Monday, 11 September 2017 00:00

የምንዳ ምርቃት (ወግ)

Written by  ሚኪያስ ጥ.
Rate this item
(2 votes)

   ‹‹ከፍ በል-ልጄ!››
‹‹አሜን!››
‹‹ቤተሰብ አፍራ!››
‹‹አሜን…››
ላባቸውን እያንጠባጠቡ ይመርቁኛል፡፡ ሰውየዉ በድንገቴው ዓለሜ የመጡ ድንገተኛ ሰው ናቸዉ፤ ወይም ‹‹መሲህ›› ናቸው፡፡ አላውቃቸውም፣ አያውቁኝም  ግን በፍቅር ይመርቁኛል፡፡
‹‹ልጄ! ከክፉው፣ከአረማዊው ሰው ይሰውርህ!››
‹‹አሜን!››
እርሳቸው እጃቸውን ሲያሻቅቡ፣እኔ እጄን ወደ ታች በእፍኝ ቅርጽ እያነሳሁና እየጣልኩ፤የምርቃቱን ስነ-ስርዓት በሰከነ መንገድ እናከናውናለን፡፡
‹‹ልጄ! ምርቃቱ ይብቃንና ምክር ልምከርህ›› በጎረነነ ድምጽ፡፡
የጸሃይዋ ነበልባል በጭንቅላቴ ውሃ- ልክ ሲንቀለቀል ይታወቀኛል፡፡ እግሬ ስር የተነጠፈዉ አስፋልት፣ ሙቀቱን ወደ እግሬ የጣት ሸለቋቂቶች መርጨቱን ተያይዞታል፡፡ ቀኑ የሆነ የበርሃማ ቦታ መገለጫ ለመሆን እየቃጣው ነው፡፡ ከቀኑ ጋር አካባቢው ወደ በርሃማ ቦታ ለመለወጥ ዳድቶታል፡፡
‹‹ልጄ! መጀመሪያ እግዚአብሄርን ፍራ፡፡ ከ’ርሱ በኋላ፣ መንግስትን ፍራ፡፡ ለጥቀህ፣ ቤተሰብህን ፍራ፡፡ በአጠቃላይ የሚፈሩትን ፍራ! እነርሱን ካልፈራህ፣ የሰውነትህ ክብር ተገፍፎ በቁምህ ልትሞት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ታላላቆችን ፍራ!››
‹‹እኚህ ሰውዬ የመንግስት ሰላይ ናቸዉ?›› ተጠራጠርኩ፣‹‹ለምን ‹መንግስትን ፍራ› ይሉኛል?›› ወደ ውስጤ ጓዳ ዘልቄ ጠየቅኩ፡፡
ባለፈው ዓመት፣ ነሃሴ ወር ላይ በተደረገዉ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ ለሁለት ሰዓታት እንደ አረሆ ጮኽን፡፡ ደቂቃዎች ስድሳ ደረጃዎችን ሲያልፉ፣ የ’ኛ ጩኸት በጠብመንጃ ድምጽ ተተካ፡፡ በርካቶች ሃብለ-ሰረሰራቸውንና ግንባራቸውን በጥይት እየተመቱ ሲወድቁ፣ እኔ ግን በድንጋጤ ቀልሃ ተመትቼ፣ ራሴን ሳትኩ። ከሰመመኔ ስነቃ፣ራሴን ያገኘሁት ‹‹ፈለገ-ሞት›› ሆስፒታል፣ የአስክሬን መከዘኛ ክፍል ውስጥ ነበር። በጣም ደነገጥኩ፡፡ ከተኛሁበት የብረት አልጋ ተነስቼ፣ የክፍሉን በር ከፍቼ፣ ዋይታና ለቅሶዎችን ከኋላዬ አስከትዬ፣ በብዙ መከራ ቤቴ ገባሁ፡፡
ልቤ ከዚያን ዕለት በኋላ ለመንግስት ተገዢ ሆናለች፡፡
‹‹መንግስትን እየፈራሁ፣ለምን እንደ አዲስ ‹መንግስትን ፍራ› ብለው ይመክሩኛል?››
እርሳቸው ግን ቀጥለዋል…
‹‹ሌላዉ ደግሞ፣ የጠጉር አቆራረጥ ከአምላክ ጋር ለመወዳጀትም ሆነ ለመቆራረጥ ብርቱ ጉዳይ ነዉ፡፡ እንደዚህ (ሌባ ጣታቸውን ወደ ራስ ቅሌ እያወዛወዙ) ጅብና አንበሳ ተጋግዘው ስጋውን የጋጡት በሬ መስለህ፣ ከጌታ ጋር መታረቅ አትችልም፤ በፍጹም አትችልም፡፡ ስለዚህ ይህን ጠጉርህን ከዚህ መዳመጫ ራስህ ባታነሳ፣ ወዮልህ! ከጌታ ጋር ትቆራረጣለህ! ቀልብህ ዕቶነ-እሳት ላይ፣ ማደሪያህ የቀላዔዎች መንደር ውስጥ ይሆናል››
በልቤ ሳቅኩ፤ ገጼ ላይ ግን ፈገግታ አልተነበበም።
ስለ ጸጉር አቆራረጤ የሰፈሬ ሰዎች በሃሜት መልኩ ማውራት ከጀመሩ ቆዩ፡፡ የሰፈር ‹‹አድባር›› የተባሉት ሽማግሌዎች፣ ‹‹አሄሄ! ይህ ልጅ ሊባልግ እየቃጣው ነዉ›› ብለዉ፣ በየቡና ካድሚያውና በየዓውደ-ምህረቱ ያወራሉ፡፡ እኔ ግን እንኳን ልባልግ፣ ራሴን መሆኑ በጣሙን አቅቶኛል፡፡
የጠጉር አቆራረጤ ለውጥ ማሳየት የጀመረው፣ የዛሬ ሁለት ሳምንት ግድም ነበር፤ አንድ ጠጉር አስተካካይ ወዳጅ አለኝ- ‹‹ጎፋ›› አካባቢ ያለ፡፡ እዛ እየሄድኩ ቁመተ- ጠጉሬን አሳጥራለሁ፣ ገጸ-ጠጉሬን ደግሞ ቅርጽ አስወጣለሁ፡፡
ከተረገሙ ቀናት በአንዱ ወደ‹‹ጎፋ›› ዉ ወዳጄ ጸጉር ቤት እግሬን ሰደድኩ፡፡
ሞቅ አድርጎ ሰላም አለኝ፡፡ (ካለፈ ሳስተውል፣ ለካንስ አሙቆ ‹‹ሰላም›› ሲለኝ ለአንድ ተንኮሉ መለማመጃ እኔን ማጨቱን ለማሳየት አስቦ ኖሯል! )
ተለምዷዊዉ የተከርካሚ ወንበር ላይ ተዘርፍጬ፣ ዓይን -ዓይኑን ማየት ጀመርኩ። ‹‹ጀለሴ›› እቃዎቹን ወላውሎ- አቀማጥሎ- በአልኮል ኩሎ፣ ክርከማዉን  ፩ አለ፤ ሲገጣጥበኝ ‹‹ተዉ! እንደ’ርሱ አታድርግ!›› ብዬ ተማጠንኩት፡፡ ‹‹እስታይል ነዉ!›› እያለ፣ በመገጣጠቡ ቀጠለ፡፡
የእርሱ ‹‹ስታይል›› ጭንቅላቴ ላይ እንደ ዘዉድ ሲደፋ፣ ከ’ርሱ ጋር አብሮ የተሰጠኝን የእፍረት ካባ ደርቤ ለበስኩ፡፡
ተወገዝኩ፤ ተወገርኩ፡፡ ‹አያፍሩ› እፍረት አፍሬ ወደ ጎሬዬ ገባሁ፡፡ እስከአሁን ድረስ፣ ግጥብጥቡ ጭንቅላቴ ጠጉር ሳያበቅል ይኸዉ አለ፡፡
አይታወቄዉ ሰዉዬ እየተናገሩ ነዉ…
‹‹…ደግሞ፣ ሴትን ልጅ አምነህ አትቅረብ፡፡ አፋፉ ላይ ገፍትራ ልትጥልህ ትችላለች፡፡ ብዙዉን ጊዜ ሙልጭልጭ ባህርይ ስላላት፣ ከብዙ ሰዉ ጋር ስሙም አይደለችም፡፡ ከዘርፈ-ብዙ ችግሮቼ አንዱ፣ ይህ ሴትን ልጅ ‹የማመኑ› ችግር ነዉ። አትመናት፣ አትቅረባት፡፡ እንዲያውም ራቃት፤ ስትርቃት ነዉ - ያ’ንተ መጥፋትና የማስፈለግህን መጠን የምትረዳዉ…››
አሁንም ግራ ተጋባሁ፡፡
ብዙዎቹ ሴቶች ከቀረቡኝ በኋላ፣‹‹ሌላ ነገር እንዳትጠይቀኝ! ... በወንድምነት- በእህትነት!›› ምንትስ-ምናምንትስ ይሉኛል፡፡ ከብዙዎቹ ፈንጠር ያሉቱ ደግሞ የምናብ ‹‹ፍቅረኛ›› ስለዉ፣ ‹‹አለኝ›› ብለው፣ ቤተ-መቅደስ እንደገባ ዉሻ በቃላት ሽመል ያባርሩኛል፡፡ የ‹‹ብዙዎቹ››ንና የ‹‹ብዙዎቹ›› ቅንጣቶችን ሃሳብ በአንድ የዕይታ ድር ውስጥ ሳምገው  የሚመጣልኝ ተዛናቂ ርዕዮት፣ ‹‹ጸለምተኛ ናቸው›› የሚል ይሆናል፡፡ ‹‹ጸለምተኛ›› ስል፣ፍቅርን ወደ ጉሮኖነት፣ ፍቅርን ወደ አልጋ ላይ ስሪያ ለውጦ መመልከት ማለት ነዉ፡፡ በመጀመሪያ ፍቅር ራሱ ዕውርና እያየ የማያይ ነዉ፡፡ የኛ ትውልድ ግን ሃሳቡን ስቶታል፡፡ በውዳሴ -ከንቱ እየተገዘተ፣ በዛላ መንዘላዘል እየተማረከ፤የፍቅርን ዕውነተኛ ስሜት ይስታል፡፡ ስህተቱ ለሁሉ-እንደየ ድርሻዉ - ይደርሰዋል፡፡ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ ተቆንጥሬ፣ ከብዙሃኑ የስህተት ቅርጫ ውስጥ ተሻኩቼ፣ የራሴን የከሸፈ ታሪክ የምዘግን ሰዉ እንደመሆኔ፣ ብዙ ነገሮችን ዓይቶ እንዳላየ የማለፍ ጽናት አለኝ፡፡ በአዕምሮዬ ላይ እነዛ ጥንብ ቃላት እያቃጨሉ ሰላም ቢነሱኝም፣ጠባሳዬን እየነካኩ ቢያስለቅሱኝም፣ ኑሮን እንደ ጤነኛ- መንገድን እንደ ደህነኛ እያየሁና እየተጓዝኩ ነዉ፡፡ በፍቅር ላይ ማጋጣ ሆነው ለተጫወቱብኝ ሴቶች የምመኘው ነገር ቢኖር፣’ ርግማን የላይኛዉ ጎይታ እንዲያወርድባቸዉ ብቻ ነው፤ ኬረዳሽ!
ሽማግሌው ግን ከነጭራሹኑ ‹አትቅረብ› ነው የሚሉኝ፤ለምን? እኔ እንዳሰብኩት አስበው ይሆን?
…ጸሃዩ በረድ ወደማለቱ ተቃርቧል፤ ብዙ ያልሰማኋቸውን የምክር ዶፎች ከ’ነላቦታቸዉ አዝንበውብኛል፡፡ ሰዉነቴ ዝሎ ምኝታ ፍለጋ ላይ ነዉ፡፡ ሰዉዬዉ አልተበገሩም፡፡ ይመክሩኛል…ይመክሩኛል…
‹‹ለዕውነት ኑር- ልጄ፡፡ የውሸት አክራሞት ላ’ንተ አይጠቅምህም፡፡ እኔን ከጣሉኝ ችግሮች ዉስጥ አንዱ፣ ውሸት ነዉ፡፡ ብዙ ሰዎችን ዋሸሁ፤ የተከበርኩ ሰዉ ነበርኩ፡፡ ባንድ ጊዜ ወደ ታች ተፈጥፍጬ ‹አንተ› ለመባል በቃሁ፡፡ ብዙ ሃብት ነበረኝ፡፡ በመዋሸቴ ሰበብ፣ እ’ሱንም አጣሁት። ልጆቼንም አጣሁ…›› በመዳፎቻቸዉ መሃል የያዙትን ሽመል በጣሙን ያሻሹታል፡፡ ቁጭት ስሜታቸውን እየተመተመ ነው መሰል፡፡
‹‹ብቻ፤ ብዙ ነገር በመዋሸቴ አጣሁ፡፡ እና፣ አትዋሽ!›› ከወፋፍራም አይኖቻቸዉ እንባ ፈለቀ። በሁለቱም አይኖቻቸው ላይ የፈለቁትን የእንባ ምንጮች በሻካራ መዳፋቸዉ ጨፈለቁ፡፡
ረዥም ነፋስ ከሰፊዉ ሃይቅ ተነስቶ፣ በገጻችን ላይ ሲነፍስ ታወቀኝ፡፡
ነፋስ ሲነፍስ ደስ ይለኛል፡፡ በተለይ የሃይቁ ነፋስ፣ ለኔ ወዳጄ ነው፤ ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን ገልቦ ያሳየኛል፡፡ የሰውነቴ ስስ ቆዳዎችን ነካክቶ ሲሰወር፣ ነፍሴ ሃሴት ታደርጋለች፡፡ ከንክኪው ባሻገር፣ ሁሉን ነገር ሲያመሳቅል፣ ሲያመነቃቅርና ሲያራቁት ደስ ይለኛል፡፡
ከሽማግሌው ራቅ ብላ የቆመችው  አጭር ቀሚስ - ለባሽ ሴት፣ በነፋሱ ክፉኛ ስትቸገር አየኋት። በፊትም-በኋላም የሚቀማጠለው ነፋስ፣ ገላዋ ላይ  የተንሰራፋውን ሚጢጢዬ ቀሚስ ‹‹ሰብሬ ካላለፍኩ!›› እያለ ነዉ፡፡ በፊቷ ሲመጣ፣ እጇን ወደፊት አንፈራጥጣ ስትመክተው፤ የጭኗና የመቀመጫዋ ግማሽ ክፍል ይታያል፡፡ የኋላዋንም እንደቀደመው ስታደርግ ያስቸግራታል፡፡
ነፋሱ በነጻ የእንስት ገላን በትንሹ እንድንጎበኝ ይረዳናል፡፡ ከቀሚስ-ገለባ ሲያልፍ፣ የእንስት ጃንጥላን ነጥቆ ወደ’ሚሰወርበት ሰማይ እየተራወጠ ይሄዳል፡፡ ያኔ የሴት ንዴት ወይም ቅብጠት- አመጣሽ ለቅሶ ሳንወድድ በግድ እንሰማለን፡፡
‹‹ነፋስ ገልቦ-አሳዪና ነጣቂ ነዉ›› ማለት፣ እንደዚህ አይደል! ለዚህ’ኮ ነዉ - ሲነፍስ ደስ የሚለኝ፡፡ በጊዜዬ ያላገኘሁትን የሴት ገላ እንደ መዳበስ ያህል ከሩቁ በዓይኔ የምገረምመው  በነፋሱ ምክንያት አይደል፤ በመከራ ያልሰማሁትን ቅብጠት- ሰራሽ የሴት ለቅሶ የምሰማው በነፋሱ አይደል፡፡ ታዲያ! በምን ይሆናል?
‹‹ልጄ! ስሞትልህ፣ በእመ-አምላክ ይዤሃለሁ!›› የልመና ድምጽ ቀልቤን ሰረቀው፡፡
‹‹ምነው፣ ጋሼ?›› ጠየቅኳቸዉ፡፡
‹‹በክርስቶስ ይዤሃለሁ!...››
‹‹ምነዉ፣ጋሼ? ምን ሆኑ?›› ደንግጬ፡፡
‹‹አምስት ብር ስጠኝ፣ የቡና መጠጫ፡፡ አንተን በመመረቅና በመምከር ጉሮሮዬ ደረቀ፡፡ ለ’ርሱ ማራሻ ትንሽ…አምስት ብር ስጠኝ››
ከጅንስ ሱሪ ኪሴ በራብሬ፣ አምስት ብር መዝዤ ሰጠኋቸዉ፡፡
‹‹ተባረክ!…››
በጠንካራው ተራመድኩ፡፡ በጀርባዬ ምርቃት ይንቆረቆራል፤ በምንዳ የተገዛ ምርቃት፡፡
‹‹ወይ አልገፋኝ - ወይ አልጣለኝ…››
አሰናኝ ያ’ጣሁለት ግጥም በልቤ እያዜምኩ ነበር…

Read 2959 times