Sunday, 03 September 2017 00:00

የኢትዮጵያ ሩጫ ሲለካ 1

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  · ከ1.784 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት
                · በ13 ኦሎምፒያዶች 53 ሜዳሊያዎች
                · በ16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 77 ሜዳሊያዎች
                · 8 የዓለም፣ 3 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ 2 የኦሎምፒክ፣ 5 የኢንዶር ሪከርዶች

             የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም ዙርያ በሚካሄዱ የትራክ፤ የአገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ባለፉት 37 ዓመታት በሁለቱም ፆታዎች 71 ሚሊዮን 578ሺ 075 ዶላር በይፋ የሚታወቅና የሚገለፅ የገንዘብ ሽልማት  ሰብስበዋል፡፡ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች  ማህበር ARRS ድረገፅ በሰፈሩ መረጃዎች ለማወቅ እንደተቻለው በዓለም ሻምፒዮናዎች፤ በዳይመንድ ሊግ ፤ በአገር አቋራጭ እና በተለይ በማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚያገኙት ስኬት ከሽልማት ገንዘብ የሚኖራቸውን ድርሻ አሳድጎታል፡፡
በARRS ድረገፅ በተለያዩ ሰንጠረዦች የቀረቡት ያለፉት 37 ዓመታት የገንዘብ ሽልማት  ዝርዝር መረጃዎች  እንደተመለከተው የኢትዮጵያ አትሌቶች በወንዶች ምድብ 35 ሚሊዮን 229ሺ 663 ዶላር እንዲሁም በሴቶች ምድብ 36 ሚሊዮን 148ሺ 412 ዶላር በማግኘት በሁለቱም ፆታዎች ከዓለም አገራት ሶስተኛ ደረጃዎችን ይዘዋል፡፡ ኬንያ በወንዶች 101 ሚሊዮን 168ሺ 366 ዶላር በሴቶች 43 ሚሊዮን 240ሺ 623 ዶላር በመሰብሰብ ከዓለም አገራት አንደኛ ደረጃ ስትይዝ አሜሪካ በወንዶች 35 ሚሊዮን 897ሺ 551  ዶላር በሴቶች 41 ሚሊዮን 559ሺ 414 ዶላር በማግኘት በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡
በሌላ በኩል በሩጫ ዘመን ጠቅላላ የገንዘብ ሽልማት   በሁለቱም  ፆታዎች የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው ኃይሌ ገብረስላሴ በ3 ሚሊዮን 549ሺ 248 ዶላር ሲሆን በዚሁ የደረጃ ሰንጠረዥ ከ1 እስከ 50 በተቀመጡት ደረጃዎች በወንዶች ምድብ  11 በሴቶች ደግሞ 17 አትሌቶች ከኢትዮጵያ ተመዝግበዋል፡፡ በሩጫ ዘመን ጠቅላላ የገንዘብ ሽልማት ከኃይሌ ገብረስላሴ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የኬንያ ኤሊውድ ኪፕቾጌ 2 ሚሊዮን 029ሺ 165  ዶላር ሲሆን ዊልሰን ኪፕሳንግ በ1 ሚሊዮን 964ሺ 940 ዶላር፤ ሳሙኤል ኢንጅሩ በ1 ሚሊዮን 886ሺ ዶላር እንዲሁም ቀነኒሳ በቀለ በ1 ሚሊዮን 882ሺ 063 ዶላር እስከ 5ኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ የኬንያዋ መሪ ኪታኒ በ2 ሚሊዮን 724ሺ 925 ዶላር መሪነቱን ስትይዝ፤ ኤድና ኪፕላጋት ከኬንያ በ2 ሚሊዮን 313ሺ 231 ዶላር፤ ፓውላ ራድክሊፍ ከእንግሊዝ በ2 ሚሊዮን 236ሺ 415 ዶላር፤ ኢሪን ሚኪቴንኮ ከጀርመን በ2 ሚሊዮን 048ሺ 595 ዶላር እንዲሁም ካተሪን ንድሬባ ከኬንያ በ1 ሚሊዮን 795ሺ 184 ዶላር እስከ አምስተኛ ደረጃ ይከተላሉ፡፡ በሩጫ ዘመን ጠቅላላ የገንዘብ ሽልማት ከኢትዮጵያ አትሌቶች አንደኛ የሆነችው ጌጤ ዋሚ በ1 ሚሊዮን 438 ሺ 280 ዶላር ከዓለም ሰባተኛ ናት፡፡ በተያያዘ በአንድ የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ አትሌቶች ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት በማግኘት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በ2002 እኤአ ላይ በ3 የገንዘብ ሽልማት በሚያበረክቱ ውድድሮች 1 ሚሊዮን 076ሺ 890 ዶላር ያገኘው ኃይለ ገብረስላሴ ሲሆን በ2013 እኤአ ፀጋዬ ከበደ በ4 የገንዘብ ሽልማት በሚያበረክቱ ውድድሮች 695ሺ ዶላር፤ በ1998 እኤአ ኃይሌ ገብረስላሴ በ9 የገንዘብ ሽልማት በሚያበረክቱ ውድድሮች 595ሺ 333 ዶላር፤ በ1993 እኤአ አዲስ አበበ በአንድ ውድድር 525ሺ ዶላር እንዲሁም በ2009 እኤአ በ5 የገንዘብ ሽልማት በሚያበረክቱ ውድድሮች 499ሺ 333 ዶላር በማስመዝገብ እስከ 5ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ገንዘብ በመሸለም ግንባር ቀደም የሆነችው በ2007 እኤአ ላይ በ4 ውድድሮች 737ሺ 500 ዶላር የተሸለመችው ጌጤ ዋሚ ናት፡፡ በ2008 እኤአ ብርሃኔ አደሬ በ4 ውድድሮች 357ሺ 500 ዶላር፤ በ2010 እኤአ ማሚቱ ደስካ በ10 ውድድሮች 320ሺ 050 ዶላር፤ በ2015 እኤአ አሰለፈች መርጊያ በ4 ውድድሮች 307ሺ ዶላር እንዲሁም ብዙነሽ በቀለ በ2014 እኤ በ3 ውድድሮች 278ሺ 033 ዶላር በማስመዝገብ እስከ 5ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡

                            በሩጫ ዘመን ጠቅላላ የገንዘብ ሽልማት የኢትዮጵያ አትሌቶች ደረጃ
በመሃል ቅንፍ ውስጥ የተቀመጡት ቁጥሮች አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት  ያገኙባቸው ውድድሮች ብዛት  ሲሆን  በዳር ቅንፍ የተቀመጡት ቁጥሮች ባገኙት በሩጫ ዘመን ጠቅላላ የገንዘብ ሽልማት መጠን ከዓለም አትሌቶች የሚገኙበት ደረጃ ነው፡፡
በወንዶች
$ 3,549,398 (53)  ኃይሌ ገብረስላሴ (1)
1,882,063  (52)  ቀነኒሳ በቀለ     (5)
1,626,205  (23)  ፀጋዬ ከበደ      (6)
1,015,445    (32)  ሌሊሳ ዴሲሳ   (14)
648,500    (10)  አዲስ አበበ     (19)
615,947  (40)  ገብረ እግዚአብሄር  ገብረማርያም (24)
570 190      (38)    ፈይሳ ሌሊሳ (27)
558,598    (32)  ጥላሁን ረጋሳ  (31)
544,700    (32)  ድሪባ መርጋ   (34)    
508,133   (37)  ታደሰ ቶላ     (37)
489,135     (6)  ለሚ ብርሃኑ ኃይሌ (41)
በሴቶች
$ 1,438,280   (44)  ጌጤነሽ ዋሚ    (7)
1,259,395   (67)  ብርሃኔ አደሬ   (9)
1,179,544   (29)  አሰለፈች መርጊያ (10)
1,142,156   (48)  ጥሩነሽ ዲባባ    (11)
1,090,760   (74) ማሚቱ ደስካ    (13)
998,893   (59)  መሰረት ደፋር (18)
904,855   (24)  ትርፊ ፀጋዬ  (19)
741,775   (31) አፀደ ባይሳ (28)
701,150   (45) መሰለች መልካሙ (30)
684,150   (91) ብዙነሽ ዳባ (31)
665,595   (28)  አበሩ ከበደ (32)
665,595   (28)  ማሬ ዲባባ (33)
649,148   (47)  ደራርቱ ቱሉ (34)  
636,508   (25)  ብዙነሽ በቀለ (35)  
625,068   (55)  አማኔ ጎበና(36)  
624,053   (36) ድሬ ቱኔ(37)  
546,810   (36)   ሙሉ ሰቦቃ (45)  

በነገራችን ላይ ስፖርት አድማስ የARRS ድረገፅን በመንተራስ ከሁለት ዓመት በፊት ተመሳሳይ ሪፖርት አቅርቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ከዚያን ግዜ ወዲህ የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለያዩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና የማራቶን ውድድሮች በሰጡት ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እያገኙ እና ብዙ እየተሸለሙ በመሆናቸው ብዙ መረጃዎች ላይ ለውጦች ተስተውለዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በምንግዜም የገንዘብ ሽልማት ሰንጠረዥ ከ1 እስከ አምስት ባሉት ደረጃዎች ብዙ ለውጥ ባይኖርም በተቀሩት እርከኖች ግን መቀያየሮች አጋጥመዋል፡፡ በተለይ በሴቶች ምድብ የኢትዮጵያ ምርጥ ማራቶኒስቶች እያስመዘገቡ ባለው ውጤት የደረጃ ለውጦች ተስተውለዋል፡፡ ARRS በድረገፁ የሚያሰፍራቸው መረጃዎች እውቅና ፕሮፌሽናል አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫ ፤ በትራክና በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የሚያስመዘግቡትን ውጤት በትኩረት በመከታተተል እንዲሁም በገንዘብ ሽልማት በይፋ የሚታወቅና የሚገለፅ ድርሻቸውን በማስላት ነው፡፡ የገንዘብ ሽልማቶቹ በይፋ የሚገለፁና የሚታወቁ የሪከርድና የምርጥ ሰዓት የቦነስ ክፍያዎችንም የሚያካትቱ ሲሆን በዶፒንግ እና በተለያዩ ጥፋቶች ውጤታቸው የተሰረዘባቸው አትሌቶች ያገኙትን ድርሻ በመቁረጥ እና ውጤታቸው ተስተካክሎ የገንዘብ ሽልማቶቻቸው ለተስተካከለላቸው አትሌቶች የደረጃ እርከኖችን በማሻሻል ስሌቱ የሚኖራቸውን ድርሻ ከግምት ውስጥ አስገብቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን ARRS በዝርዝር እንዳመለከተው የውድድር አዘጋጆች እና አትሌቶች በግል የሚያደርጓቸውን የክፍያ ድርድሮች፤ አትሌቶች ከትጥቅና ከሌሎች ስፖንሰሮቻቸው የሚያገኟቸውን ቦነሶች፤ አትሌቶች በውድድር ላይ ለማሳተፍ የውድድር አዘጋጆች የሚከፈሏቸው ቅደመ ክፍያዎች እንዲሁም ከገንዘብ ውጭ የሚያገኟቸው የተለያዩ ልዩ ሽልማቶች እና ስጦታዎች በየትኛውም ሰንጠረዥ እንዳልተካተቱ እና ከገንዘብ ሽልማት የሚቆጠሩ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
ከ1985 እኤአ ጀምሮ ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ጋር በተያያዘ የተለያዩ የስታትስቲክስ መረጃዎችን በዜና መረብ በማሰራጨት የሚታወቀው ARRS ከ2003 እኤአ ጀምሮ የተሟላ ድረገጹን አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን የማህበሩ አባላት በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉበት ነው፡፡ ከ3000 ሜትር ጀምሮ ባሉ የረጅም ርቀት ውድድሮች ፤የጎዳና ላይ ሩጫዎች ፤ የትራክ እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ የገንዘብ ሽልማቶች፤ ዓመታዊ የውጤትና የሰዓት ደረጃዎች፤ ሪከርዶች…. ወዘተረፈ የሚገኙበት ድረገፁ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የአትሌቶች ብቃትን የሚለኩ የውድድር ውጤቶች የተመዘገቡበት፤ ከ95ሺ በላይ እውቅና ፕሮፌሽናል አትሌቶች የሰፈሩበት እንዲሁም ከ220ሺ በላይ ውድድሮች የተከማቹበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት በ ARRS ድረገፅ የተገኙ መረጃዎች ናቸው፡፡ የገንዘብ ሽልማቶቹ የተቀመጡት በዶላር ሲሆን አንድ ዶላር 25 ብር በኢትዮጵያ ይመነዘራል፡፡
ባለፉት 37 ዓመታት በጎዳና ላይ ሩጫ ፤ በትራክ  እና በአገር አቋራጭ ውድድሮች 449 ሚሊዮን 617ሺ 826 ዶላር የሽልማት ገንዘብ የተከፈለ ሲሆን በወንዶች ምድብ 242 ሚሊዮን 749 630 ዶላር በሴቶች 206 ሚሊየን 868ሺ 196 ዶላር ነው፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫ 441 110 678፤ በትራክ  24 921 798 እና በአገር አቋራጭ ውድድሮች 13 585 360 ነው፡፡
በ2017 እኤአ ከ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፊት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 14 ሚሊዮን 922ሺ 473 ዶላር የገንዘብ ሽልማት ሲቀርብ በወንዶች ምድብ 7 ሚሊዮን 650ሺ 630 ዶላር በሴቶች 206 ሚሊየን 868ሺ 196 ዶላር ነው፡፡
በ2017 የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ መዝገብ
የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የ2017 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የስታትስቲክስ መዝገብ በ812 ገፆች የተዘጋጀ ነው፡፡ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የኮሚኒኬሽን ዲፓርትመንት ያዘጋጀው ሲሆን አርትኦቱን አንጋፋው የአትሌቲክስ ስፖርት እውቅ ጋዜጠኛ ማርክ በትለር ሰርቶታል፡፡
ይህ መዝገብ በ16ኛው የዓለም አትቲክስ ሻምፒዮና ዋዜማ ታትሞ የተሰራጨ ሲሆን ያለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ሙሉ ታሪኮች፤ ዝርዝር መረጃዎች፤ ሰዓቶችና ሪከርዶች… ያለፉት 31 ኦሎምፒያዶች ታሪክ፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ  የአትሌቲክስ ብቃቶች፤ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይኤኤኤኤፍ ስር የሚዘጋጁ ሁሉም ውድድሮች ታሪካዊና አሃዛዊ መረጃዎች የተሰነዱበት ነው።  በእያንዳንዱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 30 ገፅ አዳዲስ የስታትስቲክስ መረጃዎች ይመዘገባሉ፡፡
53 የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች
31 ኦሎምፒያዶች ተካሂደዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ13 ተሳትፋለች
22 የወርቅ፣ 10 የብር እና 21 የነሐስ ሜዳሊያዎች፤  4ኛ ደረጃዎች 17፤ 5ኛ ደረጃዎች 8፣ 6ኛ ደረጃዎች 11፣ 7ኛ ደረጃዎች 6 እና 8 ደረጃዎች
53 ሜዳልያዎች ከዓለም 16ኛ
5 የኢትዮጵያ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሪኮርዶች
ቀነኒሳ በቀለ
5 ሺ ሜትር 12፡49.60 - በርሚንግሃም - 2004 እ.ኤ.አ
ገንዘቤ ዲባባ
በ1500 ሜ. – 3፡55.17 - ካርሉስልህ - 2014 እ.ኤ.አ
በ5 ሺ ሜ. – 314፡18.86 - ስቶክሆልም - 2016እ.ኤ.አ
1 ማይል – 3 4፡13.31 - ስቶክሆልም - 2014 እ.ኤ.አ
3 ሺ ሜ. – 8፡16.60 - ስቶክሆልም - 2015 እ.ኤ.አ
የኢትዮጵያ ውጤታማ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች
በወንዶች ኃይሌ ገሥላሴ 4 የወርቅ፣ 2 የብር፣ 1 የንሀስ ሜዳሊያዎች - 52 ነጥብ
በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ  5 የወርቅ - 1 የብር፣ 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች - 50 በጥብ
የ21ኛው ክፍለ ዘመን  ምርጥ የአትሌቲክስ ውጤቶች
ቀነኒሳ በቀለ - በ10 ሺ እና በ5 ሺ ሜትር
ጥሩነሽ ዲባባ - በ5 ሺ ሜትር
አልማዝ አያና - በ10 ሺ ሜትር
ገንዘቤ ዲባባ - በ1500 ሜትር እና በ300 ሜትር
ልዩ ውጤቶች
ጥሩነሽ ዲባባ - በ2003 እ.ኤ.አ - በ17 ዓመት ከ333 ቀናት ዕድሜ በ5 ሺ ሜትር የዓለም ወጣቷ ሻምፒዮን
መሰረት ደፋር - በ2003 እ.ኤ.አ በ21 ዓመት ከ271 ቀናት ዕድሜ በ5 ሺ ሜትር - የዓለም አንጋፋዋ ሻምፒዮን
የኢትዮጵያ 77 የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያዎች
ኢትዮጵያ ባለፉት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 27 የወርቅ፣ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳሊያዎች፣ 20 አራተኛ ደረጃዎች፤ 18 አምስተኛ ደረጃዎች፣ 14 ስድስተኛ ደረጃዎች፣ 121 ሰባተኛ ደረጃዎች 15 ስምንተኛ ደረጃዎች 77 ሜዳሊያዎች ከዓለም 8ኛ
8 የኢትዮጵያ የዓለም ሪከርዶች
በወንዶች
ቀነኒሳ በቀለ - 5 ሺ ሜ - 12፡37.35 - ሄንግሎ 2004  እ.ኤ.አ
ቀነኒሳ በቀለ - 10 ሺ - 26፡17.52 - ብራሰልስ - 2005 እ.ኤ.አ
ኃይሌ ገ/ሥላሴ - 20 ሺ ሜ - 56፡26 - ኦስትራቫ - 2007 እ.ኤ.አ
ኃይሌ ገ/ሥላሴ - 1 ሰዓት - 21,258 ሜትር  - ኦስትራቫ - 2007 እ.ኤ.አ
በሴቶች
ጥሩነሽ ዲባባ - 5 ሺ- 14፡11.15 - ኦስሎ - 2008 እ.ኤ.አ
አልማዝ አያና - 10 ሺ - 29፡17.45 - ሪዮ ደ ጀኔሮ - 2016 እ.ኤ.አ
ገንዘቤ ዲባባ - 1500 ሜ.- 3፡50.07 - ሞስኮ -2015 እ.ኤ.አ
ድሬ ቱኔ - 1 ሰዓት - 18,517 ሜትር - ኦስትራቫ - 2008 እ.ኤ.አ
2 የዚትዮጵያ ኦሎምፒክ ሪከርዶች
በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ - በ10 ሺ ሜ. - 27፡04.7 - ቤጂንግ 2008 እ.ኤ.አ
በሴቶች አልማዝ አያና - በ10 ሺ ሜ.  - 29፡17.45 - ሪዮ ዴጄኔሮ 2016 እ.ኤ.አ
3 የኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች
ቀነኒሳ በቀለ - 10 ሺ ሜትር - 26፡46.31 -በርሊን 2009 እ.ኤ.አ
አልማዝ አያና - 5 ሺ ሜትር - 14፡26.53 - ሪዮ ደ ጀኔሮ 2015 እ.ኤ.አ
ብርሃኔ አደሬ - 10ሺ ሜትር - 30፡04.58 - ሴንትሊውስ 2003 እ.ኤ.አ
6 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ከኢትዮጵያ
ባለፉት 29 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት የሽልማት ስነስርዓቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች 6 ጊዜ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በወንዶች ምድብ  በ1998 እኤአ ላይ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ከ6 የውድድር ዘመናት በኋላ በ2004 እና በ2005 እኤአ አከታትሎ የዓለም ኮከብ አትሌት የሆነው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ከቀነኒሳ በኋላ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ለመሸለም በመብቃት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት የሆነችውበ2007 እኤአ ያሸነፈችው መሰረት ደፋር ናት፡፡  በ2015 እኤአ ላይ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እንዲሁም ገንዘቤ ዲባባ በ2016 እኤአ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ሆነዋል፡፡

Read 2282 times