Monday, 11 September 2017 00:00

ጥበብና የጠየመች ሃዘን

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

 “ሙዚቃ… ጥልቅ የነፍስ እርግብግቢት፣ የትንፋሽ ውልብታ፣ ሙዚቃ… ድቅል የስሜት ውል፣ የቃልና የፊደል ሽልምልም ፈትል፣ ሹክሹክታ፣ ውልብታ… ሙዚቃ… የትም የምትገኝ እንቁ፣ የሁሉም ጌጥ፣ የሁሉም ፈርጥ፣ የሁሉም ልሳን፣ የሁሉም ቋንቋ… ሙዚቃ…”
              
     በመጨረሻ የጥበባት ሁሉ ቅመም ሐዘን ነች ወደሚል መደምደሚያ ለመድረስ ተቃርቤአለሁ። በእርግጥስ በሰው ልጆች የጥበብ መዓድ ላይ ለሺህና ለመቶ ዓመታት የሚሰለጥኑት ዕፁብ ድንቅ ጥበባት የሚቀሰሙት ከመቃብር አፋፍ፣ ከብቸኝነት ገደል ጫፍ፣ ከወናነት ክቡድ ጥላ ማጥ፣ ከውድቀት አዘቅት ዘብጥ ሳይሆን ይቀራል? ከሆሜር ድንቅ ስራ ‹‹የትሮይ ጦርነት›› እስከ ዊሊያም ሼክስፒር ግሩም ተውኔቶችና የራምብራንት አስደማሚ የራስ ምስሎች (self portraits) እንዲሁም የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን እና ደበበ ሰይፉ ነፍስን የሚነዝሩ ምትሀተኛ ግጥሞች ድረስ ጥበብ የምትቀነቀነው የጠየመ ሐዘንን እንደ ምህዋር በመጠቀም ይመስላል፡፡ Neil Straussept የተሰኘ አሜሪካዊ ፀሐፊ፤ ከመስከረም አስራ አንዱ የኒውዮርክ አደጋ ሁለት ቀናት በኋላ በኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ በፃፋት መጣጥፉ፤ ‹‹nothing provokes artistic sensibility like grief.›› ብሏል፡፡
ራምብራንት እጅግ የተደነቀ ጀርመናዊ ሰዓሊ ነው፡፡ ገና ከለጋነት እድሜው ጀምሮ የተሰጠውን መክሊት በመጠቀም የራሱን ምስሎች (self portraits) በብሩሹ እየከተበ ማስቀመጥ ጀመረ። በእያንዳንዱ የሕይወት ዘመኑ በግንባሩ ላይ የምትታየውን ጥቂት የሽብሽባት ለውጥ በነፍሱ ጥልቅ ስርቻ ከሚካሄደው የማያባራ ፍልሚያ ጋር እያናበበና በሐዘን እያጠየመ ሳለ፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ይህንን ሂደት ከቀጠለበት በኋላ የራሱን ምስሎች ስብጥር እስከተሸከሙት ጠጣር የሕይወት አስተውሎት ለእይታ አበቃቸው። ይህንን ከተመለከተ በኋላ ይመስላል ዓለም በሙሉ ያደነቀው፡፡ ጣሊያናዊው የቅብ ሰው ፓብሎ ፒካሶም፤ ‹‹ሁላችንም [ሰዓሊያን] መሆን የምንፈልገው ልክ እንደ ራምብራንት ነው›› ብሎ አጀግኖታል፡፡ የራሱም የፒካሶ ‹‹Guernica›› የተሰኘው ሐዘን የተሸከመ የስዕል ስራው የተጠነሰሰው በዚያች ቅጽበት ሊሆን ይችላል፡፡ እንግሊዛዊው የተውኔት ሰው ዊሊያም ሼክስፒርም ቢሆን የተወደዱለትን የመድረክ ስራዎች የጻፈው የልጁ ሞት ከፈጠረበት ጥልቅ ሐዘን በኋላ እንደሆነ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡
 የግጥምና የቅላፄ ውህድ የሆነው ሙዚቃ ይሉት የጥበብ ምትሃት ግን የሆነ የተለየ አቅም አለው። አንዳንዴ እንዲያውም ከፀሐፍቶቻችንና ሌሎች ጠቢባኖቻችን ይልቅ ሙዚቀኞቻችን የተረሱ፣ ችላ የተባሉ፣ ተመልካች ያጡ፣ የበደኑ የሕይወት ክፋዮቻችንን የሚያስሱልን ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በእኔ ሙዚቃን የማጣጣም አቅም፣ ሙዚቃ ምታዊ ስልቷ (Rhythm) እጅግ እየፈጠነ፣ የድምፁም ከፍታ እያደገ ሲሄድ፣ ለዛዋ በዛው መጠን ሲኮሰምን አያለሁ፡፡
የትኛውም የጥበብ ስራ ምርጥ ይሆን ዘንድ ከተፈለገ፣ በውስጡ የግድ የጠየመ ሐዘንን መሸከም ይኖርበታል፡፡ የጠየመች ሐዘን፣ የጥበባት ሁሉ ቅመም እንደሆነች አትስቱትም፡፡ የምትወዷቸውን ሙዚቃዎች ስትሰሙ ከመንጋው ጋር ሆናችሁ እንኳን ብቻችሁን የሆናችሁ ያህል ብይተውርና እንዲሰማችሁ ያደርጓችኋል፡፡ ሙዚቃ ልሳኗ ብዙ ነው፡፡ የልጃገረዷ መልስ ያላገኘ ናፍቆት፣ የጉብሉ ድብቅ ፍቅር፣ ባሏ የሞተባት ሴት እህህታ… የእናትና ልጅ መፈላለግ… ወዘተ ወዘተ-- ሁሉ ይሰበክበታል፡፡
ሙዚቃ ወደ ሰዎች ጥልቅ የነፍስ ስርቻ ገብታ፣ ንዝረትን በመፍጠር የሚስተካከላት የለም፡፡ ይህን ግዙፍ አቅም ያዳበረችው ከጠየመ ሐዘን ጋር ባላት ጥብቅ ትስስር ይሆን? ሊሆን ይችላል፡፡ ኦስካር ዋይልድ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹one thing is dead in each of us. That dead thing is hope.›› እውነት ነው፡፡ ሆኖም እኔ ይህን የጽልመት መጋረጃ ሰብሬ፣ ስለ ዓለም ጥቂት ፈገግ እንድል የምታደርገኝ ሙዚቃ ብቻ ነች፡፡
ሙዚቃ… ጥልቅ የነፍስ እርግብግቢት፣ የትንፋሽ ውልብታ፣ ሙዚቃ… ድቅል የስሜት ውል፣ የቃልና የፊደል ሽልምልም ፈትል፣ ሹክሹክታ፣ ውልብታ… ሙዚቃ… ስሜትና ብስለት ባለበት ሁሉ የምትገኝ እንቁ፣ የሁሉም ጌጥ፣ የሁሉም ፈርጥ፣ የሁሉም ልሳን፣ የሁሉም ቋንቋ… ሙዚቃ…         
 በሰው ልጆች የጥበብ ገበታ ላይ ዘመናትን የሚሻገሩት የጥበብ ስራዎች የሚፈሉት ከሚያባብለውና በሳቅ የተሸፈነው የሕይወት ውጫዊ ወለል በታች፣ በሐዘን ጥላ ስር ይመስላል። ብዙ ሰው፤ ሀዘንና ደስታ ሁለት የተለያየ ጣዕም ያላቸው፣ የሕይወት መንታ ገጾች እንደሆኑ አድርጎ ያስባል፡፡ ይሄንን ሚሊዮን ምንትስ ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ ሆኖም ራሱን ችሎ ለብቻ የሚቆም ልሙጥ ሐዘንም ሆነ ደስታ የለም፡፡ ግን ግን ደስታ ይሉት ስም የለሽ ቅኔ ከጥላነት ያለፈ ሕልውና እንደሌለው እንዴት ላስረዳችሁ ይቻለኛል? ለምሳሌ ከመስታወት ፊት ለፊት እርቃናችሁን ቆማችኋል እንበል፡፡ በመስታወቱ ውስጥ የሆነ ሞጋጋ፣ የራሳችሁ ምስል አጎንቁሎ ይታያችኋል፡፡ እናም የወረሳችሁትን እናንተነት ረስታችሁ በመስታወት ውስጥ ለምትመለከቱት ምስል ትማረካላችሁ፡፡ ሆኖም ልትጨብጡትም ሆነ ልትዳስሱት የማይቻል እንዲሁ አጥበርባሪ ምስል ይሆንባችኋል፡፡
ደስታ ለእኔ እንዲያ ነው፡፡ ልክ እንደ “ዲምላይት” የሚብለጨለጭ ሆኖም የማይዘገን የማይጨበጥ… አዕምሮአችሁን በሚገባ ካሰለጠናችሁትና ካበቃችሁት፣ ሳቅ ከስቃይ ምርቅዝ ቁስል በጭካኔ የሚገሸለጥ ገላ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ የእኛ ሳቅ ውልደቷ በሌሎች ሰዎች ሐፍረት፣ ውርደት፣ እጦት መሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡ በአንደኛው ውርደት ሌላኛው ሳቅ የሚሸምትበት የሕይወት ቅዝምዝም ቅኔ ግን አይገርምም? ጊዜው ሆኖ ሌሎችም ከእናንተ ስቃይ፣ ሐፍረትና ውርደት ርካሽ የሳቅ ትርፍ የሚያጋብሱበት ቀን ይመጣል፡፡ እንደው በሌጣው እናውራ ከተባለ፣ ደስተኛ የመሆን መንጠራወዝ፣ ከሚያንዘፈዝፍ ረሀብ በኋላ ፈንዲሻ በልቶ ለመጥገብ እንደ መሞከር አድካሚ ይሆንብኛል፡፡
ሰው የመሆን መውተርተር ራሱ፣ ሰው በመሆን የተጣለብንን ስቃይ የመቀነስ አታካች ጉዞ አይደለምን? አስቀድሞውኑ እንድትታገላት እንጂ እንዳታሸንፋት ሆና በተሰራች ዓለም፣ በብዙ ታግለህ በመጨረሻ በእጅህ ምንም የለም፡፡ ግን ይሄ የምነግርህ ሀቲት የሚገለጠው፣ ከየትኛውም ሕይወትን መመልከቻ የዋህ መነፅር (perspective) ነፃ ሆኖ፣ ሕይወትን በሌጣው ለሚመለክት ሰው ነው፡፡ ሐዘን ግን ቅመም ነች፡፡ ጥበብን ወደ ዘላለማዊ ማንነት የማሸጋገሪያ ቅመም…ወድዳችሁ የምትሰሟቸውን ዘፈኖች አጢኑ፡፡ አብዛኞቹ የጠየመ ሐዘን ያጠላባቸው ናቸው፡፡ እመኑኝ፤ የትኛውም ሰው ንጉሥ ወይም ቱጃር ወይም ውበቷ የዓለምን ስቃይ  ሁሉ ልታባብል የምትጥር ልዕልት፤ ሁሉም በየዕለቱ በራቸውን ዘግተው ለብቻቸው የሚያለቅሱበት አብይ ጉዳይ አላቸው፡፡ ጥበብ ይህን ክቡድ፣ የብቻነት ዓለም፣ እንደ ጌጥ ጥለት እየፈተለች ትዋብበታለች፡፡
ማወቅ የሚባል የለም፡፡ ያለው መንቃት ብቻ ነው፡፡ እናም በሕይወት ምህዋር ላይ በንቃት ስትመላለስ፣ ይህን የሲሲፐስ ጥብቅ ቀንበር የመሸከም ግዴታ አለብህ፡፡ የብዙዎቻችን ሕይወት ሲነበብ፣ ኑሮአችን የውሸት፣ ሞታችን መራር እውነት --- የመሆኑ ነገር ይህንን ስለማንገነዘብ ይሆን? ምናልባት…                  

Read 603 times