Monday, 11 September 2017 00:00

የዘንድሮ የአዶስ ዓመት የበአል ገበያ ንሯል

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(5 votes)

 በዘንድሮ የአዲስ አመት የበአል ግብይት በአብዛኞቹ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየ ሲሆን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ በበኩሉ፤ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ወደ ሁለት አሃዝ ማሻቀቡን አስታውቋል፡፡
የበአል የሸቀጦችን ዋጋ ለመቃኘት ተዘዋውረን በተመለከትናቸው የአቃቂ የቁም እንስሳት መሸጫ የግብይት ማዕከል፣ የሣሪስ ገበያና የመሿለኪያ አካባቢ ገበያዎች፣ የእርድ ከብቶች ዋጋ ንሯል፡፡
በአቃቂ ገበያ ባለፈው አመት ከ1700 እስከ 3200 ብር የነበረው የበግ ዋጋ፣ በዘንድሮ በአል ዝቅተኛው 2500 ብር ከፍተኛው 5 ሺህ ብር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፍየል ዋጋ አምና ከ1300 እስከ 4 ሺ ብር የነበረው ዘንድሮ ከ2 ሺህ እስከ 7500 ብር እንደሚገኝ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች ገልፀውልናል፡፡
የበሬ ዋጋ እንደየመጠኑ ከ12 ሺህ ብር እስከ 35 ሺህ ብር ዋጋ የሚገኝ ሲሆን ይህም ባለፈው አመት ከነበረው የበሬ ዋጋ በአማካይ እስከ 6ሺ ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በሣሪስና በመሿለኪያ አካባቢ በሚገኙ የበግ ገበያዎች ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች፤ በአብዛኛው ለገበያ የቀረቡ በጎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ የገጠር አካባቢዎችና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው ዋጋቸውም በእጅጉ መናሩን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው አመት ከ1900 ብር እስከ 4 ሺህ ብር የተሸጡ በጎች፤ ዘንድሮ ከ2500 እስከ 7 ሺህ ብር እየተሸጡ ነው፡፡
በአቃቂና በሣሪስ ገበያ ዶሮ ከ150 ብር እስከ 450 ብር የሚሸጥ ሲሆን በመሿለኪያ አካባቢ ደግሞ ከ250 እስከ 500 ብር እንደደረሰ ለማረጋገት ተችሏል፡፡
እንቁላል በአብዛኞቹ አካባቢዎች አንዱ በ3፡50 ብር ሂሣብ ሲሸጥ 1ኛ ደረጃ ቅቤ በኪሎ በሣሪስ ገበያ በ250 ብር ይሸጣል፡፡
የዘንድሮ የበዓል ገበያ ከባለፉት የበዓል ገበያዎች በዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን አዲሱ ገበያ መንገድ ላይ የሚገኘው በተለይ በዶሮ ገበያ የሚታወቀው የሾላ ገበያ ነጋዴዎች ይገልፃሉ፡፡ ሰኞ ጀምሮ በተለያዩ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የሚገልፁት ነጋዴዎች፣ የዶሮ ዝቅተኛ ዋጋ 200 እና 220 ብር፣ እንቁላል 4 ብር ከ25 ሳንቲም የሀበሻ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 30 ብር የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርት 18 ብር፣ የምግብ ቅቤ ከ190 እስከ 280 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የበርበሬ ዋጋ በዓሉ ከመድረሱ በፊት በኪሎ እስከ 180 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን ሰሞኑን ወደ 220 ብር እና ከዚያ በላይ ማሻቀቡን ለማወቅ ተችሏል አይብ በኪሎ 120 ብር የነበረ ሲሆን በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ 135 ብር  መድረሱን ሸማቾች ይናገራሉ፡፡
በዚሁ የገበያ አካባቢና ቀጨኔ መድሀኒያለም ቤተ-ክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው የበግ ገበያ ተዘዋውረን እንደጠየቅነው፤ የበግ ዋጋ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ አነስተኛ የሚባለው በግ ከ2 ሺህ ብር ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን ሙክት 5 ሺህ ብር በላይ ይሸጣል፡፡
በፒያሳ አትክልት ቲማቲም በኪሎ 18 እና 20 ብር - ቀይ ሽንኩርት 16 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 55 ብር፣ ቃሪያ በኪሎ 40 ብር፣ ካሮት 24 ብር፣ ዝንጅብል በኪሎ 80 ብር፣ ድንች በኪሎ ሰባት ብር እየተሸጡ ሲሆን ቲማቲም ዋጋው ከፍልሰታ ፆም አንፃር ሰሞኑን ዋጋው መለስ ያለ ቢሆንም ሌሎቹ ግን ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
በአዲሱ ገበያ በሬ ነጋዴዎች እንደተናገሩት፤ አንድ በሬ ከ11 ሺህ 200 ብር እስከ 40 ሺ ይሸጣል፡፡

Read 6489 times