Saturday, 02 September 2017 00:00

6ኛው ክፍለ ዘመን - ሥር ነቀሉ የባህል ለውጥ!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

 “ደምፀ እገሪሁ ለዝናም” - የዝናብ እግሩ ተሰማ!!
                                 ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)

      እስቲ ዛሬ ደግሞ የሥነ ፅሁፋችን፣ የኪነ ጥበባችንና የፍልስፍናችን መነሻ ዘመን ስለሆነው ስለ 6ኛው ክፍለ ዘመን እናውራ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተስተካካይ የሌለውና የሀገሪቱን ቀጣይ መፃዒ ዕድል በመወሰን ረገድ 6ኛው ክፍለ ዘመንን የሚያክል የለም፡፡ 6ኛው ክ/ዘ ላይ የታየው የአዲስ ባህል መወለድና የነባሩ አክሱማዊ ባህል መዳከም፣በዋነኛነት ከ9ኙ ቅዱሳን መነኮሳት መምጣት (ከባህል ግጭት) ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ዘመን ላይ የተጀመረው አዲሱ የምንኩስና ባህል ለሚቀጥሉት 1400 ዓመታት ያህል፣የሀገሪቱ ባህልና የህዝቡም የዕለት ተዕለት ሕይወት ሆኖ ዘልቋል − የሀገሩ፣ የህዝቡና የሃይማኖቱ ጠባቂ የሆነው ንጉሳዊ የዘውድ ሥርዓት እስከተገረሰሰበት እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ፡፡ እስቲ እነዚህን ነገሮች በየተራ እንመልከታቸው፡፡
የነባሩ አክሱማዊ ባህል መውደቅና አዲስ የባህል ውልደትና ዕድገት
6ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው አጋማሽ ቁሳዊው የአክሱም ሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ወቅት ነው፡፡ ይሄም የሚገለፀው በቁሳዊ ሐብቱ በጣም የበለፀገው የአክሱም መንግስት፣ በአፄ ካሌብ ዘመን ኃያልነቱን ደቡብ አረቢያ ድረስ ማስከበሩ ነው። 6ኛው ክ/ዘ ሁለተኛው አጋማሽ ግን የነገስታቱም ሆነ የማህበረሰቡ አመለካከት ከምድራዊ ብልፅግና ወደ መንፈሳዊ ጭምትነት መቀየር የጀመረበት ዘመን ሆነ፡፡ ይሄም በአክሱም ሥልጣኔ ላይ ሁለት ውጤቶች ነበሩት። የመጀመሪያው፣ የቀይ ባህሩ የንግድ መስመር በ578 ዓ.ም በፐርሺያኖች ሲነጠቅ ለማስመለስ አለመሞከራችን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የእጅ ሙያዎችና ለዓለማዊ ህይወት ብልፅግና መጣር የተንቋሸሸበት፣ በአንፃሩ ደግሞ ምንኩስናዊ የዓለም አመለካከት ገዥ ሐሳብ ሆኖ የወጣበት ዘመን ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች “ምድራዊ የበላይነትን መጎናፀፍ“ በሚል መርህ ላይ የቆመው አክሱማዊው ባህል መዳከም የጀመረበት ዘመን ነው - 6ኛው ክ/ዘ።
የ9ኙ ቅዱሳን መምጣትን ተከትሎ፣በ6ኛው ክ/ዘ ላይ የታየውን የአዲስ ባህል ውልደትና ዕድገት በሁለት ዘርፎች መጥቀስ ይቻላል፤ እነሱም በአንድ በኩል የሥነፅሁፍና የኪነ ጥበብ ውልደትና ዕድገት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምንኩስና ባህል መጀመርና መስፋፋት ናቸው፡፡ 9ኙ ቅዱሳን ከእነ ተከታዮቻቸው የተለያዩ መፃህፍትን ይዘው በመምጣታቸው፣ 6ኛው ክ/ዘ በርከት ያሉ ሃይማኖታዊ መፃህፍት ወደ ግዕዝ የተተረጎሙበት ዘመን ነው፤ ለምሳሌ መፅሐፍ ቅዱስ፣ መፅሐፈ መነኮሳት፣ የቄርሎስና ሌሎች የታወቁ የአበው የተግሳፅ፣ የቅዱሳናትና የሰማዕታት ድርሳናት ወደ ግዕዝ እየተተረጎሙ፣ለየአድባራቱ እንዲዳረሱ ተደርገዋል፡፡ በየትኛውም ዓለም ላይ የማይገኙ እንደ መፅሐፈ ሔኖክ ያሉ ተጨማሪ 15 የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው የመጡት 9ኙ ቅዱሳን ናቸው፡፡
ከኪነ ጥበብ አንፃር ካየነው ደግሞ፣ 6ኛው ክ/ዘ ቅዱስ ያሬድ የተነሳበትና በቅዱስ ያሬድም አማካኝነት የቤ/ክ የውዳሴ፣ የቅዳሴና 3ቱ የዝማሬና የዜማ ስልቶች (ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ) የተደረሱበት ዘመን ነው፡፡ ፕ/ር ስርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ቅዱስ ያሬድን “የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትምህርት መስራች ነው“ ይሉታል፡፡ 6ኛው ክ/ዘ ጠንካራ የባህል መሰረት መያዙን የምንረዳው፣ አዲሱ ባህል በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የራሱን ዜማና የቤ/ክ ሥርዓት መፍጠር መቻሉ፣ እንዲሁም የራሱ የሆነ የሥነ ስዕልና ከሶሪያ ጋር የሚመሳሰሉ የኪነ ህንፃ ዘዴዎችን መፍጠሩ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች 6ኛው ክፍለ ዘመን፣ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሥነፅሁፍና የኪነ ጥበብ ዘመን ተብሎ ይጠራል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ድምፅን ወደ ፅሁፍ (ድርሰት) የቀየረ የዓለማችን የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ስለ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ይላሉ፡-
ለቅዱስ ያሬድ ይህ ዓለም በመላ ልክ እንደ አንድ ትልቅ ማህሌት (ሲንፎኒ) ነው - ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት በዜማ የሚያመሰግኑበት ሲንፎኒ፡፡
ይሄም ማለት ቅዱስ ያሬድ ተፈጥሮን የሚገነዘበው በቀለሙ፣ በልስላሴው አሊያም በቅርፁ ሳይሆን በድምፁ ነው – ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት ዜማው ነው፡፡ ለዚህም ነው “ደምፀ እገሪሁ ለዝናም” (የዝናብ እግሩ ተሰማ) ያለው – ዜማን ከዝናብ ድምፅ ፈልቅቆ ሲያወጣ!! የ6ኛው ክ/ዘ ባህል እንደዚህም ዓይነት አስደናቂ ሰው ፈጥሯል፡፡
የምንኩስና ባህል መጀመርና
መስፋፋት (የላሊበላዊነት ዘመን መጀመር)
ከ6ኛው ክ/ዘ በፊት በአክሱማውያኑ ላይ ፈፅሞ ያልታየ፣ ሆኖም ግን ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ በጣም እያደገ የመጣ አዲስ አመለካከትና ባህል ህዝቡ ውስጥ መፈጠር የጀመረበት ወቅት ነው፡፡ ይሄውም በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወት መካከል ቅራኔ መፈጠር የተጀመረበትና ይሄም ቅራኔ እያደገ የሄደበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ቅራኔ ነው እንግዲህ የሀገሪቱንና የህዝቧን ቀጣይ እጣ ፋንታ የወሰነው። በዚህም  ምንኩስናዊ በሆነው አዲስ ባህል የተነሳ አጠቃላይ ህዝቡ በመንፈሳዊ ህይወት እያደገ ሆኖም ግን በቁሳዊ ሐብቱ እየደኸየ የሄደበት፣ ግሪክና ህንድ ለንግድ መመላለሱ ቀርቶ እየሩሳሌምን ለመሳለም የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በጣም ከፍ ያለበት፣ በሃይማኖታዊ ዕውቀቱ እየተራቀቀ ሆኖም ግን በዓለማዊ ዕውቀቱ እየደነቆረ የሄደበት፣ በፆምና በጸሎት እየበረታ ሆኖም ግን በእጅ ሙያዎች እየዘቀጠ የሄደበት የተቃርኖ ዘመን ነው፡፡ ይሄንን ነው ላሊበላዊነት የምንለው፡፡
የምንኩስና ህይወት ወደ ሀገራችን የገባው በ9ኙ ቅዱሳን መነኮሳት አማካኝነት በ5ኛው ክ/ዘ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ (460−472) ዘመን ቢሆንም ምንኩስናዊ ህይወትና የዓለም አመለካከት የተስፋፋውና የህዝቡ ባህል ሆኖ የወጣው ግን 6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ነው፡፡ ነገሥታቱ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እየተው መመንኮስ የጀመሩበት ወቅት ነው - 6ኛው ክ/ዘ፡፡
ከዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት (ከዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ) እስከ አፄ እለ ገበዝ (የአፄ ገብረ መስቀል ልጅ) 591 ዓ.ም ድረስ ያለውን ዘመን ብንቆጥር 130 ዓመታት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከነገሱት አምስት ነገስታት (ዳግማዊ እለ አሚዳ፣ ታዜና፣ ካሌብ፣ ገብረ መስቀልና እለ ገበዝ) ውስጥ አራቱ ሥልጣናቸውን ትተው መንኩሰዋል፡፡ ይሄም የሚያሳየው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአክሱምና በአካባቢዋ ላይ የምንኩስና ህይወት ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ነው፡፡
ነገስታቱ ከሥልጣን ገናናነት ይልቅ ግላዊ ነፍሳቸውን ለማዳን ያደረጉት ሩጫ፣ ለህዝቡ ትልቅ መልዕክት ነበረው፡፡ የምንኩስና ህይወት ከእምነት አልፎ ለህብረተሰቡ ዓለምን መመልከቻ መነፅር ለመሆን የበቃው ነገስታቱ ከዓለማዊ ድሎት ይልቅ የምንኩስና ህይወትን ሲመርጡ መታየታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ምንኩስና ከእምነት ወደ ባህልነት ሰፋ፡፡ ምንኩስና የተመረጡ ጥቂቶች የሚኖሩበት እምነት ከመሆን አልፎ ህዝቡ ገዳም መግባት ሳያስፈልገው በየዕለቱ የሚኖረው ህይወት ሆነ፡፡
በዚህም ዓለምን የሚጠየፍ፣ ስጋዊ ህይወትን የሚያንቋሽሽ፣ “እኔ የምድር ቆሻሻ ነኝ!” የሚል ህብረተሰብ ተፈጠረ፡፡ እንኳን የስራ መሳሪያዎችን ሊያሻሽል ይቅርና በአክሱማዊነት ዘመን እንኳ የነበሩትን ጥበቦችና የእጅ ሙያዎች ማስቀጠል የማይችል ማህበረሰብ ተፈጠረ፡፡ ጭራሽ ከዚህ በተቃራኒ ለዓለማዊ ብልፅግና መጣር እንደ ከንቱ ድካም ተቆጠረ፤ ግንበኝነት፣ አናጢነት፣ ቀጥቃጭነትና ሌሎችም የእጅ ሙያዎች ከመከበሪያነት ወደ መሰደቢያነት ተቀየሩ፡፡ በ6ኛው ክ/ዘ፣ ከአክሱማዊ ባህል ወደ ላሊበላዊ ባህል ያደረግነው “ሽግግር” ላይ የተፈጠረው ማህበረሰባዊ ቀውስ ነው፣ ለ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍና መወለድ (ለእነ ዘርዓያዕቆብ መነሳት) ምክንያት የሆነው፡፡
6ኛውን ክ/ዘ በመንፈሳዊ ከፍታው ዶ/ር እጓለ፣ የ“ያሬዳዊ ሥልጣኔ” መነሻ ሲሉት፤ ባስከተለው የዓለማዊ ህይወት ድንዛዜ ደግሞ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ”የብሕትውና ዘመን ጅማሮ” ይሉታል፡፡ የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን ”የአክሱማዊነትና የላሊበላዊነት” ወግ የምናገኘውም እዚህ ዘመን ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች 6ኛው ክ/ዘ፣ ለኢትዮጵያ ፍልስፍናም ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡
(ሰሞኑን ለገበያ ከቀረበው
”የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ የተወሰደ)

Read 4745 times Last modified on Saturday, 02 September 2017 12:17