Monday, 11 September 2017 00:00

“ዘሩባቤል (አክሳሳፎስ)” እንዲህም ታይቷል

Written by  ቀለሙ ዘለቀ
Rate this item
(0 votes)

  “ኢትዮጵያ ጥበበኛ መሪ፣ ጥበበኛ ትውልድ ያስፈልጋታል”
                     
     በ“ዘሩባቤል (አክሳሳፎስ)” የመጽሐፍ ምረቃ ዕለት፣ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም የመጽሐፉን ዳሠሣ ካቀረቡ አንጋፋ ምሁራን መካከል የመምህር የሻውንና የደራሲውን ፍጥጫ የዛሬ ሁለት ሳምንት አቅርቤ ነበር፡፡ የዚህ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከፈቀደልኝ፣ ሁለተኛውን ዳሠሣ እንደማስከትልም ቃል ገብቼ ነበር ጽሁፌን የቋጨሁት፡፡ በዚሁ መሰረት፤ ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ፣በመፅሐፉ ላይ ያቀረቡትን አስደማሚ ዳሰሳ እንደሚከተለው አጠናቅሬዋለሁ፡፡ በመግቢያቸው ላይ የተናገሩትን ትቼ፣ በቀጥታ ወደ ዳሰሳው ልግባ፡፡  
‹‹ለእኔ እንደገባኝ፤ ዘሩባቤል ወይም በበረሓ ስሙ አክሳሳፎስ መነሻው ጥበብ ነው፡፡ ጥበብ ትሔይስ እምኵሎን መዛግብት -› ከምንም ነገር በላይ፣ ከንብረቶች ሁሉ ጥበብ ትሻላለች ይለናል ታላቁ መጽሐፍ፡፡ ሰሎሞን በነገሠ ጊዜ እግዚአብሔር ‹ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?› ሲለው ቤት፣ መኪና፣ አውሮፕላን… ምናምን አላለም፡፡ ‹እስራኤላውያን ክፉዎች ስለሆኑ በጥበብ ኃይል እመራቸው ዘንድ ጥበብን ስጠኝ!› ነበር ያለው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ዋናው መልእክትም፡- ኢትዮጵያ እነ አኵስምን፣ ላልይበላንና ሌሎችንም ተዐምር የሚመስሉ አስደናቂ ሥራዎችን የሠራችው በጥበብ እንጂ በጦር ኃይል፣ በዘመኑ ሳይንስ ወይም በሌላ በምንም አይደለም፤ ኢትዮጵያ የወደቀችው ያ አስደናቂ ጥበቧ ከተሰረቀና ከተተወ በኋላ ነው፡፡ እናም ጥበበኛ መሪ፣ ጥበበኛ ትውልድ ያስፈልጓታል› የሚል ጩኸት አለው በውስጡ፡፡
‹‹ኹለት ጎራዎች አሉት፡፡ በእርግጥ…›› ወደ ደራሲው እየተመለከቱ፤ ‹‹በእርግጥ ቴክኒካሊ የምንነጋገርበት ጉዳይ አለና በኋላ እንመጣበታለን።›› ወደ መጽሐፉ አተኩረው እያዩ ዳሰሳውን ቀጠለ - ደራሲ አበረ አዳሙ፡፡ ‹‹በአንደኛው ጎራ፣ ይሄ የመንደር ወስላታ አወናባጅ ሕዝብን ሲያታልል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አታላይ እንዳታለለ መኖር የለበትም ብለው ታጥቀው የተነሡ እንደነ አፈወርቅ ያሉ ቅኖች፣ በራሳቸው ውሳኔ ወንበዴዎችን በማሠራቸውና በመግደላቸው የዐሥር ዓመት የእሥር ፍርድና የገንዘብ ቅጣት እስኪተላለፍባቸው በዓላማቸው ጸንተው ሕዝቡን የሚታደጉም አሉበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የዓለም ቁንጮ ለመባል የበቁት በጥበብ ነው፡፡ ይሄ ጥበብ የተሰረቀው ደግሞ ከኢትዮጵያ ነው ብለው ከመብከንከን አልፈው ያን የጥበብ መጽሐፍ ለማስመለስ አለብን ብለው የተነሡ ሦስት ሳተና ወጣቶች፣ ለሀገራቸው ፍጹም ቀናዒ የሆኑ ወጣቶች ጥበብን ፈልገው፣ ለሀገራቸው የጥበብ ሸማን ለማልበስ ሲኳትኑ ይታያል። በኋላም ተሳክቶላቸው ከፓሪስ ምሥጢራዊ ቦታዎች፣ ከእነቶኒ ብሌርና ከባዕድ አምልኮ አዳራሽ የውስጠኛው ምሥጢራዊ ቦታ ድረስ በሚያስደንቅ ጥበብ ገብተው፣ የጥበብ መጽሐፍቱን ያወጣሉ፡፡ ዋሽንግተን ቤተ መንግሥት ገብተውም በተመሳሳይ ያወጣሉ፡፡ የሚገርመው፣ እነዚህን ከዚያም ከዚያም ያመጧቸውን መጻሕፍት የሚሰጧቸው ዘጌ ውስጥ በብሕትውና ለሚኖሩ ለአንድ ምሥጢራዊ አባት ነው፡፡
‹‹እዚህ ውስጥ ቅድም የተነሣችው ከመጽሐፉ ጋር መዥርጠው ያመጧት ዩክሊና የምትባል ባለ ታሪክ አለች፡፡ እንደ መጻሕፍቱ ሁሉ ከቶኒ ብሌር ቤት ተሰርቃ የመጣች ናች፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ እንዲህ ስንነጋገረው በዚህ ዘመን የሚሰጠው ዓይነት ትርጉም ያለው አስማት ምናምን ይመስላል። እንደ’ኔ፣ እንዳባቶቼና እንደ መምህር ይባቤ በአብነት ትምህርት ለተካነ፣ በዳመና መጓዝ አዲስ ነገር አይሆንበትም፡፡ ነገሩ እንዴት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታመናል? ይሄ አዲሱ የሳይንስ ትውልድ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ምንድነው… ሆረር ፊልም ይሠራል አደል? ሐሳቡ የተወሰደው እኮ ከ’ኛ ነው››
ደራሲ አበረ በቁጭት ስሜት ነው የሚናገሩት። ‹‹ሆረር ሲታይ የሚሆን ነገር አይደለም’ኮ፡፡ ግን እየሠሩት ረብጣ ዶላር እያፈሱበት ነው፡፡ እኛ ከጎንጅ - ጎጃም ቁጭ እንዳለ፣ ያ ሁሉ ዘበኛ ባለበት ማንም ሳያያው፣ ጎንደር ቤተ መንግሥት ገብቶ ከእነ ዐፄ በካፋ ማዕድ ላይ መመገብ የሚችል ተዋነይ የተባለ ሊቅ ነበረን፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ በእግሩ ይንሸራሸር እንደነበርም አባቶቻችን ነግረውናል፡፡ ቀደም ሲልም እነ ሲሞን የሚባሉ በዳመና ተጭነው ይጓዙ እንደ ነበር የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡››
‹‹ስለሆነም ይሄ ትንግርት ነገር ሳይሆን ሊደረግ የሚችል ነው፡፡ አሁን ዋናው አከራካሪው ነጥብ፤ ‹ጥበቡ የት ነው ያለው?› የሚለው ነው፡፡ ወደድነውም ጠላነውም፣ አመንነውም ተጠራጠርነውም ጥበቡ እዚያችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊቃውንቱ ሥር ነው ያለው፤ ሞልቷል፡፡ ችግሩ ፊታችን ወደ ፈረንጅ ከተጣመመ ቆይቷል፡፡ ንግግራችን ፈረንጅ ነው፤ አመጋገባችን፣ አረማመዳችን ሁሉ ፈረንጅ ነው። የዕቃዎቻችን፣ የውሾቻችን ስም ሁሉ የፈረንጅ ነው፡፡ ሥራችን ብቻ ነው ያልተለወጠው›› ሲሉ ከታዳሚው የውስጥ ለውስጥ የበቆሎ ሣቅ ዓይነት ድምፅ አስተጋባ፡፡
‹‹ከሁለት አንድ ያጣ ጎመን ነው የሆንነውና እንንቃ ነው የሚለው መጽሐፉ ኢትዮጵያዊ ከሆንን ጥበቡ እጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ ይሄ ደብተራ ምናምን እያልን ሊቃውንቱን ከምናንቋሽሽና ፈረንጅ ከምንከተል፣ እኛው ቤት ውስጥ ወርቃማ ሀብት፣ ወርቃማ ዕውቀትና ጥበብ አለና እሱን እንፈትሸው፤ የተሰደዱ ምሁራንና መጻሕፍት ወደ እናት ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ይምጡ የሚል ነው መልእክቱ፡፡        
‹‹ዩክሊና የተባለችውን…›› (መምህር የሻውና ደራሲው ጠንከር ባለ መልኩ ተከራክረውበት ስለነበር ወደ የሻው መቀመጫ እየጠቆሙ) ‹‹ቅድም መምህር የሻውና ይባቤ የተሟገቱባት ሴት በአስማት ወይም በፍቅር ተለክፋ አለያም ተሰርቃ መጥታለች፡፡ እዚህ መጥታ ግን ለሴተኛ አዳሪነት አይደለም የተጋለጠችው፡፡›› (የየሻውን ሐሳብ ነቅፈው የደራሲውን በመደገፍ ‹‹አዎ መጥታለች። አምጥቶ ግን ገዳም ነው ያስገባት፡፡ ለምን? ፈረንጆችን ሁሉ ንስሐ ለማስገባት የተጠቀመበት ‹ሲምቦሊክ› የሚባለው ዓይነት ስልት ነው፡፡ መጽሐፉ ረቀቅ መንጠቅ ማለቱ አከራካሪ አይደለም ጎበዝ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በደል ሲፈጽሙ ለኖሩት፤ በኢትዮጵያ ላይ በነበረው ብጥብጥ ሁሉ፣ እሳት ባለበት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ሁሉ ፈረንጆች - እንግሊዞች አሉበት፡፡ ይሄን መሠረት አድርጎ ይመስለኛል … ማስተሥሪያ ቦታ ነው የከተታቸው፡፡
‹‹እነዚህ፣ ደብተራዎች (የጥበብ ሰዎች)፣ አሜሪካ ቤተ መንግሥት ገብተው ይጫወቱበታል። የቶኒ ብሌር ቤትና የፓሪስ ቤተ መንግሥት ሁሉ አልቀራቸውም፤ ገብተው ሲምነሸነሹበት፡፡ ሲፈልጉ ጉንዳን፣ ሲፈልጉ በረሮ፣ ሲፈልጉ ሳሙና… እየሆኑ ቁምስቅላቸውን ነው ያሳይዋቸው ፈረንጆችን፡፡
ወደ ታዳሚው ዐይኖቻቸውን እያንከራተቱ በዝምታ ቃኘት ቃኘት አደረጉና፣ ‹‹ዕፀ መሠውር የሚባል ነገር አለ ጎበዝ፡፡ መሠወሪያ ዕፅ ማለት ነው፡፡ ያ ነው ምሥጢሩ፡፡ ዕፀ መፍዝዝ የሚያፈዝ የሚያደንዝዝ አለ’ኮ፡፡ ግን ዛሬ ዛሬ ጫካው ሁሉ ተመንጥሮ እነዚህን ዓይነት ዕፀዋት የት ነው የምታገኛቸው ብትሉኝ መልስ ላላገኝ እችላለሁ፡፡ ምሥጢራዊና አያሌ መናፍስት የተሸከሙ ዕፀዋት እንዳሉ ግን እመሰክራለሁ፡፡ ወደ ሊቃውንቱ ዞረው፤ ‹‹ሊቁ ተዋነይ ሞትን ለሰባት ዐመታት እንዲቆም አድርጓል ይባላል አደል ሊቃውንት?›› ‹‹አዎ›› መለሱ መምህራኑ፡፡ እውነት ወይም ሐሰት ብለን ልንወስደው ብንችልም ሞትን የሚያህል ነገር ለሰባት ዐመታት ያቆመ ሊቅ ነበረን፡፡ ስለሆነም ሊሆን የማይችል ትንግርት አድርገን ልናየው አይገባም። የበለጠ ልናጠናውና ልንመራመርበት የሚገባ ምሥጢር እንዳለ መገንዘብ ነው የሚጠበቅብን፡፡
‹‹አከራካሪ ቢሆንም አንድ ነገር ልጥቀስ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ 500 ሺ የብራና መጻሕፍት አሉ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ነው ይሄ ያለው ሲሉ፤ ሌሎቹም በኢትዮጵያ ያለው ከ200 ሺ እስከ 300 ሺ የሚሆኑ ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የብራና መጻሕፍት ዝም ብለው የተቀመጡ ሳይሆኑ የተደበቀ ምሥጢር የያዙ ናቸው፡፡ ስለ ሥነ ከዋክብቱ፣ ስለ ሕክምና እና ስለ መድኃኒቱ፣ ስለ ሐሳብ፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ ባሕረ ሐሳብ… አጭቀው ይዘዋል፡፡
‹‹የሀገሬ ገበሬዎች ወደ ሰማይ አንጋጠው በጨረቃ እያዩ፤ ‹እነ ሦስቶ/እነስድስቶ ዛሬ ወጥተዋልና የሆነ ነገር ይከሰታል ይላሉ፡፡ እነ ሦስቶ/እነ ስድስቶ መደዳውን ተደርድረው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው። ይሄ ስለ ከዋክብት ያለንን ምርምር የሚያሳይ ነው፡፡ የተማሩትን ሊቃውንት ደግሞ አስቧቸው፡፡
‹‹ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ እስራኤል ድረስ በከዋክብት ተመርተው የሄዱት ሰብአ ሰገል የሚባሉ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚል ጥናትም እየመጣ ነው፡፡ ጥንትም ከዋክብትን መመራመርና በጥበብ መመራት የተለመደ ነገር ነበር ማለት ነው፡፡
‹‹ስለዚህ አንሞኝ ጎበዝ! ጥበቡ አለ፡፡ ግን እዚህ ከተማ ለከተማ እየዞርን ዕድሜያችንን እንጨርሰዋለን፤ እንደ እራፊ ጨርቅ በፌዝ። ወጣ ብንል በየገዳማቱ በየአድባራቱ… ዳባ ለብሰው፤ ጉስቁል ብለው ከሚኖሩ ሊቃውንት ጉያ ውስጥ በርካታ ነገር አለና ከፈረንጁ ይልቅ እነሱን እንደሚገባቸው እንቅረባቸው! የሚል አብሣሪ መጽሐፍ ነው፡፡ እናም ወንድማችን የሚለን፡- የሚጠቅመን ማንነትና ጥበብ እዚህ ነውና እንመለስ ነው፡፡ በእርግጥም ከእኛ ተሰርቀው ሄደው ጀርመን የሚገኙ 20 ሺ መጻሕፍት አሉ፡፡
“…Travels to Discover the Source of the Nile…” የሚለው መጽሐፍ አቃጨለባቸው መሰል፤ ‹‹ዐባይን አጠናለሁ ብሎ ያ ማነው…?›› ሲሉ ጥያቄ “ጀምስ ብሩስ” ምላሽ ከታዳሚው መሃል ተሰነዘረ። ‹‹ጀምስ ብሩስ በዓለም ላይ የሌለውን መጽሐፈ ሄኖክን እኮ ነው ሰርቆት የሄደው፡፡ ግን ተመራማሪ ነው ይባላል፡፡ ያልተዘረፍነው የለም ጎበዝ! So ወደ ሀብታችን እንመለስ፤ በጥበባችን እንኩራ ነውና እያለን ያለው፣ በእውነቱ እጅህን ያበርታው! አእምሮህን ከዚህ በላይ ይክፈትልህ ነው የምለው፡፡
በመጨረሻም ተደጋግሞ መታተሙ እንደማይቀር በመገመት ቢስተካከሉ ጥሩ ነው ያሏቸውን ለምሳሌ አልፎ አልፎ የሚታዩ የፊደል ግድፈቶች እንዳሉ ጠቆሙ፡፡ “ክልሎች ላይ ፍትሕ ቢሮ እንጂ ፍትሕ ሚኒስቴር የለም፡፡ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተፈጸመ ብሎ የሚያምነው ወንጀል ካለ መግለጫ ይሰጣል እንጂ ፍ/ቤት ቆሞ የመከራከር ሥልጣን የለውም፤ ይኼ ሥልጣን የዐቃቤ ሕግ ነው።” ሲሉ እርምት ሰጥተው አለፉ፡፡
ቅድም ሳልጠቅስ ያለፍኩት፡- አልፎ አልፎ ያሉ የግእዝ ዐረፍተ ነገሮች በጣም በሚገባቸው ቦታ እያስገባህ እንደ ቅመም ነው የተጠቀምካቸውና በጣም ይበል ያሰኛል፡፡
ወጥ ያለ ቅመምና ያለ ጨው እንደማይጣፍጥ ሳይገባህ የቀረ አይመስለኝም፤ እንደ ጨውና እንደ ቅመም ነው የተጠቀምክባቸው። ሌሎች የሚጎደፍሩ ጥቃቅን ስሕተቶች ያሉ ይመስለኛል፤ ለራሱ እነግረዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ ይበቃኛል፡፡ እግዜር ይስጥልኝ!›› አሉና ዳሰሳቸውን ቋጩ - ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ፡፡ ከዚህ በተረፈ መፅሐፉን አንብባችሁ የበለጠ እንደምትደመሙበት ተስፋ አደርጋለሁ ሠናይ ቅዳሜ!!

Read 348 times