Monday, 11 September 2017 00:00

በተቃርኖና በእንቆቅልሽ የተሞላ ዓመት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 · ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ጸረ ሙስና-ዘመቻ
                       
    ተቃውሞና ሹም ሽረት
በተቃውሞና በግጭት ታጅቦ የተቀበልነው 2009 ዓ.ም በተቃርኖ የተሞላ ነበር፡፡ በዓመቱ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢዎች፣ግጭትና ተቃውሞ አይሎ የነበረ ሲሆን የክልሉ መንግስት ፖለቲካዊ ቀውሱን ለማብረድ እንደ መፍትሄ የወሰደው አመራሩን መለወጥ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፤ ከስልጣናቸው ተነስተው፣በምትካቸው አቶ ለማ መገርሳ አመራሩን ተረክበዋል - በመስከረም መጀመሪያ ላይ፡፡
አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዚዳንት በሆኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተከሰተው አጋጣሚ  በእጅጉ አሰቃቂና አስደንጋጭ ነው፡፡ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪው ምስጋና በሚያቀርብበት የኢሬቻ በዓል ላይ በተቀሰቀሰ ተቃውሞና ግርግር፣ከ56 በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ግን የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ መሆኑን መሞገታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን ጨምሮ በአብዛኞቹ የክልል ከተሞች፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቃውሞና ግጭቶች ተባብሰው ሰነበቱ - ለአንድ ሳምንት ያህል፡፡ በዚህ ወቅትም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ  ፋብሪካዎች፣ ሎጆች፣የባለሃብት እርሻዎች፣ የውጭ ዜጎች ኢንቨስትመንቶች ወድመዋል፡፡ የበርካቶች ህይወትም ጠፍቷል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና አዲስ ካቢኔ
ይኼኔ ነው ኢህአዴግ በ25 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ላይ ያወጀው - “ሀገሪቱ ከባድ አደጋ ላይ ወድቃለች” የሚል ስጋት እንዳደረበት በመግለፅ፡፡ መንግስት፤ የሚኒስትሮች ካቢኔ ስብሰባ በማካሄድ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን አዋጁ በመጀመሪያ ለ6 ወር፣ ከዚያም ለ4 ወር ተራዝሞ፣ ለ10 ተከታታይ ወራት ዘልቋል፡፡ በመጨረሻም  ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በአገሪቱ “አንፃራዊ ሰላም” መስፈኑን በመግለፅ አዋጁን አንስቷል፡፡ ይህን አዋጅ ለማስፈፀም የተቋቋመው በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሣ የሚመራው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት፤ ከ25 ሺህ በላይ ግለሰቦችን “የአመፅ ተሳታፊዎች ናቸው፤ በሃገር ላይ ጉዳት አድርሰዋል” በሚል ወደተለያዩ እስር ቤቶች ያስገባ ሲሆን ለታሣሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ በየጊዜው ከእስር መልቀቁን መግለፁ ይታወሳል፡፡ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑት ታሣሪዎች ግን ጉዳያቸው ወደ ህግ ተጠያቂነት ማምራቱን ኮማንድ ፖስቱ ጠቁሟል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ያለበትን ፖለቲካዊ ችግር ለመቅረፍ በጥልቅ እንደሚታደስ የገለፀው መንግስት፤ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ካቢኔውን እንደ አዲስ አዋቅሯል - በ2007 ምርጫ ማግስት የመሰረተውን  ካቢኔ በማፍረስ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነበሯቸው 30 የካቢኔ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን በአብዛኛው በምሁራን ሹመኞች መተካቸው ይታወሳል፡፡ ከተለወጡት ሚኒስትሮች መካከልም፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣የትምህርት ሚኒስትር፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይገኙባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደትም አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ አቶ በከር ሻሌ፣ አቶ ተፈራ ደርበው፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አለማየሁ ተገኑ የመሳሰሉት ከሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም፣ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ፣ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ፣ ፕ/ር ይፍሩ ብርሃኔ፣ ዶ/ር ኢያሱ አብርሃ … በሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡  
በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር በመሆን በጥቅምት 2009 የተሾሙት አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቤ ፕ/ር መርጋ በቃና፣ በጥቅምት 2009 የትምህርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አሊ ሱለማን፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬን ጨምሮ 12 ባለስልጣናት በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡
አላባራ ያለ የህዝብ አመፅና ግጭት የፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ውጥረት ውስጥ ቢደነግጡ  ብዙም  አይገርምም፡፡ ሆኖም ከድንጋጤም አልፎ ግራ መጋባት ውስጥ ገብተው ነበር - በዚሁ ባሳለፍነው ዓመት፡፡ የመንግስት ግራ መጋባትና መደናገጥ ደግሞ የመንግስት ሹመኞችን ሥልጣን፣ የዛፍ ላይ እንቅልፍ አድርጎት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የስጋት እንቅልፍ!
በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መንግስት ሹመታቸውን የፐወዘባቸው ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ ከአካባቢና ደን ሚኒስትር ተነተስተው፣ በጥቅምት ወደ ትምህርት ሚኒስትርነት፣ ከዚያም በሐምሌ በአምባሳደርነት የተሾሙት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ከንግድ ሚኒስትርነት ተነስተው፣ በጥቅምት ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊ ሚኒስትርነት ቀጥሎም በሐምሌ ወደ ፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትርነት የተሸጋገሩት አቶ ከበደ ጫኔ፡፡ በጥቅምት የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ካሳ ተ/ብርሃን፤ በሐምሌ በአምባሳደርነት ተሹመው ወደ አሜሪካ ተልከዋል፡፡
የኢህአዴግ አራቱ ድርጅቶች በየክልላቸው ባደረጉት የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማም፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮች፤ ከስልጣን የመባረር እጣ ፈንታ የገጠማቸውም በዚሁ አመት ነበር፡፡  በኦሮሚያ ከ4 ሺ በላይ የወረዳ፣ የዞንና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መባረራቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ዓመት ከተከናወኑ ጉልህ ፖለቲካዊ ክስተቶች አንዱ፣ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች የጀመሩት ድርድር ነው፡፡ ምንም እንኳ ውጤቱ ገና ባይለይም፡፡ በርግጥ ገና ከጅምሩ መድረክና ሠማያዊ ድርድሩን አቋርጠው የወጡ ሲሆን ሌሎች 17 ፓርቲዎች ግን  በሂደቱ ቀጥለዋል፡፡ መንግስት፤ በአመቱ መጀመሪያ ላይ የሃገሪቱን ችግር ለመፍታት ህገ መንግስቱን እስከ ማሻሻል የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ቃል መግባቱን የሚያስታውሱት ተቃዋሚዎች፤ የማታ ማታ “ቃል አባይ” ሆኖብናል፣ “የገባውን ቃል አጥፏል” ሲሉ መንግስትን ክፉኛ ይተቻሉ፡፡ በህገ መንግስት ማሻሻያ ጉዳይ ላይ ለመደራደር አሻፈረኝ ማለቱን በመግለጽ፡፡
ፍትህና የህግ የበላይነት
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤የአውሮፓ ኮሚሽን ፓርላማ ስብሰባ ላይ ተጋብዘው መሳተፋቸውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት እንደተመለሱ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ተከሰው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በአመቱ አጋማሽ ላይ የዶ/ር መረራ ጉዲናን እስር በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ሲሆን የሠብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የአውሮፓ ፓርላማ፣ የፖለቲከኛውን መታሰር በመቃወም መንግስትን ኮንነዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግስት ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ በጀመረው የፀረ ሙስና ዘመቻ፤ ወደ 60 የሚጠጉ ተጠርጣሪ የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሃብቶች የታሰሩ ሲሆን ግዙፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ ከ200 በላይ የሚሆኑ የግለሰቦች፣ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ንብረትም ታግዷል፡፡ በአጠቃላይ ከሙስና ጋር በተገናኘ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የሃገሪቱ ሃብት መመዝበሩንም መንግስት አስታውቋል፡፡
የዕድገትና ረሃብ እንቆቅልሽ
ኢትዮጵያ የ8.3 በመቶ አማካይ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ፣ ከዓለም ፈጣን አዳጊ አገራት መካከል የመሪነት ደረጃን መያዟን የዓለም ባንክ ሪፖርት ይፋ ያደረገው በዓመቱ መገባደጃ ላይ ነበር፡፡ ወዲያው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የተራድኦ ኮሚሽን፣ በሀገሪቱ 8.5 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ ምክንያት እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውን የሚገልጽ ሪፖርት አወጣ፡፡ ከእነዚህ መካከልም 7 መቶ ሺዎቹ የረሃብ አደጋ አንዣቦባቸዋል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም፣ ይሄን መረጃ በማስተጋባት፣ለአለማቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአንድ በኩል ሀገሪቱ በእድገት ከዓለም ትመራለች እየተባለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ 8.5 ሚሊዮን ዜጎቿ ለምግብ እርዳታ እጃቸውን መዘርጋታቸው እውነትም የዕድገትና ረሃብ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በዓመቱ የሀገሪቱ አጠቃላይ የውጪ ንግድ የተቀዛቀዘ ሲሆን የውጪ ብድርና እዳ ወደ 23 ቢሊዮን ዶላር አናጥጧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት ለ2010 ዓ.ም 320.8 ቢሊዮን ብር በጀት፣ ለምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴው መከወኛ መመደቡን አስታውቋል፡፡
የግብር ትመና የቀሰቀሰው አድማ  
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የአነስተኛ ነጋዴዎችን ገቢ በግምት በማስላት የተመነው የግብር ምጣኔ፣ ዳግም ተቃውሞና ውጥረት መፍጠሩ ይታወቃል - በዓመቱ የመጨረሻ ወራት፡፡ በግምት ከተጣለው የገቢ ግብር ትመና፣ 40 በመቶ ስህተት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያረጋገጡ ሲሆን ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ የግምት ትመናውን በመቃወም በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይ በአማራና ኦሮሚያ እንዲሁም በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የንግድ መደብራቸውን ለተከታታይ ቀናት በመዝጋት አድማ መተዋል፡፡ አድማው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችንም ያሳተፈ ነበር፡፡ እስካሁን ግን ለዚህ ቀውስ መፈጠር ተጠያቂው ማን እንደሆነ ተለይቶ አልታወቀም ወይም አልተገለጸም፡፡  
የዓመቱ አሰቃቂ አደጋና ስደት
መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት የደረሰውና ከ120 በላይ ዜጎችን በድንገት የቀጠፈው የ”ቆሼ” የመሬት መስመጥ አደጋ፣ የዓመቱ ሰቅጣጭ አደጋ ነው፡፡ ለአንድ ሣምንት በዘለቀ የአስክሬን ፍለጋ፣ መንግስት በድምሩ የ115 ሰዎች ህይወት ማለፉን ይፋ ሲያደርግ፣ በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች በበኩላቸው፤ ከ120 በላይ ሠዎች በአደጋው መሞታቸውን  ጠቁመዋል፡፡ ከአደጋው የተረፉ ተጎጂዎችን ለማቋቋም ከባለሃብቶችና ከተለያዩ የህብረተሠብ ክፍሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደተሰበሰበ  ይታወቃል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም መኖሪያ ቤት ለፈረሠባቸው መኖሪያ ቤት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር፡፡
በተሠባሠበው ገንዘብና ቃል በተገባው የቤት ስጦታ ጉዳይ ላይ አሁንም ድረስ ከተጎጂዎች ቅሬታዎች እየተሰነዘሩ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከተው የአዲስ አበባ መስተዳድር ግን ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጠም፡፡
በድርቅ ተጎጂ አካባቢዎችና በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ከግንቦት ወር ገደማ ጀምሮ የተከሰተው የአተት ወረርሽኝም ሌላው በ “እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖ የዘለቀ ችግር ነው፡፡ በአማራ ክልል የ42 ሰዎች ህይወት በዚሁ ወረርሽኝ ሲያልፍ፣ በሶማሌ ክልል ጉዳቱ ከዚህም የባሰ እንደሆነ ቢነገርም በተጨባጭ የቀረበ አሃዛዊ መረጃ ግን አልተገኘም፡፡ በሌላ በኩል  ስደትም የዜጎችን ህይወት መንጠቁን ባሳለፍነው ዓመትም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በነሐሴ አጋማሽ 150 ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች፣ ወደ ባህር ተገፍትረው ተጥለው የሞቱበት አጋጣሚ በእጅጉ አሳዛኝ ነበር፡፡
የሁለቱ “ቴዲዎች” ከፍታ - በዘፈንና በጤና
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ለረጅም አመታት ያገለገሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት በተገባደደው አመት፣ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከፓኪስትናዊቷ ዶ/ር ሣኒያ ኒሽታር፣ ከእንግሊዛዊው ዴቪድ ናባሮ ጋር ተወዳድረው ነው አሸናፊ የሆኑት፡፡ ከዚህም በላይ ግን በማህበራዊ ሚዲያ፣ በዳይሬክተርነት እንዳይሾሙ ተከፍቶባቸው የነበረውን የተቃውሞ ዘመቻ፣ ማሸነፍም ነበረባቸው፡፡ ተቃውሞው ደግሞ በራሳቸው አገር ዜጎች የተቃጣባቸው መሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያውንና ማህበሰረቡን አስገርሟል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለዶ/ር ቴዎድሮስ ዓመቱ የከፍታ ነበር፡፡
 በሌላ በኩል ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) “ኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲስ አልበሙ መውጣቱን ተከትሎ ዝናው ይበልጥ የናኘበት ዓመት ነበር፡፡
 ከሃገር ቤት ዝናም ተሻግሮ በአለም የቢል ቦርድ የሙዚቃ ሠንጠረዥ፣ የሽያጭ ሪከርድ በመስበር፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ፣ የመጀመሪያው በአለም የታወቀ አልበም ሆኗል፡፡ ቴዲ በዚህ አልበም ዝና ብቻ ሳይሆን ዳጎስ ያለ ገቢም እንዳገኘበት ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  ጳጉሜ 5 ቀን 2009 ዓ.ም በሚሊኒዬም አዳራሽ ሊያቀርብ አቅዶት የነበረው ኮንሰርት ተሰርዞበታል፡፡
በቅርቡ በሒልተን ሆቴል ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የአልበም ምርቃትም፣ “ፍቃድ የለውም” በሚል መከልከሉ ታውቋል፡፡ ቴዲ አዲሱ አልበሙ መውጣቱን ተከትሎ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰጠው ቃለምልልስ፤በየጊዜው የሚሰረዝበት የሙዚቃ ኮንሰርት የገንዘብ ጉዳት እንዳደረሰበት ገልጾ ነበር፡፡ አሁንም ግን ቀጥሏል፡፡
የኢትዮጵያ “ታላላቆች” ህልፈት
በተጠናቀቀው የዘንድሮ አመት በየሙያቸውና ችሎታቸው፣ ለኢትዮጵያ የተጉና የለፉ ታላላቅ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ የህግ ምሁሩና የፖለቲካ ተንታኙ (ፀሐፊው) አቶ አሰፋ ጫቦ፣ አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኢ/ር ሃይሉ ሻውል፣ “የቱሪዝም አባት” በመባል የሚታወቀት አቶ ሃብተ ስላሴ ታፈሠ፣ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ባለቤት የነበሩት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)፣ “ማርሽ ለዋጩ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፣ “የበጋው መብረቅ” በመባል የሚታወቁት ሌ/ጄነራል ጃገማ ኬሎ፣ የእግር ኳስ ምትሃተኛው አሰግድ ተስፋዬ እንዲሁም አርቲስት ሰብለ ተፈራ  በሞት ተለይተውናል፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅና የታሪክ ተመራማሪ የነበሩት ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባሳለፍነው ዓመት ነበር፡፡ ለሁሉም እግዜር ነፍሳቸውን ይማር!!
መልካም አዲስ ዓመት!

Read 2010 times