Monday, 11 September 2017 00:00

ያለፈው ዓመትና አዲሱ ዓመት - በመንግሥት መነፅር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   “ለሀገር አንድነት፣ ሠላም፣ እድገት … ተግተን መስራት አለብን” - ዶ/ር ነገሪ ሌንጮየመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ኃላፊ ሚኒስትር

        መንግስት ያለፈውን ዓመት እንዴት አሳለፈ? ሊጋፈጣቸው ያልቻላቸው ተግዳሮቶች ምን ነበሩ? ስህተቶቹንና ጉድለቶቹን ያውቃቸዋል? ካወቃቸው … ለማረም ምን አደረገ? የአዲሱ ዓመት ፈተናዎችና ተስፋዎች ምንድን ናቸው ይላል? የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በ2010 ዋዜማ ላይ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የገለፁትን እነሆ፡-
ያለፈው አመት በመንግሥት በኩል ምን ተከናወነ? እንዴትስ አለፈ? ምንስ ተግዳሮት ገጠመው?
በአንድ ዓመት ውስጥ የተከናወኑ ስኬቶችና ተግዳሮቶችን በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ በዝርዝር ለመግለፅ ያስቸግራል፤ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በ2008 ዓ.ም በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልል አንድ ዞን ላይ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት አዳዲስ አሰራሮችን የተከተልንበት ጊዜ ነው - 2009 ዓ.ም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የነበረበት ዓመት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ሀገርን ለማሳደግ፤ በኢኮኖሚ፣ በማህራዊ መስክ ሀገሪቱን ወደፊት ለመውሰድ የታቀዱት ስራዎች፣ በታቀደላቸው እየሄዱ እንደሆነ ነው፤ ግምገማው የሚያሳየው፡፡ ውጤትም ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይሄ ውጤት የመጣው ግን እንዲሁ አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ አይደለም፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች የታለፈበት ነው፡፡ ይሄም ሆኖ በዓመቱ መንግስት ትላልቅ አላማዎችን አስቀምጦ፣ ከህዝቡ ጋር በመተባበር አከናውኗል፡፡ በተለይ የሠላም ጉዳይ ለህዝባችን ወሳኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በ2008 አካባቢ የነበሩ የሰላም ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከህዝቡ ጋር በመተባበር፣ ትልቅ ውጤት የተገኘበት አመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መንግስት የያዛቸው እቅዶችም ነበሩ፡፡ ዓመቱ ተግዳሮቶችን በመቋቋም፣ ውጤት የተገኘባቸው ጊዜ ነበር፡፡ ይህም የሆነው በህዝብ ትብብርና በመንግስት መሪነት ነው፡፡ በኢኮኖሚው ትልቅ ውጤት ተገኝቷል፡፡
በተለይ በ2009 መሪው ፓርቲ ራሱን የፈተሸበት ዓመት ነው፡፡ እንደገና ደግሞ በመንግስት ደረጃ ያሉትን ችግሮች በመዳሰስ፣ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው አባላትና አመራር ላይ እርምጃ በመውሰድ፣ የአቅም ግንባታን በመስራት፣ የአመለካከት ቀረፃ ላይ በሚፈለገው ደረጃ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ እንዲሰፍን፣ መሪው ፓርቲ ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ በፌደራልና በክልል ደረጃ ትልልቅ ለውጦች የተካሄዱበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከካቢኔ ለውጥ ጀምሮ በርካታ ትልልቅ ለውጦች ተደርገዋል፡፡
የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እንደ ጥፋታቸው መጠን፣ ከኃላፊነታቸውና ከፓርቲው እንዲባረሩ የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ሚዲያው ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ፣ ለህዝቡ አሳውቋል የሚለው ነው ጥያቄው እንጂ በ2009 መንግስት ትልልቅ ስራዎችን የሰራበት አመት ነው ማለት እንችላን፡፡ ለምሳሌ ጊዜያቸው ተጓትቶ የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የተደረገበት አመትም ነበር፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ሌሎችም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጀምሯል፡፡
ከሰላምና መረጋጋት ጋር በተያያዘም ትልቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ መሃል ግን በአንዳንድ ክልሎች የወሰን ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉልና በኦሮሚያ፣ በአፋርና በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ አጎራባች ክልሎች … ህዝብን ያጋጩ የነበሩ የድንበር ችግሮችን ለመፍታት፣ በትጋት ተሰርቷል፡፡
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድርድር አለ፡፡ የሲቪክና የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲበረታቱ የተደረገበት ሁኔታም አለ። የሚዲያ ተቋማት፣ ዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መድረኮችን እንዲያዘጋጁ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲያሳትፉ … ጥረት ተደርጓል፡፡ በሚዲያው ረገድ አጠቃላይ ሪፎርም ለማከናወን እየተሰራ ነው ያለው፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት የተሻሻለበት ሁኔታ አለ፡፡ ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋርም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ተገኝተዋል። ከሩቅ ሆነው ሀገሪቷን ለማተራመስ የሚሞክሩ፣ በተለይ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ሆነው፣ የሀገሪቷ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ነገር ግን ከልማቷ ወደ ኋላ ለማስቀረትና ጫና ለማድረግ የሚያስቡ አካላት አላማቸው እንዳይሳካ የተደረገበት አመት ነበር፡፡ በዚህም ትልቅ ድል ተገኝቷል፡፡
ድርቅ አንደኛው ተግዳሮት ነው፡፡ ከድርቅ ጋር በተያያዘ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለጎዳበት ተዳርገዋል፡፡ እነሱን ለመታደግ መንግስትና ህዝብ በጋራ ተረባርቧል፡፡ በሚገርም ሁኔታም አንድ ክልል እህል፣ ግጦሽና ውሃ እየጫነ፣ ለሌላው የሚያደርስበት መተሳሰብና መተጋገዝ የታየበት ሁኔታም ነበር። መንግስት ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል፡፡
ሌላው ተግዳሮት፣ በ2008 መገባደጃ እና በ2009 መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ያለመረጋጋት ነው፡፡ ያ የሰላምና መረጋጋት ችግር ባይኖር ኖሮ፣ በሙሉ አቅም በልማት ላይ መስራት ይቻል ነበር። የመልካም አስተዳደር ችግርም ቀላል ተግዳሮት አይደለም፡፡ ጊዜ የፈጀ ጉዳይ ነበር፡፡ የተፈጥሮ አደጋዎችም ነበሩ፡፡
መንግስት አዲሱን ዓመት ከወትሮው በእጅጉ በተለየ መልክ ለመቀበል ምን አሳሰበው?
በሚሊኒየሙ መግቢያ፣ መሪዎቻችን ኢትዮጵያን ወደ ሚፈለገው ስልጣኔ ለመምራት “መጪው የኢትዮጵያ ህዳሴ ነው” ብለው ከህዝቡ ጋር ቃል የገቡበት ነበር፡፡ ባሳለፍነው 10 ዓመት ውስጥ ያገኘናቸው ስኬቶች ምንድን ናቸው? ጉድለቶቻችንስ? ብለን የምናስብበት ነው፡፡ መጪው አስር ዓመት ደግሞ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በጥንካሬ እየተሰራ ነው፡፡ ስለዚህ ዜጎቻችን ይሄን አላማ ማወቅ አለባቸው፡፡ ለአላማው ስኬት መነቃቃት አለባቸው፡፡ የሀገር ፍቅር ስሜታችን መነሳሳት አለበት፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠልና በዓለም ደረጃም የምንፈልጋት ሀገር ለማድረግ የምናስታውሳቸው እሴቶቻችን ስላሉ ነው፣ ቀናቶችን ሰይሞ መዘከር ያስፈለገው። ለሠላም፣ ለሀገር አንድነት፣ ለሀገር ፍቅር፣ ለአረጋውያን፣ ለመሪዎቻችን፣ ለታዳጊዎች ያሉን እሴቶች አሉ፡፡ 2010ን በመነቃቃት የምንቀበል ከሆነ፣ ሁሉም በየፊናው፣ በንቃት ተሳትፎ፣ ለውጥ የምናመጣበት ይሆናል፡፡
የመንግስት የአዲስ ዓመት ተስፋዎች ምንድናቸው?
በሚቀጥለው ዓመት በመንግስት በኩል የተያዙ ትላልቅ የልማት እቅዶች አሉ፡፡ በዋናነት ህዝባችንን ማብቃት ነው የሚያስፈልገው፡፡ የህዝብ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ እንዲያድግ፣ መንግስት በቁርጠኝነት ይንቀሳቀሳል፡፡ ቁርጠኝነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የተሻለ አመራርና ተስፋ እንዳለ ማየት አለበት። ለያዝነው የእድገት እቅድም ሁኔታዎች የተሻሉ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ህዝቡን ለማዳመጥና ለማገልገል ያለው ቁርጠኝነት በጣም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ኃላፊነቱን፤ ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለመወጣት፣ እየሰራ ያለው ስራ፣ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ሁላችንም የተሻለ መልካም ውጤት የምናስመዘግብበት ዓመት ይሆናል፡፡
አዲሱ ዓመት የተሻለ፣ ብሩህ ዘመን እንደሚሆን በማወቅ መቀበል አለብን፡፡ ሀገራችንን የተሻለች የምናደርገው እኛው ነንና፣ በውጪም ሆነ በሀገር ውስጥ የምንኖር ሁሉ፣ ከምንም በላይ ለሀገር አንድነት፣ ለሀገር ሰላም፣ ለሀገር እድገት … ተግተን መስራት አለብን፡፡ በተረፈ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

Read 899 times