Sunday, 03 September 2017 00:00

የቄሳር መንፈስ በ“ታላቁ ተቃርኖ” መጽሐፍ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     ሀብታሙ አለባቸው፣ ዛሬም ብዕሩንና ብራናውን አጣምሮ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመቃኘት ሞክሯል።  ቅኝት በመቃኘት ይታዘዛል። ጥሩ ቃኚ፣ ጥሩ ዜማን እንደሚያወጣ እሙን ነው፡፡ ሀብታሙ በቅኝቱ ጥሩ ዜማን አውጥቶ ይሆን የሚለው እንደ አድማጮቹ የሚወሰን ነው፡፡ በበኩሌ ያልተደፈረውን የቤተ መንግስት ጓዳ፣ ያልተደፈረውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና ያልተለመደውን የኢህአፓ ዘመን ድብብቆሽ ባለፉት ስራዎቹ ለመቃኘት መሞከሩን ወድጄለታለሁ፡፡
ዛሬ በወፍ በረር ለመቃኘት የፈለግሁት “ታላቁ ተቃርኖ” የተሰኘውን ስራውን ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን መጽሐፍ ለማሔስም ሆነ ጥናታዊ ዳሰሳ ለማድረግ አቅሉም አቅሙም ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሆኖም እንደ አንባቢና በአገር ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ/ለመጠየቅ/ እንዲሁም የግል አስተያየትን መስጠት የተፈጥሮ መብትና/ግዴታ ከመሆኑ አንጻር፣ ስለ መጽሐፉ ጥቅል ሐሳብ የተሰማኝን ለማስቀመጥ  ነው፡፡
በበኩሌ የምስማማበት ጉዳይ (ከሌሎች ጋር አለመስማማት እንዳለ ሆኖ) የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ችግር ከአንድ ነጠላ መንግስት እና “ሬዥም” ጋር ማያያዙ የውድቀታችን መነሻ ነጥብ ነው፡፡ በዚህም አግባብ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያ፣ ታሪክ ማጠንጠኛ “የትክተት ነጥብ” ሆነው ሲወሰዱ፤ ልንወጣው ወደማንችልበትና ሸክማችንን የሚያበዙ ጋሬጣዎችን ይሰበስባሉ። ሌላኛው አስከፊ ችግር ጋሬጣዎች መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ጋሬጣውን የምናስወግድበት እሾኩ ላይ ይሆናል፡፡
ሀብታሙ አለባቸው፣ የዚህ ምሳሌ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡ በመጽሐፉ ሽፋን፣ የመሃል ኢትዮጵያንና የሰሜን ጫፍ ድንበርን እንደ መነሻ በማድረግ፣ “ታላቁ ተቃርኖ”ን በማመልከት፤ “አጼ ምኒልክ ሠርተውት ያለፉት ነገር በትክክል ምንድን ነው?” ሲል የአጼ ሚኒልክን ምስል አስቀምጦ፣ይጠይቃል፡፡ በእርሱ አተያይና ጥልቅ ምርምር፣ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የተገለጸው ወይም የተጠቀለለው በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስትና ከዚህ ወዲህ ነው ማለት ነው፡፡
ይህን መሰል የምሁራን ቅኝት (ቅዠት ላለማለት)፤ ከ1960ዎቹ የምዕራባዊያንና የምስራቁ ዓለም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውዥንብር በፈጠራቸው አስተሳሰቦች (የያ ትውልድ አባላት) ኢትዮጵያን ቀርጸው (የፈጠሯት እስኪመስል ድረስ) የዘመናችንን ትኩሳትና የወደፊት እጣ ፈንታችን በየመቶ አመት ታሪክ ብሂል ውስጥ ይቀብረናል። ይህ በራሱ የታላቁ ተቃርኖ አንኳር መነሻ ነው፡፡ (በኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ የክርክር ሐሳብ፤ እነ ዮሐንስ አድማሱን፣ እሸቱ ጮሌን፤ ፈቃደ አዘዘንና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ተችተው የተነሱበትን ዘመን ያስታውሷል)
የፖለቲካ ድንበርና የአገርን ማስተዳደር ቅርጽ፣ መልኩን ቀይሮ፣ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በተስፋፋበት ዘመን ላይ ቆመን፤ መፍትሄም ይሁን የጥናታችንን ዛቢያ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ሆነን ስናንዣብብ “የታላቁ ተቃርኖ” መነሻም መድረሻም እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ “የኤርትራ” ችግር እና “የደቡብ ቅራኔ” በምኒልክ መጀመሩን እንደ ፖለቲካዊ ትንታኔ አድርጎ መነሳት፣ የሃብታሙ አለባቸውና የመሰሎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ውድቀት መሆኑ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ (የግል እይታዬ) ነው፡፡
የዳዕማት ሥልጣኔ አንድምታው ምንድን ነው? የአሁኑ ትውልድ ምን ያህል ያውቀዋል? የአክሱምን ሥልጣኔ ማን አቆመው?  ማን መራው? ማን ማን ገበረ? የትኛው ሕዝብ በየትኛው ህዝብ ትስስሩን ፈጠረ? በምን መንገድ ከየት ወደየት? ሕዝብ በምን ተለያየ? በምን ተሳሰረ? የዛጉዌ ሥልጣኔ ከየት የት ይደርስ ነበር? የውጭው ዓለም በወቅቱ በምን መልኩ ይረዱት ነበር? በዚህ ወቅት የደቡቡ ይዞታ በምን መልኩ ይተሳሰር ይተዳደር ነበር?
የመካከለኛው ዘመን የይኩኖ አምላክ መንግሥት፤ ከደቡቡ ጋር የነበረው ትስስር? የሸዋ ነገሥታትና ቀሪው ማሕበረሰብ የነበራቸው ገጽ፤ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ሶማሌ ድንበር ድረስ ሄደው የገነቡት ልማት፣ ጥፋት፣ የትዳርም ይሁን የማስገበር/የመገበር ታሪካችን፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እስከ ቀይ ባሕርና ህንድ ውቅያኖስ ወይም የአፍሪካ ቀንድ ጫፍ መታየት፤ የልብነ ድንግል ንጉሳዊ ስም አጠራር በራሱ የሚሰጠው ትርጓሜ፤ የምስራቁ ዘመቻ ወደ ሰሜን ያመጣው ለውጥ፤ ለምላሹም የተሰጠው አጸፋ (አሉታዊም አዎንታዊም የአገር ግንባታ ሂደት...)
የእነ ሰርጸድንግል ታሪክ፤ የጎንደር ነገሥታት ከደቡቡ በተለይም ከኦሮሞው ሕዝብ ጋር የነበራቸው ትስስር፤ የየጁ መሳፍንት በጎንደር ዘመን የነበራቸው ሚና፣ ኦሮምኛ በጎንደር የነበረው ቦታ፤ ባሕረነጋሽ/ኤርትራ የነበረችበት ሁኔታ (ይዞታ)፤ የአጼ ቴዎድሮስ አነሳስ፣ ዘመኑ የጠየቀው መስፋፋት ምክንያት፤ ለምን አጼ ቴዎድሮስ? በዘመኑ የነበረው የግዛት አወሳሰን እንዴት ይገለጽ ነበር? ነው ወይስ “አቢሲኒያ”ን ቀርጸን ማነብነብ ይቀልለናል? …
(እዚህ ላይ ትልቅ የሚዘነጋ ሐሳብ ይታየኛል፤ ይሄውም የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ከታቢና ምጡቅ ግለሰብ አለቃ ዘነብ፣ የኦሮምኛን ቋንቋ ማጥናታቸው፤ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ ለመተርጎም ማሰባቸው፤ አስበውም መተግበራቸው በምን መልኩ የሚታይ ነው?)
በአጼ ዮሐንስ ዘመን መባቻ ላይ የተደረገው የባዕዳን ወረራና ተጽዕኖ፤ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ለምን?  የባሕረ ነጋሽስ ይዞታ፤ የሂወት ውል፤ የምዕራባዊያን ቅኝ ግዛት ዘመቻ፤ የፖለቲካ አስተሳሰብ ዘመቻ፤ የመንግሥታት ትብብር ሐሳብ፤ የዘመናዊነት ትርጓሜ፤ … ወዘተ እንዲህ እንዲህ እያልን ጥናታዊ ምርምር፤ የታሪክ ጥናት የሚጠይቀውን መነጽር እየተጠቀምን፣ “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ሐሳብ እያላወስን፤ የኢትዮጵያን ችግር ነቅሰን እናውጣ ቢባል፣ አዕምሮዬንም ሆነ ስሜቴን የሚገዛ ጭብጥ የማገኝ ይመስለኛል፡፡
ዋናው ሀብታሙ አለባቸውን የምሞግትበት ነጥብም ይሄው ነው፤ ከእነዚህ ጭብጦች ውስጥ ነበር የአጼ ምኒልክን ቦታ ፈልቅቀን በማውጣት፣ ወዳለንበት ደረጃ ደርሰን፣ ተቃርኖንም ይሁን የግጭት መንስኤዎችን አልያም ስኬቶችን ልንገልጽ የምንገደደው፡፡ ከአንድ ትልቅ ሰፌድ ውስጥ አንዱን ሰንደዶ አውጥቶ፣ የሰፌዱን ሕልውና አድርጎ መውሰድ፣ በሰፌዱና በሌሎች ሰንደዶዎች ላይ የሚሰራ ደባ ሆኖ መታሰቡ አይቀሬ ነው! ኤርትራ ከምኒልክ በፊት የኢትዮጵያ ግዛት የሆነችበትና ያልሆነችበት ጊዜ በታሪክ ተፈትሾ ሲጠና፤ የደቡቡን ይዞታና ትስስር ቅድመ ታሪክ ጥናት ሳናደርግ፤ ምኒልክን መነሻም መድረሻም ማድረጉ ትልቅ የታሪክ ሸፍጥ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ምኒልክ ሳይፈጠሩ ኤርትራ የነበረችና ለበርካታ ነገስታት የድልም የውድቀትም የስኬትም የክሽፈትም ማጠንጠኛ ሆና የዘለቀች በመሆኗ፤ “ኤርትራ” “ኤርትራ” የምንለው የምዕራባዊያኑ እርኩስ መንፈስ ወርሶን ለመግባቢያነት የምንጠቀምበት የቦታ ስም ብቻ ሳይሆን ለውድቀታችን የተበተብነው የቄሳሩ መንፈስ አዚም /አዙሪት/  ነው፡፡ ደቡቡንም በመቶ አመት ውስጥ የተፈጠረ መልክዓ ምድራዊ ይዞታ እስኪመስል ድረስ፤  ስለ ሺሕ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት እያወራን ቦታና የሕብረተሰብን ፍልሰት ሳናጤን፤ የጥንቱን ስያሜ በዘመነኛ “ሰካራም” ስያሜ እየሰጠን፤ በአሁኑ ትርጉምና ዘመን አመጣሽ መቀመርያ መመዘን፤ የውድቀታችን መነሻና የታላቁ ታቃርኖ ክስተት መደምደሚያው/መፈጸሚያው/ ነው፡፡
ሀብታሙ አለባቸው፣ በመጽሐፉ በርካታ የአገር ውስጥ እና የባዕዳንን ስም እየጠቀሰ፤ የሐሳብ ክርክሩን ለማጠናከር ሲሞክር እናስተውላለን። የምሑራኑን ሐሳብም እየጠቀሰ፣ ለ“ታላቁ ተቃርኖ” መፍትሄ ‹‹ፋይዳ የሌለው›› እና ‹‹ያለው›› እያለ ሲገልጽ እናስተውላለን፤ በተለይም ከአገር ውስጥ ገብረሕይወት ባይከዳኝንና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ማስተዋላችን አልቀረም፡፡
በበኩሌ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ባሕልና ፖለቲካ ትንታኔ አረዳድ በአንድ እና በሁለት መጽሐፎቻቸው ዙሪያ ብቻ በማተኮር፣ አጠቃላይ ሐሳባቸውን መተቸቱም ሆነ መፍትሄ የለውም ብሎ መነሳቱ  ጸሐፊውን ያስገመግመዋል ባይ ነኝ፡፡ “አዳፍኔ” ይህንን አላስቀመጠም ብሎ ወደ ፍረጃ መሄድ ጸሐፊው የተልዕኮ ማስፈጸሚያ አንደበት መያዙን ያሳብቅበታል፡፡ (አንባቢ ሆይ፤ በሀብታሙ አለባቸው መጽሐፍ ውስጥ ከበርካታ ምሁራን ሐሳቦች ከመጡ መደምደሚያዎች አንጻር፤ “መስፍን ወልደማርያም በዘመናቸው ያልጠቀሱት ሐሳብ (መፍትኄ) ይሄ ነው” ብሎ የሚያሳየኝ ሰው ካለ፣ ለመቀጣት ዝግጁ ነኝ! - ፕሮፌሰሩ ከጻፏቸው መጽሐፍት ውስጥ እንደ ዋቢ የጠቀሳቸው ከሶስት አለመብለጡን ያጤኗል!)
መጽሐፉ የበርካታ ምሁራንን ሐሳቦች በቁንጽልም ቢሆን መያዙ ምሁራኑ ተሰባስበው እንዲመካከሩበትና እንዲወያዩበት፣ የኢትዮጵያን ትልቁን ቁልፍ ችግር ለመያዝም ሆነ የተዘጋብንን ደንቃራ አስተሳሰብ ለመክፈት፤ ብሎም ቁልፉን ለእያንዳንዱ ዜጋ ሰጥቶ ወደ ብርሃናማው “የታሪክ አቅጣጫ” እንድንዘልቅ ለማድረግ ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ጸሐፊው፣ ለመማርም ይሁን ለመታረም ዝግጁነቱን ሲያሳይና በአካለ መንፈስ ሲገኝ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
መጽሐፉን በተደጋጋሚ እየተመለስኩ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምርምራዊ ሂደትን ለመከተል የታሰበ ከመሆኑ አንጻር አሁንም ልዩ ትኩረትና አንጽንዖት ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ እንደ መቋጫ ሁለት ነጥብ ብቻ ላንሳ፡፡ አንደኛ፤ የኔ የአስተሳሰብ አድማስ ልኬት በእጅጉ የተወሰነ መሆኑን ወይንም በሌላኛው ጎን የጸሐፊው ሐሳብ በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ዙሪያ አዲስ አስተሳሰብን ይዞ ስለመጣ ለመረዳት አዳግቶኛል፡፡ በበኩሌ ጸሐፊው (ለእኔ) ይህንን የፈጠረበት ምክንያት  ምንድን ነው ብዬ ሳስብ አንዳንድ ነጥቦችን ማስቀመጥ ይኖርብኛል። በተቻለኝ መጠን በማሳጠር በሦስት ነጥቦች ብቻ ላጠቃልል፡፡
የኢትዮጵያን ችግር ከአጼ ምኒልክ ጋር አቆራኝቶ በመነሳቱና የመፍትኄ ሐሳቡንም እዚያው ዙሪያ በማድረጉ፣
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የባዕዳን ተልዕኮና ጫና ራሱን የቻለ ሰፊ ቦታ ያለው ቢሆንም ጸሐፊው ጥናቱን በዚያ ላይም ባለማድረጉ፣
አሁንም በምሁራን እይታ ይቀርቡ የነበሩ ቃላትንን ለምሳሌ፤ ብሔር፣ አገር፣ ሐገረ መንግስት፣ ስልጣኔ፣ ባሕል፣ መንግስት ሬዥም…. ወዘተ መሰል ቃላትን አጠቃቀማቸውን ከእነ ልዩነታቸው ለማስረዳት ቢሞክርም በተለያዩ ገጾች ላይ ግን ራሱ ሲዳክርባቸው መመልከታችን አልቀረም።
ሶስቱን ነጥቦች በመያዝ ሌላ አንድ ረዥም ትንተና የሚያስፈልገው ጽሑፍ ማሰናዳት ይቻላል፡፡
ለማጠቃለል ግን፣”ታላቁ ተቃርኖ” በባዕዳን አስተሳሰብ የተቃኘ የምሁር እይታ መሆኑን መካድ አልችልም፡፡ የገብረህይወት ባይከዳኝ ሐሳቦች ላይ አተኩሮ ሚዛኑን እሱ ላይ መድፋቱን ሲገልጽ እናየዋለን፡፡ የሌሎች ባዕዳን አስተሳሰቦች/ጥናታዊ እይታ/ ከውስጣዊ ታሪካችን ጋር እያነጻጸሩ ለመግባቢያነት መቀመጡ፣ በተደጋጋሚ ውስጤን ኮርኩሮታል፡፡ የበርካታ ምሑራንን ሐሳቦች፣ ጥናታዊ ስራዎችና የምርምር ውጤቶችን ጠልቆ ገብቶ ዋኝቶ በመውጣት - የ”አዕምሯዊ ጅምናስቲክ” ጽሁፍ  እንዳይሆን ጸሎቴን አድርሼ፤ በመጽሐፉ ዙሪያ የወጡ አስተያየቶችን ለማንበብም ሆነ ለመሳተፍ ዝግጁነቴን ጀምሬያለሁ፡፡ መጽሐፉ አሁንም በተደጋጋሚ ሊመረመርና ሊታይ የሚገባው መሆኑን ግን የሚክድ አንደበት የለኝም፡፡

Read 5580 times