Monday, 11 September 2017 00:00

የዓመቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ - በኮሚሽኑ ሪፖርት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    · ስጋታችን፤ ሰብአዊ መብትን በተመለከተ በህብረተሰቡና በመንግስት ያለው ግንዛቤ ደካማ መሆን ነው
       · የመንግስት አስፈፃሚዎች ወደ ጥሰት ሲገቡ ፣“በህግ ይጠየቁ” ብሎ በድፍረት የጠየቀ ተቋም ነው
       · ገለልተኛ ባንሆን መንግስትንና ሥራ አስፈጻሚውን የሚያብጠለጥል ሪፖርት አናቀርብም ነበር

      በሀገሪቱ ተፈጥረው የነበሩ ተቃውሞና ግጭቶችን በመመርመር በዓመቱ አጋማሽ ላይ ለፓርላማ ሪፖርት ያቀረበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፤ የሰብአዊ መብትን በተመለከተ በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት አካላት ዘንድ ያለው ግንዛቤ ደካማ መሆን እንደሚያስሳስበው ጠቁሟል፡፡ በ2009 ዓ.ም በአጠቃላይ 5836 አቤቱታዎች ለኮሚሽኑ በስልክ እንደደረሱት፤ የአብዛኞቹ ትኩረትም ከአላግባብ ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀል፣ ንብረትን የማጣት፣ አስተዳደራዊ ችግሮችና ከሰራተኞች መብት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር፤ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ተለይተውና ማጣራት ተደርጎ፣ እልባት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ 2090 ያህል የመብት ጥሰት አቤቱታዎች መቅረባቸውን በመግለጽም፣ ከነዚህ ውስጥ 1086 ያህሉ በህግ በመታየት ላይ ያሉ በመሆኑ ኮሚሽኑ ጣልቃ መግባት እንዳልቻለ፣ ቀሪዎቹ ግን በተለያዩ አካባቢዎች መፍትሄ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ፤ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የተለያዩ ሚዲያዎችን ከወከሉ ጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ ከአዲስ አድማስ በግል ተጠይቀው የሰጡትን ምላሾች ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

     በቅርቡ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ነበር፡፡ የጉዞው ዓላማ ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር የተገናኘ ነው? ከሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር የመነጋገር እድል አግኝተዋል?
እዚያ ሀገር ያሉ የሴኔትና የኮንግረስ አባላት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን የሚሉ ቡድኖች የተካተቱበት ስብሰባ አድርገን ነበር፡፡ አንደኛ የኮሚሽኑን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ሁኔታ ለማወቅ ፍላጎት ስለነበራቸው  ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ነን የሚሉ ድርጅቶችም የየራሳቸው ሪፖርት አላቸው፡፡ ከሩቅ ሆነው ክትትል አድርገናል፣ መርምረናል በማለት የያዙት  ሪፖርት አለ፡፡ በኛ ግምት ግን ሩቅ ሆኖ ክትትልም ሆነ ምርመራ ማድረግ በሳይንስም ደረጃ አይቻልም። ምርመራ የሚደረገው መሬት ወርዶ ከህብረተሰቡ ጋር ነው፡፡ አሜሪካ ተቀምጦ  ምርመራ አደረግሁ የሚል ድርጅት የሚያወጣው ሪፖርት፣ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ጭምር ነው በውይይታችን የተነጋገርነው፡፡ እዚህ እንኳ ሆነን ወደ የአካባቢው የምርመራ ቡድን ስንልክ፣ ምርመራው የሚጣራው በርካታ አካላትን በማነጋገር ነው፡፡
የሃገሪቱ የኮንግረስና የሴኔት አባላትም በኢትዮጵያ የነበረው የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዴት እንደነበር በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው በተሰጣቸው ምላሽ የነበራቸው ብዥታ የተቀረፈበት  ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ይሄን አላማ ከማሳካት አንፃር ጥሩ ውይይት ነበር ያደረግነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት ጥሠቶች ይፈፀማሉ የሚሉ አቤቱታዎች በየጊዜው ይደመጣሉ፡፡ ማረሚያ ቤቶች ላይ ምርመራ አድርጋችኋል ?
ማረሚያ ቤቶች የተሠጣቸው ኃላፊነት፤ ታራሚዎችን የመጠበቅ፣ የማረም፣ የማነፅ፣ ብቁ ዜጋ አድርጎ ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ነው፡፡ እኛም ከዚህ አንፃር ክትትል እናደርጋለን፡፡ የሠብአዊ መብታቸው ተጠብቆ እየተያዙ ነው ወይ? ማረሚያ ቤትስ እያረመ እያነፀ ነው? የሚለውን ምርመራ በየ3 ወሩ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ አንፃር የታራሚውን ሠብአዊ ክብር ጠብቆ በመያዝ ብቁ የሆኑ አሉ። እንዲሁም እጥረት ያለባቸውም አሉ፡፡ ችግር ያለባቸውን ማረሚያ ቤቶች፣ የችግሩ መነሻ ምን እንደሆነ በመጀመሪያ በጥናትና ምርምር እንለያለን። ከለየናቸው መካከል ትልቁ ችግር፣ የሠብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ያለ የግንዛቤና የእውቀት ችግር ነው። በዚህ ችግር፣ የተለዩ ማረሚያ ቤቶች፣ ለሰው ኃይላቸው ስልጠና እንዲሠጥ ይደረጋል፡፡ ምክረ ሃሳቦችም ለአስተዳደሮች ይቀርባሉ፡፡ የሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦችን ተቀብለው አሰራራቸውን ያሻሻሉ በርካታ ማረሚያ ቤቶች አሉ፡፡ ባለፈው ግንቦትና ሰኔ ወር፣ ከ60 በላይ በሆኑ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ምክረ ሃሳቦችን ስለመፈፀማቸው የክትትል ምርመራ አድርገን፣ ሪፖርቶችን በቀጣይ ለፓርላማ እናቀርባለን፡፡
ፍ/ቤት የሚቀርቡ ተጠርጣሪዎች በተለይ የሽብር ተጠርጣሪዎች፣ በፖሊስ ጣቢያ የተለያዩ የስቃይ ምርመራዎች እንደሚደረግባቸው አቤቱታ ያሰማሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እስከ ዛሬ ያደረጋችሁት ምርመራ አለ?
በፖሊስ ጣቢያዎች ያሉ ተጠርጣሪዎችን የሠብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ አቤቱታ ቀርቦልን የመረመርናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ጥያቄ ቀርቦልን፣ ጉዳዩን መርምረን በክትትል እንዲስተካከሉ የተደረጉ አሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመነጋገር በርካታ የተፈቱ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ልደታ ፖሊስ ላይ አቤቱታ ቀርቦልን፣ የክትትል ባለሙያዎች በመላክ፣ ችግሩ መኖሩን ካረጋገጥን በኋላ በፖሊሶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገናል፡፡ ይሄ በ2009 ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ ነው፡፡ ሌላው ጅግጅጋ ላይ እንዲሁ ጥያቄ ቀርቦልን፣ በፖሊስና በማረሚያ ቤቶች አጣርተን፣ ኃላፊዎች ሳይቀሩ የተጠየቁበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ የመብት ጥሠት ተፈፀመብኝ የሚል ካለ፣ አሁንም ወደ ኮሚሽኑ አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በርካታ የሠብአዊ መብት ጥሠቶች መፈፀማቸውን፣የሃገር ውስጥና የውጭ አገር የሠብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርት አድርገዋል፡፡ እናንተ በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ዝምታ መረጣችሁ?
እኛ አቤቱታ ቀርቦልን ሣንመረምር ያለፍነው የለም፡፡ ድብደባና የመብት ጥሰት ሊኖር ይችላል፤ ግን ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ለመብት ጥሰት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህም ለሚቀርቡልን አቤቱታዎች እስካሁን ፈጣን ምላሽ እየሠጠን ነው። በአዋጁ ጊዜ ውስጥ ቀርበውልን እንዲስተካከሉ የተደረጉ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከማረሚያ ቤቶች ጋር በመነጋገር፣ ወዲያው ለሚፈቱ ችግሮች ለፓርላማ ሪፖርት ማቅረብ ስለማያስፈልግ ነው፡፡ በመመካከር እዚያው የተፈቱ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡  
በሃገሪቱ ሁኔታ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ ዲፓርትመንት ማቋቋማችሁን ገልጸውልናል፡፡ የዚህ ዲፓርትመንት ጥናቶች ዓላማ ምንድን ነው?
በመሠረቱ ጥናት የሚያስፈልገው ችግር እንዳይፈጠር ለመከላከል ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩ አንዴ ከተፈጠረ በኋላ የእሳት ማጥፋት ሥራ ውስጥ እንዳንገባ ነው፡፡ ጥናት የሚያስፈልገው አስቀድሞ ችግሮችን ለመለየት ነው፡፡ ለምሳሌ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ምርመራ ብናደርግ፣ በምርመራው የለየናቸው ችግሮች ወደ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ይወስዱናል፡፡ ኦሮሚያ ላይ ሪፖርት ስናቀርብ፣ አንዱ የግጭቱ መነሻ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ሲነሱ በቂ ካሳ ሳይከፈላቸው መቅረቱ እንደሆነ  ለይተናል፡፡ ይሄ ወደ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ይወስደናል ማለት ነው፡፡ በጥናትና ምርምራችን፣ ለፖሊሲ አመንጪዎችና አስፈፃሚዎች የሚሆን ግብአት ነው የምናቀርበው። ወደ ችግር እንዳንገባም፣ ይህ ጥናትና ምርምር፣ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን  ምክረ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
ከተሰሩ  ጥናቶች ለአብነት የሚጠቅሱልን ይኖራል?
ለምሳሌ ከጉዲፈቻ ጋር በተያያዘ፣ ከኤችአይቪ ጋር ከሚኖሩ ወገኖች ጋር በተያያዘ፣ ከከተማ ልማት ጋር በተያያዘ … ከአካል ጉዳተኞች ታሳቢ መሆን ጋር በተያያዘ ጥናቶች እያጠነናን ነው፡፡ በተጨማሪም ከግጭት መከላከል ጋር በተያያዘም እያጠናን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገሪቱ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዳትገባ፣ የሁከትና ብጥብጦችን መሰረታዊ መንስኤዎች የመመርምና ከህብረተሰቡ ጋር ችግሮችን የመለየት ተግባር እያከናወንን ነው፡፡ ጥናትና ምርምር በተለይ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ወደ እሳት ማጥፋት እንዳንገባ አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ ለችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠቆም ነው ጥናትና ምርምሩ የሚያግዘን፡፡
በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ በእርስዎ በኩል ከፍተኛ ስጋት ናቸው የሚሏቸውን ቢጠቅሱልን?
ኮሚሽኑ ስጋት ነው የሚለው በዋናነት፡ የሰብአዊ መብት ጉዳይን በተመለከተ በህብረተሰቡም በመንግስትም ዘንድ ያለው ግንዛቤ ደካማ መሆን ነው፡፡ በፍትህ አካላትም ሆነ በሌሎች የመንግስት አካላት.፣ የህብረተሰቡ አገልጋይ መሆንን የመረዳት ጉዳይ እየዳበረ መምጣት ይገባዋል፡፡ ህብረተሰብን ከማገልገል ጋር በተያያዘ  ያለውን የግንዛቤ ችግር ከፈታን ስጋቱ ይቀንሳል፡፡ ህብረተሰቡ ለሚጠይቃቸው ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ባህል ከዳበረ፣ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ ብዙም ስጋት አይኖርም፡፡ እነዚህ ከሌሉ ግን ስጋቱ ይኖራል። ሰብአዊ መብት እንዲሁ በቃላት የምንገልፀው አይደለም፡፡ የተግባር ጉዳይ ነው፡፡ በድርጊቶች የሚታይና የሚጨበጥ ነው፡፡
በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ይነሣል፤እናንተ ምን ያህል ገለልተኛ ነን ብላችሁ ታምናላችሁ? ለገለልተኝነታችሁስ ማስረጃው ወይም ማረጋገጫው ምንድን ነው?
እርግጥ ነው ይሄ ጥያቄ በተደጋጋሚ ነው የሚቀርበው፡፡ እኛ ገለልተኛ ባንሆን መንግስት የሚያብጠለጥል፣ አስፈፃሚውን አካል ተጠያቂ የሚያደርግ ሪፖርት አናቀርብም ነበር፡፡ ገለልተኛነት የሚለካው በተግባር ነው፡፡ ከቃላት ይልቅ ተግባር ይናገራል፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኑ ገለልተኛ እንደመሆኑ መጠን ምርመራውን በገለልተኝነት መርህ ነው የሚሠራው፡፡ የመንግስት አስፈፃሚዎች ወደ ጥሰት ሲገቡ፣ “በህግ ይጠየቁ” ብሎ በድፍረት የጠየቀ ተቋም ነው፡፡ ይሄ የገለልተኝነት አንዱና ዋናው መስፈርቱ ነው፡፡ ገለልተኛ ባይሆን ኖሮ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ሪፖርት አያቀርብም ነበር። ኮሚሽኑ የገለልተኝነት መለኪያው ተግባር ነው። ለገለልተኝነቱ ምስክሩ ያቀረባቸው ሪፖርቶች ናቸው፡፡

Read 3042 times