Monday, 11 September 2017 00:00

በኢሬቻ በአል ላይ ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች የቆመውን ሃውልት ኦፌኮ እቃወማለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ዓመት መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በኢሬቻ በዓል ላይ ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች መታሰቢያ በሚል በክልሉ መንግሥት የቆመው ሃውልትና የተገነባው ፓርክ ከቦታው እንዲነሳ ጠየቀ፡፡
“ሟቾችን ለማስታወስ ሲባል የመታሰቢያ ፓርክ ተገቢ ባልሆነ ቦታ ተገቢ ባልሆነ አካል ተሰርቷል” ያለው ኦፌኮ፤ “በወቅቱ የሟቾች ጉዳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ፣ በኦሮሞ ህዝብ ደንብ መሰረት ጉማ ወይም የደም ካሳ ባልተከፈለበት ሁኔታ ሃውልቱ መሰራቱን እቃወማለሁ” ብሏል፡፡
ከመንግስት ይጠበቅ የነበረው ለህይወት መጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ለፍርድ ማቅረብና የሟቾችን ማንነት ከገለልተኛ አካል በማረጋገጥ የደም ካሳ መክፈል ነበር ብሏል - ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፡
በሃውልቱ ላይ በተቀረፀው ዜጎች የሞቱት በድንገተኛ ሁኔታ እንደሆነ ተደርጎ በፅሑፍ መስፈሩ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሃውልቱ ከቦታው እንዲነሳ እጠይቃለሁ ብሏል - ኦፌኮ፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ላይ በሚነሱ የድንበርና መሬት ጥያቄዎች ምክንያት በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ተባብሷል ያለው ፓርቲው፤ በአፋጣኝ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ለማነጋገር በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ የክልሉን መንግስት ሃሳብ ማካተት አልቻለም፡፡ 

Read 4065 times