Monday, 11 September 2017 00:00

ህዝብና ትውልድ

Written by  ደረጀ ኅብስቱ (derejehibistu@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

 “--- ስለ ኢትዮጵያዊ ባህላዊ እሴቶች የሚወያይና የሚከራከር ካገኘች፣የዚያ ዘመኗ ኢትዮጵያ፣ በአድሃሪነት ወይም በፊውዳልነት እየፈረጀች፣አገራዊ ተቆርቋሪዎችን ማንቋሸሹንና ማሸማቀቁን ተያያዘችው። ፍጻሜውም ይሄው እስከ ዛሬ ከፍለን ያልጨረስነው የጥላቻ ፖለቲካ ሆነ። የራሱን ማንነት የካደ ትውልድ፣ ቀድሞውንስ እርስ በእርስ እንደማይካካድ ምን ዋስትና አለው።---”
                  
     ይሄ እራሱን የቻለ ወንበር ዘርግቶ አልተፈላሰፈም የምንለው ህዝባችን፤  ፍልስፍናን ለማህበራዊ፣ ለመንግስታዊና ሃይማኖታዊ ህይወቱ እንደ ማጣፈጫ ቅመም እየመጠነ በያቅጣጫው ተክሏታል። በማህበራዊ ዘርፉ የስነምግባር መመሪያዎቻችን፣ የጎሳ/አካባቢ ሽምግልና፣ የመንደር ትምህርት ቤቶቻችንና ሌሎችም መዋቅሮቻችን የፍልስፍና ወዝ ያረፈባቸው ናቸው። በመንግስታዊ መዋቅሮች ውስጥ ነገስታት ፍትሃዊነትን፣ የሞራልና ፈጣሪን የመፍራት እሴቶችን ተላብሰዋል፤ በተጨማሪም ነገስታት እራሳቸውን የመግዛት ጥበብን በፍልስፍና ቅባት አብሰው ሽማግሌዎቻቸውን አስተምረዋቸዋል። በሃይማኖታዊ ሥርዓታችን ምንም የማያከራክሩ የፍልስፍና መሰረታዊያንን እናገኛለን።
ደርግ በአገዛዝ ዘመኑ ከራሱ ጋር መታረቅ አቅቶት ገና ከጅምሩ እድሜያቸውን ሙሉ ለሃገራቸው የገበሩትንም ሰብስቦ ፊውዳል የሚል ታርጋ ለጥፎ ፈጃቸው። በእርሱ ቤት የወዛደሮች ጠላት ፊውዳሉ ስለሆነ ፊውዳሉን በአብዮት ማስወገድ ሐቀኛ ማርክሳዊ እርምጃ መሆኑን ማስመስከሩ ነበር። የኢትዮጵያው ፊውዳል እኮ የደርግ ሻለቆችንም ከጭቁን ማህበረሰብ አንስቶ በአውሮፓና አሜሪካ የስልጣኔን ብርሃን እንዲያዩ ያደረገ፣ በትምህርት ያበለጸጋቸው ፊውዳል እንጂ እንደ ማርክስ ዘመን የአውሮጳ ፊውዳል፣ አጥንታቸው ያልጠነከረ ህጻናትን ከማሽን እግር ጋር በሰንሰለት እያሰረ ጉልበት የሚበዘብዝ ፊውዳል አልነበረም። በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ማርክሲዝም የሚባል ጭራቃዊ አስተሳሰብ ነገሰ፡፡ የደንቆሮ ዘመን ሆነና የዩኒቨርሲቲ መምህሩም፣ ተማሪውም፣ ወታደሩም እኩል የሚመዘን ገለባ ሆነ። የተማርን ነን የሚሉትም ተመሳሳይ የማርክስ ርዕዮት ዓለም እናራምዳለን እያሉ፣ ጥቃቅን ስህተቶቻቸውን ማረምና ማስታረቅ አቅቷቸው ወደ እርስ በርስ እልቂት ገቡ።
ማርክስን ሸምድዶ በጓደኞቹ ፊት እንደ ውዳሴ ማርያም ያነበነበ ሁሉ፤ምሁርነው፤ ተራማጅ ነው እየተባለ ማህበረሰቡ ውስጥ አዲስ ደረጃ ይሰጠው ጀመር። ማን ከማን ሊያንስ ነው በሚል ስሜት አዳሜ ኩራዟን እየለኮሰች፣ሌሊቱን ሙሉ ከማርክስ ጋር ስትነዛነዝ ማደር ጀመረች። ምድረ ተማሪ የኢትዮጵያን መሬት ትረግጠዋለች፣ ትመላለስበታለች እንጂ በልቧ አውሮጳዊ ሆናለች። ማርክሳዊ ኤንግልሳዊ አስተሳሰብ ይለምልም!! የዘመኑ መሪ መፈክር ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን በአውሮጳዊ መነጽር ብቻ ማየት አዋቂነት ነበር። የአውሮጳ ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው ለኢትዮጵያ መኮረጅ የምሁርነት ማእረግ ያሰጣል፡፡
ስለኢትዮጵያዊ ባህላዊ እሴቶች የሚወያይና የሚከራከር ካገኘች፣ የዚያ ዘመኗ ኢትዮጵያ፣ በአድሃሪነት ወይም በፊውዳልነት እየፈረጀች፣ አገራዊ ተቆርቋሪዎችን ማንቋሸሹንና ማሸማቀቁን ተያያዘችው። ፍጻሜውም ይሄው እስከ ዛሬ ከፍለን ያልጨረስነው የጥላቻ ፖለቲካ ሆነ። የራሱን ማንነት የካደ ትውልድ፣ ቀድሞውንስ እርስ በእርስ እንደማይካካድ ምን ዋስትና አለው። አለቃ አስረስ የኔሰው፤ በዘመኑ ሊከሰቱ የሚችሉ ክፍተቶችን በተለያዩ ዘዴዎች ለትውልዱ ለማስተማር መሞከራቸው የዘመኑ ጋዜጦችና የሬዲዮ ስርጭት ማህደሮች ምስክሮች ናቸው፡፡ ዶክተር እጓለ ገ/ዮሐንስም፤ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› ብለው ያሳተሟቸው የሬድዮና የጋዜጣ ጽሑፎቻቸው፣ የአለቃን ያህል በጠንካራ መንፈስ ሆነው የአውሮጳ ‹‹ስልጣኔ›› የኢትዮጵያን ባህልና አስተሳሰብ ሊያበላሽ እንደሚችል ስለመከራከራቸው ምስክሮች ናቸው፡፡
ማህበረሰባችን ጥንታዊ እንደ መሆኑና እንደ አጥቢያ ኮከብ ሥልጣኔውን ብልጭ አድርጎ  እንደ መሰወሩ አንዳች የደበቀው፣ ያልተገለጠልን መንግስት ያለው ይመስለኛል። ርዕሰ ጉዳዩ የሚያምታታ እንዳይሆን ግልጽ ለማድረግ ያህል፣ መንግስት እያልን የምናውቀውን/የሰየምነውን አካል መደበኛ መንግስት እንበለውና ምናልባት ደግሞ በትላልቅ ተቋማት እራሱን ያልገለጸ፣ እንደ የለምለም መስክ ምንጭ፣ ድምጽ ሳያሰማ ኩልል እያለ የሚፈስ፣ ስርለስር የሚሰራ መንግስት ይኖር እንደሆን ደግሞ ትንሹ መንግስት እንበለው። ትንሹ መንግስት ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ሽምግልና፣ ጎሳ መሪ፣ ዕድር፣ እቁብ፣ ሰንበቴ፣ የቡና አጣጭ፣ የጥዋማህበር ወዘተ መገለጫው ሊሆን ይችላል።
አሁን ባነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ግን በኔ ግምት፣ የኛ ማህበረሰብ ጥንታዊ ስልጡን መንግስት ያለው መሆኑን ማሳያ የሚሆኑ አራት ማህበራዊ እሴቶችን  ልጠቀም፦ እነዚህም ማህበራዊ ጤናማነት፣ ምጣኔ ሐብት፣ ማህበራዊ ፍቅርና አመራር ናቸው። የሽምግልና፣ የእርቅ፣ የምክክር፣ የአካባቢ ደህንነት/ቅራት ወዘተ ጉዳዮችን ማህበረሰባችን የሚፈታባቸው/የሚያስተናግድባቸው መንገዶችን በቅርበት ብናጠናቸው ማህበራዊ ጤናማነትን ይወክልልናል። ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት እንኳን የየአካባቢው ሰዎች ተመካክረው ስለልጆቹ የአስተዳደግ ሁኔታ፣ ስለቤተሰቦቻቸው የቀድሞ ታሪክ በማጥናት አዲሶቹ ተጋቢዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጠንቅ አብጠርጥረው በማውጣት ይወያያሉ፣ ይወስናሉ።
ምጣኔ ሃብት፦ ገንዘብን፣ ሃብትን፣ ንብረትን አንድ ማህበረሰብ የሚያስተዳድርበት ዘዴን ምጣኔ ሃብት ልንለው እንችላለን። እቁብ ፣ብድር፣ መዋጮ፣ ደቦ፣ አቆልቋይ፣ ወንፈልና ሌሎች ቤሳ ቤስቲ ሲያጥረን ጎደሏችንን ለመሙላት የምንጠቀምባቸው የባህል ባንኮቻችንን ያጠቃልላል። ትዳር እንዳይፈርስ፣ ቤተሰብ እንዳይናጋ፣ ማህበረሰብ እንዲረጋጋ የራሳቸው ቁልፍ አስተዋጽዖ አላቸው፤ እነዚህ የገንዘብ ተቋማት።
እነ ደቦ፣ ወንፈል፣ መቀናጆ የመሳሰሉትን የጋራ የሥራ ትብብሮችንም ብንመለከት ቀጥታ የገንዘብ አስተዋጽዖ ባይኖራቸውም ለጉልበት ሃይል ይከፈል የነበረውን ገንዘብ በመቆጠብ በኩል እገዛ ያደርጋሉ። እገዛ የተደረገለት ሰውም እዳውን በመቆጠር በሌላ ጊዜ በጉልበት ይከፍላል።
ማህበራዊ ፍቅር፦  የጡት አባት ፣ሞግዚት፣ አበልጅ ፣ የክርስትና አባት፣ የተረት አባት፣ ማደጎ፣ ጉዲፈቻ፣ ሙገቻ፣ “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የምንባባልባቸው ጎረቤቶቻችን፤ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ” የምንባባልበት መንደራችን፤ “እንዴ ይሄ ልጅ የእከሌ/ት ልጅ አይደለም እንዴ? ከመቸው እንዲህ ተመዘዘ” እየተባባልን ጉንጭና ግንባር እየሳምን፣ የምናሰርጸው ማህበራዊ ፍቅር፤ በግድ አጣብቆ አንድ የሚያደርግ ማህበራዊ ሲሚንቶ ይመስለኛል።
አመራር፦አባወራዎች/እማወራዎች በየቤታቸው መታፈሪያ  የሚሆኑ፤ የተከበሩ ሞገስ ያላቸው ባለትህትና በሞራል የበላይነት ቤተሰቦቻቸውን ቀጥ አድርገው የሚያስተዳድሩ አሉን። እነዚህም በየመንደራችን ብንቆጥራቸው ብዙ ይሆናሉ፤ ከነሱም ደግሞ  ደረጃ ደረጃ አላቸው። የክብር የማእረግ ልዩነት።
አንተም ተው፣ አንቺም ተይ ማለትና ተጽእኖ ማድረግ የሚችሉ ብዙዎች አሉን። በይሉኝታም የምንታዘዛቸው፤ ጥላቸው እንደ ዋርካ የሚከብደን። እነዚህ ሁሉ የየአካባቢዎቻችን ገዥዎች ናቸው። አስተዳዳሪዎቻችን።
ገድለ አዳም የሚባለው መጽሐፋችን ብቻ ኢትዮጵያችን ምን ያህል የጥንታዊ እውቀት ባለቤት መሆኗን ይመሰክራል፡፡ እኛ አዳም ከጭቃ ተቦክቶ የአምላክ እስትንፋስ እፍ ተብሎበት አይኑ ሲገለጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማውን ስሜት በደማችን ውስጥ ይዘናል። ምናልባት የዳርዊንን የኢቮሊውሽን (ዝግመተ ለውጥ) ሃልዮት መጠቀም ካለብን በዚህ መልኩ ነው። በጦርነትና በውስጣዊ ግጭት ምክንያት መደበኛው መንግስት ሲዳከም፣ የማህበረሰቡን አንድነት አስጠብቆ የሚሄደው በጥንታዊ መንግስት ጥንካሬ ነው፤ መደበኛው መንግስት ጠንከር ሲል ደግሞ መደበኛ መንግስታት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ተቋቁሞ፣ ቋንቋ ሳይገድበው አብሮ እየሰራ መኖር የቻለ ህዝብ። ምናልባትም በጣም ውስብስብና  ከባድ ከሆኑት የዓለማችን ማህበረሰቦች ውስጥ አንዱ የኛ ማህበረሰብ ይመስለኛል።
ከማርክሳዊ ፍልስፍና በኪሳራ የተማርናቸው ነገሮች እንዳሉን ሁሉ ከዘመናዊ የፖለቲካ ፈላስፎችም የምንማረው ብዙ ቁምነገር እንዳለ መካድ አይቻልም፤ስለዚህም የፖለቲካ ፈላስፋው ለማህበረሰቡ ሲሞግት መንግስታት ለማይገረሰሰው የህዝብ ዳኝነት ባያሌው/ፍጹም ረዳቶች መሆን ይገባቸዋል፤ እያንዳንዱ የማህበረሰቡ አካል የሆነ ግለሰብ ሁሉ እኩል ድምጽ ኖሮት፣ እኩል የሚያዝዝበት መንግስት ነው መመስረት ያለብን። ስለሆነም የመንግስታት ቅርጽ እንደየ ማህበረሰቡ ስሪት ተስማሚ መዋቅር ሊኖራቸው ይገባል። ይህም ማለት የኛ ዘመናዊ/መደበኛ መንግስታችን፣ የማህበረሰቡን ጥቅም ያስከብር ዘንድ የማህበረሰቡን እሴቶች የሚመስሉ መዋቅሮች ሊኖሩት ይገባል  ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ ግን የታደልን ማህበረሰብ ነን ብዬ አላምንም። ከማህበረሰባችን እሴቶች ጋር የሚጋጩ ሁልቆ መሳፍርት ችግሮችን እያስተዋልን ነው።
“የብሔረሰቦችን ጥቅም እናስከብራለን” ስንል፣የጋራ እሴቶቻቸውን ድራሻቸውን ልናጠፋ እንችላለን። እያደረግነውም ነው። የፖለቲካ ፈላስፎቹ፣” ጥቅምን መሰረት አድርጎ የሚመሰረት ውልም በሂደት እራሱን እያጠበበ፣ በውል ውስጥ ትልቁን የጥቅም ድርሻ የሚሻሙ ወደል አይጦችን ይፈጥራል” ይላሉ፤ ፈጥረናልም። ሕግን ከለላ አድርገው የራሳቸውንና የጥቅም አጋሮቻቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስከብሩ የመንግስት ተቋማት እስከ መመስረት ደርሰናል።
የማህበረሰቡ ባህል፣ ይሉኝታ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ልማድና እፍረት የራቃቸው መካከለኛ ገቢ ማህበረሰቦችን እየመሰረትን ነው። በዛሬ ጊዜ እንኳን ፖለቲከኞቻችን የሃይማኖት መሪዎቻችንም ዘመናዊ መኪና የመግዛት እሽቅድምድም እንጂ ከጎረቤት ጋር አብሮ ለመብላት ለመጠጣት፤ የተራበ ለማብላት፣ የታረዘ ለማልበስ ስልቹዎች ብቻ ሳይሆን ጥዩፎች ሆነዋል። አዲሱ ዓመት ከኢትዮጵያ መንፈስ ጋር የምንታረቅበት ዘመን ይሁንልን!!

Read 519 times