Monday, 11 September 2017 00:00

“አፈንጋጩ” የፈጠራ ጽሁፍ ደራሲ

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(2 votes)

 “የፍቅርን ዋና ትርጉም ለመረዳት ይመስለኛል፣ አንዳንድ ጊዜ የምጽፈው፡፡ ፍቅርን ለመረዳት ብጽፍም ተረድቼው አላውቅም።      የማውቀው ነገር ግን አለ፡፡ ---- ይኸውም የፍቅር ተቃራኒ ፍርሃት መሆኑን ነው፡፡ የጨዋታው ህግ ይሄ ብቻ ነው፡፡ በአለፈው ወር አንድ ፒያኖ የሚጫወት ሰውዬ፣ ትርኢት ባሳየበት ምሽት ላይ ተገኝቼ ነበር። ሰውየው መጫወት ሲጀምር ገና ነው ፍርሃት እንደሌለበት የገባኝ፡፡ --- ሰውየው ፒያኖውን ከሚወደው በላይ ፒያኖው ሰውየውን ያፈቅረዋል። ፒያኖው ሰውየውን ያፈቀረበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ አንዳችም ፍርሃት ስለሌበት ነው፡፡---” (“እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች”፤ገጽ 239)
ከላይ ያነበባችሁትን ሃሳብ የቀነጨብኩት፣ በቅርቡ ለንባብ ከበቃው የደራሲ ሌሊሳ ግርማ “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” መድበል ላይ ነው፡፡ በ243 ገጾች ከተቀነበበውና 38 ታሪኮች ከቀረቡበት መድበል፣ “እስቲ ሙዚቃ” ከተሰኘው ላይ ለመቀንጨብ የመረጥኩት በዘፈቀደ አይደለም፡፡ አንድም  የመጽሐፉ  አውራ ርዕስ ተደርጎ የተሾመ በመሆኑ  ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍቅር በላይ ክብደት ያለው  ርዕሰ ጉዳይ ሊኖር አይችልም በሚል ቅን የፍቅር ሃሳብ ነው፡፡ በእርግጥ ደራሲው ለታሪኩ እንደ መግቢያ የተጠቀመበት፣ የፒያኖ ተጫዋቹና የፒያኖው ፍቅር ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ቀጥሎ ለሚመጣው ዋና ታሪክ ማዘጋጃም ጭምር ነው፡፡  ሙሉ ታሪኩን በፍቅር እንድታነቡት ጋብዤአችኋለሁ፡፡     
የዛሬዋ ጽሁፌ ታሪካዊ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ለመጻፍ ሰበብ የሆነኝ የደራሲው “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ ይመረቃል ተብሎ ዕቅድ መያዙና እኔም ስለደራሲው በምረቃው ላይ ጥቂት ነገሮች እንድጽፍ በአዘጋጆቹ በመታዘዜ ነው፡፡ ለጽሁፉ ለመዘጋጀት መጽሐፉን እያነበብኩ ሳለ ግን ከተገቢው ላይ ተመሰጥኩበት። በዚህ መሃል የምረቃ አዘጋጆቹ ድምጽ ጠፋ፡፡ ይሄኔ ከራሴ ጋር ተማከርኩና ለመድረክ የታሰበውን ለጋዜጣ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ለአዲስ አድማስ የጥበብ ቤተሰቦች ማለት ነው፡፡ ይኸው ነው ሰበቡ፡፡ እናም በዚህ ጽሁፍ  የሌሊሳ ግርማን አዲስ መጽሐፍ፣ በወፍ በረር አስቃኛችኋል ማለት ነው፡፡ እግረ መንገዴን ግን  ደራሲውን በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ እሞክራለሁ፡፡ እኔ የማውቀውን ያህል፡፡ ከዚያ በፊት “እስቲ ሙዚቃ” ከተሰኘው ድርሰቱ በድጋሚ ጥቂት መስመሮች ላስነብባችሁ፡-
“--- እናም በአለፈው ወር ሰውየው ገና መቀመጫውን ስቦ ፒያኖዋ ሥር እንደተቀመጠ፣ እጁን ሳያሳርፍባት በፊት፣ መሣሪያዋ ጥዑመ ዜማዋን ለቀቀችው፡፡ የፒያኖውን ቁልፎች እየጎረጎረ አልነበረም፣ ሙዚቃውን የሚያፈልቀው። በመጎርጎርማ መኪናም የሞተር ድምጽ ከተኛበት ተቀስቅሶ ያወጣል፡፡ ሰውየው የፒያኖው ቁልፎች ላይ የተቀመጠለትን ሙዚቃ---በሁለቱ እጆቹ ማፈስ ነው የጀመረው፡፡ በሁለት መዳፎቹ፣ ከጥግ እስከ ጥግ እየተመላለሰ፣ፒያኖዋ የምትሰጠውን ፍቅር፣ ሙዚቃ አስመስሎ አፈሰ፡፡ ጉያዋን፣ ደረቷን፣ ዳሌዋን እያሸ ዜማዋን አስጨረሳት፡፡ በመጨረሻ በአንድ እጁ ጭንዋ ውስጥ ገብቶ ሲቀር--- እና ፒያኖዋም ተንሰቅስቃ ዜማዋን ስትጨርስ---አዳራሹ በጭብጨባ መሃል ለመሃል ተገመሰ፡፡----” (ገጽ 239-40)
የሃሳብ ችግር የሌለበት ደራሲ
ሌሊሳ ግርማንና ሥራዎቹን እኩል ነው የማውቃቸው፡፡ በሥራ አጋጣሚዬ፣ የሚጽፋቸውን ታሪኮች በእፍታ፣ ቀለሙ ሳይደርቅ የማንበብ ዕድል አግኝቼአለሁ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አድማስ ላይ የወጡለት ጽሁፎች በእኔ በኩል ነው ያለፉት። ይሄን ሁሉ ያተትኩት፣ ከሥራዎቹ ጋር ያለኝን ትውውቅ ለመግለጽ  ያህል ነው፡፡ ሥራዎቹን ጠንቅቄ  አውቃቸዋለሁ ለማለት፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የሌሊሳ ሥራዎች “አይገባንም” የሚሉ አንባቢያን ይገጥሙኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በጊዜ ሂደት ግን እንዲህ ያሉት አንባቢያን፣ ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ደራሲውን እየተረዱት የመጡ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶቹም ቀንደኛ አድናቂዎቹ  ሳይሆኑ እንዳልቀሩ እገምታለሁ፡፡   
ሌሊሳ የሙሉ ሰዓት ፀሃፊ ነው፡፡ እንጀራዬ ብሎ የያዘው ድርሰትን ብቻ ነው፡፡ የፈጠራ ጽሁፍ ደራሲ ነው፡፡ የሌሊሳን የሥነ ጽሁፍ ሥራዎች  በሦስት ዘርፎች መክፈል ይቻላል፡፡ አጭር ልብወለድ፣ ወግና በሁለቱ መሃል የሚወድቁ በሚል። በሁሉም  ሥራዎቹ  ላይ የሚስተዋል የጋራ ባህርይ ግን አለ፡፡ ይኸውም የፈጠራ ሥራ ወይም ፈጠራ ቀመስ መሆናቸው ነው፡፡ አጭር ልብወለዶቹም ሆኑ ወጎቹ፣ ከተለመደው የአጻጻፍ ዘይቤ  ለየት ያሉ ናቸው፡፡ የሚለዩት በአጻጻፍ ዘይቤአቸው ብቻ አይደለም፤በሚያነሱትም ሃሳብ ይለያሉ። በአብዛኛው ሥራዎቹ ላይ አፈንጋጭ  ሃሳቦች ይንጸባርቃሉ፡፡  አልፎ አልፎ  ጅምር ሃሳብ (ስኬች) የሚመስሉ ታሪኮችንም ይጽፋል፡፡  ጅምር ቢሆኑም ግን “ተራ ተርታ” ሃሳቦች አይደሉም፡፡ ደርዝና ወግ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ አንባቢን ለጥያቄና ለምርምር የሚያነቁና የሚያተጉ ናቸው፡፡ የአዕምሮ ጅምናስቲክ የሚያሰሩ፣ ወደ ፍልስፍና ያደጉ ወይም የሚንጠራሩ  ሃሳቦች--- ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ሌላው የሌሊሳን ሥራዎች ለየት የሚያደርጋቸው ደፈር ማለታቸው  ነው፡፡ ሃሳቦቹ ደፋር ናቸው፡፡  የሰነፍ ድፍረት ግን አይደለም፡፡ እውነትን ለማግኘት  ከሚደረግ የነፍስ መፍጨርጨር  የሚመነጭ ድፍረት ነው፡፡ “የነፍስ ድፍረት” በሉት!
አብዛኛው አንባቢ ሌሊሳን የሚያውቀው በአጭር ልብወለድና በወግ ጸሃፊነቱ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ግጥምም ይጽፋል። በአማርኛም በእንግሊዝኛም፡፡ በእንግሊዝኛ የጻፋቸው ከደርዘን በላይ የአጭር ልብወለድ ሥራዎችም አሉት፡፡ የህትመት ብርሃን የሚናፍቁ። ማለፊያ ተርጓሚም እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የተለያዩ የትርጉም ሥራዎችን አብረን ሰርተናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ በረከቶች ላይ ደግሞ ትጉህና ታታሪ  ነው፡፡ ጥብቅ የሥራ ዲሲፕሊን አለው፡፡  በአንድ ቁጭታ፣ አንድ አጭር ልብወለድ አሊያም  ወግ ጽፎ ማጠናቀቅ አይገደውም፡፡  የሃሳብ እጥረት  የለበትም። “ሃሳብ አልመጣልኝም” ብሎኝ አያውቅም፡፡ ያነበበው መጽሐፍ ወይም ከባልንጀሮቹ ጋር ያወጋው ጨዋታና የተከራከረበት ውይይት አሊያም በቴሌቪዥን የተመለከተው አስገራሚ ዜና  - ብቻ ፖለቲካም ይሁን ማህበራዊ ጉዳይ፣ ሃይማኖትም ይሁን ጥበብ፣ ባህልም ይሁን ሳይንስ ---- ለጽሁፉ በግብአትነት መጠቀም ተክኖበታል፡፡  ምድራዊው ሃሳብ ሳሳ ሲልበት ደግሞ ወደ “ሰማያዊው ዓለም”  በምናብ ፈረስ ያስጋልበናል፡፡  ሌሊሳ ዘንድ የማይጻፍ ሃሳብ የለም፡፡ ሁልጊዜ ለመጻፍ ዝግጁ ነው፡፡  “የጥበብ ቆሌ” አሊያም “ራይተርስ ብሎክ” የሚሉት ነገር እሱ ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ ራሱን የገራ ጸሃፊ ነው፡፡   
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለብዙ ዓመታት ጽሁፍ በማቅረብ ከሚጠቀሱ ጸሐፍት መካከል ሌሊሳ አንዱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ የወጣው “እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች”፣ አምስተኛው መጽሐፉ  ሲሆን ከዚህ ቀደም “የነፋስ ህልም እና ሌሎች የምናብ ታሪኮች”፣ “አፍሮጋዳ”፣ “መሬት-አየር-ሰማይ” እና “የሰከረ እውነታ” የሚሉ መጻህፍትን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ ስለ ደራሲው ይህን ያህል ካወጋኋችሁ ይበቃል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሥራው ልውሰዳችሁ፡፡  ቅኝቴ የሚያተኩረው ግን በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ አይደለም፡፡ በታሪኩ ላይ ብቻ ነው - በሚያነሳቸው ሃሳቦች፡፡     
“እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎች ታሪኮች”ን በወፍ በረር
ሌሊሳ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን  የታሪኩ ጭብጥ ወይም ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ ለመጻፍ ይደፍራል። ኢየሱስና ሌሎች መላዕክት፣ ገጸባህርይ ሆነው የተቀረጹበት ድርሰቶች አሉት፡፡  የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳቦችን የአጭር ልብወለድ መነሻ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ የደረጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ስላለው፣ ሃይማኖታዊ ታሪክ በማዛበት አይታማም። ለምሳሌ “i-prophet” በተሰኘው ድርሰቱ፣ አንደኛው ገጸባህሪ እግዚአብሄር ነው፡፡  
“i-prophet” ከርዕሱ ጀምሮ ይለያል፡፡ ታሪኩ በአማርኛ፣ርዕሱ በፈረንጅ አፍ ነው የተጻፈው። ተራኪው የሚያስተዋውቀን እግዚአብሔር ደግሞ እኔና እናንተ የምናውቀው ዓይነት አይደለም። ፌስቡክ ተጠቃሚ ነው፡፡ የፌስቡክ አካውንት አለው፡፡ ምናልባት ርዕሱ በእንግሊዝኛ የሆነው፣ የፌስቡክ ማህበረሰብን የሃሳብና የቋንቋ ጉራማይሌነት ለማሄስ  ሊሆን ይችላል፡፡  ተራኪው፤ በፌስቡክ የሚያውቀውን እግዚአብሔር፣ እንዲህ ያስተዋውቀናል፡-
“--እግዚአብሔርን በfriend request መጠየቂያው ላይ add friend ብዬ እጋብዘዋለሁ። በቅጽበት ይቀበለኛል፡፡ እስከ አሁን የለጠፋቸውን መልዕክቶች ተራ በተራ ማንበብ እጀምራለሁ። አብዛኛው መልዕክት ከመጽሐፍ ቅዱስ --ከራሱ ድርሰት ላይ የተጠቀሱ  ናቸው፡፡ በራሱ ድርሰት እንዲህ እንደሚመሰጥ አላውቅም ነበር ---” (ገጽ 140)
ከዕለታት አንድ ቀን ግን  “God” በሚል ስም ፌስቡክ የከፈተው እግዚአብሔር፣ከወትሮው የተለየ መልዕክት ፖስት ማድረጉን ተመለከትኩ ይለናል - ተራኪው፡፡   
“-- ስለ ዓለም መጥፋትና ስለ መጪው የሰው ልጅ ውድቀት አይደለም መልዕክቱ፡፡ መልዕክቱ ለራሱ መቆዘሚያ የተጻፈ ነው፡፡ የሰው ልጅን በመፍጠሩ በአንድ ጎኑ እንደተደሰተና በአንድ ጎኑ እንዳዘነ ይገልጻል፡፡ በተለይ ከሰው ልጅ የገረመው ይህ የናኖ ቴክኖሎጂ ቢሆንም ግን ተስፋ ያስቆረጠውም እሱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በአጭሩ ይሄ ጽሁፍ ስለገረመኝም ስላሳዘነኝም -- ተመስጬ አነበብኩት--” ተራኪው ነው ያለው፡፡ (ገጽ 140)
 እግዚአብሔር በፌስቡኩ ላይ ፖስት ያደረገው መልዕክት ምን እንደሆነ የማይጓጓ አንባቢ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ በፈጣሪ መኖር የማያምን፣ኢ-አማኝ  ካልሆነ በቀር፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር በፌስቡኩ ላይ ከለጠፈው ጥቂቱን ቀንጭበን እናንብ - ለመደመም ያህል፡፡
 “ፌስቡክ ተጠቃሚ ከሆንኩ በናንተ አቆጣጠር ብዙ ዓመት ሆኖኛል፤ እንዲያውም ከመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች አንዱ ነኝ ማለት እችላለሁ። ግን አብዛኞቹ ተከታዮቼ እስካሁን አብረውኝ አልዘለቁም፡፡ ገና ከመጀመሪያውም እውነተኛ ስሜን በመግለጼ በውስጥ መስመር እየገቡ የሚሰድቡኝ ነበሩ፡፡ በተለይ ለሰዎች የሚጠቅም የወደፊት አቅጣጫ ስጠቁም ---ከተለያዩ የሃይማኖት ጎራ እየተነሱ የሚያንጓጥጡኝ ቁጥራቸው ይሄ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ለሃይማኖቱ ሁሉ መንስኤ እኔ ሆኜ ሳለሁ -- በእኔ ስም ተከፋፍለው እርስ በራስ መተላለቃቸው ሳያንስ ----ተመልሰው እኔንም መስደብ ጀመሩ፡፡ ከስድብ ለመትረፍ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ --- እነሱ በሚገባቸው ቋንቋ ከመጠቀም በስተቀር፡፡ ይኸውም -- እኔም መልሼ እነሱን ብሎክ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ---” እያለ እግዚአብሄር ምሬቱን ማተት ይቀጥላል፡፡ (ገጽ 140-141)
ይሄ  መልዕክት ብዙ ማብራሪያና ትንተና የሚያሻው አይደለም፡፡ የፌስቡክ ማህበረሰብ  ለእግዚአብሔርም እንኳን  እንደማይመለስ የሚያጸኸይ ታሪክ ነው፡፡ እንደው ግን የእግዚአብሔር መጨረሻ ምን ይሆን? በፌስቡክ ማህበረሰብ እንደተማረረ ይቀጥላል ወይስ ፌስቡኩን ይዘጋል? አጓጊ ታሪክ ይመስላል፡፡
“የገነት መግቢያ ፈተና” በተሰኘው ታሪክ ደግሞ ባቢሌ የተባለ ገጸባህርይ፤ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ነፍሱ ለፈተና ይቀርባል - በሰማያዊው ዓለም፡፡ በመንግስተ ሰማያት ደጃፍ ላይ፡፡ ምንም የማይገደው ደራሲው፤ ከምድራዊው የስጋ ዓለም ወደ ሰማያዊው  የነፍስ ዓለም በምናብ ይዞን ይከንፋል። ለነፍስ ከቀረበለት “የገነት መግቢያ ፈተና” ጋርም ያፋጥጠናል፡፡ እኛም “ያለ ዕዳው ዘማች” ሆነን፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ፍለጋ  መዳከራችን አይቀርም፡፡
“---ሟቹ ምድር ላይ ህይወቱን በሚገፋበት ጊዜ ራሱን አንባቢ ወይም  ጸሐፊ ነኝ ብሎ ያስብ ነበር አሉ። እናም መጀመሪያ የቀረበለት ጥያቄ “ሽማግሌውና ባህሩ” የማን ድርሰት ነው የሚል ነበር፡፡ ጥያቄው  የቀረበለትም ሆነ እንዲመልስ የተጠበቀው በጽሁፍ ነው፡፡ የተጠየቀው ጥያቄ በሁለት ቃላት የሚመለስ መሆኑን እርግጠኛ ቢሆንም ለመልስ የተተወለት ባዶ ቦታ ግን የኑዛዜ ያህል የረዘመ በመሆኑ ጥርጣሬ ገባው፡፡ ጭራሽ የክፍት ቦታው መስመሮች በሂሳብ ምልክቶችና ሰንሰለታማ እንቆቅልሻዊ ሳጥኖች የተሞላ ነው፡፡---” (ገጽ 126)
የባቢሌ ነፍስ  የቀረበለት ፈተና  ትንሽ ያወዛገበው ይመስላል፡፡ ጥያቄዎቹን እየዘለለ ይሄድና፣ 10ኛው ጥያቄ ላይ ይደርሳል፡፡ የመጨረሻው ጥያቄ መሆኑ ነው፡፡ ቀለል እንደሚል አስቦ ነበር፡፡
 “-- አስረኛው ጥያቄው የመጨረሻ ብቻ ሳይሆን --- “ብቸኛውም ነው” ይላል - መግለጫው። እስካሁን እያነከሰና እየዘለለ የመጣቸው ጥያቄዎች -- አስረኛውን መፍታት ይችል ዘንድ ልቦናውን እንዲያፍታታባቸው ተብለው የተቀረጹ መሆናቸውን አያይዞ ይገልጻል፡፡ ከመግለጫው ስር በአስረኛው ተራ ቁጥር ትይዩ የጥያቄ ምልክት ተቀምጧል፡፡ ጥያቄው ግን የለም፡፡ --- ወረቀቶችን እያገላበጠ አሰበ፡፡ ልብስ መስቀያ የሚያክል የጥያቄ ምልክት ብቻ ነው ያለው፡፡---” (ገጽ 131)
ግን የባሰ ገጠመው፡፡ የባቢሌ ነፍስ መጨረሻ ምን ይሆን? ከ10 ጥያቄዎች ስንት ያመጣ ነው ፈተናውን የሚያልፈው? ፈተናውን የወደቀስ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆን? እንጦሮጦስ ይወርዳል ወይስ ወደ ምድር ይመለሳል? ከደራሲው የፈጠራ ዓለም ብቻ ነው መልሱን ማግኘት የሚቻለው፡፡ ግን ጉጉት ያጭራል፡፡
“ናኦል” በሚለው  ታሪክ ውስጥ ደራሲው የሚፈነድቅበትን ገጸባህርይ የፈጠረ ይመስላል፡፡ ናኦል፤ በሌላ ደራሲ የተፈጠረ ጅምር ገጸባህርይ ነው - ያልተጠናቀቀ፡፡ “-- የጠራሁት ገጸ ባህሪ፣ሰሞኑን በሙሉ በዙሪያዬ ሲሽከረከር እያየሁ እንዳላየሁ ችላ ብዬው ነበር፡፡ ገጸ ባህሪዎች ካልተጻፉ አይሞቱም። በጭንቅላቴ ጀርባና ዙሪያ እየተሽከረከሩ ዕድሜ ልኬን ሰላም የሚነሱኝ ብዙ ሌሎች ገጸ ባህሪዎችም አሉ፡፡ የመግደያ ጊዜ አጥቼ ጭጭ ብዬአቸዋለሁ፡፡ --- በመጻፍ ገጸ ባህሪን ገድለህ ሐውልት ማድረግ ካልቻልክ፣ በማውራት ግን ፓራላይዝ አድርገህ ዊልቸር ላይ ዘላለም ማስቀመጥ ትችላለህ፡፡--” ይላል ተራኪው፡፡ (ገጽ 121)
በታሪክ ውስጥ ታሪክ (“ኤ ስቶሪ ዊዚን ኤ ስቶሪ”) እንደሚባለው፣ በገጸ ባህርይ ውስጥ ሌላ ገጸ ባህርይ (“ኤ ካራክተር ዊዚን ኤ ካራክተር”) ዓይነት ነገር ነው፡፡ ሌሊሳ  የፈጠረው ደራሲ ገጸባህርይ፣ ስለሚገጥሙት ገጸባህርይዎችና ተፈጥሯቸው ነው የሚተርከው፡፡ ለፈጣሪ ጸሎቱን እንዲያደርስለት የፈለገው “ናኦል” የሚል ስም የወጣለት፣ በሌላ ደራሲ የተጀመረ ገጸባህሪን እንደገና በራሱ አምሳል ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋል - ተራኪው፡፡
“--ከዚህ በፊት መጻፍ የጀመረህ ደራሲ ነበር? አልኩት፤ ቀና ብዬ በምናብ ዓይኔ ሳላየው፡፡ -- እኔ የምሰጠው ማንነት እንጂ ከዚህ ቀደም ስለተሰጠው እኔን አይመለከተኝም፡፡  “ከዚህ በፊት መጻፍ ተጀምሬ የነበረው በእርሳስ ነበር--ስምም ሰጥቶኝ ነበር፡፡ ናኦል ነበር የመጀመሪያ ስሜ” -- ድንገት አስጠላኝ። ናቅሁት፡፡ ገጸ ባህሪውን ብቻ ሳይሆን በእርሳስ ጽፎ የጀመረውን ደራሲም ጨምሬ። ምን ማለት ነው ዘላለማዊ ጸሎትን በእርሳስ መጻፍ? በእርሳስ የሚጽፍ መሳሳት የሚያበዛ ደራሲ ነው፡፡ በላጲስ ለማጥፋት የማይሳሳ፡፡-- ናኦልን የጀመረው ---ጀማሪ ደራሲ መሆን አለበት፡፡ --- ጅማቱን ያጠነከረ ደራሲ፤ በቀለም ነው የሚስለው፤ በእስክሪፕቶ የዘይት ቀለም፡፡ ስርዝ ድልዝ በማይፈቅደው፤ አንዴ ከተጀመረ መጠናቀቅ ባለበት የውሳኔ አቋም ቀለም፡፡---” (ገጽ 122) ተራኪው ደራሲ እንደሚለው፤ ናኦል  በአዲስ መልክ ተጽፎ ይሞት ይሆን? ለፈጣሪ እንዲያደርስ የተፈለገው ጸሎት ምንድን ነው? በ4 ገጽ ተኩል የተቀነበበ አጓጊ ታሪክ ነው፡፡
“ሰው ሲሸነፍ” የሚለው ድርሰት፣ ለሞት የተዘጋጀ ሰው የጻፈው ኑዛዜ ነው፡፡ ታሪኩ በጨለምተኝነት የሞላ ይመስላል፡፡ ግን ደግሞ ራሱን ለሞት ያዘጋጀ ሰው፣ በተስፋ ብርሃን ሊጥለቀለቅ አይችልም፡፡ ይልቅስ ገጸባህርይውን ምን አግኝቶት ነው የሚያሰኘው፣ በአንዳች ተዓምር ለሁለተኛ ጊዜ የመኖር ዕድል ቢሰጠው እንኳን ፈጽሞ የማይፈልግ ብሶተኛና ምሬተኛ  መሆኑ ነው፡፡ ከህይወት ጋር የማይታረቅ  ቅራኔ ያለው ይመስላል፡፡
“ያ በቀን ውስጥ ወደ ሺ ጊዜ በአንድ ዓይነት መንገድ የሚወራለት ፈጣሪ ካለ እና ከቅርብ ሰዓታት በኋላ ስሞት ወደሱ ፊት ወስደው ካቆሙኝ፣ “ለምንድን ነው እንደዚህ የሆንከው” ብሎ እስኪጠይቀኝ እጠብቃለሁ፡፡ መልስ አልሰጠውም። እሱ ሲናገር መልስ አልሰጠውም፡፡ አባቴ ድሮ መጥፎ ነገር ስሰራ፤ “ለምንድን ነው እንደዚህ የሆንከው?” ብሎ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ ለሱም መልስ አልሰጠውም ነበር፡፡ ብቻ ደሜ ይፈላል፡፡ እንባ በዓይኔ ግጥም ይልብኛል፡፡ መልስ አልሰጠውም፡፡ ደግነቱ ከሞት በኋላ ምንም ነገር የለም፡፡ ለመልስና ጥያቄ የሚበቃ ህይወት አይደለም፤ የሰው ልጅ ተብዬ የኖርኩት። “ደግመህ መወለድ ትፈልጋለህ ወይ?” ብሎ ከጠየቀኝ ብቻ መልስ እሰጠዋለሁ፡፡ “አልፈልግም- አልፈልግም-አልፈልግም፡፡---” (ገጽ 230)
ራሱን ለሞት ያዘጋጀው ተራኪ፤ ከምድራዊ ህይወት ያተረፈው፣ ለትዝታ የሚበቃ ነገር እንደሌለ ይገልጻል - በምሬት፡፡ ከዚህ ዓለም በመለየቱ - በመሞቱ ቅንጣት ታህል  የሚቆጨው ነገር የለም፡፡ እንደውም እስከ ዛሬ በምድር ላይ መኖሩ ሳያስቆጨው አይቀርም፡፡ ባላነበባቸው ሳይሆን ባነበባቸው  መጻህፍት የሚቆጭ፣ ያልታደለ ገጸ ባህርይ ነው፡፡  አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ!
“---ያ መጻህፍት የሚሰጠኝ ልጅ ማንበብ አለብህ ብሎ የሰጠኝና አንድ ጥግ የቆለልኳቸውን መጻህፍት ከመሄዴ በፊት አለመጨረሼ አልቆጨኝም። የሚቆጨኝ እንዲያውም አንዳንዶቹን ማንበቤ ነው። በተመሳሳይ ድምጽ የሚዘምሩ ቁራዎች፣ ሁሉም የየራሱ አዲስ ነገር ያለው ይመስለዋል፡፡ እነዛ ሁሉ መጻህፍት ለውበት ወይ እውነት ወይንነት ቢጨመቁ አንድ ስንኝ ግጥም አይወጣቸውም፡፡ ህይወትን የሚሻገሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሞት ይዤ የምሄደው አንድም ነገር አላተረፍኩም፡፡ ደግነቱ ከሞት በኋላ ምንም የለም፡፡--” (ገጽ 230-231)
ለሞት ራሱን ያዘጋጀው ምስኪን፤ከሞት በኋላ ምንም የለም ይበል እንጂ ከሞት በፊትም (ስለ ኋላ ታሪኩ) በተመሳሳይ ምንም እንደሌለ ነው  የሚነግረን፡፡ ትውስታው በምሬትና በቁጭት ብቻ የተሞላ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ --- የሆነበት የአዳም ዘር! በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ  ከህይወት መፋታት፣ ዓለምን መሰናበት ክፉ እጣ ነው፡፡ ወደዚች ምድር መምጣቱ ራሱ ከንቱ ድካም ነው፡፡ መንገድ ተሳስቶ ይሆን? የሚያስብል ነው፡፡
ሌሊሳ ግርማ፤ ወደፊት (አልፎ አልፎም ቢሆን)  የሚፈጥራቸው  ገጸ ባህርያት፤ በተስፋ የተሞሉና በተስፋ የሚሞሉ፣ የመኖር ጉጉት ያላቸውና የመኖር ጉጉት የሚፈጥሩ፣ የኑሮ እስክስታ የሚመቱ፣ ሳቃቸውና ደስታቸው የሚጋባ --- እንደሚሆኑ  ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተረፈ ለደራሲው  ስራዎች አዲስ የሆኑ አንባቢያን፣ በተቻለ መጠን ሥራዎቹን አስሰው እንዲያነቡ እጠቁማቸዋለሁ፡፡ ያተርፉበታል እንጂ አይከስሩበት፡፡  
መልካም አዲስ ዓመት! ዘመኑን የጥበብ ያድርግልን! አንባቢያንን ያበረክትልን! የሙሉ ሰዓት ደራሲያንን ያብዛልን!

Read 601 times