Monday, 11 September 2017 00:00

የአዲሱ ዓመት የፖለቲካ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ምንስ ይለወጣል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 · የፓርቲዎች ድርድር፣ያልተመለሱ ጥያቄዎች፣አድማና አመጽ፣የጸረ-ሙስና ዘመቻ፣የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ
       · ተቃዋሚዎች በተስፋ መቁረጥና በጭላንጭል ተስፋ መሃል ሆነው አዲስ ዓመትን ሊቀበሉ ነው

      ሊጠናቀቅ 48 ሰዓት ብቻ የቀረው 2009፣የመከራና የሰቆቃ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ለጠላትም እንኳን የማይመኙት ክፉ ዓመት፡፡ ብዙዎች ህይወታቸውን ያጡበት፣አያሌዎች ለእስር የተዳረጉበት፣በርካቶች የተሰደዱበት----አሰቃቂ ጊዜ፡፡ በእርግጥ እንደ አመጣጡ ከዚህም የከፋ ቀውስ ሊከሰት ይችል ነበር፡፡ በአንዳች ተዓምራዊ ሃይል ተርፈናል፡፡ ክፋቱ ግን ችግሮቻችን ገና አልተፈቱም፡፡ አዲሱን ዓመት የምንቀበለው እኒህን ችግሮች የመፍታት አቅምና ጥበብ ሰንቀን መሆን ይኖርበታል። ገዢው ፓርቲ ምን አስቧል? ተቃዋሚዎችስ እንዴት ነው ለመጓዝ ያቀዱት? ወደ አዲሱ ዓመት አዝለናቸው የምንሻገራቸው ችግሮችና እክሎች ምንድን ናቸው? የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ያሳለፈነውን ዓመት በመገምገም በአዲሱ ዓመት ምን እንደሚጠብቁ፣ህልምና ዕቅዳቸውን፣ ተስፋና ስጋታቸውን እንዲሁም ለአገራቸው የሚመኙትን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ለአለማየሁ አንበሴ ነግረውታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡

                    “የህዝብ ብሶትን ይዘን ነው ወደ አዲስ ዓመት የምንሸጋገረው”
                       ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)

       ፓርቲያችን ዓመቱን ያሳለፈው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በተለይ በዜጎች ላይ በተለያየ ሁኔታ የሚፈፀሙ በደሎችን በማጣራት፣ መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት መፍትሄ እንዲያበጁለት ስንጠቁም ቆይተናል፡፡ ውጥረት አይሎባቸው በነበሩት የኦሮሚያም ሆነ የአማራ ክልል ህዝቡ “ተበድያለሁ” የሚል እሮሮና ብሶት ነበር የሚያስተጋባው፡፡ ለዚህ የህዝብ ብሶት የተሠጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም፡፡
አሁንም ብዙ ያልተሰሙ የህዝብ ድምፆችንና ብሶቶችን ይዘን ነው ወደ አዲሱ ዓመት የምንሸጋገረው፡፡ መንግስት እነዚህን የህዝብ ድምፆች እንዲያደምጥ ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህ ጥረታችን ውጤት ያገኘንባቸው የመኖራቸውን ያህል ያልተገኘባቸውም ቀላል አይደሉም፡፡
በ2009 መጀመሪያ ላይ ሁሉም እንደሚያውቀው፣ መንግስት፣ ህገ መንግስቱንም ቢሆን ለማሻሻል ዝግጁ ነኝ ብሎ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን በቃሉ አልተገኘም። በወቅቱ ያን የተናገረው የህዝቡን ግፊት ለመቀነስ መሆኑን በኋላ ላይ ነው የገባን፡፡ እርግጥ ነው በድርድሩ ውስጥ እኛም አለንበት፡፡ ለችግሮች መፍትሄ እናገኛለን ብለን ነው የገባንበት፡፡ መቼም በዚህች ሃገር ጉዳይ ስልጣን ላይ ካሉት የመንግስት አካላት ጋር እንጂ ከፈጣሪ ጋር መደራደር አይቻልም፡፡ እኛ በውይይትና በድርድር የምናምን በመሆኑ ነው ወደ ድርድሩ የገባነው። በአሸባሪነት ተወንጅለው የታሠሩ ፖለቲከኞችና ግለሰቦችን በዚህ ድርድር ለማስፈታት አስበን ነበር፡፡ ሆኖም በተጠናቀቀው ዓመት ይህ አልተሳካም፡፡ በቀጣይ አመት ይሳካል ብለን እናስባለን፡፡ እነዚህን ወገኖቻችንን ብናስፈታ እንኳ ለኛ ከድርድሩ የተገኘ ትልቅ ስኬት አድርገን እንወስደዋለን፡፡
በአዲሱ ዓመትም የተሻገሩ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንግስት አሁንም ካድሬዎቹን ትቶ፣ የህዝብን ድምፅ መስማት አለበት፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ሥራ በሰፊው ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡
በአዲሱ ዓመት መንግስት እነዚህ ወጣቶች የት ነው የሚወድቁት ብሎ መጨነቅ አለበት፡፡ በየዓመቱ የሚመረቁ ተማሪዎችን መቁጠር ብቻ ሣይሆን የሥራ ፈጠራ አዳዲስ እቅዶችን መውጣት ያስፈልጋል፡፡
ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች  ሳይሟሉ የሃገር እድገት የማይታሰብ ነው። እድገት ሲባል መጀመሪያ የህዝብ ኑሮ ነው መሻሻል ያለበት እንጂ ዜጎች እየተቸገሩ መንገድና ፎቅ ቢሰራ፣ ለህዝቡ ችግር ፈጣን ምላሽ አያመጣም፡፡ 2010 የዜጎች መሠረታዊ ነገሮች የሚሟሉበት ዓመት መሆን አለበት፡፡

---------------------------

                                 “በአዲስ ዓመት ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት እድል መፈጠር አለበት”
                                     ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

      ዓመቱ ጥሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበትና የፖለቲካ ምህዳሩን ፈፅሞ ያጣንበት አመት ነበር፡፡ ስለዚህ ምንም አይነት የፖለቲካ ስራ ሳንሰራ ያለፍንበት ዓመት ነው - 2009፡፡ የፖለቲካ መሠረታችን ላደረግነው ሕዝብ፣ ምንም አይነት የፖለቲካ መልዕክት ሳናደርስ ነው አመቱ የተጠናቀቀው፡፡
እንደ ሃገርም ስናየው፣ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው የተጎዳበት አመት ነበር፡፡ የህዝብ ጥያቄዎች በስፋት የተንፀባረቁበትና መንግስትም በጥልቅ ተሃድሶ፣ አለመረጋጋት ውስጥ ሆኖ ያለፈበት፣ ተሃድሶውም ምንም ውጤት ያላመጣበት፣ እንዲያውም የመልካም አስተዳደር፣ የፖሊሲና የአፈፃፀም ችግሮች ገዝፈው የታዩበት ዓመት ነበር። ህዝቡን ወዳልተፈለገ እንቅስቃሴ ያስገባው የገቢዎችና ጉምሩክ የግብር ትመና ጉዳይም ኢኮኖሚውን የጎዳው ሲሆን ሕዝቡን በድጋሚ ለአመፅና ለአድማ አነሳስቶታል፡፡  
በእነዚህ ችግሮች ታጅበን ነው አዲሱን አመት የምንቀበለው፡፡ ችግሮቹም ቀጣይ የቤት ስራዎች ሆነው ነው የሚሻገሩት፡፡ በሌላ በኩል፤ በብሄራዊ መግባባት ላይ ምንም የተሠራ ነገር የለም፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት ባለፈው ዓመት መንግስት ያስተምራል የሚል ግምት ነበር፤ ይሄ አልተሣካም፡፡ የፖለቲካው ምህዳር አሁንም እንደጠበበ ነው፡፡ እኛ እንደ ፓርቲ፣ ለ2010 አዳዲስ እቅዶችን ይዘናል። የከተማና የአካባቢ ምርጫም የሚካሄድበት አመት እንደመሆኑ፣ ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እንደጠበበ የሚቀጥል ከሆነ ግን ከህዝቡ ጋር ተገናኝተን፣ ስለ ፖለቲካ አመለካከታችን አስረድተን፣ ምረጡን ለማለት እንቸገራለን፡፡
የተጀመረው ድርድር መልካም ቢሆንም አሁንም የኢህአዴግን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሆኖ ነው ለ2010 የተሸጋገረው፡፡ ገዥው ፓርቲ በቁርጠኝነት ትኩረት ሰጥቶ፣ ፖሊሲዎችንና አዋጆችን ጨምሮ ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት እድል በአዲሱ አመት መፈጠር አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ ስልጡን ፖለቲካ በዚህች ሃገር ማራመድ  የሚቻለው፡፡ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር እውን የሚሆነው መንግስት ቁርጠኛ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

--------------------------

                                  “የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣበት ምልክት መታየት አለበት”
                                       አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢራፓ ፕሬዚዳንት

    ዓመቱ ያለፈው በምንፈልገው መንገድ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ከዘመን ዘመን መሸጋገርም መልካም ነውና ቀሪውን የሠላማዊ ትግል ጉዞ ለማስቀጠል፣ ደግሞ ጥረት እናደርጋለን፡፡  ሕዝባችንም እንደ ሕዝብ፣ ሀገርም እንደ ሀገር ይሄን አንድ ዓመት የባሰ ቀውስ ሳይደርስ ማሳለፉ፣ተደቅኖ ከነበረው የከፋ አደጋ ማምለጥ  በራሱ መልካም ነው፡፡
በፖለቲካ እንቅስቃሴው ግን የተለወጠ ነገር የለም፡፡ በተለይ በብሔራዊ መግባባት በኩል ያን ያህል አልተሰራም፡፡ የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል ብለን ስንጮህ ነበር፡፡ ይሄ ቅቡል አልሆነም፡፡ ለሀገር የሚበጀው፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያየት ነው፡፡ ጥገናዊ ለውጥ የትም አያደርስም ስንል ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ረገድ ምንም የተሰራ ጠንካራ ስራ የለም፡፡ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር እንዳለበት ሁልጊዜ እንናገራለን፡፡ ባለፈው ዓመትም ይኸንኑ ሀሳብ ስናቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን “ማን ከማን ጋር ተጣላና ብሔራዊ መግባባት እያላችሁ ታራግባላችሁ” የሚል ወቀሳና አስተያየት ተሰንዝሮብናል፡፡ ብሔራዊ መግባባትን በማንሳታችን፣ ወደ ስልጣን በአቋራጭ ለመምጣት አስባችሁ ነውም ተብለናል። አሁንም ብሔራዊ መግባባት ለሀገር አስፈላጊ ነው። ብሔራዊ መግባባት በየትኛውም መመዘኛ ወደ ስልጣን አቋራጭ መንገድ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ኋላ ላይ የብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን ተቀባይነት አግኝቷል ማለት እንችላለን፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የተለያዩ ሙከራዎች እያደረገ ነው፡፡
አሁንም በቀጣይ ዓመት ብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን ሊሆን ይገባል የሚል ፅኑ አቋም ይዘናል። የኢትዮጵያን አጀንዳ አስቀድመን እንቀጥላለን። ስሜት በሚኮረኮሩ የሕዝብ አጀንዳዎች ላይ በትኩረት እንሰራለን፡፡ ሕዝብ ይሄን ሀሳባችንን እየተቀበለን መሆኑ ወደ ፓርቲያችን ከሚመጡ አዳዲስ አባላት መረዳት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ዓመት የተመጣጣኝ የምርጫ ስርዓት እንዲመጣ የመንግሥትን ቃል ይዘን እንሞግለታን፡፡ የአገሪቱ መሪዎች በይፋ ተናግረው ካበቁ በኋላ፣ ለምን እስካሁን ዝም እንደተባለም ግራ የሚያጋባ ነው። በምንቀበለው አዲስ ዓመት፣ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ይደረጋል። እኛም የምርጫ ፓርቲ እንደመሆናችን የመሳተፍ ሀሳብ አለን፡፡ ነገር ግን በምርጫው ስለመሳተፋችን የድርድሩ ውጤት፣ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና የፖለቲካ ምህዳሩ ይወስነዋል፡፡
በእርግጥ ሊራዘም ይችላል እንጂ ለውጥ የማይቀር ነው፡፡ ነገር ግን አነጋጋሪው ለውጡ እንዴት ይምጣ? በማን ይምጣ? የሚለው ነው። በአዲሱ ዓመት የሕዝብ ሰላማዊ የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣበቸው ምልክቶች መታየት አለባቸው። እርግጥ ነው አሁን ባለው ሁኔታ፣ ብዙ የፖለቲካ ለውጥ ይመጣል የሚል ሙሉ ተስፋ የለኝም። የለውጥ ፍላጎቱ ብዙ ነው፤ ለዚህ መንግስትም ሆነ ገዥው ፓርቲ  ጆሮውን መስጠት አለበት። ተቃዋሚዎችም በተናጠል መሮጣችን የትም እንደማያደርሰን አውቀን፣ በአዲሱ ዓመት የምንሰባሰብበትና የምንቀራረብበት ጊዜ እንዲሆን በኛ በኩል እንተጋለን፡፡  

-------------------

                              “ወደ አስቸኳይ አዋጁ የምንመለስበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም”
                                አቶ ጎይቶም ፀጋዬ (የአረና ም/ሊቀመንበር)

     በ2009 ዓ.ም መባቻ ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግርግሮች ነበሩ፡፡ በትግራይም የወረዳና ዞን እንሁን ጥያቄዎች ያነገቡ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል፡፡ የአክራሪ ብሔርተኛነት እንቅስቃሴም ታይቶ ነበር፡፡ ሕዝብ ግን ጉዳዩን ብዙም አልተቀበለውም፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ የፖለቲካ ምህዳሩ ታጥሮ ነው የቆየው፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ለመስራት አመቱ አስቸጋሪ ነበር፡፡ የፓርቲ ጉባኤያችንን እንኳ ያደረግነው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ጉባኤ በመለስ ወደ ሕዝብ ገብተን፣ ስብሰባና ቅስቀሳዎች ማድረግ ሳንችል ነው ዓመቱ የባከነው፡፡
አሁን እንግዲህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደመነሳቱ፣ በአዲሱ ዓመት እውነተኛ የፖለቲካ ምህዳር እንፈልጋለን፡፡ ይሄ የፖለቲካ ምህዳር እውን እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ኢህአዴግም ከልቡ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሀገሪቱ ሰላም በማሰብ ነገሮችን ማቅለል አለበት፡፡ በምንም ምክንያት ተመልሰን ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምንገባበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ በርካታ ማሻሻያዎችን ሕዝቡ ይፈልጋል፡፡ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች መፈታት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ነው መንግስት ከህዝቡ ጋር ሊተማመን የሚችለው፡፡ መንግስት ይሄን ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ በአዲሱ ዓመት መተግበርና የሥራ ዘመኑ መጀመሪያ ቢያደርግ መልካም ነው፡፡

-----------------------

                             “በአዲሱ ዓመት በብሔርና በሐይማኖት መከፋፈል አይገባንም”
                               ዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶ (የመድረክ ሊቀ መንበር)

      አመቱን ያሳለፍነው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በነበሩ የፖለቲካ ውጥረቶች፣ በህዝብ ጥያቄዎች ታጅበን ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም አብዛኞቹ ለአዲሱ ዓመትም እንደ የቤት ስራ ተሸጋግረዋል፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስር የተዳረጉ አሉ፡፡ 2009፣የሀገሪቱ ፖለቲካ በጣም አሳፋሪው ዓመት ነበር፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት፣ በርካታ ወጣቶች ህይወታቸው በፖለቲካ ምክንያት ያለፈበት፣ ሊከሰት የማይገባው አሳፋሪው የፖለቲካ ታሪካችን ነው፡፡ መነሻው ደግሞ ዞሮ ዞሮ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ እንዴት የሰው ህይወት መጥፊያ ይሆናል? መሬት ቁስ ነው፡፡ ስለ መሬት የሰፈሩ ፖሊሲዎች  ሊሻሻሉ የሚችሉ፣ ሰዎች የፃፏቸው ናቸው እንጂ የፈጣሪ መልዕክቶች አይደሉም፡፡ ይሄ ትልቁ የፖለቲካችን ኪሳራ ነው፡፡
የሰው ልጅ አንድ ነው፡፡ በብሔር፣ በሐይማኖት ሊከፋፈል አይገባውም፡፡ ባለፈው ዓመት ግን አስቀያሚ መከፋፈሎች ነበሩ፡፡ ይሄ ለአዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር እንመኛለን፡፡ በዚህች ሀገር ጥላ ስር እንደመሰባሰባችን መጠን ልንከፋፈል አይገባም፡፡ መንግስት ይሄን የተጣመመውን አመለካከት የማረቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚህች ዓለም ውስጥ የሚሰነብት ህግ እንጂ ዘላቂ ስርአት የለም፡፡ ህዝብ ነው በዚህ ዓለም ዘላቂው፡፡ ይሄን ገዥዎች መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሀገሪቱ ያለፈውን ዓመት ያሳለፈችው በብዙ ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች መሃከል ሆና እንደመሆኑ፣ መንግስት ብዙ የቤት ሥራ አለበት። እኛ ተቃዋሚዎችም የሚጠበቅብንን የፖለቲካ ስርአት የምንከውንበትን የፖለቲካ ምህዳር የምናስከፍትበትና ተግባራችንን የምናከናውበት አመት ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ እስረኞች፡- እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሊፈቱ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ ነው ሊባል የሚችለው፣ የእነዚህ ሰዎች መፈታት ፍንጭ ሲታይ ነው፡፡ አዲስ ዓመት ብሩህ ይሆን ዘንድ እነዚህ ሰዎች መፈታት አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ የሰከነ፣ የተረጋጋ፣ በሳል ፖለቲካ ለማራመድ፣ ሁላችንንም በአዲሱ ዓመት ልብ ይስጠን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር! የሚለውን አጉልተን እናስተጋባለን።         

Read 3184 times