Monday, 11 September 2017 00:00

የጎደለው ይሙላ፣ ያጋደለው ይቅና!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሳችሁ
እስቲ እልል እልል በሉ እስቲ እልል በሉ ሁላችሁ
የሚሏት ዘፈን አለች፡፡ እውነትም እንዲህ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ “እልል” ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ “እንኳን አደረሰህ/ሽ፣”  “እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገረህ/ሽ፣” መባሉ ጥሩ ነው፡፡  “እህህ!” የሚያሰኙን፣ ጥርስ የሚያስፋጩን፣ ትንፋሽ የሚያሳጥሩን…ነገሮች ቢበዙም ደግ ማሰቡ የሚቀንስብን ነገር ስለሌለ መጪውን በተስፋ ማየቱ አሪፍ ነው፡፡
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ሲገባ
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኵን ይውሰደው
ጤና መሆንን ነው እኛ የምንወደው
ተብሎ ተዘፍኗል፡፡ ‘ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኵን ይውሰደው’ የምትለዋ ስንኝ ብዙ ነገር ትገልጻለች፡፡ ‘ተውሳክ’ የምትለው ቃል በብዙ አይነት ልትተረጎም ትችላለችና፡፡ ደግሞላችሁ … ጤንነት በእርግጥም የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዴ ጉንፋን ሲመጣ ከተማው ሁሉ ሳል በሳል በሚሆንበት ጊዜ፣ “ውሀ አፍልታችሁ ጠጡ፣” “ምግብ አብስላችሁ ብሉ፣” ወዘተ ማስጠንቀቂያዎች የሚያስከትሉ በሽታዎች ደግመው የማያምሱን ዘመን ይሁንልንማ፡፡
“ህዝቡን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል፣” “አገልግሎት አሰጣጣችንን ለማሻሻል ቃል እንገባለን፣” ምናምን የምንላቸው ነገሮች፣ የለበጣና ለዜና ሽፋን ብቻ  የተባሉ ከመሆን ይልቅ ከልብ የተባሉ የሚሆኑበት ዘመን ይሁንልንማ!
እየወጣ ባለው (“እየሸኘነው” ነው ወይስ “እያባረርነው!” የሚባለው) ዓመት ውስጥ ብዙ ነገሮች ተብለው፣ የተሠሩት ነገሮች ግን ትንሽ፣ እጅግ በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ በሥራ ውጤት ከማሳየት ይልቅ በመገናኛ ብዙኃን ቀርቦ የቅጽል መአት በመደርደር ማሞገስ፣ ‘የብቃት ማረጋገጫ’ የመሰለበት ዓመት ነበርና፡፡
እንቁጣጣሽ፣ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ
የምትለዋ ‘ዘመን ተሻጋሪ’ የምንላት አይነት ስንኝ እውን ሆና፣ “እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ” ስንል ከአንጀታችን የሚሆንበት ዘመን ይሁንልንማ! ብዙ ነገራችን ከአንገት በላይና መባል ስላለበት ብቻ የሚባል ሆኗልና፡፡
በሆነ ባልሆነው ‘ልታይ፣ ልታይ’ እያልን የቴሌቪዥኑን መስኮትና የስብሰባ አዳራሹን የምንሞላ ሰዎች ልብ የምንገዛበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡ በስልጣናችን ወይም በገንዘባችን ወይም በዘር ግንዳችን በሌላው ላይ የምንታበይ ሰዎች፣ ልብ የምንገዛበትና ስልጣን፣ ገንዘብና እዚህ ቦታ ወይም እዛ ቦታ መወለድ ማለት የተለየ አዋቂነት እንዳልሆነ እውነቱን ፊት ለፊት የምናይበትና የምንገነዘብበት  ዘመን ይሁንልንማ፡፡
“ዝለል” በምንባልበት ጊዜ  “ምን ያህል ሜትር ልዝለል?” ከማለታችን በፊት “ለምንድነው የምዘለው?” ብለን የምንጠይቅበት ህሊና የምናገኝበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡ “ዝለል!” ባይ ልብ ባይገዛ፣ “ዝለሉ!” የምንባለው “ለምን?” የምንልበት ዘመን ይሁንልንማ!
“የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚሏት ነገር አለች…እውነትም ምንም እንኳን የወለዱት ይጥፋ ማለቱ ትንሽ ቢከፋም የተናገርነው የማይጠፋበት ዘመን ይሁንልንማ! ዛሬ እናደርጋለን ያልነውን ነገ፣ ከነገ ወዲያ “መቼ ነው እንዲህ ያልኩት!” እያልን የማንሸመጥጥበት፣ “ብልስ ምን ይጠበስ!” የማንልበት ዘመን ያድርግልንማ፡፡
ብርቅዬ እንስሳት እንዲጠበቁ እንለፍፋለን፣ ብርቅዬ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ እንለፍፋለን። እናማ…መጪው ዘመን ብርቅዬ አብሮ የመኖር ልማዶች የሚጠበቁበትና ጫፍ ላይ የተንጠለጠሉትም ነፍስ የሚዘሩበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡
“ሚስቴን ዳርኩለት እህቴ ነች ብዬ…” ከሚል በእምነት ሳይሆን በፍርሀት ነገሮችን ለማድረግ የማንገደድበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡ ከእምነትና እውነትን ከመፈለግ ውጪ፣ “እንዲህ ካላደርግሁ እንዲህ ያደርጉኛል” ከሚል ፍርሀት የምንላቀቅበት ዘመን ይሁንልንማ!
ሰው ሁሉ እንዳይሆን ፍጹም ደመኛዬ
እያጣራ ይስማ ስግብግብ ጆሮዬ
የምትለው ስንኝ ከተዘፈነች ከስንት አስርት ዓመታት በኋላም ጠቃሚነቷ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ የምንፈልገውን  ብቻ  የምንሰማ በዝተናል፡፡ ነጭ ነው ተብሎ የተነገረንን፣ ጥቁር ነው ብለን የምንሰማ፣ ተነሳ ተብሎ የተነገረንን፣ ወደቀ ብለን የምንሰማ በዝተናል፡፡ ከእኛ ወደ ሌላ ሲተላለፍ በተነገረን መልክ ሳይሆን በሰማነው መልክ ይሆናል፡፡
እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ዘንድሮ እውነተኛ መረጃ የምናገኝበት እንጂ ባልተጣራ ወሬ የማንታመስበት ዘመን ይሁንልን፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ የታመስንባቸው፣ እንቅልፍ ያጣንባቸው፣ ጊዜያት በርካታ ናቸው፡፡ “እግረኛ ያወራውን ፈረሰኛ አይመልሰውም” የምንላት ተረት ዘንድሮ በእርግጥም ደጋግማ ስትከሰት አይተናታል፡፡ ፈረሰኞች ያወራነውን እርቆ ሳይሄድ፣ እግረኞች ልንመልስው የምንችልበት ዘመን ይሁንልንማ!
“ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ነገር ከንቱ…” እያልን ነው፡፡ እንዲህ ስንል ደግሞ ሁሌም ጨለምተኞች ስለሆንን፣ መልካም ነገር መስማትና ማየት ስለማንፈልግ ሳይሆን፣ የምንሰማውና የምናየው መልካም ነገር በጣም ስላነሰብን ነው። “ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ነገር ከንቱ…” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ እየደጋጋምን፣ በሰውና በህይወት ተስፋ የማንቆርጥበት ዘመን ይሁንልንማ!
ዘንድሮ መቼም ኮሽ ባለ ቁጥር አየሩን የሚሞላው ተንታኝ ብዛት የጉድ ነው፡፡ ልክ አለ አይደል… ወቅት ጠብቀው መሬት እየፈለፈሉ የሚወጡ የሚመስሉ አሉ፡፡ እኔ የምለው በዓመትም በመንፈቅም እንደ መደበሪያ ይቆጥሩናል እንዴ! እኛ ፈጣሪ፣ አድራጊ እንጂ ተንታኝ መቸ አነሰን! መጪው ዓመት ከትንታኔው ቀነስ ብሎ ከድርጊቱ በርከት የሚሉበት ዘመን ይሁንልን፡፡
‘እውነት’ ስቃይ ላይ ያለችበት ዘመን ነው፡፡ ከእውነትና ከሀቅ ይልቅ ቅጥፈትና ሸፍጥ የገነኑበትና እንደ አዋቂነት ምልክቶች የሚታዩበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡   
እውነት የማታ ማታ ግንባሯ መች ይታጠፋል
እውነት የማታ ማታ ክንዷ መች ይዘነጠፋል
የማታ ማታማ ምላስ’ንኳ ቢቀጥፍ
መልሕቅ የጣለ ሐቅ አይነጥፍ
ይላል ሙሉጌታ ተስፋዬ፡፡ ‘እውነት’ እንደገና ጉልበት የምታገኝበት፣ ቅጠፈትና ሸፍጥ የሚያስፎክሩበት ሳይሆን አንገት የሚያስደፉበት ዘመን ይሁንልን፡፡ ከእውነትና ከእውነት በስተቀር ምንም አማራጭ የለምና፡፡
እግረ መንገዴን፣ ይቺን ስሙኝማ…ሰዎቹ በሆነ ቤት አጠገብ ሲያልፉ ድምጽ ይሰማሉ፡፡
“የምን ድምጽ ነው የምሰማው?”
“አይ፣ ያቺ ቀዩዋ ረጅም ልጅ ታውቃት የለ?”
“አውቃታለሁ…”
“እሷ ዘፈን እየተለማመደች ነው፡፡”
“ነው እንዴ! እኔ ደግሞ የሆነ ነገር አውጪ እያሉ እየገረፏት መስሎኝ ነበር፣” አለና አረፈው፡፡ እንዲህ ፈገግ የምንልበት ዘመን ይሁንልንማ፡፡
በደስታ እንዲረዳዱላት
በደስታ እንዲፋቀሩላት
ህዝቦቿን፣ ልጆቿን ባርክላት
ተብሎ ተዘፍኗል፡፡ መጪው ዓመት ይህ ስንኝ ከዳር እስከ ዳር እውን የሚሆንበት ዘመን ይሁንልንማ! የጎደለው ይሙላ፣ ያጋደለው ይቅና!
እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሳችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2420 times