Monday, 11 September 2017 00:00

የ”መኢአድ” እና የ”ሰማያዊ” አመራሮች በአሜሪካ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

  “ሰማያዊ” በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅዷል

        በውህደት አንድ ፓርቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን  ያስታወቁት  የመኢአድ እና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበሮች፤በአሜሪካ ድጋፍ እያሰባሰቡ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ሊቀመንበሮች በአሜሪካ ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በውህደታቸው ዙሪያ ማብራሪያ እንደሚሰጡ የታወቁ ሲሆን ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ  ካናዳም ይሻገራሉ ተብሏል፡፡  
የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ ሰሞኑን ወደ አሜሪካ የተጓዙት፣ በአገሪቱ የሚገኙ የሁለቱ ፓርቲዎች ድጋፍ ሰጪ ማህበራት ባደረጉላቸው ግብዣ መሆኑን፣ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ አበበ አካሉ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ የፓርቲዎቹ አመራሮች በአሜሪካ ቆይታቸው፣ ከደጋፊዎች ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ ከአሜሪካ የሴኔት አባላት ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር እቅድ መያዛቸው ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ቆይታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ካናዳ እንደሚያመሩ የጠቆሙት አቶ አበበ፤ ጉዞአቸው በአጠቃላይ እስከ 2 ወራት ሊፈጅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች በአሁኑ ወቅት ለመዋሃድ የሚያስችላቸውን መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም በጋራ ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት እያሰናዱ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡  
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ማቀዱንና ይኸን በተመለከተም ለከተማው አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት፣ የሰላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ፍቃድ ክፍል የማወሳወቂያ ደብዳቤ ማስገባቱን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ አስረድተዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ከፒያሳ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ተነስቶ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበበ፤ የሰልፍ እውቅና መጠየቂያ ደብዳቤውን ለከተማ አስተዳደሩ ሲያስገቡም ይኸንኑ መጥቀሳቸውን አስታውቀዋል። ፓርቲው ሰልፉን መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም ለማካሄድ አቅዶ ደብዳቤውን ቢያስገባም ቀኑ መለወጥ እንዳለበት አስተዳደሩ መጠቆሙን ተከትሎ ሰልፉ በሚደረግበት ቀን ላይ ድርድር እንደሚደረግ አስታውቀዋል - አቶ አበበ፡፡
የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ፣ ለ2010 የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ፣ ፓርቲው ድጋፍ ለማሰባሰብ እንዲረዳውና ከህብረተሰቡ ጋር በግብር፣በመልካም አስተዳደርና በሙስና ጉዳይ ለመንግስት አቤቱታ ለማቅረብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Read 4183 times