Saturday, 02 September 2017 12:55

“ጳጉሜን አስጎብኚ” ድርጅት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች አስተዋውቃለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ካፒታሉን ወደ 80 ሚ.ብር በማሳደግ ሥራ ሊጀምር ነው
                                            
      በ8.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው “ጳጉሜን” አስጎብኚና የጉዞ ወኪል አክሲዮን ማህበር፤ በኢትዮጵያ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን በማስጠናትና በመለየት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡
በአሁን ወቅት ካፒታሉን ወደ 80 ሚሊዮን ብር በማሳደግና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት በይፋ ስራ ለመጀመር መዘጋጀቱን ያስታወቀው አክሲዮን ማህበሩ፤ የፊታችን ማክሰኞ ጳጉሜን 2 በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ተከፍቶ በይፋ ስራ እንደሚጀምር ጠቁሟል፡፡
አስጎብኚ ድርጅቱ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት በዘመናዊ መልክ መደራጀቱ የተገለፀ ሲሆን በቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችም የህብረተሰቡን ባህልና ሃይማኖታዊ ስርአት ያገናዘበ፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዳዲስ እቅዶች ይዞ ወደ ቱሪዝም አገልግሎቱ እንደተቀላቀለ ባለሃብቶቹ አስታውቀዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ልምዶች የተሻለ አዲስ አሠራሮችን ይዞ መምጣቱን የሚገልፀው አክስዮን ማህበሩ፤ ከተለመደው የውጭ ሃገር ቱሪስቶችን የማስጎብኘት አገልግሎት ወጣ ብሎ ኢትዮጵያውያን ልጆችና ወጣቶች ታሪካቸውን፣ እንዲሁም ባህልና ወጋቸውን የሚያውቁበት ትምህርታዊ ጉብኝቶች የማዘጋጀት፤ በሃይማኖታዊ ጉብኝት ትኩረት አድርጎ የመሥራት እቅድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
በማስታወቂያ ሙያ የካበተ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በመቅጠርም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢትዮጵያ የቱሪስት መስህብ፣ በአግባቡና በስፋት የማስተዋወቅ ዓላማ እንዳለው “ጳጉሜን” አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 18 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለ1 የውጭ ሀገር ዜጋ የስራ እድል መፍጠሩንና ለወደፊት እስከ 60 የሚደርሱ ሰዎችን ቀጥሮ የማሰራት እቅድ እንዳለው የጠቆመው “ጳጉሜን” በረጅም ጊዜ እቅዱ በቱሪዝም እና መስተንግዶ የስልጠና ተቋም ማቋቋም፣ በመዳረሻ ቦታዎች ማረፊያዎችን መገንባት እንዲሁም የራሱ የሆነ የበረራ አገልግሎት የመስጠት እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

Read 3342 times