Monday, 11 September 2017 00:00

ማኅበረ ቅዱሳን ከነገ በስቲያ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይጀምራል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

   · የቤተ ክህነት የብዙኃን መገናኛ ድርጅት: “ፕሮግራሙን አላውቀውም፤” አለ
        · “የቤተ ክርስቲያኒቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ መጠቀም ስላልቻልን ወደ ሌላ ሔድን”
        · “እያስተማርን መጥተናል፤ እንቀጥላለን፤ልዩ ፈቃድ አይጠበቅብንም፤”
        · “ቅዱስነታቸው፥ የራሳቸውን ፕሮግራም ይጀምሩ፤ብለዋል፤”

      ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከነገ በስቲያ የዘመን መለወጫ ዕለት፣በአሌፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ መደበኛ ሥርጭቱን  እንደሚጀምር ያስታወቀ ሲሆን፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፣ “የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩን  አላውቀውም፤” አለ፡፡
ማኅበሩ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ አሜሪካን ሀገር በሚገኘው አሌፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የአየር ሰዓት በመግዛት በሳምንት ለ7 ሰዓታት፥ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች ትምህርተ ወንጌል  ለማስተላለፍ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ከነገ በስቲያ የመክፈቻ መርሐ ግብሩን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ፥ ማኅበሩ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ሥርጭት እንደሚጀምር በድረ ገጹ ቢያስተዋውቅም፣ ድርጅቱ ግን የሰጠው ፈቃድ እንደሌለ ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ጉዳይ ለኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተጻፈው ደብዳቤ፣ በማኅበራትና ቡድኖች ላይ የተላለፈውን እገዳ የሚጥስ አካሔድ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
የድርጅቱ ቦርድ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ከተወያየ በኋላ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፤ ጉዳዩን ለፓትርያርኩ ከማሳወቅ ውጭ ሌላ የገለጸው ነገር እንደሌለ ምንጮቹ አስረድተዋል። “ክፈቱም ዝጉም ማለት አንችልም፤የላይኛው አካል ይወስንበት፤” ተብሎ በተደረሰው ስምምነት መሠረት እንደተጻፈ፣ ጉዳዩም በሒደት ላይ እንዳለና ውሳኔ አለማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ፣ የጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተ አዲስ አድማስ የጠየቃቸው የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፤ በመረጃ ደረጃ ከመስማት በቀር ከየትኛውም ወገን በይፋ ለማኅበሩ የደረሰ ክልከላ ወይም እግድ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
“ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበራችን አስቀድሞ በሰጠው እውቅና፣ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ለትውልዱ የማስተላለፍ ሓላፊነት አለብን፤” ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ “የቴሌቪዥን ሥርጭቱም ከመገናኛ ዘዴዎቹ አንዱ በመሆኑ በደንቡ የተፈቀደ ነው፤ እያስተማርን መጥተናል፤ አሁንም እንቀጥላለን፤ ልዩ ፈቃድ አይጠበቅብንም፤ በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ዕውቅና ያለን ማኅበር ነን፤” ብለዋል፡፡
ማኅበሩ ባለፉት 25 ዓመታት በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በራድዮና በመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች የሃይማኖቱን አስተምህሮ ሲያስተላለፍ እንደቆየና የዚሁ አካል ተደርጎ የሚታየው የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩም የተለየ ተግባር እንደማይሆን አስረድተዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመጠቀም እስካለፈው ግንቦት ድረስ የአየር ሰዓት በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ እንዳልተሰጠው የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በቀረበበት ወቅት፣ ፓትርያርኩ፤ “አቅም ስላላቸው የራሳቸውን ጣቢያ መክፈት ይችላሉ፤” ማለታቸውን ተናግረዋል።
በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ መርሐ ግብሩን ለመጀመር የተነሳሳውም ከዚህ በኋላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ በዘመን መለወጫ በሚጀምረው የማኅበሩን የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም፤ ብለዋል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገውና በባህላዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያተኩረው የአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋራ መዋዋሉን በተመለከተ፣ “ለምን ደግማችሁ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ አላሳወቃችሁም?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “ተስፋችን የነበረው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋራ አብረን እንሠራለን፤ ኃይል እንሆናለን ብለን ነበር፣ አልሆነም፤ ወትሮም መተዳደርያ ደንቡ ማኅበሩ እንዲሠራ ይፈቅድለታል፤ ቅዱስነታቸውም፣ የራሳቸውን መጀመር ይችላሉ፤ እያሉ ሌላ ፈቃድ መጠየቅ አይጠበቅብንም፤” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም ሆኖ፣ ማኅበሩ፣ ከብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የጠየቀው የአየር ሰዓት ቢፈቀድለት፣አሁንም ተመልሶ ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ማኅበሩ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የዘመኑን ትውልድ ለማስተማር የሚያስችል ሞያዊ አቅምና ዝግጅት እንዳለው አቶ ተስፋዬ ገልጸው፣ “የቤተ ክርስቲያን አቅም ነው፤ ልትጠቀምበት ይገባል፤” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከሚነሣው የተደራሽነት ጥያቄና ካለው ክፍተት አንጻርም፣ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓትም አስገንዝበዋል፡፡  
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተቋቋመበት ደንብ፣ በማንኛውም መልክ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚሠራጩ ሚዲያዎችን የማስተዳደርና ፈቃድ የመስጠት፤ የአየር ሰዓት ኪራይ ለሚጠይቁትም ውል የመዋዋል ሥልጣን እንዳለው የጠቀሱት የቦርዱ ምንጮች፤ ፓትርያርኩ በቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ የሰጡት ምላሽ እንደ ውሳኔ አልያም ፈቃድ መስጫ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም፣ ማኅበሩ በኢቢኤስ ያስተላልፍ የነበረው ፕሮግራም መታገዱን ያስታወሱት ምንጮች፤በተመሳሳይ ከነገ በስቲያ በአሌፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የማኅበሩ መርሐ ግብርም እንዳይሰራጭ ሊታገድ  እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 5828 times