መስጠት ብቻ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ሁሉ የውጭ ኃይሎች ሴራና የፀረ ሰላም ኃይሎች ነው ብሎ ችላ ማለት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መቼም ህዝብ አይሳሳትም። በዚህ ደረጃ በውጪ ኃይሎች የተሳሳተ ህዝብ አለ ከተባለም፣ ለስህተቱ ተጠያቂ የሚሆነው መንግስት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስት ለህዝቡ ተስፋ የሚሰጥ ስራ አልሰራም ማለት ነው፡፡ ሌላው መፍትሄ ከህዝቡ ጋር መወያየት ነው፡፡ ጊዜ ለሁሉም ነገር ወሳኝ ነው፡፡
በጊዜ መልስ መስጠትና ማረሚያ መውሰድ ከፀፀት ያድናል፡፡ ይሄ ጉዳይ ለሥርአቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱም አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ በሀገሩ ጉዳይ የተገለለ ሰው መኖር የለበትም፤ በሀገሩ ጉዳይ ማንም ሰው የመገለል ስሜት እንዲሰማው መደረግ የለበትም፡፡

Read 4889 times Last modified on Saturday, 16 September 2017 11:11